መነሻ ገጽ - ሌሎች አምዶች - ማህበራዊ ጉዳዮች - ዲያስፖራ - እንቁልልጭ
Buy Valtrex Online Buy Albuterol inhaler Online Buy Prinivil Online

ትውልድ አገራቸውን ጥለው እንዲሰደዱ ያደረጋቸው በ1960ዎቹ መጨረሻ የነበረው ቀይ ሽብር ነው፡፡ በወቅቱ በጅቡቲ አቋርጠው ከአገር ሲወጡ ጨርቄን ማቄን አላሉም፡፡

ደርግ ትርፍ ቤትን ለመውረስ ባወጣው አዋጅ 47/67 መሠረት ከእናታቸው በውርስ ያገኙትን ቤት እንኳን በቅጽ 004 የምርጫ ቤታቸውን ሞልተው የውሳኔ ማረጋገጫቸውን በእጃቸው ሳያስገቡ ነው ሕይወታቸውን ለማትረፍ ከአገር የሸሹት፡፡ ሆኖም በወቅቱ ቤቱን በእጃቸው አስገብተው ከአገር አይውጡ እንጂ ደርግ ባወጣው አዋጅ 47/67 አንቀጽ 111፣ ማንኛውም ግለሰብ ወይም ቤተሰብ አንድ መኖርያ ቤትና 500 ካሬ ሜትር ቦታ በሚፈቅደው መሠረት በአሁኑ በአዲስ አበባ ቂርቆስ ክፍለ ከተማ ወረዳ 4 የቤት ቁጥር 172/04 እና 05 ለእሳቸውና ለእህታቸው ተፈቅዶላቸው ነበር፡፡

በአሜሪካ ነዋሪ የሆኑት ትውልደ ኢትዮጵያዊው አቶ ዳንኤል ጌታቸው በቂርቆስ ክፍለ ከተማ ወረዳ 4 የቤት ቁጥር 172 የሆነውን በውርስ የተገኘ የመኖርያ ቤት ጥለው ከአገር ቢወጡም፣ ኢሕአዴግ ከአዋጅ ውጭ የተወሰዱ ንብረቶችን ለማስመለስ ባወጣው አዋጅ ቁጥር 110/87 መሠረት ቤታቸውን ለማስመለስና በአገራቸው ለመሥራት ወደ ኢትዮጵያ ይመጣሉ፡፡

አቶ ዳንኤል ወደ አገራቸው የተመለሱት በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ወደ ትውልድ አገራቸው ተመልሰው በውጭ አገር ቆይታቸው ያፈሩትን ሀብት፣ ዕውቀትና ልምድ ለትውልድ አገራቸው እንዲያበረክቱ በወቅቱ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር የነበሩት ሥዩም መስፍን ለዳያስፖራው ባደረጉት ጥሪ ነበር፡፡ ሆኖም ያሰቡትን ማሳካት አልቻሉም፡፡ በውርስ ያገኙትን መኖርያ ቤታቸውን ለማስመለስ 1988 ዓ.ም. ጀምሮ እስካሁን ድረስ ይዋትታሉ፡፡ በአገራቸው ለመሥራት የነበራቸው ሞራልም በጥያቄ ውስጥ ወድቋል፡፡ ደርግ የሰጠንን ኢሕአዴግ ነጠቀን ወደሚል መደምደሚያ ላይም ደርሰዋል፡፡ ጂ+1 ከሆነው ቤት ለድርጅትነት በተፈቀደው 172/03 ቤት ውስጥ ከነቤተሰባቸው ተፋፍገው ለመኖርም ተገደዋል፡፡

በ365 ካሬ ሜትር ላይ ያረፈው ቤት ጂ+1 ሆኖ 5 ክፍሎች ያሉት ሲሆን፣ ሁለቱ ቤቶች ትርፍ ቤት ተብለው በደርግ ተወርሰዋል፡፡ አቶ ዳንኤል እንደሚሉት ደግሞ በደርግ ጊዜ ሁለቱ ክፍል ለእሳቸውና እህታቸው ተፈቅዶላቸዋል፡፡

አቶ ዳንኤል ከ1988 ዓ.ም. ጀምሮ በመጠየቅ ላይ የሚገኙት ደግሞ በትርፍ ቤትነት የተወረሰውን ሁለቱን ቤት ሳይሆን ለእሳቸውና ለእህታቸው ለእያንዳንዳቸው አንድ አንድ በመኖርያ ቤትነት በወቅቱ የተፈቀደላቸውን ነው፡፡

የኢትዮጵያ ፕራይቬታይዜሽን ኤጀንሲ መስከረም 30 ቀን 1995 ዓ.ም. አቶ ዳንኤል አቤቱታ ያቀረቡበትን ቤት፣ ባቀረቡት ማስረጃ መሠረት የሚገባቸው መሆኑን ወስኖ ለወቅቱ ኪራይ ቤቶች አስተዳደር ድርጅት (ኪቤአድ) አሳውቆ ነበር፡፡ ሆኖም በወቅቱ ቅፅ 004 ላይ ማጭበርበር ተሠርቷል፤ ችግር ነበረበት ከሚል የአቶ ዳንኤልን ጨምሮ ብዙ የይመለስ ውሳኔ ያገኙ ቤቶች እንዳይመለሱ ታግደዋል፡፡

አቶ ዳንኤል ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴርን ጨምሮ አቤት ያላሉበት ቢሮ የለም፡፡ ሆኖም ቤታቸውን ከእጃቸው ማስገባት አልቻሉም፡፡ ጉዳያቸውን የያዘው ከአዋጅ ውጭ የተወሰዱ ንብረቶች ጉዳይ ማስፈጸሚያ ፕሮጀክት ጽሕፈት ቤትም የእሳቸውንና 23 ሺሕ የሚደርሱ አቤቱታ አቅራቢዎች የጠየቁትን ንብረት አይገባችሁም ሲል ውሳኔ ሰጥቷል፡፡   

በፕራይቬታይዜሽን ኤጀንሲ ከአዋጅ ውጭ የተወሰዱ ንብረቶች ጉዳይ ማስፈጸሚያ ፕሮጀክት ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ኃይለ ማርያም ይትባረክ፣ አቶ ዳንኤል ቤቱን በውርስ ያገኙት መሆኑን ያምናሉ፡፡ ሆኖም በወቅቱ የምርጫቸውን ቤት ቢሞሉም አልተረከቡም፤ አላስፈጸሙም፡፡ በመሆኑም ዛሬ ላይ ቤቱን ሊያገኙ አልቻሉም፡፡ አዋጅ 110/87 የሚለውም ምንም ቤት ሳይቀራቸው ለተወረሰባቸው እንዲመለስ በመሆኑና እነ አቶ ዳንኤል አንድ ክፍል ቤት ስላላቸው ቀሪው አልተመለሰላቸውም ብለዋል፡፡ አቶ ዳንኤል ደግሞ አንድ ክፍል ቤትም የመኖርያ የለንም፣ ለድርጅት በተፈቀደው ውስጥ ከነቤተሰቤ ታጭቄ እየኖርኩ ነው ብለዋል፡፡

በወቅቱ ስደት ላይ የነበሩት አቶ ዳንኤል ደርግ የፈቀደላቸውን ቤት ማስፈጸም አልቻልንም የሚሉ ቢሆንም አቶ ኃይለ ማርያም ቢኖሩም አያስመልሱም፤ አገር ውስጥ የነበሩትም በፍርሃት ፀጥ ብለው ነበር የተቀመጡት ብለዋል፡፡

በወቅቱ እነ አቶ ዳንኤል መርጠዋል፡፡ ሳይመርጡ ቀርተው የኮብላይ ነው ተብሎ ተወርሶ ቢሆን ኖሮ ይመለስላቸው ነበር፡፡ ሆኖም መርጠው የሞሉትን ቅጽ 004 የሚያፀድቀው አካል አላጸደቀላቸውም፡፡ በመሆኑም ያልተሟላ ሰነድ ነው፡፡ ተሟልቶ ቢሆን ውጭም ይሁኑ አገር ውስጥ ይመለስላቸው ነበር ብለዋል፡፡ አቶ ዳንኤል ግን ሰነድ እንደሚጠፋ፣ እነሱ በእጃቸው ያለው ሰነድ እንኳን ለሚመለከታቸው መሥርያ ቤቶች ውስጥ እንደማይገኝ፣ ሆኖም በእሳቸው በኩል ሰነዶችን አሟልተው መቅረባቸውን ይናገራሉ፡፡

ጽሕፈት ቤቱ አቶ ዳንኤልን ጨምሮ ብዙ የደርግ ተበዳዮችን ሳያስደስትና የጓጉለትን ንብረታቸውን ሳያስመልስ ቢሮውን ለመዝጋት የጥቂት ወራት ዕድሜ ቀርቶታል፡፡ የኤጀንሲው ቦርድ የቀሩትም አራት ጉዳዮች ብቻ ናቸው፡፡ ለእነዚህ ውሳኔ ሰጥቶ ቢሮውን ይዘጋል፡፡

ኤጀንሲው ሥልጣኑ በአዋጅ ከተሰጠው ከ1987 ዓ.ም. እስከ 2000 ዓ.ም. ድረስ 35 ሺሕ አቤቱታዎችን የተቀበለ ሲሆን፣ አግባብነት ያላቸው ብሎ ምርመራ ያካሔደባቸው 25 ሺሕ ያህሉ ላይ ነው፡፡ ከእነዚህ ውስጥ 1,200 የይመለስላቸው ውሳኔ ሲያገኙ 23 ሺሕ ያህሉ አይመለስ የሚለው ውሳኔ የደረሳቸው ናቸው፡፡ 

አቶ ዳንኤል መንግሥት የሰጠው ውሳኔ እንዳሳዘናቸው ይናገራሉ፡፡ ከ15 ዓመት ላላነሰ ጊዜ ቤታቸውን ለማስመለስ ከኤጀንሲው ሲመላለሱ፣ ጊዜያቸውን ሲያጠፉ ከርመዋል፡፡ ‹‹መንግሥት ቤቴን በጉልበት እንደወሰደው እቆጥረዋለሁ፤ ምን ሥልጣን ኖሮት ነው ቤቴን የሚወስደው?›› ሲሉም ይጠይቃሉ፡፡

ደርግ የፈቀደውን ቤት ኢሕአዴግ ሲነጥቅ ዜጋ መሆንን ያጠራጥራል የሚሉት አቶ ዳንኤል ‹‹ሌላው ትውልደ ኢትዮጵያዊስ ይህን በደል እያየ አገሩ ላይ እንዴት እምነት ይኖረዋል?›› ብለዋል፡፡

ልጆቻቸውን ሳይቆጥሩ 17 የተማሩና ገንዘብ ያላቸው ቤተሰቦቻቸው በኢትዮጵያ በኢንቨስትመንቱና በእውቀት ሽግግሩ ለመሰማራት አቅደው እንደነበር፤ በዚህ ሁኔታ ግን እምነት ማጣታቸውን ገልጸዋል፡፡

በአሜሪካ የሚኖሩ ቤተሰቦቻቸውም ኢሕአዴግ እንቁልልጭ ተጫወተብን ማለታቸውን ነግረውናል፡፡