መነሻ ገጽ - ሌሎች አምዶች - ሕግ እና ፖለቲካ - ልናገር - ከጉባዔው ብዙ ነገር እንጠብቃለን!
Buy Valtrex Online Buy Albuterol inhaler Online Buy Prinivil Online
20 March 2013 ተጻፈ በ 

ከጉባዔው ብዙ ነገር እንጠብቃለን!

በተጋዳላይ በራሕለ

ሰሞኑን የሕወሓት 11ኛ ጉባዔ በመቀሌ ከተማ በመካሄድ ላይ ነው፡፡ ለአሥር ጊዜ ያህል ጉባዔውን ሲመሩ የነበሩት ባለራዕዩ መሪያች የቀድሞው ጠቅላይ ሚንስትር መለስ ዜናዊ ጥሩ ነገራቸውን ትተውልን ይህንን 11ኛ ጉባዔ እሳቸውን በመዘከር እየተካሄደ ነው፡፡

ለዝግጅቱ መላው የትግራይ ሕዝብ ሲረባረብ ሰንብቷል፡፡ ድምቀቱ የሕወሓት ምሥረታ ሲከበር በተለይ ከ20ኛ እሰከ 35ኛ የነበሩት በዓላትን ያስንቃል፡፡

  በእውነት እኔ የትጥቅ ትግል መጀመሩ በዓል ሲከበር በጣም ደስ ነው የሚለኝ፡፡  የሰማዕታቱ ታሪክ በድምፀ መረዋዎቹ የድምፅ ወያነ ጋዜጠኞች ሲተላለፍ በከተማዋ በትላልቅ አደባባዮች  በማይክራፎን የሚተላለፉት የትግል ወቅት ዜማዎችና ዶክመንታሪ ፊልሞች ሳይ ሐሴት ይፈጥርልኛል፡፡ ከትግሉ ትሩፋት ብዙ ነገር አግኝቻለሁ፣ ደስ ብሎኛል፣ በማንነቴ ኮርቻለሁ፡፡ ደርግ ባለቀ ሰዓት ሊሞት ሦስት ወራት ሲቀሩ ከመቐለ ተፈናቅዬ  ደሴ መጠለያ እያለሁ በግድ ታፍሼ ኢሕአዴግ ደረሰልኝ፡፡ ከድል በኋላ ያቋረጥኩትን ትምህርት ቀጥዬ አሁን በሰላም ሕይወቴን እየመራሁ እገኛለሁ፡፡ በወቅቱ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የነበረ ታላቅ ወንድሜም ሳይወድ በግድ ከዘመተበት ብላቴ ተመልሶ ከሁለት ዓመት በኋላ ትምህርቱን አጠናቋል፡፡ ከአባታችን ልጆች ከአራት ሁለቱ በደርግ ተበልተው ሁለት ልጆቹ በጥሩ ሁኔታ እንገኛለን፡፡ ክብር ምሥጋና ለጀግኖች ሰማዕታት፡፡

እናም የጉባዔው ዝግጅት ደማቅ ነው፡፡ ያው ሰሞኑን በቴሌቪዥን እንደተመለከታችሁት ልዩና ለወጣቱ ወኔ የሚያላብስ ነው፡፡ ይህ እንዲህ ሆኖ ወጣቱ በተለይ በከተማ ያለው ከጉባዔው ብዙ ነገር ይጠብቃል፡፡

የትግራይ ከተሞች እዚያ መሀል አገር እንደሚወራው ሳይሆን መቐለ ውኃ የጠማት ከተማ ነች፡፡ ከዚህ በፊት በሃያ ከተሞች ለሃያ ዓመታት በሚል የተዘረጋው የመቐለ ከተማ የመጠጥ ውኃ ፕሮጀክት የሚፈለገውን ጥቅም ሳይሰጥ በሁለት ዓመት ነው የቆመው፡፡ ስለዚህ መቐለ ከፍተኛ ውኃ ችግር አለባት፡፡ መብራትና የቴሌ ኔትወርክ እንደ መሀል አገሩ ነው፡፡ ሌላው በመቐለ ከተማ የሚሠራው ኮንዶሚኒየም ቤት ጥራት እጅግ አሳሳቢ ነው፡፡ በአንድ ወቅት ከሰማዕታት ሐውልት በታች ባለው እንዳ ገብርኤል ቤተ ክርስቲያን ጀርባ ባለው ሠፈር የተሠራ ኮንዶሚኒየም በክረምት ወቅት በነበረው ዶፍና ወጨፎ የቀላቀለ ዝናብ ጣሪያው በንፋስ ተወስዶ እንደነበር የከተማው ሕዝብ  የቡና መጠጫ ሆኖ እንደነበር አስታውሳለሁ፡፡ የቤቱ ጥበት፣ የተሠራበት ዕቃ ጥራት፣ አቀማመጡ፣ ኩሽናና ሽንት ቤት፣ መኝታ ቤትና ሽንት ቤት  በራቸው አጠገብ ላጠገብ መሆኑ አስገራሚ ብቻ ሳይሆን አሳሳቢ ነው፡፡ ሌላው ከአዲስ አበባ ጋር መወዳደር የለበትም ከሆነ  ክልሉ በጀት ካጠረው (ከክልላችን በጀት አኳያ ነው የምንሠራው የሚል መልስ ስለሚሰጥ ነው) ባለው በጀት ጥራቱ የተጠበቀ ሕንፃ ተገንብቶ  ለምን አይሰጥም?  በጀት የለ፣ ጥራት የለ፣ ምሥጋናም የለ አስገራሚ ነው፡፡ 

ትግራይ ውስጥ አንዳንድ ከተሞች እንዲሞቱ እየተደረጉ ነው ወይም ደግሞ መንግሥት ትኩረት ሊያደርግባቸው አይፈልግም፡፡ ለምሳሌ ማይጨውና ኮረም ከተሞች የትግራይና የኢትዮጵያ አንጋፋና ታሪካዊ ከተሞች ናቸው፡፡ ቢሆንም አሁን ባለው ሁኔታ ከተሞቹ እንቅስቃሴያቸው እየተዳከመ ይገኛል፡፡ ለዚህም እንደ ምክንያት የሚጠቀሰው አዲሱ መንገድ ሒዋነ-መኾነ-አላማጣ በመሆኑ የድሮው ሒዋነ-ማይጨው-ኮረም-አላማጣ ነበር፡፡ የማይጨው-ኮረም-አላማጣ መንገድ በወቅቱ ኮንትራት ወስዶ የሠራው የኢትዮጵያ መንገዶች ባለሥልጣን ሥራው ላይ መተኛቱ ሳያንስ ሥራውን በጥራት ባለመሥራቱ ለችግር የተጋለጠ ነው፡፡ ይህ ችግር የቁጥጥር አድራጊውና የኮንትራክተሩ ሆኖ ሳለ እነኝህ አካላት ሳይጠየቁበት ሕዝቡ ይህን ዕዳ ከፋይ አድርጎ መውሰድ እጅግ በጣም አሳዛኝ ነው፡፡ በዚህ የተነሳ ትራንስፖርቱ በሙሉ በታችኛው መስመር ስለሆነ በከተሞቹ የሚኖር ሕዝብ ሁሉ እንቅስቃሴው ቆሟል፡፡

በትግራይ ከተሞች ትልቁ ችግር የመልካም አስተዳደር ጉዳይ ነው፡፡ ጥያቄ ማቅረብ አይቻልም፡፡ ካቀረብከ ተቃዋሚ ተብለህ ትፈረጃለህ፡፡ ኔትወርክ አለ፡፡ ኔትወርኩ የመንግሥት ሳይሆን የአገር ልጅነት፣ የአካባቢና የወንዝ ነው፡፡  የተለየ ሐሳብ ያላቸውን ሰዎችን ሆን ብለህ ማጥቃት የተለመደ ነው፡፡ ለምሳሌ አንድ ሠራተኛ የተለየ አስተሳሰብ ከያዘና የመሰለውን ከተናገረ እሱን ለማባረር ኮሚቴ ይሰበሰባል፡፡ ከኮሚቴው ወደ ማኔጅመንት ይቀርባል፡፡ ከማኔጅመንት አባላት አንደኛው አባል ውሳኔውን ከተቃወመ እሱንም ከእሱ ጋር ፈርጆ ሌላ ተንኮል መሸረብ ይጀመራል፡፡ የተለየ ሐሳብ ማስተናገድ ፈጽሞ አይቻልም፡፡ የቀድሞው ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትራችንና ሌሎቹ ሰማዕታት የወደቁለት አንዱ ዓላማ እኮ ሰው የመሰለውን ሐሳብ የመግለጽ መብቱ እንዲከበርለት ነው፡፡ ሰው የመሰለውን ሐሳብ ስለገለጸ ለምን በሌሎች እንዲጠመድ ይደረጋል?

መንግሥታችን ለመንግሥት ሠራተኛው የሚሰጣቸው የተለያዩ አገልግሎቶችና ማበረታቻዎች አሉ፡፡ እንዲያውም እግዜአብሔር ይስጣቸውና ጠቅላይ ሚኒስትራችን አቶ ኃይለ ማርያም ደሳለኝ በኮንዶሚኒየም ምረቃ ሥነ ሥርዓት ላይ የመንግሥት ሠራተኞች ኮታ ሊሰጣቸው እንደሆነ ሲናገሩ ደስ አለኝ፡፡ የትግራይ መንግሥት ሠራተኛ ከሚያገኛት የወር ደመውዙ ለዓባይ፣ ለሐውልት፣ ለትግራይ ልማት፣ ለሌሎችም አዋጣ እየተባለ ደስ ብሎትና አምኖበት  ሲያዋጣና ሲያበረታታ የቆየ ነው፡፡ በዚህ መሠረት ይህ የመንግሥት ሠራተኛ ግን ያ ሁሉ ድጋፉ ተዘንግቶ ሌሎች ችግሮቹ ሊወገዱለት አልቻለም፡፡ ጉባዔው ለእንደዚህ ዓይነቶቹ ችግሮች መፍትሔ እንዲሰጥ  በሚል የተወሰኑትን እስቲ ላቅርብ፡፡ ቀደም ሲል ለመንግሥት ሠራተኞች በማኅበር ተደራጅተው እንዲቆጥቡና ቤት እንዲያገኙ የሚደረግበት ሁኔታ ነበር፡፡ ለምሳሌ የቁጠባ ቤቶች፡፡ ይህ መልኩን ቢቀይርም እስከቅርብ ጊዜ ድረስ ነበረ፡፡ በመቐለ ከተማ ያጋጠመውን ላቅርብ፡፡

ቁጠራቸው አራት ሺሕ የሚደርሱ የመንግሥት ሠራተኞች በ160 ማኅበራት ተደራጅተው በመቐለ ከተማ ተቋቁመው ነበር፡፡ ማኅበሮቹ ከ1998 ዓ.ም. ጀምሮ  ሕጋዊ ዕውቅና አግኝተው በዝግ ሒሳብ ከዚያች ደመወዛቸው ብር እየቆጠቡ ካጠራቀሙ በኋላ የመሬት ፈቃዱን ጠየቁ፡፡ ለገበሬው የካሳ ብር ስላነሰ እባካችሁ አንዳንድ ሺሕ ብር ጨምሩ ተብለው ገቢ አደረጉ፡፡ ከዚያ ነገ ዛሬ ነገ ዛሬ ሲባሉ አስተዳደሩ ሊፈቅድላቸው አልቻለም፡፡ ለምን ቢባል ምላሽ የሚሰጥ የለም፡፡ በአንድ ወቅት የፌደራል መንግሥት ከልክሏልና አዋጁ እስኪወጣ ጠብቁ ተባለ:: እዚህ ላይ አንባቢያን ሊያውቁት የሚገባው ማኅበሮቹ ከሚመለከተው አካል ጋር እልህ አስጨራሽ ሙግትና ክርክር ያካሂዱ ነበር፡፡ የመንግሥት ሹመኞቹ  ምላሽ ግን በጣም የሚያስገርምና  የሚያሳፍር ነበረ፡፡ በዚህ ሁሉ መሀል በስተመጨረሻ ሲጠበቅ የነበረው የፌደራል አዋጅ ወጣ፡፡ አሁንም እባካችሁ አዋጁ ወጥቷልና ፍቀዱልን ብለው ሲጠይቁ የመንግሥት ሹመኞች ምላሽ ባለጉዳዮችን ያሳዘነ ነበር፡፡ መንግሥት ማነው? ኢሕአዴግ፣ ሕወሓት፡፡ የፌደራል መንግሥት ያፀደቀውን እንዴት ነው ክልል የሚሽረው? ለምንስ የፌደራል ሕግ ይሸራረፋል? 

ሌላው እነኝህ የመንግሥት ሠራተኞች የፌደራል መንግሥት ቢፈቅድም ከክልላችን ሕግ አንወጣም ብለው ሦስት አማራጮች አቅርበዋል፡፡ ካሬ ሜትሩን አነሰ ቢባል 100 ሜትር ካሬ ይሁንልን፡፡ ሁለተኛ እሺ ነፃው ይቅርብንና መንግሥት ባስቀመጠው ባነሰ በሊዝ ዋጋ ይሰጠን፡፡ ሦስተኛ መንግሥት ባለ አራት ፎቅ ገንቡ ቢልም ባለሁለት ፎቅ ይፈቀድልን አሉ፡፡ ሆኖም እነዚህ ሹመኞች አማራጩን ሊቀበሏቸው አልቻሉም፡፡ እንዴ! መሬት እኮ በአሁኑ ጊዜ በጥቂት ሰዎች እጅ እየገባ ነው፡፡ አብዛኛው የመንግሥት ሠራተኛ ተከራይ እንዲሆን እየተፈረደበት ነው፡፡ እስቲ የሊዙ ዋጋ ይታይ፡፡ በመካከለኛ ደረጃ የሚገኝ የመንግሥት ሠራተኛ በሊዝ ተወዳድሮ መሬት ማግኘት የሚችለው እንዴት ነው?

ባለፉት አሥራዎቹ ዓመታት ግብርን በሚመለከት ጠለቅ ያለ እውቀት ያለው ነጋዴም ሆነ ዜጋ አልነበረም፡፡ ነገር ግን በቅርብ ዓመታት ሲጀመር ከየትም አምጣተው ዓይነት ነገር ነው የሆነው፡፡ ዜጎች ግብር መክፈል ግዴታ አለባቸው፡፡ ግን አከፋፈሉ ላይ ብዙ ችግር እንዳለ ነው የሚታየው፡፡ ነጋዴውን  የሚያማርር ነው፡፡ ለምሳሌ ቫት መመዝገብ የሌለበት ነጋዴ ቫት እንዲመዘገብና የካሽ ሬጂስተር ማሽን እንዲያስገባ ተደርጎ ጉዳዩ ስህተት እንደሆነ ከታወቀ በኋላ በባለሥልጣኑ አይታረምም፡፡ ካሽ ሬጅስተር አስገቡ ተብለው ካስገቡ በኋላ አናምናችሁም ስለዚህ በቁርጥ ግብር ነው  የምናስከፍላችሁ የተባሉ ነጋዴዎች ጭንቀትና ውጥረት ውስጥ እንዲገቡ ይደረጋል፡፡
እንዳንዶቹ ነጋዴዎቹ እንደሚሉት በሚሊዮንና በመቶ ሺዎች የሚቆጠር ግብር ክፈሉ ተብለን አቤት ስንል ብሩን መጀመርያ አስይዙና ወደ ፍርድ ቤት አቤት ማለት ትችላላችሁ እንባላለን፡፡ በእስካሁኑ ሒደት አቤት ቢባልም ተሳስተናል ሲባል አላየንም ሲሉ ነጋዴዎች ይደመጣሉ፡፡ እንዴት ነው ነገሩ? መንግሥት ምንድነው የሚጠብቀው? በትክክል እታች ምን እየተሠራ እንደሆነ ለምን መንግሥት ወርዶ አያይም? በእነሱ አስተሳስብ ነጋዴ አጭበርባሪ እንጂ ቅንነት እንደሌለ ነው የሚታሰበው፡፡

    ሰው እያማረረ ነው፡፡ ሕዝብ ነው ሕወሓትን ደግፎ፣ አቅፎና ተንከባክቦ እዚህ ያደረሰው፡፡ ለምንድነው ሕዝብ ምን ይላል የማይባለው? ለነገሩ ካንዴም ሁለቴ ሕዝቡ ተሰብስቦ ያላችሁን ችግር ተናገሩ ተብሎ ያለውን ችግር ዝርግፍ አድርጎ ሲያበቃ ለጥቃት ነው የተጋለጠው እንጂ መንግሥት ችግሮች ላይ ማስተካከያ አላደረገም፡፡ ከእንግዲህ ካለፈው ተምሯልና ውስጥ ውስጡን ይብላላል እንጂ አይናገርም፡፡ ውስጥ ውስጡን የተዳፈነና የታመቀ ደግሞ ምን ሊፈጥር እንደሚችል ሕወሓት ከትግሉ የተማረው ይመስለኛል፡፡ በሥነ ሥርዓት  መብትን መጠየቅ እንደ ነውርና እንደ ኃጢያት መቆጠሩ ይብቃ፡፡ የሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 29 ሐሳብን በነፃነት የመግለጽ መብት ሳይሸራረፍ መከበር ሲገባው አይከበርም፡፡ እዚያ አዲስ አበባ በስመ ነፃው ፕሬስ ሐሳብን በነፃነት የመግለጽ መብት ወደ ስድብ ተለውጦ አንዳንድ ብሔሮችን እስከ መዝለፍ እየተደረሰ፣ እዚህ ትግራይ ግን መብትን መጠየቅ ነውር ሊሆን አይገባውም ነበር፡፡ እናም ከጉባዔው ይህንን እንጠብቃለን፡፡ እኔ በትክክለኛው መንገድ መብቴን በመጠየቄ ተቃዋሚ መባል ወይም ደግሞ ሌላ ነገር ሊለጠፍብኝ አይገባም፡፡ ይህን ጉባዔ በከተሞች ላሉ ችግሮች መፍትሔ ያመጣልናል በማለት በጉጉት እንጠብቃለን፡፡

ሹመኞች በሙስናና በአካባቢያዊነት ሲገመገሙ ለምን ወደ ፀረ ሙስና ጉዳያቸው አይመራም? ለምን ወደ ሌላ ቦታ እንዲዛወሩ ይደረጋሉ?  ወይም ደግሞ እዚያው ባሉበት ቦታ ላይ ሹመት በሹመት ይደራረብላቸዋል፡፡ ሕዝብ በፍትሕ እጦት፣ በኑሮ ውድነትና በሥራ አጥነት ተማሯል፡፡ ያቺ የነበረችው ኮብል ስቶንም ኪራይ ሰብሳቢዎች ገብተውባታል፡፡ የመተካካቱ ጉዳይ ይታሰብበት፡፡ ይህንን ስንል ከአካባቢያውነት የፀዱ፣ መልካም ሥነ ምግባር ያላቸው፣ ለድርጅታቸውና ለዓላማው መሳካት ቁርጠኛ የሆኑ፣ ከኪራይ ሰብሳቢነት ጋር ያልተነካኩ እንዲሆኑ ምኞታችን ነው፡፡ ይህ ምኞታችን ግን ምኞት ሆኖ ከቀረና ጉባዔው ብቻውን ‹‹የመለስን ራዕይ አሳካለሁ›› ብሎ በጭብጨባና በመፈክር ከተለያየ  በጣም አሳሳቢና አስገራሚ ሆኖ በታሪክ ይመዘገባል፡፡

እኔ ይህንን ስሞታዬን ያቀረብኩት በከተማ ውስጥ ያለ ችግርን በመመልከት ነው፡፡ እርግጥ ነው ገጠር ያለው አርሶ አደር ኑሮው እየተስተካከለና በመስኖ ልማቱም ሆነ በአዳዲስ ቴክኖሎጂ በመጠቀም ምርታማነቱን እያሳደገና ለውጥ እየታየ በመሆኑ ኢሕአዴግን አመሰግናለሁ፡፡ ልክ ነው ኢሕአዴግ በገጠሩ ባለው ዕድገት ሊመካበት ይገባል፡፡ ግን በከተማ ያለው ችግር በጣም እየከፋ ነው፡፡ ከጉባዔው በከተሞች ውስጥ ባሉ ችግሮችና ተያያዥ ጉዳዮች ላይ ብዙ ብዙ ብዙ እንጠብቃለን፡፡