መነሻ ገጽ - ሌሎች አምዶች - ሕግ እና ፖለቲካ - በህግ አምላክ - ሰበር የዘነጋው የዓቃቤ መዝገብ ኃላፊነት
Buy Valtrex Online Buy Albuterol inhaler Online Buy Prinivil Online
25 August 2013 ተጻፈ በ 

ሰበር የዘነጋው የዓቃቤ መዝገብ ኃላፊነት

በፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት አስገዳጅ የሕግ ትርጉም መሰጠት ከጀመረበት ጊዜ ጀምሮ የሕግ አተረጓጎምን በተመለከተ የሕግ ባለሙያዎችን ያነቁ ክስተቶች ተፈጥረዋል፡፡

በየአውዱ የሚቀርቡ ትችቶች እንደሚያሳዩት፣ የተወሰኑት የሰበር ችሎቱን ጥንካሬ የሚያሳዩ አንዳንዶቹ ደግሞ ክፍተቶችን ነቅሰው የሚያወጡ ናቸው፡፡ በሰበር ችሎቱ ከሚስተዋሉ ክፍተቶች ተብለው ከሚነሱት መካከል ከሕጉ ግልጽ ይዘት የራቀ ትርጉም መስጠት፣ በሕግ ግልጽ መሠረት የሌለውን የኅብረተሰቡን እውነታ መቀበል፣ ለሕግና የፍሬ ነገር ክርክሮች ተመሳሳይ እልባት አለመስጠት ይገኙበታል፡፡ የዛሬው ጽሑፍም ሰበር ችሎቱ የሰጠውን አንድ ፍርድ ፍትሐዊነቱን መዳሰስ ያለመ ነው፡፡ ጉዳዩ ባንኮች ለሚሰጡት ብድር የሚቀበሉትን መያዣ አመዘጋገብና የዓቃቤ መዝገቡን እንዲሁም የመዝጋቢውን አካል (የመንግሥትን፣ የመሬት አስተዳዳርን፣ የማዘጋጃ ቤትን፣ የአገልግሎት አስተዳደርን) ኃላፊነት ይመለከታል፡፡ የጉዳዩን አመጣጥ በመግለጽ የሰበር ፍርዱንና ፍትሐዊነቱን ለመመልከት እንሞክራለን፡፡ 

የጉዳዩ አመጣጥ

ወጋገን ባንክ መቀሌ ለሚገኙ አንድ ደንበኛውና ለባለቤታቸው ብር 1,700,000 ብድር ይሰጣል፡፡ ለብድሩ ዋስትና ይሆን ዘንድ በብድሩ መጠን የሚገመት በመቀሌ ከተማ አስተዳደር የሚገኝ ቤት በመያዣነት ይቀበላል፡፡ ባንኩ ለአስተዳደሩ ንብረቱ ከዕዳና እገዳ ነፃ መሆኑ እንዲረጋገጥለት ጠይቆ ነፃ በመሆኑ መያዣው በአስተዳደሩ ተመዝግቧል፡፡ ተበዳሪዎቹ ከባንኩ የወሰዱትን ብድር ባለመክፈላቸው ባንኩ በአዋጅ ቁጥር 97/90 በተሰጠው ሥልጣን መሠረት ንብረቱን ለሀራጅ በማቅረብ በብር 2,000,000 ሸጦታል፡፡ ባንኩ የከተማውን መሬት አስተዳደር ስመ ንብረቱን እንዲያዛውር ቢጠይቀውም፣ ፈቃደኛ ባለመሆኑ በፍርድ ቤቱ ተገዶ ስም እንዲያዞርና የደረሰውንም ጉዳት እንዲክስ ክስ አቅርቧል፡፡ ተከሳሽ በሰጠው መልስ ንብረቱ በመያዣነት ከመመዝገቡ በፊት በሌላ የአፈጻጸም ክስ በፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤትና በመቀሌ ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት የዕግድ ትዕዛዝ ተሰጥቶበታል፡፡ በመሆኑም ባንኩ ንብረቱ የእግድ ትዕዛዝ ያለበት መሆኑን እያወቀ የፈጸመው ተግባር በመሆኑ መሬት አስተዳደሩ ስሙንም አያዛውርም፣ ለባንኩ ኪሳራ የሚከፍልበትም ምክንያት የለም ሲል ተከራክሯል፡፡ 

የክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት የግራ ቀኙን ክርክር ከመረመረ በኋላ ባንኩ ለተበዳሪዎቹ የገንዘብ ብድር ከመስጠቱ በፊት በመያዣነት የቀረበለት የማይንቀሳቀስ ንብረት ከዕዳና እገዳ ነፃ መሆኑን ያላጣራና ያላረጋገጠ መሆኑንና ከተበዳሪዎቹ ጋር የብድር ውል ከተዋዋለ በኋላ ለተጠሪ ደብዳቤ የጻፈ በመሆኑ፣ በችግሩ መከሰት ለተፈጠረው ኪሳራ የመሬት አስተዳደሩ ኃላፊነት የለበትም በማለት ወስኗል፡፡ ባንኩ ለፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት የይግባኝ ቅሬታውን ያቀረበ ሲሆን፣ ፍርድ ቤቱ የክልሉን ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፍርድ አጽንቷል፡፡ ፍርድ ቤቱ ባንኩ ንብረቱ ከዕዳና እገዳ ነፃ መሆኑ ከመረጋገጡና መያዣው ከመመዝገቡ በፊት የብድር ውል ከተበዳሪዎች ጋር ተዋውሏል፡፡ በመሆኑም ስህተቱ የመሬት አስተዳደሩ ሳይሆን የባንኩ በመሆኑ የክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት የሰጠው ፍርድ የሚነቀፍበት ምክንያት የለም ሲል ፍርድ ሰጥቷል፡፡ 

ጉዳዩን በመጨረሻ የተመለከተውም የፌዴራሉ ሰበር ሰሚ ችሎት ጉዳዩን ከፍሬ ነገርና ከማስረጃ ምዘና ጋር በማያያዝ ችሎቱ ሊመለከተው እንደማይችል ገልጿል፡፡ በሌላ በኩል ችሎቱ፣ ‹‹ባንኩ ከአዋጅ ቁጥር 97/90 ጋር ያቀረበውን ክርክር ሰበር ችሎቱ ባንኩ ስመ ንብረት እንዲዛወርለት መጠየቅ የሚችለው ንብረቱን በመያዣነት ከመያዙ በፊት ተገቢውን ጥንቃቄ በማድረግ ማጣራት የሚገባውን ጉዳይ አጣርቶና በሕግ የተጣለበትን ኃላፊነት ተወጥቶ ሲገኝ ነው፡፡ በተያዘው ጉዳይ ባንኩ በፍትሐ ብሔር ሕግ ቁጥር 3051 (2) መሠረት ማጣራት የሚገባውን በማጣራት ሳይሆን ከቅን ልቦና ውጭ በሆነ ሁኔታ ንብረቱን በመያዣነት በመያዝ ብድር ያበደረ መሆኑ በፍርድ ተረጋግጦ የተወሰነበት በመሆኑ የባንኩ ክርክር ተቀባይነት የለውም፤›› ሲል ፍርድ ሰጥቷል፡፡ 

የመያዣ አመዘጋገብ ሥርዓት

የማይንቀሳቀስ ንብረት መያዣ በቀጥታ በሕግ ወይም በፍርድ ወይም በውል ወይም ደግሞ በኑዛዜ ሊቋቋም ይችላል፡፡ በየትኛውም መንገድ የተቋቋመ የማይንቀሳቀስ ንብረት መያዣ በሕግ ፊት የፀና እንዲሆን ዋስትና የተገባለትን የገንዘብ መጠን መግለጽና መያዣውም መመዝገብ ያስፈልገዋል፡፡ (የፍትሐ ብሔር ሕግ ቁጥር 3047 እና 3052) የመያዣውን አመዘጋገብ ሁኔታ የፍትሐ ብሔር ሕግ ቁጥር 3053 በማይንቀሳቀስ ንብረት አመዘጋገብ ሥርዓት መሠረት እንደሚፈጸም ስለሚገልጽ ስለማይንቀሳቀስ ንብረት ምዝገባ የተቀመጡትን ድንጋጌዎች መመልከት ግድ ይላል፡፡ 

የፍትሐ ብሔር ሕጉ ሦስተኛ መጽሐፍ ንብረትን የተመለከቱ ድንጋጌዎችን ይዟል፡፡ ከእነዚህ ድንጋጌዎች ውስጥ የማይንቀሳቀስ ንብረት ምዝገባን የተመለከተው ከአንቀጽ 1553 – 1646 ያለው ክፍል አንዱ ነው፡፡ ይህ ክፍል በንጉሠ ነገሥቱ ዘመን የነበሩ አደረጃጀቶችን መሠረት በማድረግ የማይንቀሳቀስ ንብረትን አመዘጋገብ ሥርዓት ያስቀምጥ እንጂ ተፈጻሚነቱ በአሁኑም ዘመን የቀጠለ ነው፡፡ ለዚህ አስረጂ የሆነው የድንጋጌዎቹ በሌላ ሕግ አለመሻራቸውና በተግባርም የምዝገባው ሥርዓት መኖሩ ብቻ ሳይሆን አስገዳጅ የሕግ ትርጉም ለመስጠት ሥልጣን ያለው የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት ድንጋጌዎቹን መሠረት አድርጎ ለጉዳዮች እልባት መስጠቱ ጭምር ነው፡፡ በሌላ በኩል ግን የድንጋጌዎቹ ተፈጻሚነትን አከራካሪ የሚያደርግ የፍትሐ ብሔር ሕጉ ድንጋጌ አለ፡፡ የፍትሐ ብሔር ሕግ ቁጥር 3063 እና 3067 ጣምራ ንባብ የማይንቀሳቀስ ንብረት የአመዘጋገብ ሥርዓት በሥራ ላይ የሚውልበት ቀን በድንጋጌ ባለመገለጹ፣ ከሕጉ በፊት የነበረው ልማድ እንጂ ድንጋጌዎቹ ተፈጻሚ አይሆኑም፡፡ ሆኖም በአንዳንድ ከተሞች የማይንቀሳቀስ ንብረት ምዝገባ በአዋጅ ወይም በደንብ በማዘጋጃ ቤት ወይም መሬት አስተዳደር የሚፈጸም በመሆኑ የሕግ መሠረት አያጣም፡፡ ለምሳሌ በአዲስ አበባ በደንብ ቁጥር 28/2002 አገልግሎቱ እንደሚፈጸም ጸሐፊው ባደረገው ማጣራት አረጋግጧል፡፡ በዚህ ጽሑፍ የተመለከትነው ጉዳይ የትግራይን ክልል የመያዣ ምዝገባ ስለሚመለከት አስተያየቱ ቅቡል እንዲሆን ለጸሐፊው ተደራሽ ባይሆንም የክልሉን ሕጉ መመልከት አግባብነት እንደሚኖረው ጸሐፊው ያምናል፡፡ ያም ሆኖ በሁሉም ክልሎች የምዝገባው ሥርዓት ስለሚተገበር የሕጉ ክፍተት አካዳሚያዊ ካልሆነ ተግባራዊ ረብ አይኖረውም፡፡  

 እነዚህ ድንጋጌዎች የማይንቀሳቀስ ንብረት ምዝገባን፣ የመዝጋቢውን ግዴታ፣ የአመዘጋገቡን ሥርዓት እንዲሁም ምዝገባው የሚያስከትለውን ውጤት ደንግገዋል፡፡ ለዚህ ጉዳይ የሚጠቅመንን የተወሰኑትን እንመልከት፡፡ 

የማይንቀሳቀስ ንብረት ዋና ዋና መዝገቦች የሚባሉት ባለሀብትን የሚመለከት መዝገብና የማይንቀሳቀስ መያዣን የሚመለከት መዝገብን የሚያቋቁመው ነው፡፡ (የፍትሐ ብሔር ሕግ ቁጥር 1556) ሕጉ መያዣን ካልተመዘገበ የፀና እንደማይሆን የደነገገው የመያዣ አመዘጋገብ ሥርዓት አደራጅቶ ነው፡፡ የማይንቀሳቀስ ንብረት መያዣን የሚመዘግቡት ዓቃቢያነ መዛግብት ሲሆኑ መዛግብቱ ለሕዝብ ግልጽ ናቸው፡፡ ዓቃቢያነ መዛግብት ጥያቄ በቀረበላቸው ጊዜ ስለአንድ የማይንቀሳቀስ ንብረት የተጻፈውን ቃል ትክክለኛ ግልባጭ መስጠት ይገባቸዋል፡፡ (የፍትሐ ብሔር ሕግ ቁጥር 1562) ይህንንም የሚያደርጉት ስለ ትክክለኛ ግልባጭነቱ በፊርማቸው አረጋግጠው የመዝገብ ቤቱን ማኅተም አሳርፈው እንዲሁም ግልባጩ ወይም ምስክር ወረቀቱ የተሰጠበትን ቀንና ዓመተ ምሕረት ገልጸው ስለመሆኑ ሕጉ ደንግጓል፡፡

የማይንቀሳቀስ መያዣን የተመለከተ መዝገብ ምን ይዘት ሊኖረው እንደሚገባም ሕጉ አመላክቷል፡፡ ከእነዚህ ውስጥ መያዣውን ለማቋቋም፣ ለመለወጥ፣ ወይም ለማስቀረት የተደረጉ ጽሑፎች (የፍትሐ ብሔር ሕግ ቁጥር 1573)፣ በፍርድ ቤት መያዣውን እንዲሰጥ ለማድረግ የቀረቡ ጥያቄዎች (የፍትሐ ብሔር ሕግ ቁጥር 1574) ይገኙባቸዋል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ አንድ አመዘጋገብ ገንዘብን ወይም መያዣ የሆነ ነገርን የሚመለከት የሆነ እንደሆነ ይህ ገንዘብ ወይም መያዣ የሆነው ነገር በአሃዝና በፊደል መመልከት አለባቸው፡፡ (የፍትሐ ብሔር ሕግ ቁጥር 1591) በጣም በሚነበብ አኳኋን ቀኑ፣ ወሩ፣ እና ዓመተ ምሕረቱ መጻፍ አለበት (የፍትሐ ብሔር ሕግ ቁጥር 1592) ዓቃቤ መዝገቡ ለሚቀርብለት እያንዳንዱ ጥያቄ ለዚህ ጥያቄ የሚሆን ተራ ቁጥር ከመዝገቡ ውስጥ ይሰጠዋል፡፡ መያዣን በተመለከተ የተደረገ ምዝገባ ገንዘብ ጠያቂውን፣ መያዣ የተሰጠበትን የገንዘብ ልክ፣ ዕዳው የሚከፈልበትን ቀን፣ የወለድ መጠኑ ወዘተ. መግለጽ ይኖርበታል፡፡ (የፍትሐ ብሔር ሕግ ቁጥር 1695)፡፡

 

የዓቃቤ መዝገቡ ግዴታ

ዓቃቤ መዝገቡ አመዘጋገቡን ሕጉ ባስቀመጠው ሥርዓት መሠረት ለመፈጸም የሚያስችሉት ፎርሞችና መዛግብት የተዘጋጁለት ሲሆን፣ በጥንቃቄ ጉድለት በአመዘጋገብ የሚፈጽመው ስህተት ኃላፊነትን ያስከትልበታል፡፡ ዓቃቢያነ መዛግብቱ በሥራቸው ለሚያደርሱት ጥፋት ተጠያቂ ሲሆኑ፣ መንግሥትም ከውል ውጭ ኃላፊነት ይኖርበታል፡፡ የፍትሐ ብሔር ሕግ ቁጥር 1566 በግልጽ እንደሚያስቀምጠው የማይንቀሳቀሱ ንብረቶች ዓቃቢያነ መዛግብት ያዥዎች ያለባቸውን ግዴታ ባለመፈጸማቸው ወይም በመጥፎ ሁኔታ በመፈጸማቸው ወይም ዘግይቶ በመፈጸማቸው ምክንያት በሌሎች ሰዎች ላይ ጉዳት ቢያደርሱ ኃላፊዎች ናቸው፡፡ በዚሁ ድንጋጌ ንዑስ ቁጥር 2 ላይ ደግሞ ‹‹ከውል ውጭ ስለሚደርሱ ኃላፊነቶች በተጻፈው ድንጋጌ መሠረት ለዚህ ጉዳይ መንግሥትም በኃላፊነት ይጠየቃል፤›› ሲል በማያሻማ መልኩ ደንግጓል፡፡ ይህ ኃላፊነት ከውል ውጭ ኃላፊነት ሕግ አንቀጽ 2126 ጋር የተጣጣመ ነው፡፡ በፍትሐ ብሔር ሕጉ ‹‹ለሌላ ሰው ተግባር ኃላፊ ስለመሆን›› በሚለው ክፍል አንቀጽ 2126(2) የመንግሥት ሹም ወይም ሠራተኛ ያደረሰው ጥፋት የመንግሥቱን ሥራ ሲሠራ የደረሰ የሥራ ጥፋት እንደሆነ የተጎዳው ሰው ኪሳራ ከመንግሥት ላይ ለመጠየቅ እንደሚችል ተደንግጓል፡፡ በዚህ ድንጋጌ መሠረት ሠራተኛው ላደረሰው ጉዳት መንግሥት ኃላፊ የሚሆነው ሠራተኛው ያጠፋው ጥፋት የሥራ ጥፋት (Professional Fault) በሆነ ጊዜ ነው፡፡ ሠራተኛው ያደረገው ጥፋት የግል ጥፋቱ የሆነ እንደሆነ መንግሥት ኃላፊነት እንደማይኖርበት በፍትሐ ብሔር ሕግ ቁጥር 2126(3) ተገልጿል፡፡ ‹‹የሥራ ጥፋት›› የሚለውን አከራካሪ ቃል ሕጉ ትርጉም ለመስጠት የሞከረ ሲሆን፣ በፍትሐ ብሔር ሕግ ቁጥር 2127 መሠረት ‹‹ጥፋቱ እንደ ጥፋት ሆኖ የሚቆጠረው ጥፋት አድራጊው በዚህ ጥፋት ላይ የወደቀው በቅን ልቦና በሥልጣኑና ለሥራው ክፍል መልካም ያደረገ መስሎት የፈጸመው ሲሆን ነው፡፡›› ከዚህ ውጭ በሆነው በማናቸውም ሌላ ጉዳይ ግን እንደ ጥፋት ሆኖ ይቆጠራል በማለት ሠራተኛው ከቅን ልቦና ውጭ በፈጸመው ጥፋት መንግሥት በሠራተኛው ጥፋት በሦስተኛ ወገን ለደረሰው ጉዳት ኃላፊነት እንደማይኖርበት ይደነግጋል፡፡ 

የምዝገባ ውጤት

ምዝገባ የራሱ የሆነ ኢኮኖሚያዊና ሕጋዊ ጥቅሞች አሉት፡፡ በዋናነት የማይንቀሳቀስ ንብረት ምዝገባ ለባለቤት የመብት ማረጋገጫና ባለሀብት መሆኑን የሚያስረዳበት ነው፡፡ ምዝገባው ከባለቤቱ ውጭ ያሉ ሰዎች ንብረቱ የእርሱ ስለመሆኑ ተረድተው መብቱን እንዲያከብሩለት ግዴታ ይጥልባቸዋል፡፡ ከመያዣ ጋር በተያያዘም ምዝገባው ከንብረቱ ጋር ውል ለሚዋዋሉ ወገኖች መሠረታዊ መረጃ ሰጪ ይሆናል፤ በንብረቱ ላይ መብት አለን የሚሉም ሰዎች በሕጉ ሥርዓት በሚፈጽሙት ምዝገባ መሠረት የመብት ቅደም ተከተል ይፈጥራል፡፡ ማንኛውም ሰው በማይንቀሳቀስ ንብረት መዝገብ የገባውን ጽሑፍ መኖሩን አላውቅም ነበር ብሎ መከራከር አይችልም፡፡ (የፍትሐ ብሔር ሕግ ቁጥር 1640) ምዝገባው ለሕዝብ ግልጽ በመሆኑ ከማይንቀሳቀሰው ንብረት አንፃር የተመሠረተ፣ የተለወጠ ወይም የቀረ መብት መኖር አለመኖሩን ከምዝገባው ይረጋገጣል፡፡ በአንድ ንብረት ላይ ብዙ ምዝገባዎች ሊኖሩ የሚችሉ ሲሆን፣ ቀድሞ ያስመዘገበ ባለመብት የተሻለ ቅድሚያ ይኖረዋል፡፡ በፍትሐ ብሔር ሕግ ቁጥር 1641 መሠረት በተመዘገቡት ሁለት ጽሑፎች መካከል ስለሚነሳው ክርክር መብቱን መጀመሪያ ላስመዘገበው ሰው ቅድሚያ ይሰጠዋል፡፡ በፍርድ ቤት አጋዥነት የሚቀርብ ጥያቄም በሦስተኛ ወገኖች ላይ መቃወሚያ ለመሆን የሚችለው ፍርዱ ከተመዘገበ ነው፡፡ (የፍትሐ ብሔር ሕግ ቁጥር 1643)፡፡

በፍርዱ ላይ የቀረበ ምልከታ

ቀደም ባሉት የጽሑፉ ክፍሎች የሰበር ችሎቱን ፍርድና ለምልከታው መሠረት የሚሆኑ የሕግ ድንጋጌዎችን ተመልክተናል፡፡ በዚህ ክፍል የሰበሩን ፍርድ መነሻ በማድረግ ፍትሐዊነቱን የሚሞግት ምልከታ ለማድረግ እንሞክራለን፡፡ 

የባንኮች አሠራር

የመያዣ ንብረት ምዝገባ በተግባር የሚከናወነው በአብዛኛው በባንኮች ነው፡፡ ባንኮች ለሚሰጡት ብድር የሚቀበሉትን የመያዣ ንብረት የሚያስመዘግቡ ሲሆን አፈጻጸሙ ልዩነት አለው፡፡ አንዳንዶቹ ዕዳና እገዳ አለመኖሩን አረጋግጠህ መዝግብልን ሲሉ አንዳንዶቹ ደግሞ የመያዣውን ውል በመላክ መዝግብልን በማለት ዓቃቤ መዝገቡን የሚጠይቁበት አጋጣሚ አለ፡፡ የሁለተኛው አሠራር (ዕዳና እገዳ መኖሩን ሳያጣራ ማስመዝገብ) የባንኮችን የመያዣ መብት የሚጎዳ ሲሆን፣ ዕዳቸውንም እንደይሰበስቡ ያደርጋቸዋል፡፡ በተያዘው መዝገብ የተከሰተው ባንኩ ዕዳና እገዳ አጣርቶ የማስመዝገቡን ግዴታ ተወጥቷል አልተወጣም የሚለው ነው፡፡ በዚህ ረገድ ባንኩ በክፍሉ መሬት አስተዳደር ዕዳና እገዳ አለመኖሩ ተጣርቶ እንዲመዘገብለት በጠየቀው መሠረት የተመዘገበለት ስለመሆኑ ማስረጃ አያይዟል፡፡ ይህ ክርክር የፍሬ ነገር ጉዳይ ቢሆንም የክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤትና የፌዴራሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ያለፉበት ምክንያት ግልጽ አይደለም፡፡ የፌዴራሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ባንኩ የብድር ውል ከተዋዋለ በኋላ የመያዣውን ውል ሲፈርም ዕዳና እገዳ ለማጣራት መንቀሳቀሱን ተገቢ እንዳልሆነ ተችቷል፡፡ የዚህን አቋም የሚያግዝ የሕግ መሠረት በአገራችን ባለመኖሩ የችሎቱ ፍርድ ፍትሐዊነት ይጎድለዋል፡፡ ሰበር ችሎቱ ዕዳና እገዳ የማረጋገጥ የባንኮችን ግዴታ የፍሬ ነገርና የማስረጃ ምዘና ጉዳይ ብቻ በማድረግ ሊኖረው በሚችለው ጠባብ ቀዳዳ ወጥቶ ፍርድ ሰጥቷል፡፡ ሆኖም ፍሬ ነገርን ከሕግ፣ ማስረጃ ምዘናን ከመሰማት መሠረታዊ መብት አንፃር መለየት ግን በጣም አስቸጋሪ መሆኑን ሁሉም ይረዳዋል፡፡ የሰበር ችሎቱ ምዝገባው በሕጉ አግባብ ተከናውኗል ወይስ አልተከናወነም የሚለውን የሕግ ጭብጥ መሠረት ቢያደርግ ግን ስለ ምዝገባ ሥርዓት የተቀመጠውን የሕጉን ይዘት በመተንተን ፍትሕ በሰጠ ነበር፡፡

የመያዣው ቅቡልነት

በተያዘው ጉዳይ በመያዣው ንብረት ላይ ሁለት ምዝገባ መኖሩ በግራ ቀኝ ክርክር ተረጋግጧል፡፡ ቀዳሚው የፍርድ ቤት እግድ ሲሆን ሁለተኛው እግዱ ባለበት የተፈጸመው የባንኩ የመያዣ መብት ምዝገባ ነው፡፡ ሁለቱም ምዝገባ በመዝገቡ ላይ እስከተገኙ ድረስና አንዱ ምዝገባ አለመኖሩ እስካልተረጋገጠ ወይም እስካልተዘረዘረ ድረስ የመያዣው ቅቡልነት ሊመረመር ይገባል፡፡ ሰበር ችሎቱን ጨምሮ ጉዳዩን በሁሉም ደረጃ የተመለከቱት ፍርድ ቤቶች የያዙት አቋም ባንኩ በንብረቱ ላይ ዕዳና እገዳ መኖር አለመኖሩን ባላረጋገጠበት ሁኔታ የቅድሚያ መብት አይኖረውም የሚል አንድምታ አለው፡፡ ይህ አቋም እግድ ኖሮ የተመዘገበው የመያዣ ውልን ቅቡልነት ያልመረመረ በመሆኑ በውጤት ደረጃ የተሳሳተ መደምደሚያ ላይ የሚያደርስ ይሆናል፡፡ ለምሳሌ በተለያየ ምክንያት ቀደም ሲል በፍርድ ቤት የተሰጡት የእግድ ትዕዛዛት ቢነሱ የመያዣው መብት በንብረቱ ላይ ተፈጻሚ ይሆናል፡፡ ይህ ከፍርድ ቤቶቹ አካሄድ መገንዘብ የሚቻለው ነጥብ ሲሆን፣ ሕጉን በጥሞና ለመረመረው ግን መደምደሚያው የተሳሳተ መሆኑን በቀላሉ መረዳት ይችላል፡፡ 

የፍትሐ ብሔር ሕግ ቁጥር 3049 የማይንቀሳቀስ ንብረት መያዣ የፀና እንዲሆን መያዣውን የሚሰጠው ሰው ችሎታ ሊኖረው እንደሚገባ ይደነግጋል፡፡ በዚህ አንቀጽ ንዑስ አንቀጽ 2 መሠረት ለራሱ ዕዳ ዋስትና እንዲሆን አንድ የማይንቀሳቀስ ንብረትን ለዕዳ በመያዣነት ለመስጠት የሚቻለው የማይንቀሳቀሰውን ንብረት ለመሸጥ ችሎታ ያለው እንደሆነ ነው፡፡ ንብረቱን እንዳይሸጥ የተከለከለ ወይም መሸጥ የማይችል ሆኖ የመያዣ ውል ከመሠረተ ውሉ ዋጋ እንደማይኖረውና እንደማይፀና የፍትሐ ብሔር ሕግ ቁጥር 3050 በግልጽ ደንግጓል፡፡ በተያዘው ጉዳይ ባንኩ መያዣውን የመሠረተው ንብረቱ ላይ የተሰጠ እግድ (ለመሸጥ ለመለወጥ የሚከላከል የፍርድ ቤት ትዕዛዝ) ባለበት በመሆኑ የባንኩ የመያዣ ውል በሕግ ፊት የፀና አይደለም፡፡ መያዣው ከተመሠረተ በኋላ እንኳን እግዱ ቢነሳ ይህ ኩነት ወደ ኋላ ተመልሶ መያዣውን የፀና እንዲሆን ሊያደርገው እንደማይችል በፍትሐ ብሔር ሕግ ቁጥር 3050 (2) ላይ ተደንግጓል፡፡ ከዚህ በመነሳት ጉዳዩን የተመለከቱት ፍርድ ቤቶች እግድ ባለበት ሁኔታ ባንኩ የገባው የመያዣ ውል ስለመጽናት አለመጽናቱ ጭብጥ በመመሥረት መዝገቡን ቢመረምሩት ሕጉን የተከተለ አካሄድ በሆነ ነበር፡፡ ሰበር ችሎቱም የሥር ፍርድ ቤቶችን የያዙትን ጭብጥ በማስተካከል የተከሰተውን መሠረታዊ የሕግ ስህተት በተገቢው የፍትሐ ብሔር ሕጉ ድንጋጌ መርምሮ ፍትሐዊ ፍርድ በሰጠ ነበር፡፡

የዓቃቤ መዝገቡ ኃላፊነት

በክርክሩ ሒደት ለመረዳት የሚቻለው ባንኩ በንብረቱ ላይ ዕዳና እገዳ አለመኖሩን አረጋግጦ መያዣውን ማስመዝገቡን ነው፡፡ ምዝገባው እንዲፈጸም የተደረገው ደግሞ ዓቃቤ መዝገቡ እግዱ መኖሩን እያወቀ በሰጠው የተሳሳተ ማስረጃ ነው፡፡ የመቐለ ከፍተኛ ፍርድ ቤት በመዝገብ ቁጥር 10749 ጥር 17 ቀን 2005 ዓ.ም. በሰጠው ፍርድ ዓቃቤ መዝገቡ የተሰጠውን የመንግሥት ኃላፊነት ወደ ጎን በመተው በፈጸመው የሙስና ወንጀል ሰባት ዓመት ተፈርዶበታል፡፡ ከዚህ አንፃር ዓቃቤ መዝገቡ ለባንኩ በሰጠው የተሳሳተ መረጃ መሠረት በመያዣ ውሉ መሠረት ባንኩ ዕዳውን እንዳያስመልስ ስላደረገው ጥፋቱ የዓቃቤ መዝገቡ ነው፡፡ የፍትሐ ብሔር ሕግ ቁጥር 1566 በግልጽ እንደሚያስቀምጠው ዓቃቤ መዝገብ ያለበትን ግዴታ ባለመፈጸሙ ወይም በመጥፎ ሁኔታ በመፈጸሙ በሦስተኛ ወገን ላይ ለሚያደርሰው ጉዳት ኃላፊ ነው፡፡ ስለዚህ የባንኩ የመጀመሪያ አማራጭ በተሳሳተ ምዝገባ ምክንያት ሊመለስ ያልቻለውን ገንዘብ ዓቃቤ መዝገቡን በመክሰስ እንዲመለስ ማድረግ ነው፡፡ በተያዘው መዝገብ ዓቃቤ መዝገቡ ባልተከሰሰበት ሁኔታ ችሎቱን ጨምሮ ጉዳዩን የተመለከቱት ፍርድ ቤቶች የዓቃቤ መዝገቡን ኃላፊነት አለመመርመራቸው ተገቢ ቢሆንም፣ የመሬት አስተዳደሩን ኃላፊነት ሲመረምሩ ግን ከሠራተኛው ጥፋት የተነሳ መሬት አስተዳደሩ ያለበትን ኃላፊነት አለመመርመራቸው ተገቢ አልነበረም፡፡ ወደኋላ እንደምንመለከተው ሰበር ችሎቱ ለፍርዱ መሠረት ሊያደርገው ይገባው የነበረውን ድንጋጌ (1566) ቸል በማለት ለጉዳዩ አግባብነት የሌለውን ድንጋጌ መጥቀሱ በአካሄዱ ፍትሐዊነት ጎድሎታል፡፡ 

የመሬት አስተዳደሩ ኃላፊነት

በተያዘው ጉዳይ ከተነሱት ክርክሮች አንፃር ፍርድ የሚፈልገው ጭብጥ እግድ ባለበት ሁኔታ የተፈጸመ ሽያጭ መሬት አስተዳደር ስም ማዛወር አለበት ወይስ የለበትም የሚለው ነው፡፡ ማዛወር ካለበት ደግሞ ባለማዛወሩ ምክንያት ባንኩ ለደረሰበት ጉዳት ኃላፊ ይሆናል ወይስ አይሆንም ነው፡፡ ሁለቱም ጭብጦች የሚያነጥኑት በመሬት አስተዳደሩ ኃላፊነት ላይ በመሆኑ ኃላፊነቱ ሊመረመር ይገባ ነበር፡፡ ሠራተኛው ባጠፋው ጥፋት መሬት አስተዳደር ተጠያቂ የሚሆንበት የሕግ አግባብ በፍትሐ ብሔር ሕግ ቁጥር 1566 እና 2126 የጣምራ ንባብ ውስጥ ይወድቃል፡፡ በእነዚህ ድንጋጌዎች መሠረት መሬት አስተዳደር የመያዣ ንብረትን በመመዝገብ የሚኖርበት ኃላፊነት ከውጭ ውጪ ሲሆን፣ ኃላፊነቱ የሚኖረውም ሠራተኛው ያጠፋው ጥፋት የሥራ ጥፋት ከሆነ ነው፡፡ በተያዘው ጉዳይ ከቀረቡት ማስረጃዎች ለመረዳት እንደሚቻለው እግድ ባለበት ሁኔታ ሠራተኛው የመያዣውን ውል የመዘገበው በሙስና ስለመሆኑ የወንጀሉ ፍርድ አስረጂ ነው፡፡ ይህ ምክንያት ደግሞ በፍትሐ ብሔር ሕግ ቁጥር 2127 መሠረት ጥፋቱ ‹‹በቅን ልቦና በሥልጣኑና ለሥራው ክፍል መልካም ያደረገ መስሎት›› የፈጸመው አይደለም፡፡ ጥፋቱ የተፈጸመው በተሳሳተው ምዝገባ የግል ጥቅም ለማግኘት በማሰብ ከቅን ልቦና ውጭ በሆነ የወንጀል ድርጊት ነው፡፡ እንዲህ በሆነ ጊዜ ደግሞ ጥፋቱ የሥራ ጥፋት ሳይሆን የሠራተኛው የግል ጥፋት በመሆኑ መሬት አስተዳደሩ በሠራተኛው ጥፋት ምክንያት ከውል ውጭ ኃላፊነት አይኖርበትም፡፡ የሰበር ችሎቱ ፍርድ በውጤት ደረጃ ከዚህ አተረጓጎም ጋር ቢጣጣምም፣ አካሄዱ እውነታውን የሚደብቅና የተሳሳተ የሕግ ድንጋጌን የሚያጣቅስ ነው፡፡ ፍትሕ ደግሞ ከውጤት አንፃር ብቻ ሳይሆን በአካሄድም የሚመዘን ነው፡፡ 

ያለአግባብ በፍርዱ የታዩ ነጥቦች

በዚህ ጉዳይ ከሥር ፍርድ ቤት ጀምሮ እስከ ሰበር የታዩ ምልከታ የሚፈልጉ ነጥቦች አሉ፡፡ የመጀመሪያው ሰበር ችሎቱ የፍትሐ ብሔር ሕግ ቁጥር 3051 መሠረት አድርጎ የሰጠው ትንተና ነው፡፡ ችሎቱ ድንጋጌውን በመጥቀስ ባንኩ ማጣራት የሚገባውን ሳያጣራ ከቅን ልቡና ውጭ መያዣ መቀበሉን ተችቷል፡፡ ይህ ድንጋጌ የማይንቀሳቀስ ንብረት መያዣን የሚሰጥ ሰው ከክፍሉ አስተዳደር የተሰጠው የምስክር ወረቀት ለችሎታው ምስክር እንደሚሆን፣ በተጭበረበረ የባለቤትነት የምስክር ወረቀት ከሆነ ደግሞ ከቅን ልቡና ውጭ በዚህ ሰነድ መያዣ የተቀበለ ሰው ውል ፈራሽ እንደሚሆን ይደነግጋል፡፡ ይህ ድንጋጌ ስለ መያዣ አመዘጋገብ በተነሳው ክርክር ጠቃሚነት የለውም፡፡ አከራካሪው የመያዣው አመዘጋገብ ነው እንጂ የመያዣው ባለቤት የባለቤትነት ሥልጣን አይደለም፡፡ ሁለተኛው ሰበር ችሎቱ ከቅን ልቡና ጋር አያይዞ የሰጠው ትችት ነው፡፡  ባንኩ ዕዳና እገዳ መኖሩን ሳያረጋግጥ የመያዣ ምዝገባ አከናውኛለሁ ማለቱ ከቅን ልቦና ውጭ ነው ሲል ተንትኗል፡፡ ከመያዣ ምዝገባ ጋር በተያያዘ ቅን ልቡና ሊመረመር የሚገባው ዓቃቤ መዝገቡ ግዴታውን ስለመወጣት አለመወጣቱ በሚደረገው ክርክር ነው እንጂ ከመያዣ ምዝገባው ጋር በተያያዘ አይደለም፡፡ ማንኛውም ሰው ከመዝጋቢ አካል ከሚሰጠው መረጃ ባለፈ ዕዳና እገዳ ስለመኖሩ በቅን ልቡና የሚያደርገው ማጣራት በሕግ ባልተደነገገበት ሁኔታ የባንኩ የቅን ልቡና በችሎቱ መመርመሩ ተገቢ አይደለም፡፡ ሦስተኛው ነጥብ ከብድር ውልና ከመያዣ ውሉ አፈራረም ቅደም ተከተል ጋር የተያያዘ ነው፡፡ የፌዴራሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ባንኩ የብድር ውሉን ከተፈራረመ በኋላ የመያዣ ውሉን መፈራረሙ ዕዳና እገዳውን ላለማጣራቱ እንደ አስረጂ ቆጥሮታል፡፡ ይህ የፍርድ ቤት ትንተና የብድር ውልና የመያዣ ውሉ በተመሳሳይ ወቅት ካልተፈረሙ በሕግ ተቀባይነት የሌለው አስመስሎታል፡፡ የፍትሐ ብሔር ሕግ ቁጥር 3046 ንባብ ግን የመያዣ ውል በባህርይው የዋና ግዴታ ተቀጽላ (Subsidiary obligation) እንደመሆኑ ከዋናው ግዴታ በኋላ፣ ከዋናው ግዴታ ጋር ወይም ወደ ፊት ለሚደረግ ግዴታ ሊመሠረት ይችላል፡፡ ከዚህ አንፃር የብድር ውልና የመያዣ ውል በተመሳሳይ ጊዜ ካልተፈረሙ መያዣው ዋጋ አይኖረውም የሚለው ትንተና ተቀባይነት የለውም፡፡ የመያዣ ውሉ ተፈጻሚነትና የመብቱ ቀዳሚነት የሚወሰነው በምዝገባ ቀኑ መሠረት እንጂ የመያዣ ውሉ ወይም የብድር ውሉ በተፈረመበት ባለመሆኑ የፍርድ ቤቶቹ ትንተና አስፈላጊም አልነበረም፡፡

እንደማጠቃለያ

በዚህ ጽሑፍ የተመለከትነው የሰበር ፍርድ በጭብጥነት ሊመረምር ይገባው የነበረው የእግድ ትዕዛዝ በነበረበት የማይንቀሳቀስ ንብረት የተመሠረተ የመያዣ ውል ቅቡልነትና የመሬት አስተዳደሩን ኃላፊነት እንደነበር ጸሐፊው ያምናል፡፡ ከመዝገቡ ለመረዳት እንደተቻለው መያዣው የተመዘገበው እግድ ባለበት ሁኔታ በመሆኑ ፈራሽ ነው፡፡ ይህ ስህተት የተፈጠረው በዓቃቤ መዝገቡ የግል ጥፋት በመሆኑ ባንኩ ለደረሰበት ጉዳት መጠየቅ የሚችለው ዓቃቤ መዝገቡ ነው፡፡ ያም ሆኖ የአስተዳደሩ ግዴታ የሚመነጨው ዓቃቤ መዝገቡ በሚሠራው የሥራ ጥፋት እንጂ በዓቃቤ መዝገቡ የግል ጥፋት ባለመሆኑ ባንኩ ለደረሰበት ጉዳት ከውል ውጭ ኃላፊ አይሆንም፡፡ የሰበር ችሎቱ መደምደሚያን ጸሐፊው የሚጋራው ቢሆንም፣ ችሎቱ የሄደበት መንገድና ለፍርዱ መሠረት ያደረገው ድንጋጌ ለጉዳዩ አግባብነት የለውም፡፡ ፍትሕ ከውጤቱ እኩል ሒደቱም በጥንቃቄ የሚመራ ካልሆነ በተከራካሪ ወገኖች ላይ መተማመንን አይፈጥርም፤ በአተረጓጎም ረገድም የአስተማሪነቱ ዋጋ አነስተኛ ይሆናል፡፡ የተፈረደለትም ውስጣዊ እርካታ አይኖረውም፡፡  

ከአዘጋጁ፡- ጸሐፊው የሕግ ጠበቃና አማካሪ ሲሆኑ፣ በኢሜይል አድራሻቸው This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it.  ማግኘት ይቻላል፡፡