መነሻ ገጽ - ሌሎች አምዶች - ማህበራዊ ጉዳዮች - ዲያስፖራ - የድንጋዩ ብርሃን
Buy Valtrex Online Buy Albuterol inhaler Online Buy Prinivil Online
10 March 2013 ተጻፈ በ 

የድንጋዩ ብርሃን

‹‹ከዚህ ቀደም ሥራ አልሠራም ነበር፡፡ የጀመርኩት በዚህ ነው፡፡ ትምህርቴን ጨርሼ ዝም ብዬ ስንቀዋለል እውል ነበር፡፡

ይህ ፋብሪካ በመከፈቱ ግን በጣም ዕድለኛ ሆንኩ፡፡ ምክንያቱም በየቦታው ስደት ከመሔድ ራሴን ችዬ ወላጆቼን እያገዝኩ እዚህ ሆኜ እኖራለሁ፡፡››

ከአዲስ አበባ 746 ኪሎ ሜትር ርቀት፣ ከመቐለ 37 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በምትገኘው ዓዲጉዶም ከተማ የጂፕሰም (ጀሶ) ፋብሪካ በተመረቀበት ዕለት ያገኘናት ወጣት የተናገረችው ነው፡፡

በአገር ውስጥና በውጭ አገር በሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ባቋቋሙት ትሮፒካል ኢትዮ አሜሪካን ኢንዱስትሪያል ኢንቨስትመንት አክስዮን ማኅበር የተገነባው ፋብሪካ ዓዲጉዶም ጅብሰም ፋብሪካ (ዓጀፋ) ይሰኛል፡፡ የካቲት 9 ቀን 2005 ዓ.ም. ለምረቃ በቅቷል፡፡ አክሲዮን ማኅበሩ በ26.5 ሚሊዮን ብር ካፒታል 72% በውጭ አገር በሚኖሩ ትውልደ ኢትዮጵያውያንና 28% በአገር ውስጥ በሚኖሩ ኢትዮጵያውያን በጋራ የተመሠረተ ነው፡፡

ዓጀፋ በአሜሪካና በአገር ውስጥ የሚኖሩ 47 አባላትን ባቀፈው አክሲዮን ማኅበር የታነፀ በክልሉ የመጀመሪያው የጅብሰም ፋብሪካ ነው፡፡ በዓመት 50 ሺሕ ቶን የማምረት አቅም አለው፡፡ የጥራት ደረጃውም 96% እንዳለው ተረጋግጧል፡፡ ፋብሪካው የቴክኖሎጂ ዕውቀት ሽግግር የታየበትና 40% በአገር ውስጥ መሐንዲሶች ኮፒ ተደርጎ የተሠራ ነው፡፡

አቶ ዓባይ ወልዱ የትግራይ ክልል ፕሬዚዳንት የፋብሪካው መገንባት የአካባቢውን ማኅበራዊ ችግር ለመፍታት ከፍ ያለ አስተዋጽዖ እንደሚኖረው ሙሉ እምነታቸው መሆኑን በምረቃው ዕለት ገልጸው የአካባቢው ሕዝብ ሊደግፈው እንደሚገባም መንግሥትም ምን ጊዜም ከመደገፍ ወደኋላ እንደማይል ሳይገልጹ አላለፉም፡፡

በአገሪቱ በክልሉም ያለውን የኮንስትራክሽን ልማትና ዕድገትን ለመደገፍ ዓለም አቀፍ ደረጃ የጠበቀና ጥራት ያለው የጅብሰም ውጤት ማምረት ጀምሯል፡፡

እንደ አክሲዮን ማኅበሩ የቦርድ ሊቀመንበር አቶ አዲሱ ባሕታ አገላለጽ ማኅበሩ ራዕዩን ሰንቋል፡፡ የጊዜውን የጂብሰም ቴክኖሎጂ በማስገባትና የምርምር ሥራን በማካሔድ ለተለያዩ ጥቅሞች እንዲውል ማድረግ ነው፡፡ የመጀመሪያው ተግባሩ ጂብሰም ፓውደር ማምረት ሲሆን በቀጣይ ጂብሰም ብሎኬትና ቦርድ ያመርታል፡፡ 

ከ26 ዓመት በፊት ኢትዮጵያን ለቀው የወጡት አቶ አዲሱ ተወልደው ያደጉት በትግራይ ሲሆን መኖሪያቸው በአሜሪካ ሲያትል ነው፡፡ ትምህርታቸውም የማዕድን ምሕንድስና ነው፡፡ በ1999 ዓ.ም. አክሲዮን ማኅበሩን በአሜሪካ ሲያትል ከሌሎች ጋር ማቋቋማቸውን የሚገልጹት ሊቀመንበሩ፣ ወደ ጅብሰም ኢንቨስት ለማድረግ ከመነሳሳታቸው በፊት አቅደው የነበረው በራያ ቢራ ፋብሪካን ለማቋቋም ነበር፡፡ በወቅቱ በነበረው አለመስማማት እርሱን ትተው ወደ ጂብሰሙ ማምራታቸውን ገልጸዋል፡፡

ጂብሰሙ የሚገኝበት ቦታ ከዓዲጉዲም ከተማ ምሥራቅ አቅጣጫ 12 ኪሎ ሜትር ርቀት በሚገኝ 10 ሺሕ ካሬ ሜትር ላይ ያረፈ ነው፡፡ በጂኦሎጂስት እንደተጠናው ከ100 እስከ 140 ዓመት ሊወጣለት የሚችል ማዕድን አለው፡፡

‹‹የጂብሰም ውጤቶች ለብዙ ነገር ይሆናል፡፡ እስካሁን በኅብረተሰቡ ግንዛቤ አልነበረም፡፡ ለእርሻ ማዳበሪያም ስለሚሆን መንግሥት ከውጭ አገር የሚያስመጣውን ማዳበሪያ ወጪ ይቀንሳል፤›› የሚሉት አቶ አዲሱ፣ የፋብሪካው እውን መሆን የፈጠረባቸውን ስሜት እንዲህ ገልጸውታል ‹‹ድንጋይ ዳቦ መሆን መቻሉን ማሳየታችንና ድንጋይ ፈጭተን ወደ ገንዘብ መቀየራችን ብርሃን ማሳየታችን አርክቶናል ኅብረተሰቡም ተደስቶበታል፡፡››

የአክሲዮን ማኅበሩን በመሥራችነት ካቋቋሙት አንዷና በአሜሪካ ቦስተን ነዋሪ የሆኑት ወይዘሮ አዜብ አብርሃ ናቸው፡፡ መቐለ ያደጉትና በቀድሞዋ ሶቭየት ኅብረት በኢንዱስትሪያል ኢኮኖሚክስ የተመረቁትና ሁለተኛ ዲግሪያቸውን በአሜሪካ በቢዝነስ አድሚኒስትሬሽን ያገኙት ወይዘሮ አዜብ ‹‹ከቢሮክራሲው በላይ እንደ ችግር የማየው ድህነታችን የሚያመጣው መዘግየት ነው›› ብለዋል፡፡ በአሠራር በኩልም መስተካከል ያለባቸው ነገሮችን ሳይጠቅሱ አላለፉም፡፡

‹‹ኤልሲ ለመክፈት ያለው ዝግታ አላስፈላጊ ነው፡፡ ከአቅም ማነስ በየቢሮው የሚታይም ችግር አለ፤ አንዱ ክፍተት ለሚጠየቀው ጥያቄ አመርቂ ምላሽ አለመገኘቱ ነው፡፡›› ማሳያ ብለው ያነሱት ደግሞ ማሽኖቹ ከጂቡቲ ዓዲጉዶም ከደረሱ በኋላ ከተጫኑበት ለማውረድ ቀናት መውሰዱ ነው፡፡ በአካባቢው ክሬን እንኳን አልነበረም፡፡ ይህም አጋጣሚ ማሽነሪዎችን የሚያስገባና ለአገልግሎት የሚያውል ራህዋና ኮንስትራክሽን እንዲያቋቁሙ አድርጓቸዋል፡፡

በፋብሪካው እውን መሆን ከእርሳቸው እርካታ ይልቅ የኅብረተሰቡ ደስታ እንደሚበልጥ የአንዲትን የዓዲጉደም ነዋሪ እናት አነጋገር በምሳሌነት ያነሡታል፡፡

‹‹እኔ'ኮ ልጄ ሥራ እንዲቀጠርልኝ መቐለ እየተመላለስኩ ደጅ እጠና ነበር፤ እጠይቅ ነበር፡፡ እዚህች ደጃፌ የእኔ ልጅ ተቀጥሮ መሥራቱ እንዴት ትልቅ ነገር ነው፡፡ ይኸ ሀብት የእናንተ ሳይሆን የእኛ ነው፤ ለዚህም ነው በጧት የመጣሁት፡፡››

ፋብሪካው 60 ቋሚና ጊዜያዊ ሠራተኞች አሉት፡፡ በሙያ ትምህርት የተመረቀው ልዑል አባዲ ከፋብሪካው ዕውቀት መቅሰሙንም እንዲህ ገልጾታል፡፡

‹‹ቴክኒክና ሙያ ተምረናል፤ የተግባር ትምህርት የተማርነው እዚህ ፋብሪካ ነው፣ አስተማሩን፣ የሚጠፋን ነገር የለም፤ ብየዳውንም መገጣጠሙንም የተማርነው እዚህ ነው፡፡››

የፋብሪካውን የኢንዱስትሪያል ፊዚቢሊቲ ጥናቱን የሠሩት አንዱ ማኅበርተኛ ኢንጂኒየር ገብረ ኪሮስ ሀብቱ ናቸው፡፡ ለዚሁ ጥናቱ እንዲረዳቸውም ቻይና ድረስ በመጓዝ ጂብሰም ማምረቻ ማሽነሪዎችን የሚፈበርኩትን ጎብኝተዋል፡፡ ከተለያዩ የአውሮፓ አገሮችም መረጃዎች አሰባስበዋል፡፡

ከባሕር ማዶ ከመምጣታቸው በፊት ስለአካባቢው ማዕድን ክምችት በዛምራ ኮንስትራክሽን አማካይነት ጥናት መካሔዱን ያስታወሱት ኢንጂነሩ፣ ወደሥራ ለመግባት ከባንክ 60% ብድር ፈቃድ ለማግኘት አንድ ዓመት ያህል መውሰዱን ሳይጠቅሱ አላለፉም፡፡

እንደሳቸው አገላለጽ፣ ፋብሪካው መቋቋሙ ኅብረተሰቡን አስደስቶታል፡፡ እያደገና እየተስፋፋም ይሔዳል፡፡ የአገር ውስጥ ባለሀብቶች ውጭ ካሉት ጋር ተባብረው መሥራታቸው እንደ ትልቅ ምሳሌ ይታያልም ብለዋል፡፡ ዓዲጉዶም በአብዛኛው የእርሻ ቦታ ነው፡፡ ስንዴና ገብስ በማምረት ይታወቃል፡፡ ዱሮ አስመራ የነበሩ የዱቄት ፋብሪካዎች ጥሬ ዕቃቸውን የሚያገኙትን ከዚህ አካባቢ ነበር፡፡ በአካባቢው ጂብሰም ፋብሪካ መቋቋሙ ደግሞ ምርቱን ወደተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች ለመላክ ዕድል ይፈጥራል፡፡