መነሻ ገጽ - ሌሎች አምዶች - ማህበራዊ ጉዳዮች - ዲያስፖራ - ከ20 ዓመታት በኋላ ያየ ዓይን
Buy Valtrex Online Buy Albuterol inhaler Online Buy Prinivil Online
24 March 2013 ተጻፈ በ 

ከ20 ዓመታት በኋላ ያየ ዓይን

የዛሬ 20 ዓመት ነው፡፡ ተወልዳ የልጅነት ጊዜዋን ባሳለፈችበት ሰሜን ሸዋ ደራ አካባቢ ኩፍኝ ይገባል፡፡ እሷን ጨምሮ የአካባቢው ልጆች በሙሉ በኩፍኝ ይታመማሉ፡፡

ኩፍኝ በአካባቢው ገብቶ ሲወጣና በኩፍኛ የታመሙት ሕፃናት በሙሉ ሲድኑ እሷ ላይ ግን ጠባሳ ጥሎ አለፈ፡፡ ሁለት ዓይኗን ሰወራት፡፡ በወቅቱ የዘጠኝ ዓመት ልጅ እንደነበረች ትናገራለች፡፡ በኩፍኝ ሳቢያ ዓይኖቿ መጥፋታቸውን የሰሙትና በአዲስ አበባ ነዋሪ የሆኑት አክስቷ የልጅነት ጊዜዋን ካሳለፈችበት ደራ ወደ አዲስ አበባ ያመጧታል፡፡

የዓይን ሕክምና በሚሰጡ ሆስፒታሎች እያዘዋወሩም ያሳዩዋታል፡፡ ለዘጠኝ ዓመቷ ሕፃን ዓይኖች ግን መፍትሔ የሚሰጥ ጠፋ፡፡ በተደጋጋሚ ከውጭ የሚመጡ ባለሙያዎችም ዓይኖቿን ሊታደጉላት አልቻሉም፡፡ ዓይኖቿ ላይ ጠባሳ ስላለ እንደማይድን ለቤተሰቦቿ ተነገረ፡፡ የዓይኗ ብርሃን ባይሳካ ትምህርት ልትነፈግ አይገባም ያሉት አክስቷ ሰበታ መርሐ ዕውራን (ብሔራዊ ዓይነ ስውራን ትምህርት ቤት) አስገቧት፡፡ ትምህርቷንም እስከ 12ኛ ክፍል አጠናቀቀች፡፡

የ29 ዓመቷ ወይዘሮ ወደርየለሽ አያሌው፣ በወቅቱ የማትሪክ ውጤት ስላልመጣላት ትምህርቷን መቀጠል አልቻለችም ነበርና በ15 ዓመቷ የገባችበትን ትዳር ለማጠንከር ኦቾሎኒና የሞባይል ካርድ እያዞረች መሸጡን ተያያዘችው፡፡

ዘንድሮ በኮተቤ መምህራን ትምህርት ኮሌጅ የማታ ትምህርቷን የጀመረችው ወይዘሮ ወደርየለሽ፣ ድንገት ሳታስበውና ይሳካል ብላ ሳትገምተው በታኅሣሥ 2005 ዓ.ም. መጀመርያ ላይ የ20 ዓመት የዓይነ ስውርነት ታሪኳን የሚለውጥና ነጭ ዱላዋን የሚያስጥል አጋጣሚ ተፈጠረ፡፡

የማታ ትምህርቷን ክፍያ የሚሸፍንላት የአይሻ የበጐ አድራጐት ድርጅት መሥራችና ሥራ አስኪያጅ አዲስ የዓይን ሕክምና ማዕከል ስለተከፈተ ዓይኗን ሊያሳዩላት እንደሚፈልጉ ነገሯት፡፡ እሷ ግን አንገራገረች፡፡ የመጀመርያ ሴሚስተር አጋማሽ ፈተና ስለነበረባትም ተስፋ ለሌለው ዓይን ብላ ፈተና ባያመልጣት እንደምትመርጥ ተናገረች፡፡ ሆኖም የሐሳቡ አቅራቢ ጉልበት አየለና ዓይኗን ለመታከም ታኅሣሥ 3 ቀን 2005 ዓ.ም. ወደ ዋጋ ስፔሻላይዝድ አይ ክሊኒክ (ዋጋ የዓይን ሕክምና ክሊኒክ) አመራች፡፡

በክሊኒኩ ያሉ ዶክተሮች አይተዋት ዓይኗ የዛኑ ቀን ሊሠራ እንደሚችል ተናገሩ፡፡ ለባለቤቷና ለቤተሰቦቿ ምንም ሳትናገር ከቤት የወጣችው ወይዘሮ ወደርየለሽ፣ የዓይን ቀዶ ሕክምናው ወድያውኑ ተሠራላት፡፡ አመሻሽ ሲሆን ደግሞ ወደቤቷ መሄድ እንደምትችል ተነግሯት በማግስቱ መጥታ የታሸገበት እንዲፈታላት ቀጠሮ ተሰጣት፡፡ በማግስቱ ወደ ዓይን ሕክምና ክሊኒኩ የመጣችው ከ15 ዓመቷ የመጀመርያ ሴት ልጇና ከባለቤቷ ጋር ነበር፡፡ ወደ ሕክምና ክፍሉ ገብታ የታሸገችበት ፋሻ ተፈታ፡፡

ከ20 ዓመታት በኋላ ለመጀመርያ ጊዜ ያየችው ከኔፓል ከመጡት ሚስተር ጄፍ ጋር ሆነው ቀዶ ሕክምናውን የሠሩላትን ዶክተር ኤልያስ ኃይሉን ነበር፡፡ ቀጥላም ሴት ልጇን ተመለከተች፡፡ ‹‹ልጄን ሳያት እንቅ አድርጌ አቀፍኳት፡፡ ሰዎች ቆንጆ ናት ሲሉ እሰማ ነበር፡፡ ልጄን ሳያት እውነትም ቆንጆ ናት፡፡ ለካ እንዲህ ቆንጆ ነሽ አልኳት፡፡ ከዚህ በኋላ ባለቤቴን፣ በድምፅ ብቻ የማውቀውን ቴሌቪዥን፣ በክሊኒኩ የነበሩ ሰዎችን አየሁ፡፡ ግን ግር ነበር ያለኝ፡፡ ወደማላውቀው ዓለም ነበር የገባሁት፡፡ ደስታዬም ወደር አልነበረውም፡፡ አንደኛው ዓይኔ መታከም ባይችልም አንዱ አይቶልኛል፡፡ ዱላዬን ጥዬ፣ የሰው ዕርዳታን ትቼ በራሴ መንቀሳቀስ ጀምሬያለሁ፡፡››

የአራት ዓመት ልጇን አንበሳ ግቢ አካባቢ ከሚገኝ ሙአለ ሕፃናት ስታደርስ ያገኘናት ወይዘሮ ወደርየለሽ፣ ከዚህ ቀደም በነጭ ዱላዋና በሰዎች ዕርዳታ ስትንቀሳቀስ፣ ታክሲ ስትሳፈር፣ ትምህርት ቤት ስትሄድ የሚያውቋት መንገደኞች ሁሉ እያስቆሙ እንዴት እንዳየች ጠይቀው፤ በኋላም እንኳን ደስ አለሽ ብለው ደስታቸውን ሲገልጹላት ደስታዋ የበለጠ እንደሚያይል ነግራናለች፡፡

ላለፉት 20 ዓመታት ዓይነ ስውር የነበረችው ወይዘሮ ወደርየለሽ፣ ሕክምና እየተከታተለችበት ያለውን ዋጋ ስፔሻላይዝድ አይ ክሊኒክ (ዋጋ ቪዥን) በሕክምናው የሠለጠኑ አገሮች በሚከተሉት ደረጃ መሠረት በአዲስ አበባ የከፈቱት ሦስት ትውልደ ኢትዮጵያውያን የሕክምና ባለሙያዎችና አንድ ካናዳዊት ናቸው፡፡ ዋጋ ቪዥንን የከፈቱት በቶሮንቶ ካናዳ የሕክምና ባለሙያ በሆኑት ዶክተር ሐረጓ ጌጡ፣ ዶክተር መላኩ ጋሜ ከአልበርታ ዩኒቨርሲቲ፣ ዶክተር አዳም ዋቅሶርና ሚስ ሻረን አሽታን ናቸው፡፡ ከዚህ ቀደምም ከ10 ዓመት ላላነሰ ጊዜ በኢትዮጵያ በሕክምናው ዘርፍ የበጐ አገልግሎት፣ የአቅም ግንባታና የልምድ ልውውጥ ሲያደርጉ ቆይተዋል፡፡

በሰሜን አሜሪካ በሚኖሩ የሕክምና ባለሙያዎች ማኅበር ሥር በመሳተፍ በሕክምና ዙርያው አቅም በመገንባት፣ የልብ ቀዶ ሕክምና በማድረግ፣ ከሌሎች አጋር ድርጅቶች ጋር በመሆን የኤችአይቪ መድኃኒቶችን በመስጠት የተለያዩ የሕክምና መሣርያዎችን ለመንግሥት ተቋማት በማበርከትና በልምድ ልውውጥ ሲሳተፉም ቆይተዋል፡፡

ከዚህ ሥራ ጐን ለጐን ደግሞ በኢትዮጵያ ክፍተት ባለበት የዓይን ሕክምናው ዘርፍ ኢንቨስት አድርገዋል፡፡ ዋጋ ቪዥን በዓይን ዙርያ የሚሰጡ ሕክምናዎችን በመሉ አጠቃሎ ለመሥራት የሚያስችሉ መሣርያዎችን አሟልቶ ሥራውን የጀመረ ሲሆን፣ ኢትዮጵያውያን ለዓይን ተጨማሪ ሕክምና ብለው ወደውጭ ሄደው ለመታከም የሚያባክኑትን ገንዘብና ጊዜም ያስቀራል ተብሏል፡፡

በአሜሪካና በሠለጠነው ዓለም የሕክምና አሰጣጥ ዘዴና መሣርያዎች የተደራጀው ክሊኒክ በአገር ውስጥና በውጭው ዓለም ልምድ ያላቸውና ከዘመኑ ቴክኖሎጂ ጋር አብረው የሚጓዙ ባለሙያዎችንም ያቀፈ ነው፡፡ ክሊኒኩ አገር ውስጥ ከሚገኙ የዓይን ስፔሻሊስቶች በተጨማሪ ከሰሜን አሜሪካና ከእስያ የሚመጡ ትውልደ ኢትዮጵያውያንና የውጭ አገር የዓይን ስፔሻሊስቶች ሕክምና ይሰጡበታል፡፡

ትውልደ ኢትዮጵያውያኑ ክሊኒኩን የ40 ሚሊዮን ብር ካፒታል በማስመዝገብ ያቋቋሙት ሲሆን፣ ለዓይን ሕሙማን የሕክምና አገልግሎት ከመስጠት ባለፈም በአገር ውስጥ ያሉ የዓይን ሕክምና ባለሙያዎች፣ የሠለጠነው ዓለም የሚጠቀምባቸው የሕክምና መሣርያዎችና ቴክኒኮች ላይ ግንዛቤ እንዲያገኙና የልምድ ልውውጥ እንዲያደርጉ ሥልጠናም ይሰጣል፡፡

ላቅ ያለ የዓይን ሕክምና ዕውቀት ያላቸው ባለሙያዎች ከውጭ ሲመጡም፣ አዲስ አበባ ውስጥ ያሉ የዓይን ሐኪሞች ይጋበዛሉ፡፡ ለየት ያለ የቀዶ ሕክምና በሚኖርበት ጊዜ ገብተው እንዲሳተፉ፣ ሌክቸር እንዲካፈሉ በአጠቃላይም ክህሎታቸውን እንዲያዳብሩ ዕድሉ ተመቻችቷል፡፡

ዶክተር ሐረጓ እንደሚሉት፣ ለዓይን ሕክምና ባለሙያዎች ብቻ ሳይሆን ሁሉም ሐኪሞች መሠረታዊ የዓይን ሕክምና ክህሎት እንዲኖራቸው በየዓመቱ ቀጣይነት ያለው ሥልጠና ለመስጠትም አቅደዋል፡፡

ዋጋ ቪዥን የዓይን ሕክምና ክሊኒክ፣ የዘመኑን መሣርያዎችና ዕውቀት በማጣመር የሚሠራ ሲሆን፣ በክሊኒኩ ከገቡት መሣርያዎች ውስጥ አንዳንዶቹ በኢትዮጵያም ሆነ በአንዳንድ አገሮች የሌሉ መሆኑን ከክሊኒኩ ያገኘነው መረጃ ያሳያል፡፡

የሠለጠነው ዓለም እየሠራባቸው የሚገኙና ሕክምናውን የሚያቀሉ ዘመናዊ መሣርያዎች በአገር ውስጥ ባለመኖራቸው የተፈጠረውን ክፍተት ለመሙላት፣ በዋጋ ቪዥን ያሉ መሣርያዎች አጠቃቀም ላይ አገር ውስጥ ላሉ ሐኪሞች በተለያየ ጊዜ ከውጭ በመጡ ሐኪሞች ሥልጠና የተሰጠ ሲሆን፣ ወደፊት ደግሞ ኢትዮጵያውያን የዓይን ሐኪሞች ውጭ ሄደው የሚሠለጥኑበት ሁኔታ ተመቻችቷል፡፡ ከውጭም ሐኪሞች በየጊዜው እየመጡ ሕክምናውን ያደርጋሉ፤ ባለሙያዎችንም ያሠለጥናሉ ተብሏል፡፡