መነሻ ገጽ - ሌሎች አምዶች - ማህበራዊ ጉዳዮች - ደላላው - “መስከረም ሲጠባ አደይ ሲፈነዳ…”
Buy Valtrex Online Buy Albuterol inhaler Online Buy Prinivil Online
08 September 2013 ተጻፈ በ 

“መስከረም ሲጠባ አደይ ሲፈነዳ…”

ሰላም! ሰላም! በአዲስ ዓመት ዋዜማ ላይ ሆነን አሮጌውን ዓመት ስንሸኝ “እንኳን አደረሳችሁ” ከሚባለው የተለመደ የመልካም ምኞት መግለጫ ባሻገር “አዲሱን ዓመት የሰላም፣ የፍቅር፣ የጤናና የብልፅግና ያድርግላችሁ” መባባል አለብን፡፡

“መስከረም ሲጠባ አደይ ሲፈነዳ፣ እንኳን ሰው ዘመዱን ይጠይቃል ባዳ፤” አይደል ብሒሉ? የአሮጌውን ዘመን ግሳንግስ ከላያችን ላይ አራግፈን አዲሱን ዘመን በተስፋ ካልጠበቅነው ሌላ የሚያዋጣ ነገር የለም ብዬ አስባለሁ፡፡ ይሁንና አሮጌውን ዓመት ስንሸኝ አንዳንድ ጉዳዮችን ብናሻሽል? ለምሳሌ ከአሮጌው ዓመት ጋር የሚሸኙ አሮጌ ሱሶች፣ አስተሳሰቦች፣ ክፋት፣ ምቀኝነት፣ ተንኮል፣ ራስ ወዳድነት፣ ወዘተ ከእኛ ቢላቀቁና በቀና መንፈስ ብንነሳስ? ይኼ እንግዲህ ግዳጅ ሳይሆን በፈቃደኝነት የሚፈጸም ነው፡፡ እስቲ በርቱ ተበራቱ፡፡  

አንድ ከበርቴ ወዳጄን “የአፍሪካ ምሁራን ‘የቀድሞ ቅኝ ገዢዎች ተመልሰው ቢመጡ የአኅጉሪቱን ሕዝብ በራሱ ገዢዎች ከሚያየው ስቃይ ይገላግሉታል’ አሉ፤” ብዬ ብነግረው፣ “ቫት ላይ እነሱ አይብሱም እንዴ?” ብሎ ከት ብሎ ሳቀብኝ። ይገርማችኋል እንዲህ በተባባልን በነጋታው ሌላ ባለሀብት ወዳጄን (ካለው ተጠጋ ከሌለው ተስማማ ስለሆነ ነው ከበርቴ ወዳጅ ያበዛሁባችሁ) ታሰረ ብለውኝ ልጠይቀው ሄድኩ። እህሳ? እንዴት ነው ነገሩ ብዙዎቹ እዚያ አይደል እንዴ ያሉት? እኔማ ምናልባት ሲነገር አምልጦኝ ሳልሰማው የቀረሁት የ“ሠፈራ ፕሮግራም” መስሎኝ ደጋግሜ ጠባቂውን ‘ለመሆኑ ይኼ ቦታ ምን ይባላል?’ እያልኩ ሳደርቀው ዋልኩ። አካበድከው አትበሉኝና በየቀኑ አሜሪካ ሄደ ሲባል ከምሰማው የማይተናነሰው እዚሁ ማረሚያ ቤት መኖሪያ እየቀየረ ሳይሆን እንደማይቀር ተጠራጥሬያለሁ። ያላመነ ሄዶ ማየት ነው! ምነው መጽሐፉም የታሰሩትን ጠይቁ ይላል እኮ! አሁን ይኼን ለማሳመን የፈጣሪን ትዕዛዝ መጥራት ነበረብኝ? ለማንኛውም እስር ቤት ደርሻለሁ፡፡

ወደ ሌላ ከመሄዴ በፊት ገጠመኜን ልጨርስ ታገሱኝ። እስረኛውን ወዳጄን ገና ሳየው እውነት ለመናገር ከከተማው ወሬና ውስኪ ውጪ የጎደለበት አንዳች እንደሌለ አስተዋልኩ። መቼም ከተገኘው ሁሉ መማር እወድ አይደል? ምን ተማርክ አትሉኝም? ወዳጄ አምሮበት፣ ፋፍቶና ቀልቶ ሳየው ትልቁ እስራት የህሊናና የመንፈስ እንጂ የአካል እንቅስቃሴ መገደብ እንዳልሆነ ታዘብኩ። ደላላ ሆኜ እንጂ ከዚህ በላይ በተመራመርኩ ነበር። ዳሩ ‘ሳይበሉ ፍልስፍና የትም አያደርስም’ በሚባልበት አገር ስለምኖር ቶሎ አጨዋውቼው ወደ ሥራዬ መሮጥ ነበረብኝ። ያወቀበት ከጊዜ ጋር ነዋ የሚሮጠው፡፡ በነገራችን ላይ “ፍልስፍና” ሲባል የእነ ስቅራጥስና ፕሌቶ ትምህርት ተረስቶ ፈላስፋ ተሳዳቢና መረን የሆነበት ዘመን ላይ መድረሳችንን ታዘባችሁ? አንድ አሉባልተኛ “ፈላስፋ ነኝ” ባይ ምነው የሚገራው ጠፋ? እኔማ ይኼ “ፈላስፋ” ተብዬ የሚዘባርቀውን ስሰማ መማር ከድለላ ሥራ አነሰ ስል ከረምኩ፡፡  አይ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ?

“ወዳጄ እንዴት ይዞሃል?” አልኩት እስረኛው ተጠርቶ ሲመጣ። ሰላምታ ስንለዋወጥ ጥቂት ደቂቃዎች ነጎዱ፡፡ “እኔምልህ አንበርብር እባክህ አንተም እየተጠነቀቅክ የምታውቃቸውንም አስጠንቅቅ። ይኼ ‘የቫት’ ጉድ ነው የምታየውን ሰው ሁሉ እዚህ ያሰባሰበው፤” ብሎኝ መሬት መሬት ያይ ጀመር። “እኛ እንግዲህ ከአቅማችን በላይ ከምንበላው ዳቦ ላይ ሳይቀር ‘ቫት’ እየከፈልን ነው። ከዚህ በተረፈ ዕድሜያችሁን አወራርዱ ከተባለ የዕድሜና የደመወዙን ልክ መናገር ያቃተው ጉዱ ነው!” ስለው ሳቀ። ከአንጀቱ ከትከት ብሎ ሲስቅ እንዴት ደስ አለኝ መሰላችሁ? እኔ ልሙት! የት አባቱ ደግሞ ሳቅም በአቅሙ ይወደድብን እንዴ? እንዳሁኑ የፈረንጅ ነገር ዘልቆ ሳይገባን በግራዋ እንጨትና በከሰል ሃጫ በረዶ ባስመሰልነው፡፡ አሁን አሁን እንኳ በጫት እንጨት የሚፍቀው በዝቷል መሰለኝ። ምናልባት ለዛ ይሆናል የጥርስ ሳሙና ማስታወቂያ የበዛው? የድለላ አድማሴን ካላሰፋሁ በስተቀር መፈላሰፉ እንኳን ለእኔ ለባለቤቱም አልበጀ፡፡ 

ወዳጄን ተሰናብቼው ስወጣ ለግዳጅ የተዘጋጀ ወታደር ሰንደቅ ዓላማ በአደራ እንደሚቀበለው በርከክ ብዬ ስለ ‘ቫት’ የሰጠኝን አደራ ተቀበልኩት። ኋላ ላይ ለባሻዬ ነገሩን ሳጫውታቸው የተሰማኝን ሳልደብቅ ለእናንተ እንዳልኳችሁ ብላቸው፣ “ወይ ስምንተኛው ሺሕ? እኛ ያነበብነው በመጨረሻው ዘመን የወንጌል ቃል በደንብ ይሰበካል የሚል ነው። አሁን ግን የምናየው ከሰማዩ ወንጌል ይልቅ የመንግሥታት ወንጌል ሰውን ፋታ ሊያሳጣ ሆነ!” አሉኝ። ባሻዬ እንግዲህ የሚያዩበት መንገድ ሁሌም ይለያል። ምናልባት እንደ ዕድሜያቸው ልባቸው በጥበብና በማስተዋል ፀጋ ተጠምቆ እንደሆነስ? ዕድሜ ይስጠንና መልሱን እንመልሰዋለን አትሉኝም? ሞባይሌን አውጥቼ በይደር የተያዙ የድለላ ሥራዎችን ለመሞካከር ሳስብ ተደወለልኝ። አነሳሁና “ሃሎ?” ስል አንድ ሻከር ያለ ድምፅ የጆሬ ታንቡሬን በጩኸት አደነቆረው። ከጩኸቱ የተነሳ የሚለውን መስማት ቢያቅተኝ በፈረደበት ‘ኔትወርክ’ እየሳበበኩ ተነጫነጭኩ። (እንዲህ እኛ እንሰቃይለት እንጂ ቴሌ ቢነግሩት የሚሰማ የሚለማ አልመሰለኝም) ኋላ የሚጮህብኝ ሰውዬ ድምፅ በአንዴው የት እንደገባ አላውቅም ቀነሰ። ምናልባት የዕለት እንጀራችን ከዕለት ወደ ዕለት እየሳሳ ስለመጣ የበላው አልቆ ይሆናል። እኛም እኮ ግን እንጀራን መለመን እንጂ የመጋገር ተነሳሽነት የለንም ጎበዝ! 

“ምንድን ነው የምትለኝ?” አልኩት በስጨት ብዬ። “እናንተ ደላሎች ግን ቆይ ግዴ የለም። እንዲህ በሰው ሕይወት እየቀለዳችሁ የራሳችሁን ቤት ሠርታችሁ በድሎት የምትኖሩ ይመስላችኋል፤” እያለ ሲነጫነጭ አቋረጥኩት። ‘ረጅም ምላስ (ጦርን ለባለ ጦሮች ምላስን ለምላሰኞች በሚለው እናስበው?) ባይወጉበት ያስፈራሩበት’ ማለት እንዲህ ያለውን ነው። “ማን ብለህ ደውለህ ነው?” አልኩት ተሳስቶ ከሆነ የፈረደበት ላይ ደውሎ ያለኝን እንዲለው። እሱ እቴ! እንደ ዘመኑ ሰው ከመስማት መናገር የተፈጥሮ ሚዛኑን ያሳተው ነውና፣ “ቆይ ግድ የለም። ብላችሁ ብላችሁ የስቱዲዮ ዋጋ በባለ አንድ መኝታ ሒሳብ፣ የባለ አንዱን በባለ ሁለት መኝታ  ጣሪያ ሰቅላችሁ ሳይበቃችሁ የስድስት ወር ለሚከፍል ብቻ ካልሆነ አይከራይም ትላላችሁ?” እያለ ሲንጨረጨር የኮንዶሚኒየም ቤቶች የኪራይ ውዝግብ መሆኑ ገባኝ። የኮንዶሚኒየም ቤቶች የኪራይ እሰጥ አገባ በዚህ ሰሞን ብሶበታል። የባሻዬ ልጅ፣ “መተዛዘን ከአንዳንድ ጎጂ ባህሎቻችን ቀድሞ ሲጠፋ ከዚህ በላይ ችግር መፈጠሩ ይቀራል?” ሲለኝ ነው የሰነበተው። ሰውዬው ተሳስቶ ደውሎ እንደወረደብኝ ባልጠራጠርም ነገሩ እውነት ነበረውና ኋላ ላይ ከደላላ ወዳጆቼ ጋር እንድነጋገርበት በደንብ አዳመጥኩት። ይብላኝ አንደማመጥም ብለው ለዓመታት ዓይንና ናጫ ለሆኑት የአገራችን ፖለቲከኞች እንጂ እኔማ እያዳመጥኩ ነው፡፡ “መደመማጥ በሌለበት ሰይጣን እግሩን ሰቅሎ ይስቃል፤” የሚሉት ባሻዬ ትዝ ሲሉኝ የሰይጣን መሳቂያ የሆኑት ፖለቲከኞች ያሳዝኑኛል፡፡

ወዲያው ከተንጣለለ ግቢው ጋር የሚያምር ቪላ ቤት የሚገዛ ሰው አፈላልግ ያሉኝ በዕድሜ ጠና ያሉ ደንበኛዬ ትዝ አሉኝ። በአገርህ ግባ የተማፅኖ ሙዚቃ ብሎም የመንግሥት ውትወታ አገሩ የተመለሰ ‘ዳያስፖራ’ እንዲህ ያለ ቤት እንደሚፈልግ ሰምቼ ስለነበር ደወልኩለትና ቀጠሮ ያዝን። የሐበሻ ቀጠሮ ብዬ 30 ደቂቃ አርፍጄ ብደርስ ‘ቱ ሌት’ ብሎ ገላመጠኝ። እኔ ሆዬ በሆዴ፣ ‘አይ ሐበሻ መሆን? ለካ የፈረንጅ አገር ውኃ እስኪጠጡ ነው’ አልኩላችሁ። እንዲያው ግን እንደ እኛ በትምህርትና በምክር የማያምን ይኖር ይሆን? ሲያደርጉና ሲሆኑ ያየነውን መሆን ይቀናናል ልበል? እንዲህ ሳስብ የትምህርት ተቋማቶቻችን ነገር በቅፅበት ትውስ አለኝ። ሰሞኑን ተስፋ የማይቆርጡ ወገኖቻችን የሚታደሙበት ‘ኢቲቪ’ ስለትምህርት ጉዳይ ያስደመጠው ነገር በጣም ሲገርመኝ ሰንብቷል። ‘የአምስት ዓመቱ የትራንስፎርሜሽን ዕቅዳችን እየተጠናቀቀ ነው’ ሲሉ የጀመሩት ሹም ‘አሁን የቀረን የትምህርቱን ነገር መላ ማለት ነው’ ሲሉ ሰማሁ። ማንጠግቦሽ እንኳ በጣም ከመገረሟ የተነሳ፣ “ምን ዋጋ አለው? በሚሊዮኖች ሕይወት ተጫውተው ሲያበቁ አሥር አዋቂዎች ቢያፈሩ?” ብላ ስትናገር እሰማት ነበር። ምነው ግን እንዲህ ወድቀን ካልተነሳን አንማርም አልን? ዝንት ዓለም ከፈረሱ ጋሪው ሲቀድምብን ይኖራል? መጥኔ!

ከደንበኛዬ ጋር ቤቱን ማየት ጀምረናል። አብረውን አዛውንቱ የቤቱ ባለቤት አሉ። “ምነው ቤቱ ጨለመብኝ?” አለ ገዢው ደንበኛዬ። ሻጭ ቀበል አደረጉና፣ “ምን ቤቱ ብቻ አገሩ ጭምር መስሎኝ የጨለመው፤” አሉት። አልገባውምና ወደኔ ዞሮ ሲያየኝ፣ “መብራት ስለሌለ ነው ማለታቸው ነው፤” ብዬ ባጭሩ አስረዳሁት። ከዚያ በኋላ ‘ዳያስፖራው’ ደንበኛዬ ወደ አገር ቤት መጥቶ ባረፈባቸው ጥቂት ሳምንታት በ‘ኔትወርክ’ እና በመብራት መቆራረጥ ያየውን አበሳ ይተረትረው ጀመር። የደረሰበትን መጉላላት ዘክዝኮ ሲያበቃ፣ “መክሰስ እኮ ይቻላል ለምን ዝም ትላለችሁ?” አይለን መሰላችሁ? “ማንን?” አልነው እኔና አዛውንቱ። “የሚመለከታቸውን መሥሪያ ቤቶች ነዋ! ለምን ተብሎ ያለቅድሚያ ማስጠንቀቂያና ዝግጅት ከተማው ይጨልማል? ሰው ከሰው ይቆራረጣል?” ቢለን አላስቻለንም ሁለታችንም ሳቅንበት። ከሁሉ በላይ ደግሞ በመልካም አስተዳደርና በሕጋዊ አሠራር በሠለጠነው ዓለም ብዙ ያዩ ‘ዳያስፖራ’ ወንድሞችና እህቶቻችንን ምንም ፈር ባልያዘበት አገር ‘ኑ’ እያለ የሚያስኮበልላቸው ፀሐዩ መንግሥታችን አናደደን። (‘ካልደፈረሰ አይጠራም’ ይለን ይሆናል ይኼኔ ቢሰማን) እኛስ አንደኛችንን ፈርዶብናል። ስቀው ሲጨርሱ አዛውንቱ የቤቱ ባለቤት፣ “ክሱን ተወውና ምን ሆኖ ነው አገልግሎት የተቋረጠብን ብለን ለመጠየቅ ስንደውል አንስቶ የሚያናግረን ሰው አለ ወይ? ግለሰብ እንኳን በሕይወት ስንት ክፉና ደግ ነገር አለ እያለ ስልኩን 24 ሰዓት ክፍት ያደርጋል፡፡ እነሱ የራሳቸውን እንጂ የሕዝብ ቅሬታና ድምፅ የሚሰሙበት ጊዜም የላቸው፤” ብለው የምር ተቆጡ። ቁጣውን ለማብረድ ወደቤቱ ጉዳይ ተመለስን። እንዲህ እያበረድንና እያባረድን ካልሆነ ሲያከሩ ማክረር ማንን ጠቀመ?

በሉማ እንሰነባበት። ከብዙ ደጅ መጥናትና የዋጋ ክርክር በኋላ ቤቱን ለመሸጥ አዛውንቱ ከቀናት በኋላ ተስማሙ። እስከዚያው ድረስ እኔም ወዲያ ወዲህ እያልኩ ሌሎች ሥራዎች ላይ አሳለፍኩ። ከተሸጠው ቪላ ጠቀም ያለ ‘ኮሚሽን’ ስጨምርበት ልክ ስለገባ ማንጠግቦሽን ማስደሰት አማረኝ። ዓውደ ዓመትም አይደል እንዴ? ስበር ቤት ሄድኩና ሳታስበው ውዷን ባለቤቴን ሙጭጭ አድርጌ ሳምኳት። “ምን ተገኘ?” ብላ ስትደናገጥብኝ “እኔ አንቺን መውደዴን ለማሳየት ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ፋሽን የሆነውን ሰላማዊ ሠልፍ መጥራት አለብኝ?” ብዬ መልሼ ጠየቅኳት። እሷም፣ “እውነት ለማንጠግቦሽ ያለህን ፍቅር በአደባባይ በሠልፍ ግለጽ ብትባል . . .?”  ስትለኝ አላስጨረስኳትም። “የፍቅር ሠልፍ መሆኑን የሚያምንልኝ ካገኘሁ? እንክት!” ስላት ከጣራ በላይ ሳቀች። ለፀብና ለቅናት ጆሮውን የቀሰረ ፍቅር በሞላበት ቤታችን አንጀቱ ሲቃጠል ታየኝ። የገዛሁላትን ቀሚስ ስሰጣት ደግሞ ደስታዋ እጥፍ ድርብ ሆነ። “በአዲሱ ዓመት ምን ትመኛለሽ?” ስላት ትንሽ ዝም ብላ ቆይታ፣ “የክፋት ድስት ወጥቶ የፍቅር ድስት እንዲገባ!” አለችኝ። ‘ኅብረተስብ ከቤተሰብ ይቀዳል’ ይላሉ አበው። የእያንዳንዳችን ቤት በፍቅር ሲሞላ ማንጠግቦሽ እንዳለችው በአገር ደረጃ ዘመን መለወጫን ሰበብ አድርጎ የክፋት ድስት ለፍቅር ድስት ቦታውን መልቀቁን እንመኝ፡፡ እኔና ማንጠግቦሽ ወደ አልጋችን ከሄድን ቆየን። መጪው ዓመት በፍቅር ተጀምሮ በፍቅር ይለቅ! “መስከረም ሲጠባ አደይ ሲፈነዳ…” እያልን መልካሙን እንመኝ፡፡ መልካም አዲስ ዓመት! መልካም ሰንበት!