መነሻ ገጽ - ሌሎች አምዶች - ሕግ እና ፖለቲካ - ልናገር - ስለየትኛው ድህነታችን ነው የሚነገረን?
Buy Valtrex Online Buy Albuterol inhaler Online Buy Prinivil Online
10 April 2013 ተጻፈ በ 

ስለየትኛው ድህነታችን ነው የሚነገረን?

በ2000 ዓ.ም. ይሁን በ2001 ዓ.ም. ለጊዜው እርግጠኛ ባልሆንም ከሁለቱ በአንዱ ዓመት ይመስለኛል፡፡

በመዲናችን በአዲስ አበባ በተካሄደ ዓመታዊው የአፍሪካ ኅብረት የመሪዎች ጉባዔ ላይ የአፍሪካ ቀዳማይ እመቤቶችም በበኩላቸው ከባሎቻቸው እኩል ስለአፍሪካ ጉዳይ ተፈጥሮ የቸረቻቸውን የሴትነት ጥበብና ብልኃታቸውን በመጠቀም፣ ህልቆ መሣፍርት ለሌላቸው ለአፍሪካና ለአፍሪካውያን ችግሮችና እንቆቅልሾች መፍትሔ ለማመላከት እነርሱም በተራቸው ለስብሰባ ተቀምጠው ነበር፡፡

ከአፍሪካ ቀዳማይ እመቤቶች ከስብሰባው ማብቂያ በኋላ በተለይ የዛምቢያዋ ቀዳማይ እመቤት የቀድሞውን ገነተ ልዑል ቤተ መንግሥትን፣ የአሁኑን የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የኢትዮጵያ ጥናትና ምርምር ተቋም የኢትኖግራፊክ ሙዚየምን ለመጎብኘት አስቀድመው በስልክ ባስያዙት ፕሮግራም መሠረት በክብር እንግድነት ወደ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ  መጥተው ነበር፡፡

ለዩኒቨርሲቲው ኢትኖግራፊክ ሙዩዚየም በደረሰው መልእክት መሠረት ‹‹ለጥቁሯ እንግዳ›› ለዛምቢያዋ ቀዳማይ እመቤት ታሪካዊ ገለጻ እንዳደረግ በጊዜው በዩኒቨርሲቲው የኢትዮጵያ ጥናት መምህርና የሙዚየሙ ኩሬር ከሆኑት ዶክተር ጋር በመሆን ለእኚሁ ለዛምቢያዋ እመቤት ገለጻ በማድረግ ጥቂት ቆይታ አድርጌ ነበር፡፡

የዛምቢያዋ ቀዳማይ እመቤት በዕለቱ ሽንጣቸው ረጃጅም በሆኑ በጥቋቁር ሊሞዚን ማርቼዲስ አውቶሞቢሎችና በሞተር ብስክሌቶች ታጅበው፣ የሰማይ ስባሪ ከሚያካክሉ፣ ደረታቸው እንደ ሑዳድ እርሻ ከሰፋው፣ ዓይኖቻቸው አራቱን የምድሪቱን ማዕዘን የሚቃኙ ከሚመስሉ፣ ጡንቻዎቻቸው ከፈረጠሙ፣ አረማመዳቸውና መገላመጣቸው ምድሪቱን የሚያንቀጠቅጥ ከሚመስሉ፣ በእጆቻቸው ላይ የውሻ ሰንሰለት የሚያክል አምባር ካጠለቁ፣ በአውሮፓ ውድ አልባሳትና ጫማዎች ከተዋቡ ጠባቂዎቻቸው፣ ከተሽቀረቀረው ዘናጩ ፎቶግራፍ አንሺያቸው፣ የእኚህን እመቤት ቦርሳቸውንና አንዳንድ አስፈላጊና የሆኑ የግል ዕቃዎቻቸውን ካነገቡ፣ ውድ በሆኑ አልባሳትና ጌጣጌጦች ከተዋቡት፣ በቁመት የምታስከነዳቸውን ሞዴል የምትመስል ደንገጡራቸውን አስከትለው ነበር የዛምቢያዋ ቀዳማይ እመቤት ወደ ቀድሞው ገነተ ልዑል ቤተ መንግሥት፣ የአሁኑ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በሞቀና በደመቀ አጀብ የመጡት፡፡

 እኚህ ቀዳማዊ እመቤት ከጉብኝታቸው በፊት ወደዚህ የቀድሞው የአፄ የኃይለ ሥላሴ ቤተ መንግሥትና የአሁኑ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ሊመጡ የቻሉበትን ምክንያት እንዲህ በማለት አስረዱን፡፡ ‹‹የአገሬ ፕሬዚዳንት የሆነው ባለቤቴ በንጉሣችሁ በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዘመን ነፃ የስኮላርሺፕ ትምህርት ዕድል አግኝቶ የተማረው ንጉሡ ቤተ መንግሥታቸውን ዩኒቨርሲቲ አድርገው በሰጡት በዚህ የተከበረ ግቢ ውስጥ ነበር፡፡ እናም አዲስ አበባ ካሉ ቦታዎች ሁሉ መርጬ ወደዚህ የመጣሁበት ምክንያት?›› አሉ እመቤቲቱ፣ ‹‹ውድ ባለቤቴ የተማረበትን ይህን የአገራችሁን የነፃነት ተምሳሌት የሆነውን ዩኒቨርሲቲና ለአፍሪካ አገሮች አንድነትና ኅብረት ትልቁን መሠረት የጣሉትን የእኚህን ታላቅ አፍሪካዊ አባት የኃይለ ሥላሴን ቤተ መንግሥት ጭምር ለማየት ነው የመጣሁት፤›› በማለት የበዛ አድናቆትና አንዳች ትልቅ ጉጉት በሚንፀባረቅበት ስሜት ውስጥ ሆነው ወደ ዩኒቨርሲቲው የመጡበትን ምክንያታቸውን አስረዱን፡፡

በጉብኝታቸው ወቅት ከዛምቢያዋ ቀዳማይ እመቤት ጋር ባደረግነው ቆይታ በኢትዮጵያ ሕዝብ እንግዳ ተቀባይነት፣ ታሪክና ባህል በእጅጉ መመሰጣቸውን በአድናቆት ውስጥ ሆነው ነገሩን፡፡ በመዲናችን በተካሄደው የአፍሪካ ቀዳማይ እመቤቶች ስብሰባም መደሰታቸውንና ስለስብሰባው ፋይዳም እግረ መንገዳቸውን አብራሩልን፡፡ በተጨማሪም በወ/ሮ አዜብ መስፍን ተግባቢነት፣ እንግዳ ተቀባይነትና አክባሪነት፣ ደግነትና ርኅራኄም በእጅጉ መገረማቸውንና መደሰታቸውንም ጨምረው ገለጹልን፡፡

ወ/ሮ አዜብም የዛምቢያዋ አቻቸው እንዳረጋገጡት የእንግዳ ተቀባይነታቸውና ደግነታቸው ምስክር ይሆን ዘንድ ለአገራችን ታሪክና ሥልጣኔ እምብርት የሚባለውን የአክሱምን ታሪክ የሚያሳስብ፣ ለእርሳቸውና በስብሰባው ላይ ተካፋይ ለነበሩት አፍሪካውያን ቀዳማይ እመቤቶች ሁሉ በስጦታ መልክ የአክሱም ሐውልት ቅርፅ ያለው የወርቅ አንገት ሀብል እንዳበረከቱላቸው ደስታና ኩራት በሚንፀባረቅብት ስሜት ነገሩን፡፡
ከጉብኝቱ መጠናቀቅ በኋላ የዛምቢያዋ ቀዳማይ እመቤት በሙዚየሙ የስጦታ መሸጫ ሱቅ የሚፈልጉትንና ዓይናቸው ደስ ያሉዋቸውን ጌጣጌጦችና የስጦታ ዕቃዎች በመምረጥ በደንገጡራቸው በኩል ክፍያ እንዲፈጸም ቀጭን ትዕዛዝ ሰጥተው፣ ጠባቂዎቻቸውንና ፎቶግራፍ አንሺያቸውን አስከትለው የቀድሞውን ቤተ መንግሥት የአሁኑን የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲን፣ የባለቤታቸውን ታላቅና የማይረሳ ትዝታ በልባቸው ጽላት አትመው ወዳረፉበት ሆቴላቸው ታጅበው ተፈተለኩ፡፡

ከጉብኝቱ ፍፃሜ በኋላ የአፍሪካና የአፍሪካዊነት እሮሮዎች፣ ሰቆቃዎች፣ ውጥንቅጦችና እንቆቅልሾች በአእምሮዬ ውስጥ ይመላለሱ ጀመር፡፡ ለጥቂት ደቂቃዎች ከገባሁበት የሐሳብ ማዕበል ውስጥ ሆኜ አንድ ነገር አልኩ፡፡ መቼ ይሆን አፍሪካ የሚራሩላትና ከልብ የሚያዝኑላት መሪዎችን የምታገኘው? እስከ መቼ ልጆቿ እንዲህ ይጨክኑባታል? እስከ መቼስ እንባዋ፣ ሰቆቃዋና ዋይታዋ ከእርሷ ጋር ይዘልቃል …?!

እንግዲህ አፍሪካውያን ርዕሳነ ብሔራንና ቀዳማይ እመቤቶች በየአገሩ ለጉብኝትም ሆነ ለስብሰባ ሲሄዱ ላስከተሏቸው ጠባቂዎቻቸውና ሰዎቻቸው የሚወጣውን የአውሮፕላን ትኬት መግዣ ዶላር፣ የሆቴል ወጪ፣ ፕሮቶኮሉን፣ የስጦታ ዕቃ ግዢውን፣ ለመዝናኛ የሚወጣውን ወጪ ኧረ ስንቱ ይህን ሁሉ ማስላት ነው፡፡ ልብ ይታመማል፣ ኅሊናም ይደክማል፡፡

ይህች ናት እንግዲህ አፍሪካና መሪዎቿ፡፡ በሙስና፣ በመልካም አስተዳደር እጦት፣ በአምባገነን መሪዎቿ የተነሳ በፅኑ ስቃይ ውስጥ ሆና የምታቃስት፣ የምታጣጥር አኅጉር አፍሪካ፡፡ ሕዝቧ በእርስ በርስ ጦርነት፣ በረሃብ፣ በወረርሽኝ፣ በንፁህ ውኃ አቅርቦት እጦት፣ በትምህርት ዕድል ማጣት፣ በድንቁርና ጨለማ ውስጥ የሚዳክሩበት፣ በሆስፒታሎችና በጤና አገልግሎት ሰጪዎች እጥረት ምስኪን ሕዝቧ በሚረግፍባት አፍሪካ፣ ግና ደግሞ መሪዎቿና እመቤቶቿ በሚሄዱበት አገር ሁሉ ሠራዊትና ጠባቂዎቻቸውን አስከትተው የአፍሪካን፣ የገዛ ደሃ ሕዝባቸውን ሀብት እንደፈለጋቸው ያዙበታል፣ ይናዝዙበታል፣ ይረጩታል፡፡

 ከዚሁ ከአፍሪካውያን ቀዳማይ እመቤቶች ቅምጥልነትና አባካኝነት ጋር በተያያዘ በአንድ ወቅት የአንዲት አፍሪካዊት እመቤት የመጀመሪያዋ ጥቁር የአሜሪካ ቀዳማይ እመቤት ሆነው ለተመረጡት ለሚሼል ኦባማ የእንኳን ደስ አለዎት መልእክታቸውን ለመግለጽ ሲሉ በአልማዝ የተንቆጠቆጠ የእጅ ሰዓት ስጦታ ልከው ነበር አሉ፡፡

ይህ ውድ ስጦታ የደረሳቸው ሚሼል ኦባማም ለአፍሪካዊቷ ቀዳማይ እመቤት፣ ‹‹ስለመልካም ምኞትዎ አመስግናለሁ፡፡ ይህ በዕንቁ የተንቆጠቆጠ ውድ ሰዓትም ለእኔ አይገባም፡፡ ምክሬ ደስ ካሰኝዎ ይኼን ብዙ ገንዘብ የፈጀ ውድ ስጦታ ለእኔ ከሚሰጡት በአገርዎ በረሃብ፣ በበሽታና በድህነት እየተሰቃዩ ላሉ ሕዝቦችዎ ቢያውሉት ደስ ይለኛል፤›› በማለት ስጦታውን አልቀበልም በማለት እንደመለሱላቸው ማንበቤን አስታውሳለሁ፡፡

ይህን ከላይ የገለጽኩላችሁን የዛምባያዊቷን ቀዳማይ እመቤት ገጠመኜን እንዳስታውስ ያስገደደኝ ከሰሞኑ ወይዘሮ አዜብ መስፍን በቅርቡ ‹‹ባለቤትም ሆነ እኔ ደሃ ነን፡፡ በታላቁ ቤተ መንግሥት ኑሮአችንን ስንገፋ የነበረው በድህነት ነው፤›› ማለታቸው ግርምት ቢጤ ቢያጭርብኝ ነው፡፡

የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ባለቤት ወ/ሮ አዜብ መስፍን፣ ባለቤታቸው አቶ መለስ ከዓለም መሪዎች ሁሉ ቤሳቤስቲን የሌላቸው ምስኪን የመሆናቸውን ሚስጥር ዛሬም ደግመው በአደባባይ ድህነታችንን ያልሰማችሁ ስሙ፣ የሰማችሁም ላልሰሙት አሰሙ በሚል የመናገራቸው ነገር ለዚህ አጭር ጽሑፍ ምክንያት ሆነኝ፡፡

ወይዘሮ አዜብ ምናልባትም በዚህ ተዓምረኛ ሊባል በሚችል ኑሮአቸው የተነሳ፣ የአንድ ባለታላቅ ታሪክና ሥልጣኔ ባለቤት የሆነች አገር መሪ ሆነው በድህነት ውስጥ ያለፉ ብቸኛዎቹ አፍሪካዊ ርዕሰ ብሔርና ቀዳማይ እመቤት መሆናቸውን ለመግለጽ የፈለጉ ይመስላሉ፡፡

ከዚህ እንደ መዥገር ከተጣባቸው ድህነታቸውም የተነሳ ወይዘሮ አዜብ አቶ መለስ በሚሰጧቸው የወር ገቢያቸው ከኑሮ ውድነት ጋር እየታገሉ፣ ኑሮአቸውን እንደነገሩ ኑሮ አድርገው፣ በቤተ መንግሥት እየኖሩ፣ እንደሆነና ያሳለፉትን የኑሮን ከባድነት ነግረውናል፡፡ እዚህ ላይ መንግሥት በልዩ በጀት እንደሚያኖራቸውና ወደተለያዩ አገሮች ሲጓዙም በመልካም እንክብካቤ መሆኑን አልነገሩንም፡፡ ለጆቻቸው በምርጥ ትምህርት ቤት መማራቸውንም እንዲሁ፡፡

እናም ይኼው ወይዘሮ አዜብ በአገሪቱ የቴሌቪዥን መስኮት ብቅ ብለው ኢትዮጵያና መላው ዓለም መናጢ ደሃ መሆናችንን ይወቅልን በማለት ዳግመኛ ይህን ድህነታቸውን ነግረውናል፡፡ ወይዘሮ አዜብ ኑሮአቸው ሁሉ የችግር፣ በሚያገኟት ገቢ ወር አደረሰን አላደረሰን በሚል ከዚህም ከዚያም ብለው አብቃቅተው፣ በታላቁ ቤተ መንግሥታቸው ከድህነት ጋር አንገት ለአንገት ተናንቀው፣ ቤተ መንግሥቱ ቤተ መንግሥት ሳይመስላቸው በከፋ ድህነት መኖራቸውን የነገሩን መሰለኝ፡፡

ወይዘሮ አዜብ ድህነት፣ የኑሮ ውድነት፣ በነጋ ጠባ ችግር ችግር የምትሉት እኔስ ብሆን ከእናንተ በምን እለያለሁ እያሉን ይመስለኛል፡፡ በአንድ ወቅትም ወይዘሮ አዜብ ከዚሁ ከባለቤታቸውና ከእርሳቸው ድህነት ጋር በተያያዘ እንዲህ ብለው እንደነበር አንዘነጋም፡፡ በዕውቀቱ ዓለምን ጉድ ያሰኘ ባለቤት ኖሮኝ፣ በሺሕ ዶላሮች የሚመነዘር አዕምሮ ያለው ሰው ጋር ሆኜ በችግር የምቆራመደውና የምንቆራመደው ወድጄና ወደን ይመስላችኋል? ለማን ደስ ይበለው ብለን ነው እዚሁ ከእናንተው ጋር በችግር ተቆራምደን፣ የኑሮአችንን ጣጣ ለመድፈን ሌት ተቀን እየባዘንን በሰቀቀን እየኖርን ያለነው የሚል አንድምታ ያለው ንግግር ማድረጋቸው አይዘነጋኝም፡፡ ልዩነቱና የእኛን ድህነት ከሌላው ኢትዮጵያዊ የከፋ የሚያደርገው በመሪ ደረጃና ክብር በቤተ መንግሥት እየኖርን በችግር አለንጋ የምንገረፍ፣ በድህነት አረንቋ ውስጥ የምንዳክር መሆናችን ነው እያሉን መሰለኝ ወይዘሮዋ፡፡

እናም ዛሬም ወይዘሮ አዜብ እርሳቸውም ሆኑ ባለቤታቸው በፔይሮል ተፈርሞ በሚሰጣቸው ከአንድ እጅ ጣት በማይበልጡ ጥቂት ሺሕ ብሮች ወይም የወር ገቢ ‹‹የሴት ብልኃቱን የጉንዳን ጉልበቱን›› እንደሚባለው የሴትነት ብልኃታቸውንና ጥበባቸውን ተጠቅመው ‹‹ለባለቤታቸው ዘውድ፣ ለቤተ መንግሥቱ ንብ›› ሆነው በታታሪነት የቤተ መንግሥቱን ኑሮ በከፋ ድህነት ግን ደግሞ በሴትነት ብልኃት እንደምንም እንደተጋፈጡት እንደገና ሊነግሩን ወደዱ፡፡ ወይዘሮ አዜብ ዛሬም አስረግጠው ወደዳችሁም ጠላችሁም ስለባለቤቴም ሆነ ስለእኔ ያለው እውነታው ይኽው ነው በማለት የትናንትና ሙግታቸውን ዛሬም በአደባባይ ነግረውናል፡፡

መቼም ስለ ድህነት መልክና ገጽታ፣ ስለ መራብ፣ ስለ መራቆትና ስለ ችግር ለወይዘሮ አዜብ መናገር ለቀባሪው አረዱት እንዳይሆንብኝ እሰጋለሁ፡፡ ለምን ሲባል አሰከፊ ከሆነውና ድህነት ሥጋና ነፍስ ነስቶ በአካል ቆሞ የሚሄድበት ከሚመስልበት ከሰሜኑ የአገራችን ክፍል ደሃ ገበሬ ቤተሰብ የተገኙ ሴት ናቸውና፡፡ እናም ወይዘሮዋ ድህነት ምን መሆኑ ይጠፋቸዋል ብዬ ለማሰብ አልደፍርም፡፡

ከዚያም አልፎ ወይዘሮ አዜብ ሆኑ ዛሬ በሥልጣን ላይ ያሉ የትግል አጋሮቻቸው በረሃ ለበረሃ፣ ዱር ለዱር፣ ጥሻ ለጥሻ፣ ቆንጥር ለቆንጥር፣ ገደል ለገደል በረሃብ አለንጋ እየተገረፉ የልጅነት አንጀታቸውን በዝናር መቀነት ጥብቅ አድርገው አስረው፣ በጠኔና ውኃ ጥም ጉሮሮአቸው እየተሰነጠቀ ከችግርና ከመከራ ጋር እየተፋለሙ፣ ደግመው ደጋግመው ከፃረ ሞት ጋር ፊት ለፊት የተጋፈጡ ናቸው፡፡

ወይዘሮ አዜብ ከላይ ከሰማይ እየተመዘገዘጉ የእሳት አሎሎ ውርጅብኝ ከሚያዘንቡ፣ በታች ከምድር የእሳት ነበልባል በሚተፉ አሰቃቂ በሆኑ ዘግናኝ የጦርነት አውድማዎች ላይ የዋሉ፣ በብዙ እንደ መርግ በከበደ መከራና ጭንቅ ውስጥ ላመኑበት ዓላማ ወርቃማ የወጣትነት ጊዜያቸውን የበረሃ ሲሳይ አድርገው፣ ባመኑበት የትግል መስመር ትልቅ መስዋዕትነትን ከፍለው ለዛሬው ሕይወት የበቁ ፋኖ ሴት ናቸው፡፡

እናም በበኩሌ ድህነትን፣ ረሃብን፣ ጉስቁልናንና መከራን ከቃል ባለፈ ወ/ሮ አዜብ በእውን የድህነት ህመምና ስቃይ ብርቱ ሰይፍ ከሥጋቸው አልፎ አጥንታቸው ድረስ ዘልቆ እስኪሰማቸው ድረስ ያውቁታል ብዬ ነው የምገምተው፡፡ ደግሞም በታሪክ እንደማውቀው እነርሱም እንደነገሩን ወይዘሮ አዜብም ሆኑ አቶ መለስና የትግል ጓዶቻቸው ዱር ቤት ብለው ገና በአፍላ የልጅነት ዘመናቸው ምንም ነገር ሳያጓጓቸው ወደ በረሃ ያሳደዳቸው፣ ይህ ሊቋቋሙት ያልቻላቸውና እንቅልፍ የነሳቸው የሕዝባቸው ሁለተናዊ የሆነ መከራ፣ ጉስቁልና እና ቃል የማይገኝለት አስከፊ ድህነት ይመስለኛል፡፡

እነዚህ ፋኖዎች ሕዝባቸው ካለበት አስከፊ ድህነት ውስጥ አውጠተውታል? የጭቁኑ ሕዝብ ወገንና አለኝታ ነን ያሉ እነዚህ ሰዎቻችን የገቡትን ቃል አክብረዋል? ወይስ የሚለው ጉዳይ ሌላ ሰፊ ትንታኔ የሚያስፈልገው ጉዳይ ቢሆንም ቅሉ፡፡ ኢሕአዴግ ወደ ሥልጣን በመጣ ማግሥት የገባው ቃል ሕዝቡን በቀን ሦስቴ ለማብላት ነበር፡፡ ይኸው ዛሬም ከ20 ዓመታት በኋላ ኢትዮጵያችን በምግብ እህል ራሷን ካልቻሉ አገሮች ጎራ ለመውጣት የሞት ሞቷን እየተፍጨረጨረች ያለች አገር የመሆኗ ጉዳይ ሌላኛው እንቆቅልሽ ነው፡፡  

ግና ዛሬ ወይዘሮ አዜብም ሆኑ የመንግሥት ባለሥልጣናት ድንገት ተነስተው ኑሮአችን የድህነት ነው፣ ደሃ ነን ሲሉን መስማታችን ስለየትኛው ደህነት ነው የሚያወሩን ብለን ለመጠየቅ እንገደዳለን፡፡ ባለሥልጣናት ስለሕዝባቸው ድህነት ለመናገር ሁሌም ዝግጁና በተጠንቀቅ ላይ ናቸው፡፡ ነገር ግን ባለሥልጣናቱ ደሃ ነን ቢሉ ግን በእጅጉ የሚያስተዛዝበን ነው የሚሆነው፡፡

በእርግጥ ኢትዮጵያ በዓለማችን ከሚገኙ አገሮች ሁሉ በመጨረሻ ተርታ የምትገኝ መናጢ ከሚባሉ አገሮች የምትመደብ አገር ናት፡፡ ፈጣን የሆነ የኢኮኖሚ ዕድገት እያስመዘገበች ነው ተብላ በዓለም አቀፍ የምጣኔ ሀብት ምሁራንና በዓለም ባንክ ባለሙያዎች ሳይቀር እየተመሰከረላት ያለችው ኢትዮጵያ አሁንም ምድቧ ከመጨረሻዎቹ ደሃ አገሮች ተርታ ነው፡፡

‹‹ይሁን እንጂ….›› ይላሉ በኢትዮጵያ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የልማት ፕሮግራም አማካሪ የሆኑት ሳሙኤል በዋልያ፡፡ ‹‹ኢትዮጵያ በፈጣን ኢኮኖሚ ዕድገት ውስጥ የምትገኝ አገር ብትሆንም፣ ካለችበት ጥልቅ የሆነ ድህነት አረንቋ ውስጥ ለመውጣት የጀመረችው ጉዞ ተስፋ ሰጪም ቢሆንም፣ ኢትዮጵያ አሁንም ቢሆን ግን አስከፊ ከሆነው ድህነት ለመላቀቅ ከፊቷ ረጅም ጉዞ ይጠብቃል፤›› በማለት ነው የሚናገሩት፡፡

የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ እኛ አሁን የሚያስፈልገን ዳቦ እንጂ በምዕራባውያን ልክ የተሰፋ ዲሞክራሲና ነፃነት አይደለም ሲሉ ተናግረው ነበር፡፡ እናም የሚያሳዝነው ዳቦውን ሳንጠግብ የከፋው ድህነት ደግሞ በዜጎች ነፃነት፣ የመጻፍና የመናገር መብትና ዲሞክራሲ ጉዳይ ላይ ላይ ከዕለት ወደ ዕለት እየጠበቀ የመጣው ቀንበር፣ አገሪቱን በአፍጢሟ ሊደፋ ያለና የከፋ ድህነት ሆኖ ክፉኛ እየተፈታተነን ነው ያለው፡፡

ክፉ የሚባለው ድህነት መሪዎቻችን ከሕዝባቸው የሚያገናኛቸውንና የሚያቀራርባቸው የሕዝብ ፍቅር፣ ቀርቦ የመነጋጋርና የመወያየት ድልድይ ዛሬም እንደተሰበረና እየተንገራገጨ ያለ የመሆኑ ጉዳይ ነው፡፡ መንግሥትም ሆነ ባለሥልጣናት ባይገነዘቡት ወይም አውቀው ቢተውት እንጂ የሕዝብን ፍቅርና ተዓማኒነት ከማጣት የባሰ ምን የከፋ ድህነት ምንስ ጉስቁልና ይኖራል? መንግሥትም ሆነ ፖለቲከኞቻችን ስለዚህ የድህነታችን ሁሉ ምንጭ ስለሆነው ስለ ነፃነታችን፣ ስለ መብቶቻችን፣ ስለ ዲሞክራሲያዊ ሥርዓት መስፈንና ማደግ አጥብቀው ቢሠሩ ነው የሚያዋጣው ብዬ አስባለሁ፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጸሐፊውን በኢሜይል አድራሻቸው This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it. ማግኘት ይቻላል፡፡