መነሻ ገጽ - ሌሎች አምዶች - ሕግ እና ፖለቲካ - ተሟገት - የኢሕአዴግ ጉባዔ የዘነጋቸው ቁምነገሮች
Buy Valtrex Online Buy Albuterol inhaler Online Buy Prinivil Online
31 March 2013 ተጻፈ በ 

የኢሕአዴግ ጉባዔ የዘነጋቸው ቁምነገሮች

በዘሪሁን በላይ

አሁን ያለችው ዓለም ባለብዙ ዋልታ (Multipolar) ነች ሲባል አሜሪካን ከመሳሰሉ የአንድ ርዕዮተ ዓለም አራማጆችና የሶሺዮ ኢኮኖሚያዊ ተፅዕኖ ፈጣሪ አገሮች መዳፍ ውጭ ለማሰብ ዕድል ተፈጥሯል እንደማለት ነው፡፡

በተለይም እንደ ቻይና፣ ህንድና ብራዚል ያሉት አገሮች የጀመሩት ፈጣን የኢኮኖሚ ዕድገት፣ እንደ ኮሪያና ጃፓን ያሉት የእስያ አገሮች የቴክኖሎጂ ምጥቀት ላላደገው ዓለም የተስፋ ብርሃን እየፈነጠቁለት መሆኑ አይካድም፡፡ ይህ ማለት ግን ዓለም በአንድ የጨዋታ ሕግ አትገዛም ማለት አይደለም፡፡

የፖለቲካ ተንታኞች እንደሚያስረዱት፣ በፖለቲካ ዕርዳታቸው ሊበራል፣ ሶሻል ዲሞክራሲ፣ ሶሻሊስት ወይም ልማታዊ ዲሞክራሲም ሆነ ሌላ (ቅይጥ) የሚከተሉ አገሮች ተገዥ የሚሆኑባቸው የዓለም ድንጋጌዎች አሉ፡፡ በተለይም እ,ፈ ረጅሟ አሜሪካ በቀላሉ በምታዛቸው የኢኮኖሚና የፖለቲካ ተቋማት (አይኤምኤፍ እና የዓለም ባንክ)፣ የተባበሩት መንግሥታትና መሰል ዓለም አቀፍ ድርጅቶች አማካይነት የምታስቀምጣቸውን ቅድመ ሁኔታዎችና ድንጋጌዎችን እንደፈለጉ መሸራረፍ የራሱ ችግር አለው፡፡

ዛሬ ማንም አገር ብድግ ብሎ (ሁኔታዎች ቢፈቅዱለት እንኳን) የኑክሌር ማብላያ መገንባትና ቴክኖሎጂውንም ለጦር መሣርያ መጠቀም አይችልም፡፡ አደንዛዥ ዕፅን አምርቶ መሸጥ ወይም አካባቢን በገፍ የሚክል ከፍተኛ ካርቦን ዳይኦክሳይድ መልቀቅ ውግዘትን ያስከትላል፡፡ ሕገወጥ የሰዎች ዝውውር፣ የጦር ወንጀለኝነትና ሽብርተኝነትም ቢሆኑ ዓለም በአንድ አለቃ ሥር መሆኗን የሚያስገነዝቡ ጥፋቶች ናቸው፡፡

እነዚህና ሌሎች ‹‹The Geneva Conventions of August 12,1949›› በሚባለው ዓለም አቀፍ ስምምነት የተደነገጉ የሰብዓዊና ዲሞክራሲ መብት ጥያቄዎች ሁሉ ለዓለም ሕዝብ እንዲከበሩለት ይጠበቃል፡፡ ምንም እንኳን ዓለም ከዚህ ድንጋጌ በፊትም ሆነ በኋላ (እነ ስታሊን፣ ሂትለር፣ ሞሶሎኒ፣ ሳዳም ሁሴን፣ ጋዳፊ፣ መንግሥቱ ልብ ይሏል) በርካታ አምባገነኖች ቢፈጠሩባትም፣ ሰዎች ‹‹ሰው›› በመሆኗቸው ሊያገኛቸው የሚገቡ መብቶችና ጥቅሞች እንዳይገፈፉ በርካታ መስዋዕትነቶች ተከፍለዋል፡፡

ኢሕአዴግም ቢሆን ለአሥራ ሰባት ዓመታት በተካሄደው እልህ አስጨራሽ ትግል ውስጥ ያለፈው የዲሞክራሲያዊና ሰብዓዊ መብቶችን በፅናት ለማስተግበር ነው፡፡ በሒደቱ የቀይ ሽብር ሰማዕታትን ጨምሮ በመላ አገሪቱ ‹‹አንድ ትውልድ›› በሚባል ደረጃ መክኖ የቀረው (በዚያው መዘዝ እስኪሆን የፖለቲካ ትግልን እንደ ሞት መንስዔ የሚቆጥረው ብዙ ነው) ትልቅ ግምት ሊሰጠው የሚችል አምራች ኃይል ጭዳ ሆኖበታል፡፡ ለዲሞክራሲ፡፡

በእርግጥ ባለፉት ሁለት አሥርት ዓመታት ውስጥ ኢሕአዴግ ‹‹በመርህ›› ደረጃም ቢሆን የጄኔቫውን ዓለም አቀፍ ስምምነት በመቀበል በአገሪቱ ለመተግበር የተንቀሳቀሰ ሥርዓት መሥርቷል፡፡ ገና ከደርግ ሥርዓት መውደቅ ማግስት ከሌሎች በርካታ የፖለቲካ ፓርቲዎችና ድርጅቶች ጋር በመሆን የሽግግር ጉባዔ ቻርተር አፅድቋል፡፡ በ20 አንቀጾች የተከፋፈለው ይህ ቻርተር ዋነኛ ማጠንጠኛዎቹ የሰብዓዊና የዲሞክራሲያዊ መብቶች ነበሩ ቢባል ማጋነን አይሆንም፡፡

በባንክ ሙያ የሚተዳደር አንድ የማውቀው ሰው የሽግግሩ ዘመን በቻርተሩ ብቻ ሳይሆን በተግባርም የዲሞክራሲ ጭላንጭል የታየበት ነበር ይላል፡፡ የአምባገነኑ ሥርዓት መገርሰስ፣ በአገሪቱ የነበረው አለመረጋጋትና ከአሃዳዊ ወደ ፌደራላዊ ሥርዓት የሚደረገው ሽግግር በራሱ ፈታኝ ነበር፡፡ በዚያ ሁኔታ ውስጥ የግል ፕሬስ እንደ እንጉዳይ መፍላት፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች መቋቋምና በነፃነት መንቀሳቀስ መጀመር፣ በተቻለ መጠን ያለፍርድ ቤት ትዕዛዝ ያለመያዝ፣ ቶርችን የመሰሉ ያልተገቡ የተጠርጣሪዎች አያያዞች መቆም፣ ወዘተ መታየት ችለው ነበር እያለ ይህ የባንክ ባለሙያ ይዘረዝራል፡፡

በኋላ በኢትዮጵያ ሕዝቦች ይሁንታ የፀደቀው (አንዳንድ ያኮረፉና ያልተቀበሉት አካላት ቢኖሩም) ሕገ መንግሥት መሠረታዊ የተባባሩት መንግሥታት ድርጅትን ድንጋጌዎች ሳይሸራርፍ የተቀበለ ነው፡፡ በመሆኑም የብዙ ሰው ተስፋ የሰብዓዊና ዲሞክራሲ መብቶች ጉዳይ ይበልጥ እንደሚሻሻል ነበር፡፡ የዲሞክራሲ ባህል እየጎለበተ፣ ሁሉም ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች በእኩልነት የሚዳኙበትና ሐሳብን በነፃነት ማራመድ፣ መደራጀትና በሰላማዊ መንገድ መቃወም እየሰመረ የሚሄድበት ዕድል እየተጠናከረ ይመጣል የሚል እምነት የብዙዎች ነበር፡፡

ኢሕአዴግ በተለይ ከምርጫ 97 ወዲህ አጥብቆ የተከተለው ‹‹የልማታዊ መንግሥት›› መርህ ግን ከላይ የተጠቀሱት ጉዳዮች ላይ እንዲያተኩር አላደረጉትም፡፡ በቪኮድ የሰብዓዊና ዲሞክራሲ መርሆዎች አሠልጣኝ የሆኑት ባለሙያ እንደሚናገሩት፣ ‹‹በአገሪቱ የሚገኙ ብሔሮች፣ ሴቶች፣ አካል ጉዳተኞችና ድጋፍ የሚሹ ወገኖች ትኩረትና እገዛ እየተደረገላቸው ነው፡፡ ከቦታ ቦታ ተንቀሳቅሶ የመሥራትና የኢኮኖሚ ነፃነት (ሀብት የማፍራትም) በአጭር ጊዜ መሻሻል አሳይቷል፡፡ ወደኋላ እየተመለሰ የሚመስለው ግን የፖለቲካ ምኅዳር ማስፋትና አሳታፊ የማድረጉ ሥራ ነው፤›› ይላሉ፡፡

ለዚህ አብነት ከሚጠቀሱት አንዱ በገጠርም ሆነ በከተማ ኢሕአዴግ አባላት ማብዛትን (በተፅዕኖ ጭምር) እንደ አማራጭ መውሰዱን ነው፡፡ በተሞክሮ ለኢሕአዴግ አውራ የሆነችው ቻይና እንኳን የኮሙዩኒስት ፓርቲው አካል ያደረገችው ከሕዝቧ 0.3 በመቶ (4 ሚሊዮን) ያህሉን ብቻ ሲሆን፣ ከዓለም ሕዝብ አንድ አምስተኛውን የያዘች አገር እንደመሆኗ የሚጋነን ቁጥር አይደለም፡፡ ኢሕአዴግ ግን 6.5 ሚሊዮን (ከመላው ሕዝብ 8.2 በመቶ) የሚሆነውን አባል ያደረገ ሲሆን፣ በአንድ ዓመት ውስጥ አኅዙን በእጥፍ ለማሳደግ እየሠራ ነው፡፡ ይኼ ደግሞ አማራጭ ልዩነቶች እንዳይስተናገዱ ከመገደቡ ባሻገር ዜጎች ወደዱም ጠሉም የገዥው ፓርቲ አባል እንዲሆኑ የሚያስገድዱ ሁኔታዎች እንዲሰፉ ያደርጋል፡፡

በቅርቡ የኢዴፓ ፕሬዚዳንት አቶ ሙሼ ሰሙ ለፖለቲካ ምህዳር መጥበብ መገለጫ አድርገው የጠቀሷቸውን ነጥቦች ማንሳትም ተገቢ ነው፡፡ በሕጋዊ መንገድ ተደራጅተው የሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ ድርጅቶች ሕዝቡን በቀላሉ አግኝተው የሚያናግሩበት፣ የተቃውሞም ሆነ የድጋፍ ሠልፍ የሚጠሩበት፣ እስከታችኛው መዋቅር ተንቀሳቅሰው የሚያደራጁበትና የሚያታግሉበት መድረክ የተዘጋ መስሏል ነበር ያሉት፡፡ የገዥው ፓርቲ ካድሬዎች የሕገ መንግሥቱን ምሶሶዎች ሳይቀር እየዘጉት ከኢሕአዴግ ውጭ አማራጭ እንደሌለ አድርገው መንቀሳቀሳቸው የዲሞክራሲ ባህሉን የሚያቀጭጭና ወደኋላ የሚመልስ ነው፡፡

በዲሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ እንደ ትልቅ መገለጫ የሚቆጠረው ምርጫም ቢሆን ሒደቱ ዕድገት አላሳየም፡፡ ለዚህ ጽሑፍ ዝግጅት ሲባል ያነጋገርኳቸው አንዳንድ አስተያየት ሰጪዎች ‹‹ምርጫ አለ እንዴ?›› ሲሉ በግርምት ጠይቀዋል፡፡ ሌሎቹ ደግሞ የሚኖሩበት ቤት ድረስ እየተመጣ ‹‹ለምርጫ ተመዝገብ ኢሕአዴግን ምረጥ›› የሚለው ቅስቀሳ አሰልችቷቸዋል፡፡ ከዚያም አልፎ 1ለ5 በሚባለው ትስስር ሲገቡና ሲወጡ በጉዳዩ ላይ የሚደረገው ጉትጉታ የተለየ ሆኖባቸዋል፡፡ በእንዲህ ዓይነት ሁኔታ መንግሥትም፣ አውራ ፓርቲም ሆኖ ከሚንቀሳቀስ አካል ጋር ተወዳድሮ ለማሸነፍ መመኘት ጉልበትን ማድከሙ አይቀርም፡፡

ሐሳብን በነፃነት የመግለጽ መብት በሕገ መንግሥቱ ቢረጋገጥም የተጋረጠበት አደጋ ቀላል አይደለም፡፡ ማንኛውም ሰው በፈለገው አግባብ ሐሳቡን ሲገልጽ ‹‹ከፀረ ሽብርተኝነት›› ሕጉ ጋር ከተላተመ ወህኒ ሊወርድ ይችላል፡፡ ይህ ደግሞ በመረጃ ነፃነት ትግበራው ላይ የተደቀነ አደጋ መሆኑን ዛሬ ፍርድ ቤት በሚመላለሱ ዜጎች ማረጋገጥ ይቻላል፡፡

አንዳንድ አስተያየስ ሰጪዎች ‹‹የሕግ የበላይነት›› ጉዳይንም ሲጠራጠሩ ይስተዋላል፡፡ በየደረጃው የሚገኙ ፍርድ ቤቶች ከአስፈጻሚው ተፅዕኖ ውጭ አይደሉም፡፡ በቀርቡ የአዲስ አበባ ፍትሕ ቢሮ ‹‹የማስቀጣት አቅማችን በእጥፍ አድጓል›› ሲል የገለጸውን ማብራሪያ መንግሥት ጠንካራ መዳፉን ፍርድ ቤቶች ላይ ጭኖ እንዳሳካው አስተያየት ሰጪዎች ተናግረው ነበር፡፡ የፖለቲካ አንድምታ ያላቸው የፍርድ ሒደቶች ደግሞ ይበልጥ ለትችት የተጋለጡ ናቸው፡፡

በአጠቃላይ ሲታይ ኢሕአዴግ በአገሪቱ በልማቱ መስክ በተለይ ባለፉት አሥር ዓመታት ያሳየውን እመርታ ያህል በዲሞክራሲ ሥርዓት ግንባታው እንዳላስመዘገበ ብዙዎች ይስማማሉ፡፡ ሥርዓቱ ‹‹የመድበለ ፓርቲ›› ነው ቢባልም የተቃዋሚው ጎራ በኢሕአዴግ ጫናና በራሱ ድክመት ጭምር እየተበታተነና እየከሰመ ይገኛል፡፡ ባለፉት 21 ዓመታት አንድም የተቃዋሚ ፓርቲ ነፍስ ዘርቶ የራሱ በቂ ቢሮና አደረጃጀት ኖሮት፣ አመርቂ ፖሊሲና ስትራቴጂ ቀርጾ፣ አባላትና ደጋፊዎችን አፍርቶ ‹‹ብቁ ተወዳዳሪ›› ሲሆን አላየንም፡፡ ይኼ ደግሞ የኢሕአዴግም ውድቀት መሆኑ መዘንጋት የለበትም፡፡

በቅርቡ በተካሄደው 9ኛው የድርጅቱ ጉባዔ ላይ ስለዲሞክራሲ ሥርዓቱ ጉዞ ራሱን አስችሎ ውይይትና የመፍትሔ አቅጣጫ ያለመቀመጡ ደግሞ አሳሳቢ ነው፡፡ በአንድ በኩል የሕዝቡ ዝምታና የፖለቲካ ፓርቲዎተ መፋዘዝ፣ በሌላ በኩል ኢሕአዴግ በጀመረው ዘርፈ ብዙ የመስፋፋት ስልት የተዘነጋ አጀንዳ መስሏል - ‹‹ዲሞክራሲ››፡፡

ከቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ሕልፈት አንስቶ ሁለም ብሔራዊ ድርጅቶች ጭምር በልማትና በመልካም አስተዳደር ላይ መክረዋል፡፡ የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ አፈጻጸሙ ላይም እንዲሁ፡፡ የዓለም አቀፍ ድንጋጌው፣ የሕገ መንግሥቱም ሆነ የዋና ዋና ፖሊሲዎች ትልቁ ምሰሶ ደብዝዞ የቀረበት እንቆቅልሽ ግን ሊፈታ ይገባዋል፡፡ እርግጥ ኢሕአዴግ ‹‹የልማታዊ መንግሥት ፖለቲካዊ ኢኮኖሚ›› አጠንክሮ በመቀጠሉ ችላ ተብሎ ነው? ወይስ በወሬ ወሬ እንደሚባለው ‹‹ቅድሚያ ለዳቦ›› ሆኖ ነው?

ሌላው ቀርቶ ከአሥር ዓመት በፊት በተቀረፁት ፖሊሲዎች ላይ የተቀመጠው መሠረታዊ ነጥብ ለምን ይዘነጋል? ‹‹የውጭ ጉዳይና አገራዊ ደኅንነት ፖሊሲ›› ገጽ 8 ላይ እንዲህ ሰፍሯል ሐሳቡ፡፡ ‹‹የአሁኑ አገራዊ ውርደታችን መሠረታዊ ምንጭ ድህነትና ኋላ ቀርነት፣ የዲሞክራሲና የመልካም አስተዳደር እጦት ነው፡፡ ሕዝባችንን ከዚሁ ውርደት ለማላቀቅ አንድ የጋራ አገራዊ እምነትና አመለካከት ይዘን ተከባብረንና ተፈቃቅደን በአንድነት ለመረባረብ ያለመቻላችን ነው፡፡ . . . ከምንም ነገር በላይ በልማትና በዲሞክራሲ ላይ በመረባረብ አገራዊ ክብራችንን ማስጠበቅ ይኖርብናል፡፡ . . . አገራዊ ክብርን የማስጠበቅ ጉዳይ ከዚህ አኳያ የሚጨምረው ነገር ካለ ለዲሞክራሲና ለልማት የምናደርገው ርብርብ በፍጹም ፋታ የማይሰጥ መሆኑን፣ ከዚህ ውጭ ያለው ነገር በምንም ዓይነት መንገድ ከዋናው ዓላማችን ሊያዘናጋን የማይገባ መሆኑ ግልጽ መደረግ አለበት፤›› ይላል፡፡

እንግዲህ ከምንም በላይ ለሕዝብ ልዕልና መረጋገጥ፣ ለአገራዊ ክብር መስፈንና ውርደታችንን ለማስወገድ ዋነኛ መንገድ የሆነው የዲሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ እንዴት በግርድፍ ሊታለፍ ይችላል?

ኢሕአዴግ ባለፉት 22 ዓመታትስ ሆነ በየጉባዔ ዘመኖቹ በዘርፉ ያስመዘገበውን ውጤትና የቀረውን ሥራ ለምን ቆጥሮ መገምገም ይሳነዋል? ወይስ ሚዛኑ በልማታዊ ዲሞክራሲያዊ መለኪያ እየታየ ነው?

ልማት ፍትሐዊ ሥርጭቱን አረጋግጦ ከተስፋፋ ለዲሞክራሲ መጎልበት አስተዋጽኦ እንደሚያደርግ ግልጽ ነው፡፡ የመልካም አስተዳደር መስፍን (ገና ችግር ያለበት ነው)፣ የኪራይ ሰብሳቢነትና አድርባይነት ፈተና እስካልተወገደ ሁሉንም አስተሳስሮ እውን ማድረግ አይቻልም፡፡ ከምንም በላይ ግን ግልጽ፣ ፍትሐዊና ተጠያቂነት ያለበት የፖለቲካ ሥርዓት መስፍን ይኖርበታል፡፡ ለዚህ ደግሞ የዲሞክራሲ ምሰሶዎች ሳይሸራረፉ ሊተገበሩ ግድ ነው፡፡ እዚህ ላይ የጉባዔው ውሳኔ አለመሰማቱ አስጊ መሆኑ ከወዲሁ መረዳት ተገቢ ይመስለኛል፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጸሐፊውን በኢሜይል አድራሻቸው This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it. ማግኘት ይቻላል፡፡