መነሻ ገጽ - ሌሎች አምዶች - ማህበራዊ ጉዳዮች - ደላላው - የተተኪ ያለህ!
Buy Valtrex Online Buy Albuterol inhaler Online Buy Prinivil Online

ሰላም! ሰላም! ትንኝና ነፍሳት ውልብ ባሉ ቁጥር ቀልቧ አብሮ ስልብ እያለባት የሰነበተችውን ውዷን ማንጠግቦሽ፣ ‹‹ምንድን ነው ነገሩ?›› ብዬ ብጠይቃት፣ ‹‹አፍሪካ ውስጥ መኖሬ አንሶ በወባ ሞተች እንዳልባል ነዋ?

የወባ ትንኝን ልፍራ እንጂ አምባገነኖችና ጨፍጫፊዎች እንደሆኑ ቀስ በቀስ እያለቁ ነው፤›› አትለኝ መሰላችሁ? ጉድ አትሉም የሦስተኛው ዓለም ኑሮ?! ‹አልሰማሽ እነ ሙጋቤ ከ33 ዓመት በላይ አገር እየገዙ እንዳሉ› እያልኩ በሆዴ ጥርሴ ስቆ ዝም። የዘንድሮ አምባገነንነት ደግሞ በምርጫ ሆኗል እኮ። ወይ ዲሞክራሲ እቴ! ጉዱ አላልቅ አለ እኮ እናንተዬ!

ብቻ ወባ ያለችኝ ነገር እየቆየሁ ያስተክዘኝ ጀመር። ለካ አሁንም የዚህች አጥፊ ትንኝ ሐሳብ አለብን ጎበዝ? ‹‹ምነው ግን ቢያንስ ይኼን ሥራ ሳናጠናቅቅ?›› ብዬ አንድ ወዳጄን ብጠይቀው፣ ‹‹ምናልባት ልማቱ ጎትቶን ይሆናል፤›› ብሎ ተሳለቀብኝ። ኧረ ሰው ቀልዱ አልጥም ብሏል እናንተ። ተቀለደም ተጨፈገገም እዚያ ሰው አልባ አውሮፕላን፣ በአየር የሚበር መኪና መመረቱ፣ እዚህ ወባ የማያሰጋበት ኑሮ በገጠርም በከተማም መመቻቸቱ የማይካድ ሀቅ ነው፡፡ ችግር በመፍጠርና በማባባስ የሚደርስብን ጠፍቷል። ለኩሶ ማራገብ፣ አዋሽኮ ማጣላት፣ ዞሮ መተማማት የዘመናት ‹ስታይላችን› ሊባል ይችላል። አይገርምም ግን? እንዲያው ሌላው ቢቀር እርስ በርስ ከሚፈጠርብን ቅናት ቀንሶ ባደጉት አገሮች የቴክኖሎጂና የአስተሳሰብ ምጥቀት መቅናት እንድንችል ሩቡን ቢያድለን ምን ነበረ? ስል ሰነበትኩ። ምሁሩ የባሻዬ ልጅ፣ ‹‹የሚገርምህ አዕምሯችን እጅግ ሰፊ አቅም ከመታደሉ የተነሳ 40 የተለያዩ ቋንቋዎችን አጥንቶ በደንብ ማስታወስና ኢንሳክሎፒዲያን ከሀ እስከ ፐ መዝግቦ መያዝ የሚችል ነው። እኛ ግን በረባ ባረባው አጨናንቀን ይኼው አልታደልንም፤›› አለኝ፡፡ ትንሽ አሰብ አደረገና፣ ‹‹እንግዲህ ሳይንቲስቶች እንደሚሉት ሰው አንድ በመቶ የሚሆነውን የአዕምሮውን አቅም ተጠቅሞ ነው ይኼን ዛሬ የምንደነቅበትን ሥራ እየሠራ ያለው፤›› ሲለኝ ገረመኝ፡፡ በተለይ አሁን አሁን እንደፋሽን የተያዘውን የእርስ በርስ ጦርነት፣ በሃይማኖት ስም የሚጠፋውን ፍጡር፣ የአገር ሁከትና የሚወድመውን ንብረት እያሰብኩ እንባ ቀረሽ ምሬት እመረር ጀመር። እንዲህ አንዱ ካንዱ ይሻላል በማይባልበት ዓለም ውስጥ እየኖርን ቢያንስ ከእኛ በቀደሙት መቅናት አለመጀመራችንን ሳስብ ይኼም ‹አልበገር ባይነት› ይባል ይሆን? ከቶም አለመበገር! 

የማንጠግቦሽ ከሰሃራ በታች የሆነው የኑሮዋ ሥጋት እንዲቀረፍ ብዬ ፀረ ነፍሳትና ትንኝ ‹ፍሊት› ለመግዛት ወጣ አልኩ። ሆሆ! ካለእሷ ማን አለኝና! ‹የፈሩት ይደርሳል የጠሉት ይወርሳል› አይደል ተረቱ? የኑሮ ውድነት እንደ ምኞቷ፣ የቤት እጦት እንደ ልጅነት ህልሟ እንዳትኖር የነደፋት አንሶ ወባ ቢነድፍብኝ እኔን አበቃልኝ ማለት አይደል? ታዲያስ! ሰው እኮ አንዳንድ ጊዜ ሕልሙና ሐሳቡ በጊዜው ካልተፈጸመ  ዋጋ የለውም። አሁን መቼ ለታ በባሻዬ ሬዲዮ ‹‹አዲስ አበባን ሊያስተዳድር የተመረጠው አዲሱ ካቢኔ በመጭው አምስት ዓመታት አንድ ሚሊዮን የመኖሪያ ቤቶች ሠርቶ የቤት እጥረትን ለመቅረፍ እንደሚሠራ አስታወቀ፤›› ሲባል ሰማሁ። መቼም አይሠራ ብሎ የሚቃወም አይኖርም። ግን ችግሩ የተጋነነና የተለጠጠ ዕቅድ እየተያዘ መጨረሻ ላይ በአፈጻጸም እያመካኙ ወገቤን ማለት እንዳይመጣ ነው ሥጋታችን፡፡ እኔማ አንዳንዴ ብቻዬን መንገድ እየሄድኩ ሳወጣ ሳወርድ ቀጠሮ የማክበር ችግር የተዛመተብን፣ በሕይወታችን ጊዜውን ጠብቆ ሲሆን ያየነው ነገር ጥቂት ቢሆን ነውን? እላለሁ። እውነቴን እኮ ነው! ከበፊት ጀምሮ (የዛሬን ሳቁም ለቅሶውም  በእንግሊዝኛ የሆነውን ትውልድ አላውቅም እንጂ) እኛ ስናድግ ከእንቅልፍ ሰዓታችን ጀምሮ ተዛብቶብን ያደግን ነን። ከትልልቆቹ እኩል እያመሸን ወተት መጠጣት ባለብን ሰዓት ምራቅ ውጠን ያደግነውን ቤት ይቁጠረን። እንዴ ‹ልጅነቴ ልጅነቴ ማርና ወተቴ!› ብለን ለወጉ ዘምረን ማርና ወተት በጉልምስናችን የቀመስነው ስንቶቻችን ነን? ከእኩዮቻችን ጋር  ድብብቆሽ በመጫወቻ ጊዜያችን ከአብዮት ጠባቂ ጋር አልጋ ሥር ለአልጋ ሥር ስንደባበቅ ያደግን የለንምና ነው? ማን ነው ጊዜውን ጠብቆ በጊዜው ሁሉን አይቶና አድርጎ ያደገው? እና አንዳንዴ ነገሩ ሁላ ‹ጅብ ካለፈ ውሻ ጮኸ› ሲሆን ያናድዳል ለማለት ያህል ነው ይህን ያልኩት። ‹ሰርገኛ መጣ በርበሬ ቀንጥሱ› የሆነው የልማት ማዕበል አስቀድሞ ያልፈታቸውን ችግሮች እንደተሸከመ እስከየት እንደሚዘልቅ አሁንም ማየት እንጂ መገመት ‹የህዋ ሳይንስ› ያልሆነበት የለም። እንኳን ለእኛ ለገዢው ፓርቲ ኢሕአዴግም!

የሠፈራችን ሱቅ ከመድረሴ ባለሱቁ ወዳጄ ነውና ሰላምታ አቀረብኩላት። ለደላላ ሁሉም ወዳጁ ነው። አፀፋውን መለሰ። ‹‹ብርዱ እንዴት ነው?›› በማለት ስጠይቀው፣ ‹‹ከኑሮ ውድነት ባይብስም ጥሩ ይበርዳል!›› ብሎ ሲመልስልኝ ከነጋ ከአንጀቴ አንድ ጥሩ ሳቅ ሳቅኩ። ሳቄ የሳቅ ረሃብ በከተማው እንደገነገሰበት አስታወሰኝ። ‹‹ምን እናድርግ ብለህ ነው! በአንድ ወገን ኑሮ፣ በዚያ በኩል ፖለቲካው መጠራጠር፣ ፍርኃትና ተስፋ መቁረጥ በውስጣችን እየሰገሰገ በድን አድርጎን እኮ ነው መሳቅ የረሳነው፤›› ያለኝ ወዳጄ ትዝ አለኝ። ወደ ባለሱቁ ወዳጄ ተመልሼ፣ ‹‹ነጋዴም እንደ ሸማቹ በኑሮ ውድነት ያማርራል እንዴ?›› ብዬ ጠየቅኩት። ‹‹በእኛ አይብስም ብለህ ነው አንበርብር? ለነገሩ ንፁሁ ከቆሻሻው ጋር አብሮ በአንድ ስም ‹ነጋዴ› ተብሎ አንድ ላይ ባይታማ ነበር የሚገርመኝ፤›› አለኝ የምፈልገውን ስነግረው ከመደርሪያው ለማውረድ በዓይኑ እየፈለገ። ‹‹ሲጀመር እኮ በዚህ የንግድ ሥርዓቱና ግብይቱ በየመንገዱ በሆነበት አገር ማንም ማንንም እንዲህ ነው ማለት አይገባውም ነበር። ግብር ለመንግሥት የሚከፍለውም፣ ሠፈር እየቀያየረ መንገድ ለመንገድ የሚቸረችረውም ነጋዴ በሆነበት አገር ዋጋ ባሻቀበ ቁጥር ሁሉን በአንድ ሙቀጫ ከቶ መውቀጥ አግባብ አይደለም፤›› እያለ ብሶቱን ለመገናኛ ብዙኃን ይዘግብ ይመስል አነበነበብኝ። ለነገሩ ሳር ቅጠሉ ሳይቀር ትችት ብቻ በሆነበት አገር ሰው ብሶቱን በየመንገዱ ቢተነፍሰው ምን ይደንቃል? ምንም!

ደመና ያጨለመው ሰማይ ሲፈካና ፀሐይዋ ወገግ ስትል የቀጠሮዬም ሰዓት መድረሱን ልብ አልኩ። ምን የመሰለ ባለ ሦስት ፎቅ ቤት ከነተንጣለለ ግቢው ለማሸጥ ደፋ ቀና ስል አርፍጄ ነው የማንጠግቦሽ ታሪክ የተጀመረው። እናላችሁ ገዢው ውሳኔውን አሳውቆ ቤቱን ያለጥርጥር በእጁ እንደሚያስቀረው ሲያሳውቅ አፍታ አላመነታም። (ያለውማ እንዴት ያመነታል?) ቀጠሮውም የተዘጋጁ ቅጾችን ለመፈራረም እኔም ኮሚሽኔን ለመቀበል መሆኑ ነው። ምንም እንኳ የቤት ጉዳይ እንዲህ በቀላሉ ባያልቅም። እንደደረስኩ ጨዋታው ደርቶ ገዢና ሻጭ የማይተዋወቁ ሳይመስሉ ሲያወጉ ደረስኩ። ‹‹ኖር!›› አሉኝ በጨዋ ደንብ። ‹‹በእግዜር!›› ብዬ አረፍ አልኩ። እነርሱ ጨዋታቸውን ቀጠልዋል። ገዢ ‹‹. . .አባባሌ እንዲያው የቤትና የመሬት ነገር ሲነሳ ሕቡን በሚያንገበግበው ወቅት ያውም ይህን የመሰለ ቤት እንዴት ለመሸጥ ወሰኑ?›› ብሎ ይጠይቃል ለዘብ ባለ ድምፅ። ‹‹ይሸጥ! ያው እንዲህ ጆሮውን ተብሎ ነዋ የሚሸጠው! ስማ መጀመሪያ አገር ሲኖርህ ነው ቤት አለኝ የሚባለው፤›› አሉት ሻጭ ክፉኛ በተበሳጨ ስሜት። ‹‹እንዴት?›› ይላቸዋል ገዢው ደንበኛዬ አኳኋናቸው እያስፈራው። ‹‹ሁሉም ሊያዝህ ይፈልጋል፡፡ ማን አዛዥ ማን ታዛዥ፣ ማን መሪ ማን ተከታይ እንደሆነ አላውቅ አልን፡፡ ሕግ አስከባሪ እንጂ ሕግ አክባሪ ጠፋ፡፡ ትልቁም ትንሹም እኔ ነኝ የማውቀው ይላል። ታዲያ እኔን የመሰለ አንቱ የተባለ ስንት ያየ አዛውንት ይኼን እያየ እንዴት ሊኖር ይቻለዋል?›› እያሉ ይጮሃሉ። ጩኸት ቁጭታቸውን ይደመስሰው ይመስል፡፡

እሳቸውን እያስተዋልኩ በሰመመን አንድ ወዳጄ ሰሞኑን ከልቡ ሲያወጋኝ የነበረው ጨዋታ ትዝ ብሎኝ ተመሰጥኩ። ‹‹አንበርብር በቁጠባ ለሚሠሩት ቤቶች ተመዝግቤ መቆጠብ ከጀመርኩ ወዲህ እውነት እልሃለሁ ሁሉ ነገሬ ሲለወጥ እያየሁ ነው። ከዚህ በፊት እኮ እንዲህ አልነበርኩም። እውነቴን እኮ ነው! አሁን ለመኖር ያለኝ ጉጉት በእጥፍ ጨምሯል። ምክንያቱም ነገ የራሴ የምለው ንብረት ሊኖረኝ ነው። ከእጄ በከንቱ የሚወጣ ሳንቲም የለም። እርሱ እውን አድርጎት ቤቴ በእጄ ሲገባማ እንጃ የምሆነውን። እንዲያውም ልንገርህ? እ? (ድምፁን ዝቅ እያደረገ በሹክሹክታ) ጭራሽ ስለትዳር ማሰብ እየጀመርኩ ነው፤›› ያለኝን ሳስታውስ እዚህ የምሰማው ምሬትና እዚያ ያለው ተስፋ አልጣጣም አለኝ። በአንድ በኩል አገር ፈርሶ ቢገነባ ምንም የተሠራ የማይመስላቸውና በአንድ ወገን ደግሞ በትንሹና በግርፉ ሥራ ሐሴት የሚተናነቃቸው አሉ። አንዳንዴ ‹ይህቺ አገር ወዴት እየሄደች ነው?› በሚል ተጨባጭነት በሌለው መላምት የምንደሰኩረው ዲስኩር ሲሰለቸኝ ያን የፈረደበትን የባሻዬን ልጅ እየሄድና፣ ‹‹እኛስ የሚገባንንና የሚጠበቅብንን ያህል የጠራ አመለካከት ለፖለቲካው፣ ለማኅበራዊ ጉዳዩ፣ ለኢኮኖሚው ያለን ይመስልሃል?›› ብዬ እጠይቀዋለሁ። ሁሌም መልሱ ‹‹እንጃ!›› ነው። በተዘበራረቀ የማኅበረሰብ ንቃተ ህሊና መሀል ተጨባጭነት የጎደለው እውነት ያለ ሲመስል በሁላችንም ስሜት ግራ መጋባት ቢኖር ምን ያስገርማል? ምንም!

በሉማ እንሰነባበት። ስለመለያየት ብዙ የተዘፈነባት አገር አይደል ያለችን? ለነገሩ ዓለም በአጠቃላይ የታሪክ ግጭቷ ጀምሮ የሚጠናቀቀው ተገናኝቶ በመለያየት ነው። ይህ የጥንት ሀቅ ነው! አንጀት በምትበላ የክራር ስርቅርቅታ ካሳ ተሰማ፣ ‹ቁጭ ብዬ ግራዋ ቆሜ ኮሶ ጠጣሁ፤ እንዳንቺ መለየት የመረረኝ አጣሁ፤› ሲል የተጫወታትን ስሰማ ልቤ በትዝታ ፍስስ ይላል። ታዲያ መለያየት በራሱ ብዙ የሚያስብል ሆኖ ፀብ ሲጨመርበት አይደብርም? በጣም እንጂ! እኛ ግን እንደ አራዶቹ በፍቅርና በቁም ነገር መለያየት ነውና ልማዳችን አንድ ቁም ነገር ጣል ላድርግላችሁ። ይኼ የቁጠባ ነገር የግሮሰሪ አመሻሻችን ላይ ተፅዕኖ በማስከተሉ ዕድሜ ለሞስኮ የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና እነባሻዬ ቤት ነበር ማምሻችን። ታዲያ ደስታችንና ድላችን የጠበቅነውን ያህል አልሆን ብሎ ድል በለመድንበት የረጃጅም ርቀት ሩጫዎች መዳከምና ማቋረጥ ሲደጋገም ስናይ ሲከፋን ሰነበትን። በኋላ ግን ጀግናዋ ጥሩነሽ ብሎም መሐመድ አማን እፎይ አስባሉን። ባሻዬ ግን ነገሩ ከንክኗቸው፣ ‹‹አዬ ምነው ዘመኑ የመተካካት ነው እየተባለ ከፖለቲካ እስከ ስፖርት አዲስ ተተኪ ማየት የናፈቀን?›› ሲሉ ልጃቸው ቀበል አድርጎ፣ ‹‹ግለኝነት በዝቶ ነዋ! ከአገር ቀበሌ፣ ከሕዝብ ግለሰብ በለጠ! ምን ይደረግ!›› ሲል መለሰ። ‹‹እንዲያው ግን ምን ተሻለ? እስከመቼ በጥቂቶች ትከሻ?›› ይላሉ ባሻዬ፡፡ ‹‹ለራስ ማሰብ ሳይቆም ተተኪ ማሠልጠን፣ የመተካካት ዕቅዱን በተግባር መፈጸም፤›› ሲል ልጅ ይመልሳል። አባትና ልጅ እንዲህ ሲቀባበሉ እኔ ጮክ ብዬ ‹እስከመቼ በጥቂቶች ትከሻ?!› ማለት አምሮኝ እቁነጠነጣለሁ። የሆነ ሆኖ ግን መተካካቱ ከፖለቲካ እስከ ስፖርት መንደር ለምን አይቀጥልም? ተተኪ የሚናፍቀው አትሌቲክሳችን የተተኪ ያለህ እያለ ነው! መልካም ሰንበት!