መነሻ ገጽ - ሌሎች አምዶች - ሕግ እና ፖለቲካ - ተሟገት - ገቢና ወጪ ንግዱን ለመታደግ ምን ይደረግ?
Buy Valtrex Online Buy Albuterol inhaler Online Buy Prinivil Online
04 August 2013 ተጻፈ በ 

ገቢና ወጪ ንግዱን ለመታደግ ምን ይደረግ?

በአሳምነው ጎርፉ

የኢትዮጵያን ፈጣን የኢኮኖሚ ዕድገትና ተከታታይነት የዓለም ባንክ ማረጋገጡ አንድ እውነት ሆኗል፡፡

ምንም እንኳን በኢሕአዴግ የሚመራው መንግሥት ባለሁለት አኃዝ ዕድገት እየተመዘገበ መምጣቱን ደጋግሞ ሲናገር ቢቆይም አንዳንዶች ሲጠራጠሩት ተደምጧል፡፡ ‹‹ዕድገት ቢኖርም ባለሁለት አኃዝ አይደለም›› ከሚለው አንስቶ፣ ዕድገቱን ከዋጋ ግሽበቱ ጋር በተቀላቀለ መንገድ  ምልዓተ ሕዝቡ አለመጥቀሙን በማንሳት የሚከራከሩ ፖለቲከኞች መኖራቸውም ይታወቃል፡፡

መንግሥት በበኩሉ በጠንካራው የሞኒተሪኒግና የፋይናንስ ፖሊሲ፣ በጥሩ የልማት ስትራቴጂዎች፣ በልማታዊ ባለሀብቱ ጥረትና በሕዝቡ ተሳትፎ አመርቂ ውጤት መገኘቱን ደጋግሞ ለማስረዳት ሞክሯል፡፡ ከዚያም አልፎ ለውጡን ሽግግራዊ ለማድረግ የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ነድፎ በመተግበር ላይ ይገኛል፡፡

የዓለም ባንክ በቅርቡ ይፋ ባደረገው ሪፖርት ‹‹ፈጣን የኢኮኖሚ ዕድገት ያስመዘገቡ አገሮችና ድህነት ቅነሳ›› ለሚለው ጥናቱ የኢትዮጵያን ሁኔታም ዳሳሷል፡፡ ‹‹ባለፉት 10 ዓመታት ገደማ ኢትዮጵያ በአማካይ 10.7 በመቶ የኢኮኖሚ ዕድገት አስመዝግባለች፡፡ ይህም አገሪቱን እ.ኤ.አ በ2012 ከዓለም 12 ፈጣን የኢኮኖሚ ዕድገት ያስመዘገቡ አገሮች ተርታ አስመድቧታል፡፡ ጅምሩ ተጠናክሮ ከቀጠለ ከ12 ዓመት በኋላ (እ.ኤ.አ 2025) ኢትዮጵያ መካከለኛ ገቢ አገሮች ተርታ ትመደባለች፤›› ብሏል ጥናቱ፡፡

ትኩረት የሚሹ የዕድገቱ ፈተናዎች
ኢትዮጵያ ዕድገቷን አጠናክራ በተለይም የግሉን ዘርፍ በማሻሻል ዘላቂ የኢኮኖሚ ለውጥ ለማምጣት የገቢና ወጪ የንግድ ሎጂስቲክስ ሥርዓት (Trade Logistics) መስተካከል ይኖርበታል፡፡ እንደ ዓለም ባንክ ጥናት የመፍትሔ ሐሳብ ከሆነ የትራንስፖርት፣ የካርጎና የኮንቴይነር ሥርዓቱ ቀልጣፋ መሆን አለበት፡፡ በተለይ የመልቲ ሞዳል ትራንስፖርት ሥርዓቱን በማቀላጠፍ የወጪም ሆነ የገቢ ምርቱ ከወጪና ከጊዜ ተግዳሮት መውጣት አለበት፡፡

ኢትዮጵያ ሩዋንዳን ከመሰሉ ወደብ አልባ አገሮች አንፃር ስትታይ ሰፊ የየብስ መሬትና ወጣ ገባ አቀማመጥ ያላት አገር ናት፡፡ በዚህና በሌሎች ምክንያቶች ጭምር የጭነት ጉዞው ጊዜ የሚወስድና ከፍተኛ ዋጋ የሚከፈልበት መሆኑን ሪፖርቱ ገልጿል፡፡ እርግጥ ይኼን ለማሻሻል አገሪቱ የወሰደችው አበረታች ዕርምጃ ደረቅ ወደብ እየገነባች መሆኗ፣ ለመንገድና ለባቡር መስመር ዝርጋታ የሰጠችው ትኩረት ነው፡፡

በቅርቡ ከጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ ጋር ውይይት ያደረጉ የንግዱ ማኅበረሰብ አባላትን ይህ ጸሐፊ አነጋግሯቸው ነበር፡፡ በዚህ ጊዜ በወጪም ሆነ ገቢ ንግድ፣ ወይም ትራንዚት ዘርፍ የተሰማራ ባለሀብት ዕድለኛ ነው፡፡ ቀደም ባሉት ዓመታት ግን ዘርፉ የነበረበት ፈተና የዋዛ አልነበረም በማለት  ያስረዳሉ፡፡ ዕቃዎች ከሦስት ወራት በላይ ወደብ ላይ ተቀምጠው ለብልሽትና ዝገት መጋለጣቸው፣ አንዳንድ ጊዜ ዘገምተኛው የየብስ ጉዞ፣ በፍተሻና በሚዛን ውጣ ውረድ ቀላል የማይባል ጊዜ መባከኑ፣ በአገር ውስጥ ካለው ገበያ ጋር ያልተጣጣመ ዋጋ መታየቱን ያነሳሉ፡፡

ከኤርትራ ጋር በተፈጠረው ግጭት ምክንያት ለገቢ ምርት በቂ ዋስትና ባለመሰጠቱም ሆነ ሻዕቢያ እንደ ሥርዓት ለዓለም አቀፍ ሕግጋት ተገዥ ያልሆነ ‹‹ጉልበተኛ›› በመሆኑ፣  አሰብ ወደብ ላይ ንብረቶቻቸው ተዘርፈው ደህይተው የቀሩ ዜጎችንም የሚያስታውሱ ወገኖች አሉ፡፡ የጂቡቲ መንግሥትም ቢሆን በመጀመሪያዎቹ አሥር ዓመታት ውስጥ ቅብጥብጥ ባህሪ እንደነበረው ብዙዎች ያስታውሳሉ፡፡ ሲፈልግ በአንድ ጀንበር ተነስቶ በአንድ ቶን ላይ ከፍ ያለ የወደብ ኪራይ፣ በተሽከርካሪ ሾፌሮችና ረዳቶች የአገልግሎት ዋጋ፣ የፓርኪንግና መሰል ተጨማሪ ክፍያዎች ፈጥሮ ይቆልላል፡፡ ሲፈልግ የጭነት ክብደትና የፍተሻ ሥርዓት በማውጣት እምብዛም ለንግድ ልውውጡ አመቺ ያልሆኑ መሰናክሎችን ማሳየቱ የተለመደ እንደነበር ይጠቅሳሉ፡፡

በዚህ ረገድ የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ መለስ ዜናዊ በአገሮች መካከል ጠንካራ ግንኙነት እንዲፈጠር በመሠረተ ልማትና የጋራ ተጠቃሚነት መርህ ትስስር እንዲጎለብት የወሰዱዋቸው ዕርምጃዎች የሚደነቁ ናቸው የሚሉት አንድ ባለሀብት፣ ቢያንስ ዛሬ የጂቡቲ መንግሥትና ሕዝብ በጋራ ተጠቃሚነት መርህ እንዲያምን አድርጎታል ይላሉ፡፡

የገቢ ግብርና ጉምሩክ ሥርዓቱን በተለይም ከምዘና ፍተሻና ቀረጥ ሥርዓት ጋር አያይዞ ለመፍታት የተሄደበት ርቀት በቂ አይደለም ባይ ናቸው ባለሀብቱ፡፡ በሴክተሩ ውስጥ እስካሁን የዘለቀው ሥር የሰደደ ሙስናና መድልኦ በዚህ መዘዝ የተፈጠረ ማጉላላትና ቅልጥፍና ማጣት እንቅፋት ሆኖብናል የሚሉ አስተያየት ሰጪዎች አሉ፡፡ በእርግጥ የፍተሻ ሥርዓቱን ለማሻሻል የካሜራ ሴኩሪቲ መጀመሩ፣ የሚዛን ወረፋን ለማቃለል የተወሰዱ ዕርምጃዎችና በየመቶ ሜትር የነበረው የኬላ ፍተሻ መቀነስ መጀመሩ ‹‹ጥገናዊ ለውጥ›› ሊባል እንደሚችል አልሸሸጉም፡፡ ስለዚህ እነዚህንና ተያያዥ ጉዳዮችን በጥናት ላይ ተመሥርቶ ማሻሻልም ሆነ ማስተካከል ለነገ የሚባል ተግባር እንዳልሆነ ያሳስባሉ፡፡

   የትራንስፎርሜሽኑ ድንቅ ግቦች የት ናቸው?
የኢትዮጵያ መንግሥት በዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ላይ ስለመልቲ ሞዳል ትራንስፖርት ሥርዓትና የወደብ ሥርዓቱ ትኩረት ሰጥቶ አስቀምጧል፡፡ ‹‹የወደብ አጠቃቀም ሬሾ በዕቅድ ዘመኑ መጨረሻ ለጂቡቲ 60 በመቶ፣ ለበርበራ 30 በመቶ፣ ለፖርት ሱዳን 10 በመቶ እንዲዳረስ ይደረጋል፤›› ይላል ዕቅዱ፡፡ ይሁንና የዕቅድ ዘመኑ ከመጋመሱ ጋር ተያይዞ በተለይ በበርበራ ወደብ አካባቢ እምብዛም የተለየ ለውጥ አለመታየቱን እንደ ድክመት የሚያነሱ አሉ፡፡

በንግድ ሥርዓቱ የወደብና የትራንስፖርት ጉዳይ ዋነኛ ቢሆንም፣ በንግድ ግንኙነትና ድርድር ተጠቃሚ የሚያደርጉ ዕድሎችንም መጠቀም ይገባል የሚሉ አሉ፡፡ በተለይ እንደ ኢጋድ፣ ሰነአፎረም፣ ኮሜሳና የአውሮፓ ኅብረት የንግድ ግንኙነት ብሎም የአጋዋ ዕድሎችን ከፍ ባለ የተጠቃሚነት አግባብ ማየት ካልተቻለ፣ የወጭ ምርት ተጠቃሚነት ሊሻሻል እንደማይችል ያስረዳሉ፡፡ መንግሥት እየወሰዳቸው ያሉ በጎ ዕርምጃዎችና ጥረቶች እንደማይናቁ በመጥቀስ ጭምር፡፡ በትራንስፎርሜሽን ዕቅዱ ሌላው በግልጽ የተቀመጠው የዘርፍ ጉዳይ የነዳጅ ጭነት በራሳችን መርከብ የማጓጓዝ አቅም ወደ 3.6 ቢሊዮን ቶን ማድረስ የሚለውን፣ በእርግጥም አገሪቱ መርከብ የማሠራትና የመግዛት አቅሟን ከጊዜ ወደ ጊዜ እያሻሻለች ቢሆንም፣ በዚህ ላይ የቅርብ ጊዜ መረጃዎች ምን ያህል እንደደረሱ አለመደመጡን መገንዘብ ይቻላል፡፡ ለ1.5 ቢሊዮን ቶን የሚል መረጃ ከአስተያየት ሰጪዎች ሰምተናል፡፡

የኢትዮጵያ መንግሥት የአየር ማረፊያ የካርጎ ሥርዓቱን ለማሻሻል እያደረገ ያለውን ጥረት የሚጠቅሱም አሉ፡፡ በተለይ የሆርቲካልቸርና የቁም ከብት እንዲሁም ሥጋ ምርቶችን ወደ ውጭ በመላክ ረገድና የዕቃ ጫኝ አውሮፕላኖችን መጠቀም ከጊዜም ሆነ ወጪ አንፃር የተሻለ ነው፡፡ የኢትዮጵያ አየር መንገድ የአገር ውስጥ መዳረሻውን ከልማት ኮሪደሮች ጋር በማስተሳሰር የማረፊያና የዕቃ ጫኝ አውሮፕላኖችን አቅም ለማሻሻልም ሞክሯል፡፡

አንዳንድ ባለሀብቶች ግን ፍፁም ተመጣጣኝነት የሌለውና ከመልቲ ሞዳል ትራንስፖርት የወደብ ዕቃ ማንሳት ጋር ያልተያያዘ መሆኑን ያስረዳሉ፡፡ ለምሳሌ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ከጂቡቲም ሆነ ከሌሎች አማራጭ ወደቦች ዕቃ የሚያነሳ ከፍተኛ የጭነት ተሸካሚ የለውም፡፡ ሆልቲካልቸር ላይ ምልክት ቢኖርም በቀጥታ ከገበያው መዳረሻ ጋር የተያያዘ ነው፡፡

በዓለም ላይ በአውሮፕላን ትልልቅ ካርጎ የማንሳት ልምዱ ያላቸው ኮሪያን የመሰሉ አገሮችን በመጥቀስ ንፅፅሩን ያስረዳሉ፡፡ ኢንቾን የሚገኘው የኮሪያ አውሮፕላን ማረፊያ በዓለም ሁለተኛውና ትልቁ ሲሆን ከቡሳን ወደብ፣ ጉዋንጋያንግና ኢንቾን ወደቦች ጋር በመተሳሰርና በመቶ ሚሊዮኖች ቶን የሚገመት ዕቃ በማስወጣትና ማስገባት ከአገሪቱ አልፎ የደቡብ ምሥራቅ እስያ ዋነኛው ኮሪደር መሆን ችሏል፡፡ ከእነዚህ እውነታዎች አንፃር ለእኛ ዘወትር ትልቅ የሆነው የኢትዮጵያ አየር መንገድ የካርጎ ማጓጓዝ አቅም መፈተሽ ይኖርበታል፡፡ በቻይናና በኮሪያ አልያም በህንድና በብራዚል ዓይን አነስተኛ የሆነ የካርጎ ምልልስ ከቀጣዩ የኢንዱስትሪ መር ኢኮኖሚ ጋር ሊሄድ አይችልም የሚሉ ወገኖች አሉ፡፡ አቅም አደገ ማለት ደግሞ በዋጋ፣ በጊዜ፣ በጥራት ነው፡፡ አቅም ሲኖር ተወዳዳሪ ገበያ በመፍጠር ሊኖር የሚችለው ዕድገት ከፍ ማለት አይቀሬ ነው፡፡

የዕድገትና የንግድ ኮሪደሮችን በውጤታማነት መቃኘት
ብዙዎቹ የነብር ዓይነት ፈጣን ኢኮኖሚ  (Tiger Economy) አስመዘገቡ የሚባሉ የእስያ አገሮች ልምድ የልማት ኮሪደርና ታሳቢ ያደርጋል፡፡ በማንኛውም ምርትና ኢንዱስትሪ ‹‹ስፔሻላይዜሽንና ዳይቨርሲፍኬሽንን›› በትኩረት ይጠቀሙበታል፡፡ ሲኦል፣ ቤጂንግም ሆኑ ቶኪዮ በዙሪያቸው በአንድ ልዩ ምርት የሚታወቁ ከተሞችን እየፈጠሩ ነው፡፡ የጨርቃ ጨርቅ ኢንዱስትሪ፣ የኮንስትራክሽን ግብዓት ማምረቻ፣ የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂና ተቀራራቢ ቴክኖሎጂ፣ የባህልና ቱሪዝም ኢንዱስትሪ መናኸሪያ (የአንዶኔዥያዋ ጃካርታን ጀማሮ ልብ ይሏል) የመሆን ጉዳይ ዓለም አቀፍ ዕውቅና እያገኘ ይመስላል፡፡

ከዚህ ተሞክሮ ኢትዮጵያ ምን መማር አለባት በማለት ላቀረብኩት ጥያቄ አንድ ትውልደ ኢትዮጵያዊ ዳያስፖራ ኢንቨስተር እንዲህ መልሰውልኛል፡፡ ‹‹በእርግጥ ቀድሞ በትልቁ መመኘት  ጥሩ ሊሆን ይችላል፡፡ ነገር ግን የከተሞችን ስፔሻላይዜሽን ለማረጋገጥ በዕድገት ረጅም ርቀት መሄድ ብቻ ሳይሆን የማኅበረሰብ ትራንስፎርሜሽን የግድ ያስፈልጋል፤›› ብለውኛል፡፡ የእስያ አገሮች ከተሞቻቸውን አፍርሰው እየገነቡ፣ በትምህርትና ሥልጠና እጅግ የሚደነቅ ውጤት እያሳዩ፣ ፈጣንና የቴክኖሎጂ ሽግግርን ብቸኛ ስልት አድርገው እየሮጡ ያመጡትን ውጤት፣ ኢትዮጵያ አሁን ባለችበት ቁመናና የኅብረተሰቡ የኢኮኖሚና የግንዛቤ ደረጃ ሊታሰብ አይችልም ባይ ናቸው፡፡

ይህ ማለት ግን የልማት ኮሪደሮችን ከግብርናው ጋር አስተሳስሮ መፍጠር አይከለክልም፡፡ ለአብነት ያህል የኢትዮጵያ መንግሥት በአማራ ክልል ወሮታ አካባቢ የሩዝና የጓሮ አትክልት ኮሪደር፣ ኮምቦልቻን የኢንዱስትሪ ኮሪደር፣ የፊነፊኔ ዙርያ ከተሞችን ከኢንዱስትሪ ባሻገር በሆርቲካልቸር ምርት (ባህር ዳርም ተጀምሯል)፣ እንደ ሐዋሳና አርባ ምንጭ ዓይነቶቹን በበለጠ ወደ ኢንዱስትሪና መዝናኛ የመሳብ ጅማሮ ይታይባታል የሚሉ አስተያየት ሰጪዎች፣ ያም ሆኖ በአካባቢው ከሚኖር የተፈጥሮ ሀብት፣ ገበያና፣ አቅም ጋር አስተሳስሮ፣ የትራንስፖርትና የንግድ ሊጂስቲክስ ጋር አቆራኝቶ የንግድ ኮሪደር መፈጠር ላይ መረባረብ እንደሚያስፈልግ ያስረዳሉ፡፡

ሰሞኑን አዲሱ የትራንስፖርት ሚኒስትር አቶ ወርቅነህ ገበየሁ የአገሪቱን የመልቲ ሞዳል ትራንስፖርት ሥርዓት ለመገንዘብ የመስክ ጉብኝት አድርገዋል፡፡ በወቅቱ የሰመራ፣ የሞጆ፣ የለገጣፎና ቢሾፍቱ ደረቅ ወደቦች በመገንባታቸው የካርጎ ጉዞን ከወራት ወደ አምስት ቀናት ማሳጠር እንደተቻለ፣ በአሁኑ ወቅት ብቻ እስከ 14 ሺሕ ኮንቴይነሮችን ማስተናገድ የሚቻልበት ዕድል መፈጠሩ፣ በክብደት ድምር ሲታይም እስከ 250 ሺሕ ቶን ገቢ ዕቃ ከወደቦች ወደ ደረቅ ወደቦች ተጓጉዞ ሊያርፍ እንደሚችል ተገልጿል፡፡

ይህ እንደ አንድ ዕርምጃ የሚወሰድ ውጤት ቢሆንም የደረቅ ወደብ አድማስን አስፍቶ፣ ከደረቅ ወደብ በፍጥነት የሚያጓጉዙ አሽከርካሪዎችን አብዝቶ፣ ከደረቅ ወደብ በፍጥነት የሚያጓጉዙ አሽከርካሪዎችን ማስገባትና ሥራውን ማቀላጠፍ ያስፈልጋል፡፡ ከአዳማ አዲስ አበባ በመገንባት ላይ ያለው የፍጥነት መንገድ ሥራዎችን ማጠናከር፣ የተለመዱ ደረጃቸውን የጠበቁ የመንገድ ግንባታዎችን ማስቀጠልና የባቡር ትራንስፖርቱን ተረባርቦ ዳር ማድረስ ወሳኝ ጉዳዮች መሆናቸውን ባለሙያዎች ያስረዳሉ፡፡ አሁን ያለውን በጥቂቶች የተጨመደደ የትራንስፖርትና የትራንዚት ኢንቨስትመንት ማስፋት እንደሚገባም የሚያስረዱ አሉ፡፡

የባህር ትራንስፖርትና ሎጅስቲክስ አገልግሎት ድርጅት በአገሪቱ የገቢና ወጪ ንግድ ልውውጥ ውስጥ ቁልፍ ድርሻ ያለው መሥሪያ ቤት ነው፡፡ በአቅም፣ በክህሎትም ሆነ በሥነ ምግባር እንደተቋም ያለበት ሁኔታ መፈተሽና መገንባት አለበት የሚሉት በርካታ ባለሀብቶች ናቸው፡፡ የአገሪቱ ድንበር ጫፍ እስከሚገኙ ወደቦች እየተገነቡ ያሉ መንገዶች በጎ ሆነው ማኅበረሰቡ በመንገድ ደህንነትና የጉዞ ዋስትና ላይ እንዲሁም ከጉምሩክና ታክስ ሥርዓቱ አንፃር በንቃት የሚሳተፉበትና ተጠቃሚነቱ የሚረጋገጥበትን ሥርዓት ከወዲሁ ማበጀት ይገባል ነው የሚሉት፡፡ የበለፀገች ኢትዮጵያ የምትገኘው ዛሬ በተገነባ ፅኑ መግባባት ነውና በማለት፡፡

ምን ይደረግ?
የአገሪቱ ታዳጊ ኢኮኖሚ ከወጪ ምርት ይልቅ ገቢው እንደሚበዛ ተደጋጋሞ የተነገረ ነው፡፡ ይኼ በምርትና በፍጆታ መካከል የሚፈጠርን ክፍተት በቀልጣፋና ወጪ ቆጣቢ ትራንስፖርት ወይም ስርጭት ካልታጀበ የኪሳራ ምንጭ መሆኑ አይቀርም፡፡ የብዙዎቹ የበለፀጉ አገሮች ታሪክ የሚያስረዳው ይኼንኑ ነው፡፡

አገሪቱ ወደብ አልባ ነች፡፡ በዚህም ምክንያት በአሁኑ ወቅት ለጂቡቲ ብቻ እስከ 3.5 ነጥብ ሚሊዮን ዶላር በቀን ታወጣለች፡፡ ይኼም እስከ 23 ቢሊዮን ብር በዓመት እንደሚደርስ ይገመታል፡፡ ከዚህ በላይ በጊዜ የሚለካው ሀብት ትልቅ ነው፡፡ ስለሆነም የመልቲ ሞዳል ትራንስፖርት (በተለይ ደረቅ ወደብና የልማት ኮሪደሮችን ማስተሳሰር) ሥራን አጠናክሮ መቀጠል ያስፈልጋል፡፡

አሁን በተጀመረው መንገድ የወደብ አማራጮችን ከምር ለማስፋት መትጋት፣ እንደ ኤርትራ ካሉ አገሮች ጋርም ‹‹ያልተዘጋውን የጋራ ተጠቃሚነት አጀንዳ›› መፈተሽ ከፖለቲካ ፋይዳው በላይ ኢኮኖሚያዊ ትርፉ ትልቅ ነው፡፡ የግል ባለሀብቱም መንግሥት የገቢና ወጪ ሥርዓቱን ለማቃናት በጀመረው ዘርፈ ብዙ ጥረት ሁሉ ሙሉ አጋርና ለጥቅም ብቻ ሳይሆን ለዘላቂ ጥቅም መሥራት አለበት፡፡