መነሻ ገጽ - ሌሎች አምዶች - ሕግ እና ፖለቲካ - በህግ አምላክ - በእርግዝና ምክንያት የሚፈጸም አድልዎ
Buy Valtrex Online Buy Albuterol inhaler Online Buy Prinivil Online
24 March 2013 ተጻፈ በ 

በእርግዝና ምክንያት የሚፈጸም አድልዎ

በአንድ የግል የፋይናንስ ተቋም እንዲህ ሆነ፡፡ አንድ የድርጅት ኃላፊ የቀጠሯትን ፀሐፊ ሥራ ስትጀምር እርጉዝ መሆኗን አለመሆኗን አጥብቀው ጠየቁዋት፡፡

በጥያቄው ድንገተኝነት በመገረም እርሷም እርጉዝ አለመሆኗን ገለጸችላቸው፡፡ አዲስ ጋብቻ መመሥረቷን እንጂ እርጉዝ መሆን አለመሆኗን እርሷም አታውቅም፡፡

የሚቋጥር፣ ቋጠሮውንም የሚፈታ፣ ኩነቱንም ቀድሞ የሚያውቅ ፈጣሪ ብቻ ነው፡፡ እርጉዝ ብትሆንስ፤ ሥራ አጥ በበዛበት አገር ለተወሰነ ጊዜ ተቀጥሮ መሥራት ተስፋ ስለሚሆን መግለጹን አትወደውም፡፡ ለመመለስ ፈቃደኛ አለመሆንስ መብቷ አይደል፡፡ ማንም ሰው የሌላውን ግላዊ ምስጢር ለመጠንቅስ ከምን መብት ያገኛል?

ሥራ ጀምራ አምስት ወራትን ካሳለፈች በኋላ ግን ነገሮች ተለወጡ፡፡ የአገራችን ሰው ‹‹ቂጣ ከሆነ ይጠፋል፣ ሽል ከሆነ ይገፋል›› እንዲል ከወራት በኋላ የሠራተኛዋ የውፍረት ምስጢር ቂጣ ሳይሆን ቀረ፡፡ የሥራ ኃላፊው በጣሙን ተናደዱ፡፡ የእርሷ ዘሯን የመተካት ደስታ ሳታስበው ያለቃዋ ሐዘን ሆነ፡፡ የሥራ ኃላፊው ቁጣቸውን በትዕዛዝ ጥንካሬና በማመናጨቅ ሊገልጹ ቢሞክሩም ሊያረካቸው አልቻለም፡፡ እናም ትንሽ ተክዘው በማሰብ ‹‹ችግሩን›› በመመርያ ሊያስተካክሉት ፈለጉ፡፡ ሠራተኛ የመቅጠር ኃላፊነት ያለባቸውን የበታች ሹማምንት እርጉዝ እንዳይቀጥሩ ያልተጻፈ ማሳሰቢያ አስተላለፉ፡፡ ሹማምንቱም ከሕግ በላይ የሚፈሩትን ማሳሰቢያ በተግባር ለመፈጸም ረዥም ጉዞ ተጓዙ፡፡ የሴት ተቀጣሪ ሆድ መመልከት፣ በቀጥታ መጠየቅ፣ መረጃ ማጣራት፤ ይህን ምርመራ አልፎ በገሃድ ከተገኘም የማሰናበት ዕርምጃ በመውሰድ በኃላፊው ፊት ባለሟልነትን ለማግኘት ተጣጣሩ፡፡ ከተወሰኑ ወራት በኋላም ጥረታቸው ተሳካ፡፡ ማጣሪያውን አልፋ የተቀጠረችው ሠራተኛ፣ የሙከራ ጊዜዋን ሳትጨርስ እርግዝናዋ ታወቀባት፡፡ ሹማምንቱም ‹‹በሙከራ ጊዜ ሠራተኛን ማሰናበት ምክንያት አይፈልግም›› በሚል የተሳሳተ ብሂላቸው ሠራተኛዋን አሰናበቷት፡፡

እንዲህ ዓይነቱ ታሪክ በየድርጅቶች ሲፈጸም መስማት እየተለመደ መጥቷል፡፡ እርጉዝ ሚስት ያላቸው የሥራ መሪዎች፣ የሠራተኞቻቸውን እርግዝና በሰብዓዊነት ለመመልከት ግን ማስተዋል አጥተዋል፡፡ ተወልደው የተፈጠሩ፣ ኑረው ልጅ ያፈሩ ሁሉ ጉዳዩን ከራሳቸው ሲያርቁት ይታያሉ፡፡ ችግሩ በሁሉም ሰው ላይ የሚደርስ ሃቅ ነው፡፡ ከሞራል አመክንዮ ባለፈ፣ ሕጉም ቢሆን እንዲህ ዓይነቱን ኢ ሰብዓዊ ድርጊት በዝምታ አይመለከተውም፡፡ ሕጉ ነፍሰ ጡር ሴት ከመውለዷ በፊት፣ በወለደች ጊዜና ከወለደች በኋላ ጥበቃ እንደሚገባት ዝርዘር ድንጋጌዎችን ቀርጿል፡፡ ነፍሰጡሯ ሴት፣ ሠራተኛ በሆነች ጊዜ፣ ከመቀጠሯ በፊት፣ በሥራ ላይ እንዲሁም በስንብት ጊዜ የተለየ ጥበቃ እንደሚገባት ይደነግጋል፡፡ ታዲያ የሰብአዊ መብት ጥሰቱ ምንጭ ምንድን ነው? ነፍሰጡር ሴትን እንዳትቀጠር መከልከል፣ በሥራ ላይ እያለችም ያለአግባብ ማሰናበትን ሕጉ እንዴት ይመለከተዋል? ችግሩ እንዴት ሊፈታ ይችላል? የሚሉትን ነጥቦች በአጭሩ በዚህ ጽሑፍ ለመመልከት እንሞክር፡፡

የእርጉዝ ሠራተኛ መብቶች
ሰው በመሆናቸው ከሚጠበቁላቸው መብቶች እኩል፣ ሴቶች በሴትነታቸው ሊከበሩላቸው የሚገቡ መብቶች አሉ፡፡ ከእነዚህ መብቶች ውስጥ አንዱና ዋናው ሴቶች በተፈጥሮ ከታደሏቸው ውስጥ ከእናትነት ፀጋ ጋር የተያያዘው አንዱ ነው፡፡ ሴቶች ነፍሰጡር በሚሆኑ ጊዜ ለእነሱ፣ ለሕፃኑ ጤንነትና መልካም ኑሮ፣ ኅብረተሰቡና መንግሥት አዎንታዊ ድጋፍ ማድረጋቸው ግድ ነው፡፡ ይህ ድጋፍ በአግባቡ መሰጠቱ ደግሞ ጤናማ ቤተሰብ ለመመሥረት፣ ብቁ ተተኪ ትውልድ ለማፍራትና በአጠቃላይ የኅብረተሰብን ሕልውና ቀጣይነት ለማረጋገጥ ያለው ሚና አሌ አይባልም፡፡ ሴቶች በዓለም ዓቀፍ ሰብዓዊ መብቶች ስምምነቶች፣ በአገሮች ሕግጋት፣ እንዲሁም በብሔራዊ ሕጎች የተረጋገጡ ልዩ ልዩ መብቶች አሏቸው፡፡

ነፍሰጡር ለሆነች ሴት የሰብዓዊ መብቶች፣ በዓለም አቀፍ ስምምነቶች
በዓለም ዓቀፍ ደረጃ በተባበሩት መንግሥታት አማካይነት በሴቶች መብት ዙርያ የተፈረመው ቀዳሚና ገዥ ስምምነት በሴቶች ላይ የሚደረግ ማንኛውንም ዓይነት አድሎአዊነትን ለማስወገድ የተፈረመው ስምምነት Convention On the Elimination of All Forms of Discrimination Against Women የሚባለው ነው፡፡ ይህ ሰነድ፣ ዓላማው የሴቶችን እኩልነት በተለያዩ መስኮች ማረጋገጥ ሲሆን፣ ከፀደቀበት እ.ኤ.አ. ከ1977 ጀምሮ ኢትዮጵያን ጨምሮ ብዙ አገሮች ፈርመውታል፡፡ በዚህ ስምምነት ሴቶች በጋብቻ ወይም በወሊድ ምክንያት አድሎአዊ ልዩነት እንዳይደረግባቸው ብቻ ሳይሆን የመሥራት መብታቸውን ለማረጋገጥም አገሮች ተገቢ ዕርምጃዎችን ለመውሰድ ግዴታ ገብተዋል፡፡

በዚህ መሠረት ሴቶች በእርግዝና ወይም በወሊድ ምክንያት ከሥራ እንዳይባረሩ፣ የወሊድ ፈቃድ ከክፍያ ጋር እንዲሰጣቸውና ከወሊድ ሲመለሱ የነበራቸውን ጥቅምና የሥራ ልምድ ሳያጡ እንዲቀጥሉ፣ ወላጆች የቤተሰብ ኃላፊነትን ከሥራ ግዴታና ከማኅበራዊ ኑሮ ተሳትፎ ጋር አጣምረው እንዲይዙ ለማበረታታት፣ አስፈላጊ ድጋፍ ሰጪ ማኅበራዊ አገልግሎቶች፤ በተለይም የሕፃናት መንከባከቢያዎች በየቦታው እንዲቋቋሙና እንዲደራጁ ለማድረግ፣ በእርግዝና ጊዜ ለጤንነታቸው አደገኛ መሆናቸው የተረጋገጡ የሥራ ዓይነቶችን ለይቶ በመቆጣጠር ለሴቶች ልዩ ጥንቃቄ ለማድረግ አገሮች ተስማምተዋል፡፡

አገሮች ይህን የሴቷን መብቶች ለማረጋገጥ ሕግ የማውጣት፣ አድሎአዊነት ያላቸውን ሕጎች የማሻሻል እንዲሁም ሕጎች ተፈፃሚ እንዲሆኑ የማድረግ ግዴታ ተጥሎባቸዋል፡፡

እ.ኤ.አ. በ1989 የፀደቀውና አገራችን የፈረመችው የሕፃናት መብቶች ስምምነት (UN convention on the rights of the child)፣ ከሕፃናት መጠበቅ ጋር የእናቲቱ መብቶች እንዲጠበቁ ይደነግጋል፡፡ ይህ የሕግ ሰነድ በመግቢያው ላይ ሕፃናት የቅድመ ወሊድና የድህረ ወሊድ በቂ እንክብካቤ እንዲሰጣቸው የሚያስገድድ ሲሆን፣ በዝርዝር ድንጋጌዎቹም ለነፍሰጡሮችና ለአጥቢ እናቶች ተገቢ አገልግሎት መስጠቱን የማረጋገጥ ግዴታ በፈራሚ አገሮች ላይ ጥሏል፡፡ ተመሳሳይ ጥበቃዎች በአኅጉር አቀፍ ደረጃም የአፍሪካ የሕፃናት መብቶች ቻርተርና የአፍሪካ የሴቶች ፕሮቶኮል የተባሉት ሰነዶች ተቀርፀዋል፡፡

ነፍሰጡር ሴቶች በሥራ ላይ ያላቸውን መብቶች በግልጽ በመደንገግ ዘርዘር ያሉ ጥበቃዎችን የያዘው የዓለም የሥራ ድርጅት ስምምነቶች (International Labour Organization Conventions) ናቸው፡፡ ከእነዚህ ስምምነቶች ውስጥ እ.ኤ.አ. በ1952 በዓለም የሥራ ድርጅት የወጣውን ስምምነት ያሻሻለው የ2000ው (Maternity Protection Convention (Revised) ቀዳሚ ነው፡፡

ስምምነቱ ሴት ሠራተኞች ያሉበትን ነባራዊ ሁኔታ ያገናዘበና የመንግሥትና የሕዝብ የጋራ ኃላፊነት ለሆነው እርግዝና በቂ ጥበቃ ለማድረግ ያለመ ነው፡፡ ስምምነቱ እርጉዝ ሴቶች ለራሳቸው ወይም ለልጆቻቸው ጤንነት በማይመቹ የሥራ ሁኔታዎች እንዳይሠሩ ይከለከላል፤ ነፍሰጡር ሴቶች የሕክምና ማስረጃ ባቀረቡ ጊዜ ይወልዳሉ ተብሎ ከተገመተበት ጊዜ ጀምሮ ከ14 ሳምንት የማያንስ የወሊድ ፈቃድ መብት እንዳላቸው ይደነግጋል፡፡ ስምምነቱ ነፍሰጡር ሠራተኞች ሲታመሙ፣ ከእርግዝና ወይም ከወሊድ ጋር የተያያዙ ሕመሞች ሲሰማቸው ሁሉ በአገሮች ብሔራዊ ሕግ የሚወሰን የሕመም ፈቃድ እንዲያገኙ ደንግጓል፡፡ እንደየአገሮቹ ልምድ፣ በእርግዝና ጊዜ የሚከፈል የገንዘብ ጥቅማጥቅም ለነፍሰጡር ሴቶች እንዲሰጥ ይደነግጋል፡፡ ይህን መሰል ግዴታ ግን ባላደጉ አገሮች በተለየ ሁኔታ እንዲፈፀም ስምምነቱ ያመለክታል፡፡ ይኸውም ነፍሰጡሮች ሊያገኙ በሚገባው የሕክምና ወጪ መጠን ብቻ እንዲሆን አድርጓል፡፡ በሌላ በኩል ስምምነቱ አሠሪዎች፣ ሴት ሠራተኞች በእርግዝናቸው ወቅት ከሥራ እንዳይሠናበቱ የወሊድ ፈቃዳቸውን ጨርሰው ሲመለሱ በተመሳሳይ የሥራ ቦታ እንዲመለሱ፣ ለእነርሱ ካልጠቀማቸው በስተቀር በቅጥር ወቅት የእርግዝና ምርመራ እንዳይጠይቁ በመከልከል አሠሪዎች ላይ ግዴታ ይጥላል፡፡

የነፍሰጡር መብቶች በኢትዮጵያ ሕግ
አገራችን ቀደም ሲል የተገለጹትን ዓለም አቀፍና አኅጉር አቀፍ የሰብዓዊ መብት ስምምነትና የዓለም የሥራ ድርጅት ስምምነትን የፈረመች በመሆኗ የነፍሰጡር ሠራተኞችን ልዩ ልዩ መብቶች የማክበር ግዴታ አለባት፡፡ በዚህ ረገድ ሕገ መንግሥታችን በአንቀፅ 35፣ ሴቶች የወሊድ ፈቃድ ከሙሉ የደመወዝ ክፍያ ጋር የማግኘት መብት እንዳላቸው በመግለጽ፣ የወሊድ ፈቃድ ርዝመት ሴቷ የምትሠራውን ሥራ ሁኔታ፣ የሴቷን ጤንነት፣ የሕፃኑንና የቤተሰቡን ደህንነት ከግምት ውስጥ በማስገባት በሕግ እንደሚወሰን ይደነግጋል፡፡ ስለዚህ የወሊድ ፈቃድና ሌሎች ነፍሰጡር ሴት ያላት መብቶች ሕገ መንግሥታዊ ዋስትና ስለተሰጣቸው፣ ዝርዝር ሕጎች መብቶቹን ቢያጠናክሩ እንጂ ሊሸረሽሩ እንደማይገባ ሊታወቅ ይገባል፡፡

ሕገ መንግሥቱን መሠረት በማድረግ የአሠሪና ሠራተኛ ጉዳይን የሚገዙ ሕጎች የነፍስጡር ሠራተኞችን መብቶች በዝርዝር ደንግገዋል፡፡ በዚህ ረገድ በተለያየ ጊዜ ቢሻሻልም በሴቶች መብቶች ረገድ ተመሳሳይ የሥራ ሁኔታዎችን የደነገገው የአሠሪና ሠራተኛ አዋጅ ቁጥር 377/96 ቀዳሚ ነው፡፡ ይህ አዋጅ በክፍል ስድስት የሴቶችና የወጣት ሠራተኞችን የሥራ ሁኔታ የሚደነግግ ሲሆን፣ አንቀፅ 87 እና 88 የነፍሰጡር ሠራተኞችን የተለያዩ መብቶች ይዘረዝራል፡፡ በዚህ ሕግ ጥበቃ የሚደረግላቸው መብቶች  ለሴቶች ከባድ ወይም ለጤናቸው ወይም ለእርግዝናቸው ጎጅ የሆኑ ሥራዎች ላይ ያለመሥራት መብት፤የሌሊትና የትርፍ ሰዓት ሥራዎች ያለመሥራት መብት፤ነፍሰጡሯ የምትሠራው ሥራ አደገኛ ከሆነ ወደ ሌላ የሥራ ቦታ ተመድባ የመሥራት መብት ፤ነፍሰጡር ሴት ከሥራ ያለመሰናበት መብት ፤ነፍሰጡር ሴት የወሊድ ፈቃድ የማግኘት መብት ይገኙበታል ፡፡

ቅድመ ቅጥር የእርግዝና ምርመራ ሕጋዊነት
በዚህ ጽሑፍ መግቢያ እንደተመለከትነው አሠሪዎች እርጉዝ ወይም ለማርገዝ የቀረበች ሠራተኛን ለመቅጠር ያላቸው ተነሳሽነት በጣም አናሳ ስለሆነ እርጉዝ ላለመቅጠር የተለያዩ ዘዴዎችን ይተገብራሉ፡፡ ውጤታማ ባይሆንም ሆድን መፈተሽ፣ ስለእርግዝና ሁኔታ መረጃ መሰብሰብ ወይም በቀጥታ መጠየቅ ከተለመዱት ዘዴዎች ውስጥ የሚታወቁ ናቸው፡፡ አሠሪው እነዚህ መረጃዎችን በመሰብሰብ ላለመቅጠር ውሳኔው መነሻ ቢያደርገውም፣ በግልጽ በእርግዝና ምክንያት አለመቅጠርን አያሳውቅም፡፡ የሚሰጠው ምክንያት ከተወዳዳሪዋ የትምህርት ወይም የሥራ ልምድ ወይም በቃለ መጠይቅ የተገለጠ ችሎታ ውስጥ እንዲወድቅ ያደርጉታል፡፡ ስለዚህ በአገራችን የተለመደው የእርግዝና ሁኔታ በተዘዋዋሪ መንገድ የሴቷን የሥራ መብት እንደሚገድብ ነው፡፡ በሌሎች አገሮች ግን ሠራተኛ ሲቀጠር የእርግዝና ምርመራ እንዲያደረግ የሚጠየቅበት አጋጣሚ አለ፡፡ አንዳንዶቹ ምርመራውን የሚያከናውኑት ለሴቷ ጥቅም ሲሆን፣ ሌሎቹ ደግሞ የሴቷን ትርፋማነት ለመጨመር በማሰብ ላለመቅጠር ነው፡፡ 

ጉዳዩን ከጽንሰ ሐሳብ ትንታኔ ለመጀመር፤ የአሜሪካ ምሁራን የእርግዝና ምርመራ እንዲደረግ ማስገደድን ከጾታ አድልዎ አንፃር ይመለከቱታል፡፡ እንደእነርሱ አመለካከት፣ ጾታን መሠረት በማድረግ የሚፈጸም አድልዎ (Sex Discrimination) በሁለት መንገድ ይታያል፡፡ የመጀመርያው ከልዩነት አንፃር (The difference Approach) ሲሆን፣ የጾታ አድልዎ የሚኖረው ሴቷ በተመሳሳይ ሁኔታ ያለ የተቃራኒ ጾታ (ወንድ) በተመዘነበት መስፈርት ሳትመዘን ስትቀር የሚኖረው አድልዎ ነው፡፡ በዚህ እይታ ወንድና ሴት ተመሳሳይ በሆኑባቸው ሁኔታዎች በሙሉ እኩል አያያዝ ይገባቸዋል፡፡ ምሁራኑ በዚህ እይታ እርግዝናን መሠረት አድርጎ የሚፈጸም ልዩነት የጾታ አድልዎ አለመሆኑን ይስማማሉ፡፡ ምክንያቱም ወንዶቹ ስለማያረግዙ በተመሳሳይ ሁኔታ የሚገኙ ወንዶች የተሻለ አያያዝ ሊያገኙ ይችላሉ ተብሎ ስለማይታሰብ ነው፡፡ በተቃራኒው ያለው ሁለተኛው እይታ ከመጎዳት አንፃር (Disadvantage Approach) የሚታየው ነው፡፡

 በዚህ እይታ፣ የጾታ ልዩነቱ ላይ ሳይሆን በልዩነቱ ምክንያት የሚመጡ ውጤቶችን ዕውቅና በመስጠት ላይ ያተኩራል፡፡ ይህ እይታ በኅብረተሰቡ የዳበረ፣ ሴቶች ያላቸውን ድርሻ ዝቅ የማድረግ ልማድን ዕውቅና ስለሚሰጥ፣ የአንድ ድርጊት ውጤት ሴቶችን የሚጎዳ ከሆነ ጻታዊ አድልዎ እንዳለ ይገመታል፡፡ በዚህ መሠረት ወንዶችና ሴቶች እኩል ባይወዳደሩበትም በእርግዝና ሁኔታቸው ሳቢያ ሴቶች የሚጎዱ መሆኑ ከተረጋገጠን ጾታዊ አድልዎ ለመኖሩ በቂ አስረጅ ይሆናል፡፡ ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ሰነዶችም የሁለተኛውን እይታ እንደሚከተሉ ለአድልዎ (Discrimination) ከሚሰጡት ትርጉም መረዳት አስቸጋሪ አይደለም፡፡ በእነዚህ ሰነዶች ለአድልዎ የተሰጠው ትርጉም፣ ድርጊቱ በራሱ ሴቶችን በልዩነት የሚመለከት፣ የሚጎዳ፣ የሚያገልል መሆኑ ብቻ ሳይሆን የድርጊቱ ውጤትም የሚጎዳ/የሚያገልል ከሆነ አድልዎ ይኖራል፡፡

በዚህ መነሻነት ቅድመ ቅጥር የእርግዝና ምርመራን ከተመለከትን፣ ጾታዊ አድልዎ መሆኑን እንገነዘባለን፡፡ ሴቶች ሥራ ለመቀጠር ልጅ የመውለድ ተፈጥሮአዊ ችሎታቸው ጫና ከፈጠረባቸው አድልዎ ይኖራል፡፡ ቅድመ ቅጥር ምርመራ አድልዎ የሚሆነው በውጤቱ ነው፡፡ የእርግዝና ምርመራ ውጠቱ እርግዝና መከሰቱን ካሳየ፣ ሴቷ ሥራ አትቀጠርም ወይም ከሥራ እንድትባረር ይደረጋል፡፡ ይህም ሴቶችና ወንዶች በኅብረተሰቡ ሊኖራቸው በሚችለው ሚና ላይ ልዩነትን ያሰፋል፡፡ በተጨባጭም ከሌሎች ምክንያቶች ጋር በመተባበር በእርግዝና ሁኔታ የሚደርስ አድልዎ ሥራ ያላቸው ሴቶች ቁጥር እንዲቀንስ የራሱን አስተዋጽኦ ያደርጋል፡፡ ከዚህ በመነሳት፣ ዓለም አቀፍ የሥራ ድርጅት ኮንቬንሽን 183፣ በአንቀጽ 9(1) አባል አገሮች ሴቶች በእርግዝናቸው ምከንያት ሥራ እንዳይከለከሉ፣ ከሥራ ጋር በተያያዘ የሚያጋጥሙ የአድልዎ ተግባራት እንዲቀሩ የተለያዩ ዕርምጃዎችን የመውሰድ ግዴታ ጥሎባቸዋል፡፡

የአገራችንንም ሕገ መንግሥት ብንመረምር ቅድመ ቅጥር ምርመራን በግልጽ ሕገወጥ ባያደርገውም፣ ስለሰብዓዊ መብት በደነገገበት ክፍሎቹ የሚገኙት መብቶችና ትርጓሜዎች ሴቷን ላለመቅጠር ወይም ከሥራ ለማሰናበት ከሆነ ተገቢ እንደማይሆን ማስቀመጡን ለመገንዘብ ይቻላል፡፡ የሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 25 እና 35፣ ሴቶችና ወንዶች በሕግ ፊት እኩል እንደሆኑ ስለሚደነግግ እርግዝናን መሠረት አድርጎ የሚፈጸም አድልዎ ሴቶችና ወንዶች በሕግ ፊት እኩል እንዳይታዩ ያደርጋቸዋል፡፡ በቅድመ ቅጥር እርግዝና ምርመራው ሥራ ሊከላከሉ የሚችሉት ሴቶች ብቻ በመሆናቸው እኩልነትን ያፋልሳል፡፡ በሌላ እይታም አድልዎው ሴቷ በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 35(9) መሠረት የቤተሰብ ምጣኔ የመጠቀም ነፃነቷን ይጋፋል፡፡ ምርመራው ሴቷ በነፃነት የምትወልዳቸውን ልጆችና በመካከላቸው የሚኖረውን ርቀት የመወሰን መብቷን ይጎዳል፡፡ በሌላ በኩል በዕውቀትና በሥራ ልምድ ብቁ የሆነችን ሠራተኛ እርጉዝ በመሆኗ ብቻ አለመቅጠር በአንቀጽ 41 እንደተደነገገው፣ ሴቷ መተዳደሪያዋን፣ ሥራዋንና ሙያዋን የመምረጥ መብቷን እንዳትጠቀም ያደርጋታል፡፡ የሕገ መንግሥቱን ሐሳብ የሚደግፉ ዝርዝር ድንጋጌዎች በሌሎች የአሠሪና ሠራተኛ ሕግጋት ውስጥም እናገኛለን፡፡

በአጠቃላይ ሴት ሠራተኛን በእርግዝና ውጤት ምክንያት አለመቅጠር ወይም መካን መሆኗን ለቅጥር መነሻ ማድረግ፣ ወይም በመነሻ ጉዳዩ እንደተስተዋለው፣ ለመቀጠር የመጣችን ሴት ስለእርግዝናዋ ሁኔታ ወይም ዕቅዷ መጠየቅ ሕገ መንግሥታዊ አይሆንም፡፡ ሴቷ እርጉዝ በመሆኗ የማትቀጠር ከሆነ ከወንዶች አንፃር ብቻ ሳይሆን፣ ካልወለዱ፣ ከማይወልዱ ወይም ላለመውለድ ከወሰኑ ሴቶችም አንፃር የጾታ አድልዎ ይፈጸምባታል፡፡ ይህ መርህ ግን ልዩ ሁኔታዎች ሊኖሩት ይችላሉ፡፡ የዓለም አቀፉ የሥራ ድርጅት ኮንቬንሽን 183 አንቀጽ 9(2)፣ በብሔራዊ ሕግጋት የእርግዝና ምርመራ ሥራ ለማመልከት መስፈርት ሊሆን የሚገባው፣ የሴቷን ወይም የሕፃኑን ጤንነት ከአደጋ ለመከላከልና ለእርጉዟ ጤንነት ምቹ የሥራ ቦታ ለማመቻቸት ሲሆን ብቻ እንደሆነ ደንግጓል፡፡ አገራችን ይህንን ስምምነት የፈረመች በመሆኗ በመርህ ደረጃ የቅድመ ቅጥር የእርግዝና ምርመራን የምትከላከልና በልዩ ሁኔታ ግን ለሴቷ ጥቅም ከሆነ የምትፈቅድ መሆኑን መገንዘብ ይቻላል፡፡

እርግዝና ለስንብት እንደ ምክንያት
አንዳንድ አሠሪዎች ቅድመ ቅጥር የእርግዝና ምርመራ ካልተሳካላቸው ያለ በቂ ምክንያት ያረገዘች ሴትን የሚያሰናብቱበት አጋጣሚ አለ፡፡ ከላይ የተመለከትነውን ታሪክ ለአብነት ብንወስድ፣ አሠሪው ሠራተኛዋ እርጉዝ በመሆኗ ማሰናበቱን ባይገልጽም፣ ለስንብቷ ምክንያት ሆኗል፡፡ የአሠሪና ሠራተኛ ሕጉ በሙከራ ላይ ያለ ሠራተኛ ያለ በቂ ምክንያት እንዲሰናበት አይፈቅድም፡፡ ሠራተኛው በ45 ቀናት የሙከራ ጊዜ ለሥራው ብቁ አለመሆኑ ከተረጋገጠ ብቻ ሊሰናበት ይችላል፡፡ ስለዚህ አንዳንድ አሠሪዎች በሙከራ ጊዜ ሠራተኛ የዓይኑ ቀለም ካላማራቸውም የማሰናበት ምሉዕ ሥልጣን ያላቸው ይመስላቸዋል፡፡ ሕጉ ግን ሠራተኛው በሥራው ተመዝኖ ብቁ አለመሆኑ በአሠሪው ሊረጋገጥ እንደሚገባ ያስቀምጣል፡፡

እርጉዝ ሴትን በተመለከተ የዓለም የሥራ ድርጅት ኮንቬንሽን 138ም ሆነ የአሠሪና ሠራተኛ ጉዳይ አዋጁ በስንብት ወቅት ልዩ ጥበቃ ያደርጋሉ፡፡ የኮንቬንሽኑ አንቀጽ 8(1) ‹‹It shall be unlawful for an employer to terminate the employment of a woman during her pregnancy or absence on maternity leave or during a period following her return to work to be prescribed by national laws or regulations, except on grounds unrelated to the pregnancy ,birth of the child and its consequences on nursing›› በማለት ከእርግዝና ጋር በተያያዘ ምክንያት ሴት ሠራተኛን ከሥራ ማሰናበት ሕገወጥ መሆኑን አስቀምጧል፡፡

የአሠሪና ሠራተኛ ሕጉ፣ ሴት ሠራተኛ ነፍሰጡር በሆነችበት ጊዜና ከወለደችበት ቀን ጀምሮ በአራት ወር ጊዜ ውስጥ አሠሪው ከሥራ ሊያሰናብታት እንደማይችል ይደነግጋል፡፡ ይህ የሴቷን የሥራ ዋስትና በአግባቡ ያረጋግጣል፡፡ አሠሪው፣ ሴት ሠራተኛውን በማጣቱ ምክንያት ለመሥራት ቢቸገር እንኳ ለማሰናበት ሕግ አይፈቅድለትም፡፡ ያለው አማራጭ በእርሷ ቦታ ለተወሰነ ጊዜ ሌላ ሠራተኛ ቀጥሮ ወይም ተክቶ ማሠራት ነው፡፡ ሕጉ ሴቶች በእርግዝና ምክንያት እንዳይሰናበቱ ክልከላ ያደርጋል እንጂ ከዚህ ውጭ ባሉ፣ ከእርግዝና ጋር ተያይዥነት በሌላቸው ምክንያቶች ስንብት እንዳይፈፀም አይከለክልም፡፡

 ነፍሰጡር ሠራተኛ በፈቃዷ ሥራ ብታቋርጥ፣ ያለማስጠንቀቂያ ሊያሰናብቱ የሚያስችሉ ጥፋቶችን ብትፈጽም እንዲሁም በሥራ መቀዝቀዝ ወይም መክሰር ምክንያት የሠራተኛ ቅነሳ በሚደረግበት ጊዜ ነፍሰጡር የሆነችው ሠራተኛ ተቀናሽ ከተደረገች የአሠሪው ድርጊት ሕገወጥ ላይሆን ይችላል፡፡ ሕጉ በሠራተኛ ቅነሳ ወቅት ነፍሰጡር ሴቶች ከሁሉም ሠራተኛ መጨረሻ እንዲቀነሱ በመደንገግ ልዩ ጥበቃ ያደረግላቸዋል፡፡

የችግሩ ምንጮችና መፍትሔዎች
አሠሪዎች እርጉዝ ሠራተኛን ለመቅጠር የሚቸገሩት፣ ከቀጠሩም በኋላ ያለአግባብ የሚያሰናብቱት በዋናነት ከግንዛቤ ማነስ የተነሳ ነው፡፡ አሠሪ የድርጅቱን ትርፍ ለመጨመር ስለሚያስብ ሠራተኞቹ በወጥነት በሥራ ቦታ እየተገኙለት ምርታማ እንዲሆኑ ይፈልጋል፡፡ እርጉዝ ሠራተኛ በወሊድ ፈቃድ ጊዜና ከዚያ በኋላ ልጇን በማጥባት ከሥራ ቦታ አለመገኘቷ አሠሪው ይህን ቀዳሚ ዓላማውን እንዳያስፈጽም ይከለክለዋል፡፡ ያም ሆኖ በእርጉዝ ሠራተኞች ምክንያት አጠቃላይ ትርፉ የቀነሰበትን ድርጅት ማግኘት አስቸጋሪ ነው፡፡ አሠሪዎች ሕጉ ለእርጉዝ ሴት የሚሰጠውን የጥበቃ አመክንዮ በአግባቡ ተረድተው ቢፈጽሙት ግን ‹‹ከትርፍ ባለፈ›› ኅብረተሰባዊና ሰብዓዊነት የተሞላበት ሥራ ለመሥራት ያስችለዋል፡፡ ከላይ እንደተገለጸው ለእርጉዝ ሴት የሚሰጥ ድጋፍ ጤናማ ቤተሰብ ለመመሥረት፣ ብቁ ተተኪ ትውልድ ለማፍራትና በአጠቃላይ የኅብረተሰብ ህልውና ቀጣይነትን ለማረጋገጥ ነው፡፡

 አሠሪዎችም የእርጉዝ ሴቶችን መብቶች ባከበሩ መጠን ይህንን የሕጉን ሰፊ ዓላማ መተግበራቸውን ሊያውቁ ይገባል፡፡ ለእርግዝና ጥበቃ መስጠት የመንግሥትና የኅብረተሰቡ የጋራ ኃላፊነት መሆኑን ዓለም አቀፍ ስምምነቶችም በአግባቡ ገልጸውታል፡፡ በመሆኑም አሠሪዎች ይህን ዓላማ እንዲገነዘቡና እንዲፈጽሙት በመንግሥት፣ በአሠሪዎችና ሠራተኞች ፌዴሬሽን እንዲሁም በተለያዩ ባለድርሻ አካላት የግንዛቤ መፍጠርያ መርሐ ግብር አቅዶ መከወን ይገባል፡፡

ሌላው የችግሩ ምንጭ የአፈጻጸም ክፍተት ነው፡፡ የሕጉ ድንጋጌዎች በአሠሪዎች አለመከበራቸው፣ የእርጉዝ ሴት ሠራተኞች መብት እንዲጣስ ምክንያት ሆኗል፡፡ የአሠሪና ሠራተኛ ሕጉን አፈጻጸም ማረጋገጥና ጥብቅ ክትትል ማድረግ አማራጭ የሌለው መፍትሔ ነው፡፡ የሥራ ሁኔታ ተቆጣጣሪዎች (Labour Inspectors) በአዋጁ ከተሰጧቸው ኃላፊነቶች አንዱ ችግሮች ከመከሰታቸው በፊት በየድርጅቶቹ ያለውን የሕጉን አፈጻጸም መከታተል ነው፡፡ ይህ አገልግሎት ብዙ ሠራተኞች በሚቀጥሩ ፋብሪካዎች፣ የፋይናንስ ተቋማትና የግል ድርጅቶች ቢፈጸም፣ ተቆጣጣሪዎቹ ጥናት ቢያደርጉ፣ ድንገተኛ ምርመራ ቢያከናውኑ፣ እንዲሁም ጥቆማን በመቀበል ችግሮችን ለይተው መፍትሔ ቢሰጡ መሻሻል ይኖራል፡፡ እርግዝናን መሠረት ያደረገ አድልዎ እንደሌሎች የሠራተኛ መብት ጥሰቶች የተንሰራፋ ባይሆንም የሚታዩትን ችግሮች ከጅምሩ ማስወገድ ‹‹ሳይቃጠል በቅጠል›› ይሆናል፡፡

ሌላው በሴቶቹ በኩል የሚታይ ክፍተት ነው፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ ‹‹ሕዝቤ ባለማወቅ ጠፍቷልና›› እንዲል የመብት አለመፈፀም ዋናው መነሻ ምክንያቱ ባለመብቶቹ መብታቸውን አለማወቃቸው ነው፡፡ መብቱን ያላወቀ መጣሱን አያውቅም፤ መፍትሔውም ለመፈለግ አይተጋም፡፡ ስለዚህ ሴቶች ነፍሰጡር በሆኑ ጊዜ ያላቸውን መብቶች ማወቅ የሚገባቸው ሲሆን፣ የማያውቁ ከሆነ ደግሞ እንዲያውቁ ማድረግ ይገባል፡፡ ካወቁ ደግሞ ተጥሰው በተገኙ ጊዜ ለበላይ አስተዳደር አካላት፣ ለሕዝብ ዕንባ ጠባቂ ተቋም ወይም ለፍርድ ቤት አቤቱታ በማቅረብ መብታቸውን ሊጠይቁ ይገባል፡፡ መብትን መጠየቅ የዘመናዊነት መገለጫ ነው፡፡ አሠሪዎችም ቢሆኑ ነፍሰጡር ሴት ያላት መብት እናታቸው ወይም እህታቸው ወይም ሚስታቸው ወይም ልጃቸው ሊኖራት የሚገባ ሰብዓዊ መብት መሆኑን በማመን መብት አክባሪ ሊሆኑ ይገባል፡፡

ያለሴቶች ተሳትፎ አብዮቱ ግብ አይመታም አይደል የሚባለው፡፡ ከአሠሪዎችም በበጎ አስተማሪነት የሚጠቀሱ ስለሚገኙ የእነሱን ፈለግ መከተል ድርጅቱን ሕዝባዊ ያደርገዋል፡፡ የሠራተኞቻቸውን የእርግዝና ወጪ መሸፈን፣ ሠራተኞቻቸው ሲወልዱ ስጦታ ማበርከት፣ ሕጉ ካስቀመጠው ወራት በላይ የወሊድ ፈቃድ መስጠት፣ ሴት ሠራተኞች ልጅ ከመንከባከብ ጎን ለጎን ሥራቸውን ለመሥራት እንዲያመቻቸው በሥራ ቦታ የሕፃናት መንከባከቢያ (Day care) ማመቻቸት በአንዳንድ አሠሪዎች መፈጸሙን ልብ ይሏል፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጸሐፊውን በኢሜይል አድራሻቸው This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it. ማግኘት ይቻላል፡፡