መነሻ ገጽ - ሌሎች አምዶች - ሕግ እና ፖለቲካ - በህግ አምላክ - ፍቺና የንብረት ክፍፍል
Buy Valtrex Online Buy Albuterol inhaler Online Buy Prinivil Online
08 September 2013 ተጻፈ በ 

ፍቺና የንብረት ክፍፍል

ይህ ጽሑፍ ያለፈው ሳምንት ቀጣይ ነው፡፡ ባለፈው ሳምንት ‹ጋብቻ ሴቶችና ንብረት…› በሚል በተለይ ሴቶችን ከፍቺና ንብረት ክፍፍል አንፃር የሚያጋጥሟቸውን ችግሮች በማንሳት ሕጉን መሠረት አድርገን ለመተንተን ሙከራ አድርገናል፡፡

የዛሬው ጽሑፍ ደግሞ ከሕጉ ላይ በግልጽ ያልተሸፈኑና በፍርድ ቤቶች የተለያዩ አቋሞች የተያዘባቸውን የንብረት ክፍፍል ጉዳዮች ለማንሳት እንሞክራለን፡፡ 

እንደሚታወቀው በአሁኑ የሕግ ሥርዓት ፍቺ ለማግኘት ቀላል ነው፡፡ ተጋቢዎች በተለያዩ ምክንያቶች ካልተስማሙ የአንደኛውን ጥፋት ማስረዳት ሳይጠበቅ፣ በስምምነት ሳይቀር መፍታት ይቻላል፡፡ ይህ ባህርይ የአሁኑ ሕግ ለቤተሰብ ተቋማዊነት ቦታ አይሰጥም በሚል የሚወቀስበት ቢሆንም የግለሰቦችን (የተጋቢዎቹን) ነፃነት በመጠበቅ አወዳሽ አላጣም፡፡ ፍቺ መወሰን ግን የፍቺ ውጤቶችን የመወሰን ያህል ቀላል አይደለም፡፡ ከፍቺ ውጤቶች አንዱ የንብረት ክፍፍል ሲሆን፣ ይህ ሥርዓት የሚመራው የጋብቻን በንብረት በኩል ያለውን ውጤት መሠረት በማድረግ ነው፡፡ ይህ ማለት በጋብቻው ቆይታ የጋራ ወይም የግል የሆኑትን ንብረቶች በመለየት የጋራ የሆኑትን ለባልና ለሚስት የማከፋፈል ሥራ ነው፡፡ ባልና ሚስት ጋብቻቸውን በሚፈጽሙበት ጊዜ በየግል የነበሯቸው ወይም ከጋብቻ በኋላ በውርስ ወይም በስጦታ በየግላቸው ያገኟቸው ንብረቶች የግል ንብረቶቻቸው ሆነው የሚቀሩ ስለመሆኑ የቤተሰብ ሕግጋቱ ደንግገዋል፡፡ እነዚህ ድንጋጌዎች ግልጽ በመሆናቸው አፈጻጸማቸውን መምራት ቀላል እንደሆነ ማሰብ እንችላለን፡፡ ከሕግ ትንተናው ይልቅ የማስረጃ ምዘናው ያመዝናል፡፡ አንድ ንብረት ከግልና ከጋራ ሀብት ጋር ተቀላቅሎ የተገኘ ከሆነ ግን ሕጉ የግል ወይም የጋራ ተብሎ እንደሚቆጠር በግልጽ አያመለክትም፡፡ ሕጉ በግልጽ የማይሸፍናቸው በጋብቻ ጊዜ ወይም ከጋብቻ በፊት ተገኝተው በጋብቻ ጊዜ የበለፀጉ ሀብቶችም ይኖራሉ፡፡ የጡረታ መብት፣ ድጎማ፣ የቀበሌ ቤት ኪራይ፣ የቀበሌ ቤት የባለይዞታነት መብት፣ የኮንዶሚኒየም እጣ ወዘተ. ሕጉ በግልጽ ያልደነገጋቸው በመሆኑ ሕጉን በማንበብ ብቻ መፍትሔ ማግኘት አይቻልም፡፡ እንኳን ለሕግ ሙያ ባዕድ ለሆነ ዳኞችም በሚነሱት ነጥቦች ላይ ያላቸው አቋም ይለያያል፡፡ ሆኖም የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ችሎት አስገዳጅ የሕግ ትርጉም በመስጠት ሥልጣኑ የመጨረሻ እልባት የሰጠባቸው በመሆኑ፣ ፍርዶቹን መሠረት በማድረግ ለግንዛቤ የሚረዳ ትንተና መስጠት የሕጉን መንፈስ ለማወቅ ለሚፈልግ ጠቃሚ ሳይሆን አይቀርም፡፡ በዚህ መነሻነት በሰበር ችሎቱ የታዩትን ጨምሮ አከራካሪ የሚሆኑትን የጋራ ወይም የግል የንብረት ክፍፍል ነጥቦችን በዚህ ጽሑፍ እናነሳለን፡፡ 

ከጋብቻ በፊት የተጀመረ ቤት

ተጋቢዎች ጋብቻ ከመፈጸማቸው በፊት በግል የቤት መሥሪያ ቦታ ወይም በማኅበር የተገኘ መሬት ይኖራቸውና ቤቱን ከጋብቻ በኋላ ጀምረው ይጨርሱታል፡፡ አንዳንድ ጊዜ ደግሞ ግንባታውን በከፊል ከጋብቻ በፊት ጀምረውት ዋናውን ወይም ብዙውን የቤቱን አካል ከጋብቻ በኋላ ያጠናቅቁታል፡፡ እንዲህ ዓይነት ጉዳዮች ሕጉ በግልጽ መፍትሔ ስለማይሰጣቸው ለፍርድ ቤቶች የፍትሕ ሥራ የሚተው ሆነዋል፡፡ ተጋቢዎች ከተፋቱ በኋላ ሁለት ጠርዝ የያዙ ክርክሮች ያነሳሉ፡፡ አንደኛው ወገን ቦታውን ወይም ጅምር ቤቱን ያገኘሁት (የሠራሁት) ከጋብቻ በፊት በመሆኑ በፍቺ ጊዜ የተሠራው ቤት የግል ሆኖ ይቀራል ይላል፡፡ ሌላው ወገን ደግሞ ምንም እንኳን ቦታው ወይም ጅምር ቤቱ ከጋብቻ በፊት የተገኘ ቢሆንም፣ ዋናው ሥራ የተከናወነው ከጋብቻ በኋላ በደመወዝ ገንዘብ ወይም በባንክ በተገኘ ብድር በመሆኑ ቤቱ የጋራ ነው የሚል ክርክር ያነሳል፡፡ ሰበር ሰሚ ችሎት ለእነዚህ ጭብጦች ገዥ ትርጉም በመስጠት እልባት ሰጥቷል፡፡ 

በአንድ ጉዳይ ሚስት ከጋብቻ በፊት በማኅበር የተመራችው መሬት ነበራት፡፡ በመሬቱ ላይ ቤት ለመሥራት መስከረም 29 ቀን 1979 ዓ.ም. የጀመረች ሲሆን፣ የቤቱ ሥራ ጅምር ላይ እያለ ታህሳስ 26 ቀን 1979 ዓ.ም. ጋብቻ መሠረተች፡፡ ቤት ሥራው አልቆ ቤቱ ለማኅበሩ አባላት የተከፋፈለው በጥቅምት ወር 1980 ዓ.ም. ነው፡፡ ቤቱ ተስፋፍቶ የተሠራውና ሙሉ በሙሉ የተጠናቀቀው ጋብቻው ከተፈጸመ በኋላ ነው፡፡ ቤቱ የተሠራው ሚስት ከጋብቻ በፊት ከባንክ በብድር መልክ በወሰደችው ገንዘብ ሲሆን፣ ብድሩ ባልና ሚስቱ በፍርድ ቤት እስከተፋቱበት 1993 ዓ.ም. ድረስ ሲከፈል ቆይቷል፡፡ ከፍቺው ውሳኔ በኋላ አከራካሪ የሆነው ጭብጥ ቤቱ የጋራ ነው ወይስ የሚስት የግሏ የሚለው ጭብጥ ነው፡፡ ሚስት የቤቱ ብቸኛ ባለቤት መሆኗን ስትገልጽ ባሏ ደግሞ ጋብቻው ፀንቶ ባለበት ጊዜ የተሠራ በመሆኑ የጋራ ነው ሲል ይከራከራል፡፡ 

ጉዳዩን በመጀመሪያ የተመለከተው ፍርድ ቤትና ይግባኝ ሰሚው የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ተመሳሳይ አቋም በመያዝ ለሚስት ወስነዋል፡፡ ‹‹ቤቱ ከጋብቻው በፊት ተጀምሮ የነበረ ስለሆነ የሚስት የግል ሀብት ነው፡፡ ባል ለቤቱ ያወጣው ገንዘብ ግን ታስቦ ይመለስለት፤›› ሲሉ ወስነዋል፡፡ የሰበር ሰሚ ችሎቱ ግን የተለየ አቋም ያንፀባርቃል፡፡ ችሎቱ አከራካሪው ቤት በእርግጥም ቤት የሆነው አመልካችና ተጠሪ ጋብቻቸውን ከፈፀሙ በኋላ ነው፡፡ ለቤቱ መሥሪያ በሚል ከባንክ በብድር የተወሰደውን ገንዘብ ሲከፈል የቆየው በባል በኩል ጋብቻው ፀንቶ በነበረበት ወቅት በመሆኑ ቤቱ የጋራ ንብረት ነው፡፡ ሰበር ችሎቱ አቅሙን ሲያጠናክር፣ ‹‹አከራካሪው ቤት ያረፈበት ቦታ (መሬት) ከጋብቻ በፊት ሚስት በማኅበር የተመራችውና ጋብቻው ሲፈፀም ጥቂት ጊዜ ሲቀረው ሥራው ከመጀመሩ በስተቀር በሚስት የግል ጥረትና ሀብት የተገነባ አይደለም፤›› በሚል ንብረቱ የጋራ ነው ሲል ገዥ ፍርድ ሰጥቷል፡፡ ሙሉ ትንተናውን ከሰ/መ/ቁ 25005 ይመለከቷል፡፡ 

የሰበር ችሎቱ ፍርድ መሠረት ያደረገው የመኖሪያ ቤቱ ሙሉ የሆነውና የመጨረሻ ቅርጹን ያገኘው ከጋብቻ በፊት ነው ወይስ በኋላ የሚለውን ነጥብ በመመርመር ነው፡፡ አብዛኛው ወይም መሠረታዊው ሥራ የተሠራው ከጋብቻ በኋላ ከሆነ የሁለቱም ተጋቢዎች ጥረት ሰፊ በመሆኑ ንብረቱ የጋራ እንዲሆን ያስችለዋል፡፡ አንደኛው ተጋቢ ከጋብቻ በፊት ያደረገው ጥረት (ቦታ ማግኘት ወይም የቤት መሠረቱን ማውጣት) በራሱ ለቤቱ ምሉዕ መሆን ብቸኛና ወሳኝ ምክንያት ባለመሆኑ፣ ምሉዕነቱን በጋብቻ ውስጥ ላገኘው ቤት ያለው አስተዋጽኦ ብዙ ቦታ አይሰጠውም፡፡ ይህ የሰበር ችሎቱ አቋም ወጥነት ያለው መሆኑን በሌሎችም የችሎቱ ፍርዶችም እናስተውላለን፡፡ 

በሰ/መ/ቁ 26839 ችሎቱ የሰጠው ፍርድ ለዚህ አንዱ አስረጅ ነው፡፡ በዚህ መዝገብ አንዱ ተጋቢ ከጋብቻ በፊት የቤት መሥሪያ ቦታ የነበረው ሲሆን፣ ሌላኛው ተጋቢ ደግሞ የነበረውን ቤት ሸጣ ባገኘችው ገንዘብ በመሬቱ ላይ የመኖሪያ ቤት እንዲሠራ ሆኗል፡፡ በክርክሩ ባል ባዶውን ቦታ ከጋብቻ በፊት ያገኘ መሆኑን፤ ሚስት ደግሞ አዲሱ ንብረት በጋብቻ ወቅት የተሠራ መሆኑን በመግለጽ ንብረቱ የግል ነው/የጋራ ነው የሚል ክርክር አንስተዋል፡፡ የሥራ ፍርድ ቤቱ ከጋብቻ በኋላ የተሠራው ተገምቶ የዚህ ዋጋ ግማሹ ለሚስት እንዲሰጣት ወሰነ፡፡ ይህን ፍርድ የከፍተኛውም ፍርድ ቤት አፀናው፡፡ ሰበር ችሎቱ ጉዳዩን በመጨረሻ ተመልክቶ በእርግጥ ቤቱ የተጀመረው ከጋብቻ በፊት ቢሆንም፣ ቤቱ ተሠርቶ የተጠናቀቀው ከጋብቻ በፊትና ለቤቱ መሥሪያ የተወሰደው ብድርም ከጋብቻ በኋላ መከፈሉ ስለተረጋገጠ ቤቱ የጋራ ነው ሲል ፈርዷል፡፡ የሰበር ችሎቱ እዚህ መደምደሚያ ያደረሰውን ምክንያት ሲገልጽ ‹‹ከጋብቻ በፊት የተፈራ ንብረት የጋራ እንዳይሆን የተፈለገበት ምክንያት ጋብቻ ንብረት ለማግኘት እንዳይቋቋምና እንዳይፈርስ ለመከላከል ሲባል ነው፡፡ በሌላ አነጋገር ምንም ንብረት ያልነበረው ሰው ንብረት ያለውን ሰው በማግባት ጋብቻ ሲፈርስ ያላፈራውን ንብረት የሚካፈልበት ሁኔታ ማመቻቸት ለፍትሕና ለህሊና ተቃራኒ ተብሎ ስለሚታመን ነው፡፡ ነገር ግን ለአንድ ንብረት መገኘት ተጋቢዎች ያደረጉትን አስተዋጽኦ ተመርምሮ እንደነገሩ ሁኔታ የግል ወይም የጋራ ሊባል ይገባል፡፡ ንብረቱ በአብዛኛው ከጋራ ሀብት መዋጮ የተገኘ ከሆነና የግል ንብረቱ ትንሽ ከሆነ ንብረቱ የጋራ ሆኖ መቆጠሩ ፍትሐዊ ይሆናል፤›› በማለት ተንትኖታል፡፡ 

ሰበር ችሎቱ ተመሳሳይ ፍርዶች በመ/ቁ 25281፣ በመ/ቁ 29002 ሰጥቷል፡፡ ችሎቱ በሰ/መ/ቁ 45207 ከጋብቻ በፊት የነበረ ቤት ከጋብቻ በኋላ በተደረገለት እድሳት ብቻ የጋራ ሊሆን እንደማይችል አስገዳጅ ፍርድ ሰጥቷል፡፡ 

ንብረቱ ‹‹መተዳደሪያችን›› ተብሎ ቢገለጽስ?

አንዳንድ ጊዜ ባልና ሚስት ጋብቻ በሚመሠርቱበት ጊዜ ከጋብቻ በፊት በግል ያፈሩት ንብረት በጋብቻ ጊዜ የጋራ እንዲሆን በግልጽ አይስማሙም፡፡ በባህልም ንብረቱን በዝርዝር ገልጾ በጋብቻ ውል ላይ አስፍሮ የጋራ ስለመሆኑ የሚገልጹ የማያከራክር ሰነድ አይፈራረሙም፡፡ በአብዛኛው የተለመደው ‹‹ሀብቴ ሀብትሽ›› ‹‹ንብረቶቹ መተዳደሪያችን ይሆናሉ›› ወዘተ. የሚሉ የውል ቃላት ናቸው፡፡ ባለፈው እሑድ እንደተመለከትነው፣ ‹ሀብቴ ሀብትሽ› የሚለው ግልጽነት የሚጎድለውና ሕጉ ስለጋብቻ ውል ባስቀመጠው መንገድ ስለማይፈጸም በተጋቢዎች መካከል ንብረትን በተመለከተ የጋራ እንዲሆን የሚያደርግ ውጤት አይኖረውም፡፡ ‹‹ንብረቶችን ዘርዝሮ መተዳደሪያችን ይሆናሉ›› የሚል የውል ቃል ካለ ግን ለትርጉም የተጋለጠ ቢሆንም፣ ‹መተዳደሪያችን› የሚለው ቃል ንብረትን የጋራ ለማድረግ በማሰብ የተፈጸመ ስለመሆኑ ዓውዳዊ (Contextual) ትርጓሜ ሊሰጠው ይችላል፡፡ በሰ/መ/ቁ 38544 ባል ከጋብቻ በፊት የነበሩትን አንድ ትልቅ መኖሪያ ቤትና ስድስት የሰርቪስ ቤቶችን ከሌሎች ንብረቶች ጋር በመጨመር መተዳደሪያችን እንዲሆኑ በማለት ተፈራርመዋል፡፡ እነዚህ ንብረቶች ባልና ሚስቱ እየጠቀሙ ለ11 ዓመታት ከኖሩ በኋላ ግን ፍቺ በፍርድ ቤት ሲወሰን የግል ወይስ የጋራ መሆናቸው አከራክሯል፡፡ ይህንን ጉዳይ ከሥር ጀምሮ የተመለከቱት ፍርድ ቤቶች ንብረቱ የጋራ ነው የሚል ፍርድ የሰጡ ሲሆን፣ ሰበር ችሎቱም አፅድቆላቸዋል፡፡ እንደ ሰበር ችሎቱ አቋም ባልና ሚስቱ ደመወዝ፣ ገንዘብና አከራካሪውን ቤት ለመተዳደሪያነት በማለት በውሉ ያሰፈሩት ንብረቱን የጋራ ከማድረግ ውጭ ሌላ ውጤት አይኖረውም ሲል ፈርዷል፡፡ ስለዚህ ተጋቢዎች ከጋብቻ በፊት የተፈራን ንብረት በግልጽ የግል ሆኖ እንደሚቀጥል በጋብቻ ውሉ ላይ ካላሰፈሩ ‹‹መተዳደሪያችን›› በሚል የሚገልጹት የውል ቃል ንብረቱ የግል ሆኖ እንዲቀር እንደማያስችል ግንዛቤ ሊወስድ ይገባል፡፡ 

የኮንዶሚኒየም ዕጣስ?

በፍቺ የንብረት ክርክር ወቅት የኮንዶሚኒየም ቤት ክርክር ማስነሳቱ እየተለመደ ነው፡፡ የኮንዶሚኒየም ቤት ምዝገባውም፣ ዕጣውም የደረሰው በጋብቻ ጊዜ ከሆነ ብዙም አከራካሪ አይደለም፡፡ በተጋቢዎቹ ባንዱ ስም የወጣው የኮንዶሚኒየም ቤት በእንዲህ ዓይነት ጊዜ የጋራ ይሆናል፡፡ ዕጣው ከጋብቻ በፊት ለአንዱ ወጥቶ በጋብቻ ወቅት ከቤቶች አስተዳደር ጋር ውል ከተገባና ክፍያም ከተፈጸመ በንብረት ክፍፍል ጊዜ አከራካሪ ሆኗል፡፡ ዕጣው የደረሰው ከጋብቻ በፊት ስለሆነ የግል ሀብት ነው፤ በአንፃሩ ደግሞ ውሉ የተፈጸመው፣ ቅድሚያ ክፍያ የተከፈለውና ዕዳው መከፈል የተጀመረው በጋብቻ ጊዜ በመሆኑ ኮንዶሚኒየሙ የጋራ ነው የሚሉ ክርክሮች በፍርድ ቤት ሲቀርቡ ይታያል፡፡ ለዚህ ጉዳይ የመጨረሻ እልባት የሰጠው የሰበር ችሎት በሰ/መ/ቁ 51893 በእንዲህ ዓይነት ጊዜ ኮንዶሚኒየሙ የጋራ ነው የሚል ፍርድ ሰጥቷል፡፡ በሌላ በኩል ሰበር ችሎቱ በሰጠው ሌላ ፍርድ (የሰ/መ/ቁ 75562) ጋብቻው ፀንቶ ባለበት ጊዜ አንድ ተጋቢ የኮንዶሚኒየም ዕጣ ደረሰው፤ ከዚያ ከሁለት ወር በኋላ ጋብቻው ፈረሰ፣ የንብረት ክፍፍል ሳያልቅ ቅድመ ክፍያው ተከፈለ፡፡ በዚህ ጉዳይ ችሎቱ የኮንዶሚኒየም ቤቱ ዕጣ በጋብቻ ወቅት ስለወጣ የጋራ ነው በሚል ገዥ ፍርድ ሰጥቷል፡፡ ስለዚህ እንዲህ ዓይነት ጉዳይ የሚወሰነው ዕጣው እንደወጣበት ጊዜና እንደተጋቢዎቹ አስተዋጽኦ ነው፡፡

በሥራ ምክንያት የሚሰጥ ድጎማ

ድጎማ ሌላው አከራካሪ የንብረት ክፍፍል ጥያቄ ነው፡፡ ባል ወይም ሚስት በሥራ ቦታ ባደረጉት ልዩ አስተዋጽኦ ድጎማ ሊያገኙ ይችላሉ፡፡ ይህ ድጎማ የሠራተኛ ተጋቢ የግል ሀብት ነው ወይስ የተጋቢዎቹ የጋራ የሚለው ሲያከራክር ቆይቷል፡፡ በአንድ በሰበር ችሎቱ በታየ ጉዳይ ባል በብሩንዲ በሰላም ማስከበር ተግባር ላይ ተሰማርቶ ለነበረበት ጊዜ በድጎማ መልክ ተከፍሎታል በተባለው ገንዘብ ክፍፍል ላይ ባልና ሚስት ተከራክረዋል፡፡ ባል ገንዘቡ ከደመወዝ የተለየና በድጎማ መልክ የተሰጠኝ በመሆኑ የግሌ ነው ይላል፡፡ ሚስት ደግሞ የድጎማው ገንዘብ የተገኘው ጋብቻው ፀንቶ በነበረበት ጊዜ እስከሆነ ድረስ የጋራ ሀብት ነው ብላ ትከራከራለች፡፡ የወረዳውና የከፍተኛው ፍርድ ቤት ድጎማው የባልና የሚስቱ የጋራ ሀብት ነው በማለት ሲወስኑ የክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ግን የጋራ አይደለም ሲል ፍርዱን ሽሮታል፡፡ ፍርድ ቤቱ ፍርዱን ለመሻር የሰጠው ምክንያት ‹‹ድጎማው ባልና ሚስት በመረዳዳትና በመተጋገዝ በጋራ ያፈሩት ነው ሊባል አይችልም፤›› የሚል ነው፡፡ ጉዳዩን በመጨረሻ የተመለከተው የፌዴራሉ ሰበር ሰሚ ችሎት ‹‹ሕጉ ለጋራ ንብረት መሠረት ይሆን ዘንድ በዋነኛነት ያስቀመጠው መስፈርት በጋብቻው ጊዜ መገኘቱን ነው፡፡ ባልና ሚስት በጋብቻ ተሳስረው ባሉበት ጊዜ የሚገኘው ንብረት በሁለቱም የጋራ መተጋገዝ እንደተገኘ መቆጠር እንዳለበት ሲል ሕጉ ወስኗል፤›› በሚል ምክንያት ድጎማ የባልና የሚስት የጋራ ሀብት እንደሆነ በመግለጽ አስገዳጅ የሕግ ትርጉም ሰጥቷል፡፡ 

ጡረታስ የግል ወይስ የጋራ?

የጡረታ ጉዳይ በብዙ የፍቺ ጉዳዮች ሲያከራክር የቆየ ነው፡፡ ፍርድ ቤቶች ለዘመናት የተለያዩ አቋሞች አንፀባርቀዋል፡፡ የአቋም ልዩነቱ በሁለት መንገድ የሚታይ ነው፡፡ አንዳንዶች ጡረታ የመንግሥት ሠራተኛ ለሆነ ሰው በሕግ የሚሰጥ ክፍያ በመሆኑ የሠራተኛው የግል ሀብት ነው ይላሉ፡፡ ሌሎች ደግሞ በአገራችን ጡረታ ከሠራተኛው ደመወዝ የተወሰነ መቶኛ ከመንግሥት ደግሞ የተወሰነ መጠን በማዋጣት የሚጠራቀም በመሆኑ ‹የሠራተኛው መዋጮ የሚገኘው የጋራ ሀብት ከሆነው ከደመወዝ ነው› ስለዚህ ጡረታ የባልና የሚስት የጋራ ሀብት ሊሆን ይገባል ይላሉ፡፡ አንዳንድ ምሁራን ደግሞ ሁለቱን አቋም ለማስታረቅ የጡረታ ጉዳይ እንደጉዳዩ (እንደሁኔታው) ሊታይ ይገባል በማለት አስታራቂ ሐሳብ ሲሰጡ ቆይተዋል፡፡ ፍርድ ቤቶች የጡረታ መብቱ ፍቺ ሲከናወን በስሏል ወይስ አልበሰለም የሚለውን በማረጋገጥ የጡረታ መብቱ ከበሰለ (ለመከፈል ከደረሰ) በተለያዩ መንገዶቹ ሠራተኛ ያልሆነውን ተጋቢ ጥቅም ማስከበር እንደሚቻል ይገልጻሉ፡፡ ፍርድ ቤቶቹ በጋብቻ ጊዜ ከደመወዝ የተጠራቀመውን መጠን በመለየት ሠራተኛ የሆነው ተጋቢ ሠራተኛ ላልሆነው ተጋቢ ግማሹን እንዲከፍል በማድረግ የጡረታው ሙሉ ተጠቃሚ እንዲሆን ማድረግ ነው፡፡ አንዳንዴ የጡረታ መብቱም ሳይበስል በጋብቻ ከደመወዝ የተጠራቀመው መጠን ስለሚታወቅ ግማሹን ሠራተኛ ላልሆነው ተጋቢ ከፍሎ የጡረታ መብቱ ከተወሰነ ዓመት በኋላ ሲበስል ሠራተኛ የነበረው ተጋቢ ሙሉ ተጠቃሚ ማድረግ እንደሚቻልም ምሁራኑ ገልጸዋል፡፡ የምሁራኑ አስተያየት አመክንዮን መሠረት ያደረገ ቢሆንም፣ በተግባር በፍርድ ቤቱ ለጡረታ አበል የአከፋፈል ጉዳይ ዳኞች ሲጠቀሙበት አልተስተዋለም፡፡ 

እንዲህ ዓይነቱ የግራ ቀኝ ክርክር እልባት ያገኘው የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት አስገዳጅ የሕግ ትርጉም መስጠት ከጀመረ በኋላ ነው፡፡ ችሎቱ በሰ/መ/ቁ 34387 ግንቦት 14 ቀን 2000 ዓ.ም. በሰጠው ፍርድ የጡረታ አበል የግል ሀብት እንደሆነ ገዥ ፍርድ ሰጥቷል፡፡ ጉዳዩ ባል በወታደር ቤት አገልግሎ ዓይኑ ላይ በደረሰበት ጉዳት ቦርድ ሲወጣ አንድ መቶ ሰላሳ አምስት ብር ጡረታ ይከፈለው ነበር፡፡ ከተወሰኑ ዓመታት በኋላ ከሚስቱ ጋር በፍቺ ሲለያይ ሚስት ከሌሎች ንብረቶች ጋር የጡረታ አበሉም የጋራ ስለሆነ ልካፈል ይገባል ስትል ጥያቄ አቀረበች፡፡ የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤቱ ጡረታን የጋራ የሚያደርግ የሕግ ድጋፍ የለም ሲል በጠቅላይ ፍርድ ቤት የፀናው የከፍተኛው ፍርድ ቤት ፍርድ ደግሞ ለጡረታ መነሻው የሠራተኛው ደመወዝ ስለሆነ ሚስት ልትካፈል ይገባል ሲል ፈረደ፡፡ ጉዳዩ በስተመጨረሻ ለሰበር ችሎት ደረሰና ችሎቱ ጡረታ የሠራተኛ ተጋቢ የግል ሀብት ነው ሲል ፍርድ ሰጠ፡፡ በችሎቱ አረዳድ ‹‹የጡረታ አበሉ በመንግሥት በኩል ተቀማጭ የሚሆን ገንዘብ ያለ በመሆኑ፣ ለአንድ ሠራተኛም የጡረታ አበል የሚከፈለው ዕድሜው በገፋበት ጉልበቱ በደከመበት ጊዜ መጦሪያ የሚሆነውና ለመኖር የሚያስፈልገውን ወጪ በከፊልም ቢሆን በመሸፈንና ለማኅበራዊ ደኅንነቱ ዋስትና ለመስጠት መንግሥት ካለው የማኅበራዊ ደኅንነትና ዋስትና ፖሊሲ የመነጨ በመሆኑ እንደማንኛውም ገቢ የጋራ ንብረት ነው የሚባል አይደለም፡፡ የአንድ ሰው የጡረታ አበል በማንኛውም መልኩ በዕዳ ሊያዝ ወይም ሊታገድና ሊቀነስ እንደማይችል የፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁ. 404(ሠ) በግልጽ ስለሚደነግግ፣ ከፍተኛ ፍርድ ቤቱ የጡረታ አበል ግማሹ እየተቆረጠ እንዲከፈል መወሰኑ ተገቢ አይደለም፤›› ሲል ለፍርዱ መሠረት ያደረገውን ትንተና አቅርቧል፡፡ ይህ የሰበር ፍርድ በፍቺ ወቅት ለሚነሱ የጡረታ ጥያቄዎች እልባት እንደሰጠ ይታመናል፡፡

እንደማጠቃለያ 

ጋብቻ በፍቺ ከፈረሰ በኋላ ለተወሰኑ ወራት አልፎ አልፎም ዓመታት የሚዘልቅ ክርክር የሚደረግበት የንብረት ክፍፍል ጉዳይ ነው፡፡ ንብረቶቹ በግልጽ ከጋብቻ በፊት ወይም በኋላ ከተፈሩ፣ በስጦታ ከተሰጡ ወዘተ. የሕጉን ድንጋጌዎች በቀጥታ በመተግበር ለጉዳዮች እልባት መስጠት ይቻላል፡፡ ጊዜውን የሚያራዝመውና የፍርድ ቤቶችን አቋም የሚለያየው ግን ንብረቱ ከጋብቻ በፊት ተጀምሮ በጋብቻ ጊዜ ሲጠናቀቅ፣ የግል ሀብትና የጋራ ሀብት ሲቀላቀል ወይም በቤተሰብ ሕግጋቱ በግልጽ ያልተመለከቱ የጡረታ፣ የኮንዶሚኒየም ዕጣ፣ የይዞታ መብት፣ ድጎማ ወዘተ. ዓይነት ሀብቶችን በተመለከተ ክርክር በተነሳ ጊዜ ነው፡፡ እነዚህ አከራካሪ ጉዳዮችን እልባት በመስጠት የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት የሰጣቸው አስገዳጅ ፍርዶች ታላቅ አስተዋጽኦ አድርገዋል፡፡ ፍርዶቹ ርትዕን መሠረት ያደረጉ፣ የቤተሰብ ሕጉን ዓላማ የሚያስጠብቁ በመሆናቸው ጸሐፊው ችሎቱ በዚህ ረገድ የሠራው ሥራ ምስጋና እንደሚገባው ያምናል፡፡ ፍርዶቹ በአንድ በኩል አንድ ተጋቢ ንብረት ለማግኘት ብቻ ጋብቻ እንዳይመሠረት የሚያደርጉ ሲሆን፣ በሌላ በኩል ደግሞ ተጋቢዎች በጋራ ያደረጉትን አስተዋጽኦ ዋጋ የሚሰጥ ነው፡፡ በዚህ ረገድ ከጋብቻ በፊት በተገኘ ቦታ ወይም በነበረ ጅምር ቤት ላይ የተፈጸመ መኖሪያ ቤት የጋራ መሆኑ፣ የጋራ መኖሪያ ቤት ዕጣ ከጋብቻ በኋላ ሲደርስ ወይም ከጋብቻ በፊት ደርሶ ውሉ በጋብቻ ጊዜ ሲፈጸም የጋራ መሆኑ፣ ድጎማ፣ በጋብቻ ውል በመተዳደሪያነት የተገለጸ ቤት የባልና የሚስት የጋራ ሲሆኑ፣ ጡረታ ግን የሠራተኛ ተጋቢ የግል ሀብቱ ነው፡፡ ከሰበር ችሎቱ አስተዋጽኦ ሌላ ግን ሕጉ እነዚህ ዓይነት ጉዳዮች ዕልባት የሚያገኙበትን መርሆች ቢያካትት ለትርጉም የማያጋልጥና ለሕዝቡ ተደራሽ ይሆናል፡፡ በዚህ ረገድ የቤተሰብ ሕጉ ሲሻሻል ድንጋጌዎቹን በተሻለ ዝርዝር ለማድረግ ሊታሰብበት ይገባል፡፡ እስከዚያው ግን በዚህ ጽሑፍ በገለጽነው መሠረት ግንዛቤን ማሳደግና መብትና ግዴታን አውቆ መተግበር ብልህነት ነው፡፡ 

ከአዘጋጁ፡- ጸሐፊውን የሕግ ጠበቃና አማካሪ ሲሆኑ፣ በኢሜይል አድራሻቸው This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it. ማግኘት ይቻላል፡፡