መነሻ ገጽ - ሌሎች አምዶች - ሕግ እና ፖለቲካ - ተሟገት - አረም የወረሰው የመረጃ ነፃነት ትግበራ
Buy Valtrex Online Buy Albuterol inhaler Online Buy Prinivil Online
07 April 2013 ተጻፈ በ 

አረም የወረሰው የመረጃ ነፃነት ትግበራ

በዘሪሁን በላይ

መረጃ በመላው ዓለም አስፈላጊ ሀብት መሆን ከጀመረ ውሎ አድሯል፡፡ በተለይም ከቅርብ አሥርት ወዲህ በቴክኖሎጂ እየታገዘ በመምጣቱ ‹‹ዓለምን አንድ ማድረግ›› የቻለ መሣሪያ ነው፡፡

ዓለም ከአንዱ ጫፍ ወደ ሌላ ጫፍ በሰከንዶች ውስጥ መረጃ ይለዋወጣል፡፡ በዚሁ ተመሥርቶም የፈለገውን ሥራ ሁሉ መከወን ይችላል፡፡ ለዚህም ነው ዘመኑ (Era) ጭምር የኢንፎርሜሽን ዘመን እስከመባል የደረሰው፡፡

ከዚህ እውነት በመነሳት አገሮች መረጃን መገደብ አስቸጋሪ እንደሆነ ተገንዝበዋል፡፡ ስለሆነም የዲሞክራሲ ሥርዓት መሠረት የሆነውን የመረጃ ነፃነት (የመናገር፣ የመጻፍና መረጃ የማግኘት መብታችን) እውን ለማድረግ እየተጣጣሩ ናቸው፡፡ በዚህ ጽሑፍ ጋዜጠኛው መረጃን ከየትም ብሎ ፈላልጎ ስለሚዘግብበት መንገድ ብዙ ማለት አልተፈለገም፡፡ ከዚያ ይልቅ በአገራችን በመረጃ ነፃነት ትግበራው ዙሪያ መንግሥትና ባለድርሻ አካላት ምን ሚና እየተጫወቱ እንደሆነ ለመዳሰስ ይሞከራል፡፡ ዘርፉ የተደቀነበትን አደጋ ለመጠቆምም ጥረት ይደረጋል፡፡

አገራችን የመረጃ ነፃነት ጉዳይ በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 29 ከመረጋገጡም ባሻገር፣ የመገናኛ ብዙኀንና የመረጃ ነፃነት አዋጅ 590/2000 በማፅደቅ ለትግበራው ቁርጠኝነቷን አሳይታለች፡፡ ከዚያም አልፎ የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች በአዋጁ ክፍል ሦስት መሠረት የተጣለባቸውን መረጃ የመስጠት ግዴታ እንዲወጡ አስፈጻሚ (አመቻች) መሥሪያ ቤት ተቋቁሟል፡፡ በእንባ ጠባቂ ተቋም ሥር የመረጃ ነፃነት ዳይሬክቶሬት ማለት ነው፡፡ ትልቁ ጥያቄ አዋጁ ከወጣ አንስቶ ምን ተሠራ? ምንስ ውጤት ተገኘ? የሚለው ነው፡፡

በነገራችን ላይ አዋጁ በመረጃ ነፃነት ጉዳይ ላይ እንከን የለሽ ነው የሚባለው መረጃ ፈላጊዎች በተቻለ ፍጥነት እንዲያገኙ፣ በተለየ ሁኔታ ካልተደነገገ (የወታደራዊና ደኅንነት ሚስጥር ዓይነት) በስተቀር ማንኛውም ሰው ከማንኛውም መንግሥታዊ አካል መረጃን የመጠየቅ፣ የማግኘትና የማስተላለፍ መብቱ በማረጋገጡ ነው፡፡ የትኛውም የመንግሥት ኃላፊ (በተለይ የሕዝብ ግንኙነትና የበላይ ኃላፊው) መረጃ እንዳይከለክል ያግደዋል፡፡ አንዲህ ዓይነት በዝርዝር የተጠቀሱ አንቀጾች ዜጎች የመንግሥት መረጃን ያለገደብ እንዲያገኙ ብቻ ሳይሆን፣ የግልጽነትና ተጠያቂነት መርህ እንዲተገበር፣ በመረጃ ላይ የተመሠረተ ኪራይ ሰብሳቢነትን ለመታገልና የሕዝቡን ተሳትፎ ለማሳደግ ያግዛሉ፡፡

እንባ ጠባቂ ተቋም ግን በዚህ ረገድ ያሳካው ውጤት አይታይም፡፡ ከፌዴራል እስከ ክልል መሥሪያ ቤቶች የሚገኙ የሥራ ኃላፊዎችንና የሕዝብ ግንኙነት ባለሙያዎችን በአዲስ አበባ፣ በክልል ከተሞችና በሶደሬ ሳይቀር ለተደጋጋሚ ጊዜ እያዝናና አሠልጥኗል፡፡ በመረጃ ነፃነት ዳይሬክቶሬት ሥር ያሉ ባለሙያዎችን በተለያዩ የአውሮፓና የአፍሪካ አገሮች እያመላለሰ ልምድ እንዲቀምሩ አዟዙሯል፡፡ በመረጃ ነፃነት ዙሪያ እየተዘጋጁ ሕትመቶችና በተለያዩ መገናኛ ብዙኅን (አንድ ሰሞን አዲስ ዘመን ጋዜጣ ዋና ሥራው አድርጎት ነበር) ብዙ ሐሳቦች ተንሸራሽረዋል፡፡ በተግባር ግን የትኛው ሚኒስትር መሥሪያ ቤት ወይም ክልል በአዋጁ መሠረት በጥራት፣ በፍጥነትና በፍትሐዊነት መረጃ እየሰጠ መሆኑ አይታወቅም፡፡

እንደ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ያሉ የፌዴራል ተቋማት መረጃን በኢንፎርሜሽንና ኮሙዩኒኬሽን ቴክኖሎጂ በመደገፍ፣ በተች ስክሪን የባለጉዳዮችን ቀጠሮ መንገር ጀምረዋል፡፡ የውልና ማስረጃ የኤሌክትሮኒክ ወረፋም ሊጠቀስ ይችላል፡፡ ዛሬ እንደ ኢሚግሬሽን ባለው መሥሪያ ቤት ለሚፈጠረው ወረፋና ‹‹ድርድር›› መረጃ የራሱን ድርሻ አይጫወትም ነበር? ምንም እንኳን የተሟላ መረጃ የሚሰጡ ባይሆኑ በርካታ መሥሪያ ቤቶች የራሳቸው ድረ ገጽ መክፈታቸው አንድ አማራጭ ቢሆንም፣ ባለጉዳዮች በየተቋሙ በአካል ሄደው መረጃ በፈለጉት ይዘትና በአጭር ጊዜ እያገኙ መሆናቸው አልተደመጠም፡፡

እንዲያውም አሁን ከመልካም አስተዳደር እጦት ጋር በተጀመረው የማካካሻ መርሐ ግብር በማዘጋጃ ቤት አገልግሎት፣ በመሬት፣ በገቢና መሰል ዘርፎች የሚታየው መጉላላት ከመረጃ እጦት ጋር ይያያዛል፡፡ እንደ ቴሌ፣ ኤሌክትሪክ ኃይልና ውኃን የመሳሰሉ አገልግሎቶች በተለያዩ ምክንያቶች ሲቋረጡ እንኳን ማን ሕዝብን አክብሮ መረጃ ይሰጣል? ማንስ ይቅርታ ለመጠየቅ አንደበቱን ይከፍታል?

በየደረጃው ባለው አመራር አካባቢም የታየው ‹‹ፋሽን›› ይኼ ተከናውኗል፣ በርካታ ውጤት ተመዝግበዋል፣ ከይኼን ያህል በላይ (እስከ እልፍ አዕላፍ ሊደርስ ይችላል) ተገኘ ወይም ተፈጸመ እያሉ ጨማምሮ ማቅረብ ብቻ ነው፡፡ ወይም ያጋጠሙ ተግዳሮቶችንና ውድቀትን እየሸፋፈኑ ስኬታማ ክንውን (Success Story) ማጉላት ነው፡፡ ታዲያ በዚህ ሁኔታ እንዴት ያለ ግልጽነትና ተጠያቂነት የተላበሰ የመረጃ ነፃነት እውን ሊሆን ይችላል? በእርግጥ እንባ ጠባቂ ተቋም አዋጁ በሰጠው ሥልጣን ላይ ተመሥርቶ መረጃን የከለከሉ (ያዛቡ) ላይ ቅጣት አሳርፎ ያውቅ ይሆን? (እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ ቅሬታ አቅርበው መልስ ያላገኙ በርካታ ባለጉዳዮች እንደነበሩ ይታወቃል)፡፡

በአዲስ አበባ ከተማ አተዳደር ደረጃ ‹‹የመረጃ አቅርቦትና ስታንዳርዳይዜሽን›› የሚባል መሥሪያ ቤት ተቋቁሞ የመረጃ ነፃነት ሥራ ይሠራ እንደነበር ተደምጧል፡፡ ተቋሙ ለተለያዩ ቢሮዎች መረጃ ማዕከል (ላይብረሪና የመረጃ ቋት) ከፍቶ፣ ድረ ገጾችን እያጎለበተ፣ አትሞ የማሠራጨት ግዴታን በስታንዳርድ እየመራ እንደነበር ከእንባ ጠባቂ ተቋሙ የተገኘው መረጃ ያሳያል፡፡ ከዚህ አንፃር ሕግ ከመውጣትና ከሥልጠና ባለፈ የጀመረው ትግበራ ሊበረታታና ክልሎችም ሊሄዱበት የሚገባ መሆኑ እሙን ነው፡፡ አስተዳደሩ ግን ገና ሥራው ሳይጀመር በቦርዱ አማካይነት እያፈረሰው እንደነበር በዚሁ ጋዜጣ ላይ አንብቤያለሁ፡፡ እውን የተቋሙ ጅማሮ ታይቶ ውጤት ስላላሳየ ነው ወይስ በግለሰቦች ፍላጎት? እንባ ጠባቂ ተቋሙስ የአንድ ክልልን (ያውም የአዲስ አበባ) የመረጃ ሥርዓትን ሊያቃልል የሚችል ተቋም ላይ ምን ድጋፍ አደረገ? የት እንደደረሰስ ያረጋግጥ ይሆን?

አሜሪካን ጨምሮ ብዙዎች የአውሮፓና የእስያ (በማደግ ላይ ያሉ አገሮች) ‹‹Freedom of Information ACT›› እያወጡና እየከለሱ ነው፡፡ እንደ ጋናና ደቡብ አፍሪካ ያሉ የአፍሪካ አገሮችም የኢንፎርማሽን ኮሚሽን በማቋቋም ማንኛውም አካል (ዘር፣ ቀለም፣ ፆታ፣ አመለካከት፣ ሃይማኖተ ሳይለይ) መረጃ (በተለይ የመንግሥትና የሕዝብ መረጃ) እንዲያገኝ ማድረግ እየቻለ ነው፡፡ ይኼ ደግሞ ከልማትና ከመልካም አስተዳደር ዕድገት በላይ በዲሞክራሲ ግንባታቸውም ላይ ትልቅ ሚና መጫወት እንደቻለ አይታበልም፡፡

በአገራችን ለዜጎች መረጃን ተደራሽ ለማድረግ መገናኛ ብዙኀን ትልቅ ሚና አላቸው፡፡ (እንደሠለጠነው ዓለም የኢንፎርሜሽንና ኮሙዩኒኬሽን ቴክኖሎጂውን መጠቀም ላይ ስለሚቀረን) በተለይም የግሉ ፕሬስ ቢጠናከር ይበጃል፡፡ እዚህ ላይ የአሳታሚዎች የፋይናንስና ሙያዊ አቅም መዳከምና የጠራ ኤዲቶሪያል ፖሊሲ አለመኖር ዋነኛ ችግር ቢሆንም፣ ከመንግሥት አካላት መረጃ ለማግኘት እንደሚቸገሩ በተደጋጋሚ ተዘግቧል፡፡ ለዚህ ምክንያቱ ደግሞ ሚዲያውን በጎራ ከፋፍሎ፣ ላሻው መረጃ የሚሰጥ፣ ላልፈለገው የሚከለክል፣ ነገር ግን ‹‹የማይጠይቅ›› አመራርና ሕዝብ ግንኙነት በመንሰራፋቱ ነው፡፡ ባለጉዳዮች በአንዳንድ መሥሪያ ቤቶች መረጃ ሲጠይቁ በሠራተኞች ‹‹እጅ መንሻ›› እስከመጠየቅ እንደሚደርሱም፤ በቅርቡ በኢቴቪ ዓይናችን ፕሮግራም ላይ ሰምተናል፡፡

አዋጁ ግን በአንቀጽ 39(4) ላይ ‹‹መረጃ የማግኘት መብትን ለመጣስ በማሰብ ሆን ብሎ ሰነድ ያጠፋ፣ ያበላሸ፣ የቀየረ ወይም የደለዘ እንዲሁም የደበቀና የከለከለ ማንኛውም ሰው የወንጀል ጥፋቱ በፍርድ ሲረጋገጥበት በገንዘብ ወይም ከሁለት ዓመት በማይበልጥ እስራት ይቀጣል፤›› ይላል፡፡

ከዚህ አንፃር ሲታይ ነው የመረጃ ነፃነት ትግበራ ሥራው እሾህና አረሙ ያልተነቀለለት የጫጫ ቡቃያ ሆኖ የሚታየው፡፡ በአገራችን ነባራዊ ሁኔታ መረጃ ለመንግሥትም ቢሆን ያለው ፋይዳ ይታወቃል፡፡ በአግባቡ ተደራጅቶና ተጠብቆ፣ በቴክኖሎጂ በመታገዝ ከትውልድ ትውልድ እንዲተላለፍ መደረግ አለበት፡፡ (በዚህ ረገድ የቤተ መዛግብትና ቤተ መዘክር ኤጀንሲ የሚባል ተቋም ቢኖርም ተሳትፎው በአዲስ አበባና በፌዴራል በመሆኑ ውስን መሆኑን ልብ ይሏል)፡፡

በአሁኑ ጊዜ በየመሥሪያ ቤቱ በየቀኑ የሚመነጩ መረጃዎች አያያዛቸው መፈተሽ አለበት፡፡ በቅርቡ የሥነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን ባወጣው አንድ መረጃ (ፀረ ሙስና መጽሔት ቁጥር 3) መረጃን በመደበቅና በመደለዝ የከፋ ሙስና ይሠራል፡፡ በተለይ እንደ መሬት፣ ገቢ፣ የወሊድና ሞት መረጃዎች ይጠቀሳሉ፡፡ (እንዲያውም ቀደም ባሉት ዓመታት በአዲስ አበባ ቦሌ ክፍለ ከተማ አንድ አመራር የመሬት መረጃውን ቤቱ ደብቆ በሕግ ሲጠየቅ ማውጣቱን አትቷል)፡፡

ከመንግሥት መሥሪያ ቤቱ በሥራ መልቀቅ፣ በዝውውር ወይም ከኃላፊነት የሚነሱ ሠራተኞች (ኃላፊዎች) ንብረት እንዲያስረክቡ እንጂ ስለመረጃ ርክክብ የሚጠይቃቸው ያለ አይመስልም፡፡ በአንድ ወቅት እንባ ጠባቂ ተቋም መመርያ ይወጣል (ለጊዜው ሰርኩላር ይበተናል) ቢልም፣ የውኃ ሽታ ሆኖ ቀርቷል፡፡ ስለሆነም ዛሬ በአገር ውስጥ አጥኚዎችና በውጭ አማካሪዎች ሳይቀር እየተጠኑ በየመሥሪያ ቤቱ ያሉ ትልልቅ ጥናቶች፣ ስትራቴጂካዊ ዕቅዶችና የከተማ ማስተር ፕላኖች ሳይቀሩ ከግለሰቦች ፍላሽ፣ ሐርድ ዲስክ ወይም ቦርሳ አለመውጣታቸውን ማረጋገጥ አይቻልም፡፡

በነገራችን ላይ ይህን ስል ከመላምት ተነስቼ አይደለም፡፡ በቅርቡ በአዲስ አበባ ትራንስፖርት ባሥልጣን የመረጃ ማዕከል (ጠንካራ የመረጃ ቋት ያለበት መሥሪያ ቤት) የተገኘው የሕዝብ ትራንስፖርት ከፍተኛ ጥናት፣ ከ20 ዓመታት በፊት በውጭ ዜጎች በአስተዳደሩ ከፍተኛ ወጪ የተጠና ነበር፡፡ ይህ ትልቅ ጥራዝ የት እንዳለ እንኳን ሳይታወቅ ኖሮ ከሦስት ዓመታት በፊት አስተዳደሩ ሌላ ከፍተኛ ወጪ አውጥቶ አስጠንቷል (ፕላን አሠርቷል)፡፡ መረጃ ማደራጀት ሲጀመር ግን መገኘት እንደቻለ በቅርቡ የመንግሥት መረጃ አቅርቦት ጽሕፈት ቤት ያወጣው መጽሔት ላይ ማንበብ ችያለሁ፡፡

ከእነዚህ ዓይነቶቹ እውነቶች በመነሳት የመንግሥትን መረጃ አደራጅቶ፣ በወጉ ይዞ፣ ጠብቆና በተገቢው መንገድ ለሕዝብ ጥቅም የማዋሉ ሥራ ባለቤት ያለው አይመስልም፡፡ እንባ ጠባቂ ተቋምም ቢሆን ሥልጣኑን በወጉ ሳይጠቀም በአዋጁ የተሰጠው ሥልጣን እያበቃ ነው፡፡ እንደ አዲስ አበባ ከተማ ባሉት ክልሎች የተጀመሩ ሥራዎችም ፍሬ አፍርተው ውጤታቸው ሳይታይ ደብዛቸው እንዲጠፋ እየተደረገ ነው፡፡ (ባለፈው ጊዜ ባነበብኩት ጽሑፍ ላይ የጽሕፈት ቤቱ ቦርድ ሰብሳቢና የኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ ኃላፊ እንዲፈርሰ ግፊት አድርገዋል የሚል ሐሳብ ስላየሁ ነው)፡፡ ከዚህ አንፃር በአዋጁ መውጣት ላይ ከፍተኛ ሚና የነበረው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤትና እንደ የመንግሥት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት ያሉ ተቋማት ነቃ ብለው ትኩረት ሊሰጡት ይገባል፡፡ የመረጃ ነፃነት ትግበራውን ከሞት የምናድነው በጋራና በንቃት ችግሩን ስናስተውለው ነውና!

ከአዘጋጁ፡- ጸሐፊውን በኢሜይል አድራሻቸው This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it. ማግኘት ይቻላል፡፡