መነሻ ገጽ - ሌሎች አምዶች - ሕግ እና ፖለቲካ - ልናገር - ካለፈው ስህተት ምን ልንማር ይገባናል?
Buy Valtrex Online Buy Albuterol inhaler Online Buy Prinivil Online
21 August 2013 ተጻፈ በ 

ካለፈው ስህተት ምን ልንማር ይገባናል?

በሐዋርያው ዮሐንስ

“ታ ወር ኢን ዘ ስካይ” በአሁኑ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ቅጥር ግቢ በቀድሞው አጠራሩ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዩኒቨርሲቲ ተፀንሶና ተወልዶ ያደገ በእውነተኛ ታሪክ ላይ ያጠነጠነ ልብ አንጠልጣይ መጽሐፍ ነው፡፡

መነሻና መድረሻውን ጌታቸው ማሩ የተባለ የዘመኑ ታጋይ ወጣት በማድረግ፣ ዓላማውን ከግቡ ሳያደርስ የተቀጨው የወርቃማው ትውልድ የውጣ ውረድ ታሪክ የቀረበበት ነው፡፡

ይህ ሕይወት ተፈራ በምትባል የዚያን ዘመን ወጣት ተጽፎ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ አሳታሚነት ለአንባቢያን የቀረበው ባለ 437 መጽሐፍ፣ ለአሁኑ ትውልድ ትምህርት ይሆን ዘንድ ጸሐፊዋ ተሞክሮዋን ያካፈለችበት ድንቅ ሥራ ነው፡፡

 “ታ ወር ኢን ዘ ስካይ” በኢትዮጵያ ተማሪዎች ንቅናቄ ላይ ተመሥርቶ  በኢትዮጵያ ሕዝብ አብዮታዊ ፓርቲ (ኢሕአፓ)፣ በመላው ኢትዮጵያ ሶሻሊስት ንቅናቄ (መኢሶን)፣ በወዝ ሊግ፣ በማሌሪድና በወታደራዊ ደርግ መካከል የተደረገውን የፖለቲካና የሥልጣን ሽኩቻ የሚዳስስ ነው፡፡ እንዲሁም የጸሐፊዋን ግለ ታሪክና በኢሕአፓ ወጣቶች ሊግ የነበራትን ድርሻ ያካተተ ነው፡፡

ጸሐፊዋ ሕይወት እንደ ማንኛውም ወጣት በጅምላ በኢትዮጵያ ተማሪዎች ንቅናቄ መሳተፍ መጀመሯን፣ ቀስ በቀስም ጌታቸው ማሩ በሚባለው ፍቅረኛዋ አማካይነት በሕቡዕ “አብዮት” በተባለ ማርክሳዊ የፖለቲካ ድርጅት አባል እንደነበረች ትናገራለች፡፡ ሕይወት በሒደት ከጌታቸው ማሩ ጋር በነበራት የፍቅር መጎዳኘት ምክንያት በትግሉ ውስጥ ጠንካራ ግንኙነት ነበራት፡፡ ስለ ቅድመ አብዮት ኢትዮጵያ የተማሪዎች ትግል ስታብራራ፣ ይደረግ የነበረው ትግል በአብዛኛው በመሬት ላራሹ ላይ ያተኮረ እንደነበር ታስታውሳለች፡፡ በ1966 ዓ.ም በወሎ በደረሰው ድርቅ ምክንያት የተማሪዎች እንቅስቃሴ እያየለ በመምጣቱ፣ ሕዝባዊው አመፅ እንደ ተቀሰቀሰና ዘውዳዊ አገዛዙም ጥገናዊ ለውጥ በማድረግ ተቃውሞውን ለመግታት ቢሞክርም፣ ሊቋቋመው ባለመቻሉ ከሥልጣን መውረዱን፣ ቀጥሎም የኢሕአፓ ወጣቶች ሊግ አመሠራረትን በመጽሐፉ ውስጥ አካታለች፡፡ 

ጸሐፊዋ በኢሕአፓ አባላትና በፓርቲው አመራሮች መካከል ያለው ግንኙነት ሕቡዕ በመሆኑ፣ ማንኛውም መመርያ የበላይ አካል (Higher Body) በሚባል የተሸነፈ መሆኑን ገልጻለች፡፡ የድርጅቱ አሠራር ድክመት እንደነበረው አባላቱም እርስ በእርስ እንደማይተዋወቁ፣ በወቅቱ ይነሱ የነበሩ ጉዳዮች ባለቤት የሌላቸው በመሆናቸው ተገቢውን እርምት ለማድረግ እንዳልተቻለ ታክላለች፡፡ “እኛ ያልነውን ተቀበል” የሚል አመራር የነበረው ድርጅት እንደነበረና ለውድቀቱ ቀዳሚውን ምክንያት በበቂ ሁኔታ ግንዛቤ ያስጨበጠች ይመስለኛል፡፡ ሕይወት በወታደራዊ ደርግ፣ በመኢሶንና በሌላ በኩል በኢሕአፓ መካከል የተደረጉትን የሥልጣን ሽኩቻዎች የዳሰሰች ሲሆን፣ ወታደራዊ ደርግ ማርክሲዝም ርዕዮት ምን ማለት እንደሆነ ጠንቅቆ እንደማያውቅ አስረድታለች፡፡ ነገር ግን አገሪቱ ከምዕራቡ ዓለም ታገኝ የነበረው የጦር መሣሪያ በመቋረጡ ፊቱን ወደ ሩሲያ እንዳዞረና እንደልብ በገባው የጦር መሣሪያ ምክንያት ማርክሳዊ ርዕዮትን እንደተቀበለ ታወሳለች፡፡

እዚህ ላይ በእኔ አመለካከት ኢሕአፓ ወይም መኢሶን ለኢትዮጵያ ሕዝብ ይዘው የቀረቡት ገጸ በረከት ወታደራዊ ደርግ የተቀበለውን ርዕዮተ ዓለም ነበር፡፡ ስለዚህ ሁለቱም ድርጅቶች አንድ ዓይነት ርዕዮተ ዓለም የሚከተሉ ከሆነ ለሥልጣን የተደረገው ሽኩቻ ካልሆነ በስተቀር፣ ወደ ቅራኔ የሚያስገባቸው አንዳችም ነገር እንደሌለ ሊሰመርበት ይገባል፡፡

ሌላው በኢሕአፓና በመኢሶን መካከል የነበረው ልዩነት አነስተኛ በመሆኑ በጥቃቅን ጉዳዮች ላይ አተካራ መግባታቸው የማያስገርም ነበር፡፡ ለምሳሌ ኢሕአፓ “እናቸንፋለን” ሲል መኢሶን “እናሸንፋለን” ነው የሚባለው በማለቱ፣ መኢሶን “ወዛደር” ሲል ኢሕአፓ “ላብ አደር” በማለቱ ሁሉም ሊያስተላልፉት የሚፈልጉት መልዕክት አንድ ሆኖ ስለ የቃላት ስንጠቃ እንደ መሠረታዊ ቅራኔ ተደርጎ  ተወስዷል፡፡ ኢሕአፓና መኢሶን በመካከላቸው የነበረውን መለስተኛ አለመግባባት  ጽንፍ ድረስ በመውሰድ አብሮ ላለመሥራት ምክንያት አድርገዋል፡፡ ሌላው ቀርቶ ደርግ ውስጥ የነበሩ ተራማጅ ኃይሎችን ጭምር ከጎናቸው በማሰለፍ አብዮቱን ተረክበው መምራት ሲገባቸው በተሳሳተው ዕርምጃቸው ምክንያት ለእልቂት ተጋለጡ፡፡ በሁለቱም ወገን የነበሩት የአመራር አካላት በፈጠሩት ስህተት ምክንያት ለአገሪቱ ተዓምር መሥራት የሚችል አንድ ትውልድ ለእልቂት ተዳረገ፡፡ 

ከዚህ በተጨማሪ ኢሕአፓ በወጣቶች ላይ የነበረው አቋም በተለይ የድርጅቱ አባል ለመሆን ፍላጎት በሌላቸው ላይ የማግለል ሥራ በመሥራቱ መሠረታዊ የሆነውን የሰውን መብት የተፃረረ ነበር፡፡ እነዚህን በመሳሰሉ ጥቃቅን ጉዳዮች ምክንያት ለአያሌ ንፁኃን ወጣቶችና የድርጅቱ አባላት ሕይወት መቀጠፍ ምክንያት እንደሆነ ለመረዳት ያስችላል፡፡  

ጸሐፊዋ ኢሕአፓ ወደፊት በገጠርና በከተማ ለሚያደርገው የትጥቅ ትግል የአፍሪካ አገሮች ከቅኝ አገዛዝ ለመውጣት ያረጉትን የትጥቅ ትግል ለቅስቀሳ እንደተጠቀመ አውስታለች፡፡ ይህ በኔ አመለካከት የትጥቅ ትግሉ የሥርዓት ለውጥ እንዲያመጣ በማሰብ የተደረገ ከሆነ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ከጣሊያን ጋር ያረጉት ትግል የሥርዓት ለውጥ ባመጣ ነበር፡፡ በሌላ በኩል በተሳሳተ ውሳኔ የከተማ ውስጥ የትጥቅ ትግል እንዲደረግ የኢሕአፓ አመራሮች በጭፍን በመወሰናቸው ምክንያት፣ ከለላ የሌላቸው ወጣቶች ለእልቂት ተዳርገዋል፡፡ 

ከ1966 ዓ.ም በኋላ አያሌ የፖለቲካ ድርጅቶ ተፈጥረው እንደነበረ ይታወሳል፡፡ ለምሳሌ ማሌሪድ፣ መኢሶን፣ ኢሕአፓ፣ ወዝ ሊግና ሰደድና እንደነበሩ አይዘነጋም፡፡ ሁሉም ማርክሲስት ድርጅቶች ቢሆኑም አንድ ዓይነት ዓላማ ኖሯቸው አብረው መብረር ስላልቻሉ መስማማትና አብረው መሥራት ተሳናቸው፡፡ በኋላም በወታደራዊው ደርግ አንድ ባንድ እየተለቀሙ ብዙዎቹ ወደ እስር ቤት፣ የተቀሩት በመሣሪያ እልቂት ተፈጽሞባቸው ቀሪዎቹ የመበታተንና የመሰደድ ዕጣ ደርሷቸዋል፡፡

ሕይወት በመጽሐፏ ውስጥ “They paid ultimate price for their intolerance, ridgity, and miscalculation, fell one by one like Autumen Leaves” በማለት አስቀምጣዋለች፡፡ በወቅቱ የነበሩ የፖለቲካ ድርጅቶች በሰላም ጊዜ በክብ ጠረጴዛ ያልፈቱትን በኋላ ሁሉም ድርጅቶች በኃይል ወደ ከርቸሌ ሲወረወሩ የነበራቸውን ልዩነት በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት መሞከራቸውን፣ አንዳንዶች ታስረው ከተፈቱ በኋላ በጻፉት መጽሐፍ ውስጥ ተመልክቸዋለሁ፡፡ ታዲያ ደርግም ሆነ መኢሶን ወይም ኢሕአፓ በመካከላቸው ለተከሰተው አለመግባባት ምክንያቶች አንደኛ የሥልጣን ጥያቄ፣ ሁለተኛ ለ1966 ዓ.ም ሕዝባዊ አመፅ ምላሹ ሥልጣን በወታደራዊ ደርግ እጅ መውደቅ፣ ሦስተኛ በአገር ውስጥ በነበሩና በውጭ ይኖሩ በነበሩ ማርክሲስቶች መካከል መናናቅ መፈጠሩ ሲሆኑ፣ አራተኛው ለኢትዮጵያ ሕዝብ የቀረበው የርዕዮተ ዓለም መስተንግዶ አንድ ዓይነት መሆኑ ነው፡፡ እነዚህ ከላይ እስከ ያስቀመጥኳቸው አራት ምክንያቶች ለአያሌ ወጣቶች በከንቱ ደም መፍሰስ፣ ለእርስ በርስ ግጭትና ለውጭ ወራሪ ኃይሎች አመቺ ሁኔታ ፈጥረዋል፡፡  በአጠቃላይ የጦርነት ነጋሪት ዳር እስከ ዳር የተጎሰመባቸው ሌሎች አስቸጋሪ ጉዳዮች የተስተናገዱበት ነበርም ማለት ይቻላል፡፡ ምንም እንኳን ዛሬ  ከላይ በዝርዝር የተገለጹት ጉዳዮች  በአገራችን ሊከሰቱ የማይችሉና ጊዜ ያለፈባቸው አስተሳሰቦች ናቸው ቢባሉም፣  ለታሪክ መረጃነት ግን ለአሁኑ ትውልድ የነበረውን ሁኔታ ለግንዛቤ ማቅረቡ ተገቢ ይመስለኛል፡፡ በሌላ በኩል በአንዳንድ ፖለቲከኞች ዘንድ የሚታየው ዛሬም ከዚያ ዓይነቱ  አባዜ ያለመላቀቅ ባህሪን ለማጤን ይረዳል፡፡

ዛሬስ በአገራችን ውስጥ በሚገኙ የፖለቲካ ድርጅቶች መካከል ያለው ልዩነት ምንድነው? በአንድ ወቅት የመተባበር በሌላ ጊዜ የመለያየት እንዲሁም እርስ በእርስ መናቆር ምክንያቱ ምን ይሆን? የርዕዮተ ዓለም ልዩነት አለ ወይ? ቢኖርስ እንኳን በሚያግባባቸው ጉዳይ ላይ አብሮ የመሥራት፣ በማያግባባቸው ደግሞ የመቻቻል ወይም በክብ ጠረጴዛ ተወያይቶ በሠለጠነ መንገድ ልዩነትን ለማጥበብ መሞከር፣ ወይም አቻችሎ መሄድ አይቻልም ወይ? በአገራዊ አንድነትና  ጥቅም ላይ አንድ ለመሆን የማይቻለው ለምንድነው? ካለፈው ትውልድ ታሪክ መማርስ ለምን ያቅተናል? ለሰው ልጆች ሕይወት ክብር በመስጠት ልዩነትን በሰላማዊ መንገድ መፍታት እንደሚቻል እያወቅን፣ በዚሁ ቀና ጎዳና ለመጓዝ ምን ያዳግተናል? ለዚህ ጽሑፍ መነሻ የሆነችኝን ሕይወት ተፈራን እያመሰገንኩ፣ የታሪክ ተወቃሽ ላለመሆን በተቻለ መጠን ገንቢና አንኳር  በሆኑ አገራዊ ጉዳዮች ላይ ተባብረን ብንሠራ ምን ይመስላችኋል?  ከጊዜያዊ የፖለቲካ ፍጆታዎችና ጥቅሞች ይልቅ ለትልቁ አገራዊ አጀንዳ ስንል ችግሮቻችንን በሰከነ መንገድ ብናያቸውስ?