መነሻ ገጽ - ሌሎች አምዶች - ማህበራዊ ጉዳዮች - ዲያስፖራ - ‹‹የአሲምባ ፍቅር››
Buy Valtrex Online Buy Albuterol inhaler Online Buy Prinivil Online
28 July 2013 ተጻፈ በ 

‹‹የአሲምባ ፍቅር››

ኑሮው አሜሪካ ነው፡፡ እንደ በረሃ አጋሮቹ አገሩ መቅረት ሳይችል ኑሮው በአሜሪካ የቀጠለ ቢሆንም እነዚያን የትግል፣ የፍቅርና የመስዋዕትነት ዓመታት ሁሌም አይረሳቸውም፡፡

አሜሪካ እየኖረም ሁሌም ሐሳቡ የነበረው በለጋ ዕድሜው ለኢትዮጵያ ሕዝብ ነፃነትና ዲሞክራሲን ለማጐናፀፍ ከትግል አጋሮቹ ጋር በመሆን ስላሳለፈው አስደሳች፣ አስከፊና እልህ አስጨራሽ ትግል ላይ ነው፡፡ ታሪክ የማይሽረውንና ትውልድ የማይረሳውን የኢትዮጵያ ሕዝባዊ አብዮታዊ ፓርቲ፣ ወታደራዊ ክንፍ የነበረው የኢትዮጵያ ሕዝባዊ አብዮታዊ ሠራዊት (ኢሕአሠ/ኢሕአፓ) የትግል ወቅት በመጽሐፍ ከትቦ ማኖር የሁልጊዜም ፉከራው ነበር፡፡

ለኢትዮጵያ ሕዝብ ነፃነትና ዲሞክራሲ የተደረገውን ሕዝባዊ ትግል ከራሱ፣ ከትግል ጓደኞቹ፣ ከአገሩ፣ ከጋራ ሸንተረሩ ጋር በመተረክ እውነተኛ ታሪኩን ለመጻፍ የነበረውን ጉጉት እውን እንዲያደርግ ምክንያት የሆነው ኢሕአዴግ ከገባ በኋላ ኢትዮጵያን ለሦስተኛ ጊዜ በጐበኘበት ከዛሬ ሦስት ዓመት በፊት የተፈጠረ አጋጣሚ ነበር፡፡

የዛሬ ሦስት ዓመት ኢትዮጵያ ሲመጣ የእሱ እና የሦስት የትግል ጓደኞቹ ታሪክ በጋዜጣ ላይ መውጣቱን ጓደኞቹ አስነበቡት፡፡ ይህ ለዓመታት ታፍኖ የከረመውን የ‹‹እጽፈዋለሁ›› ፉከራ ነፍስ ዘራበት፡፡

ከ1968 ዓ.ም. እስከ 1970 ዓ.ም. ማብቂያ ድረስ የኢሕአሠ አባል ሆኖ ያሳለፈውን ግለ ሕይወት በጓደኞቹ ታሪክና በወቅቱ የፖለቲካ ትኩሳት እያዋዛ ታሪክን ለመከተብ በ2002 ዓ.ም. ብዕሩን አነሳ፡፡ ብዕሩን ባነሳ በሦስተኛው ዓመት 2005 ዓ.ም. ደግሞ የታሪኩ የመጀመርያ ክፍል የሆነው ባለ 446 ገጹ ‹‹የአሲምባ ፍቅር›› መጽሐፍ ለንባብ በቃ፡፡

ባለታሪኩና የመጽሐፉ ፀሐፊ አቶ ካሕሳይ አብርሃ ብስራት በግል ሕይወት ታሪኩ ላይ ተመሥርቶ በትግሉ በነበረበት ወቅት ያገኛቸው ጓዶችና ጓዲቶች ቦታዎችና ሕዝቡ የታሪኩ አካል ናቸው፡፡ ዛሬ በሕይወት ያሉት እንዲሁም በትግል ወቅት የተሰውት ጓዶችም እንዲሁ፡፡

ስለ አቶ ካህሳይ ወላጆች፣ እንዴት በለጋ የወጣትነት ዕድሜው ወደ ኢሕአሠ እንደተቀላቀለ፣ በትግል ወቅት ስላገኛት የመጀመርያ የፍቅር ጓዱ ድላይ እንዲሁም ከሞት አፋፍ አስመልጦ ለዛሬ ሕይወቱ ብርሃን የፈነጠቀለት ገበሬው ይመር ንጉሤ የመጽሐፉ ማዕዘን ናቸው፡፡ የኢሕአሠ/ኢሕአፓ ቁልፍ ወታደራዊ ምሽግ የነበረው የአሲምባ ተራራ የታሪኩ የመሠረት ድንጋይ ነው፡፡

ኢሲምባ ማለት ‹‹ቀይ አምባ›› ማለት ሲሆን የተራራው ከፍታ 3250 ሜትር ነው፡፡ ከአሲምባ ተራራ ወደ ቀይ ባሕር አቅጣጫ የመሬቱ አቀማመጥ እየቀነሰና እያቆለቆለ ሄዶ ከመሬት ወለል በላይ 150 ሜትር ድረስ ዝቅ ይላል፡፡ አሲምባ ከፍተኛ ከመሆኑ የተነሳ ሌሊት ሌሊት በጉም ይሸፈናል፡፡

በተራራው ጫፍ ላይ በጣም ቀዝቃዛና የጠራ ውኃ ያለው ጅረት አለ፡፡ ይህ ወንዝ ወደ ደቡብ አቅጣጫ ይወርድና ከአሲምባ በታች የሚገኘውን የጉንዳጉንዲን ታሪካዊ ገዳም ያለማል፡፡ … የአይጋ ተራራ በደቡብ በኩል ካለው የማእቢኖን ሰንሰለታማ ተራራ በሚገጣጠምበት ቦታ ላይ ትንሽ ሸለቆ ይሠራሉ፡፡ በዚህ ሸለቆ ቀዳዳ በኩል ወደ ኢሮብ መግባት ይቻላል፡፡ የቦታው አቀማመጥ ለሽፍቶች አመቺ ስለሆነ በዚያን ጊዜ ለመንግሥትም የሚያስቸግሩ ሽፍቶች አዲ ኢሮብ ወደሚገኘው የአሲምባ ተራራ ጫካ ነበር የሚገቡት፡፡ (የአሲምባ ፍቅር ገጽ 55)

ፀሐፊው አቶ ካሕሳይ በዘመናዊ ጦር መሣርያ ለታጠቀው ደርግ ፈተና ከሆነበት ተራራ ከመሸጉ፣ ከሠለጠኑ፣ የፖለቲካ አመለካከትና ክህሎት ከቀሰሙ ጓዶችና ጓዲቶች እንዲሁም የተለያየ የፖለቲካ አመለካከት ካላቸው ቡድኖች ጋር ‹‹በአሲምባ ፍቅር›› ያስተዋውቀናል፡፡ ከዚህ ባለፈም በትግል ወቅት ስለነበረ ደግነትና ክፋት፣ ክህደትና እምነት፣ ፍቅርና ጥላቻ፣ ስርቆትና ወንጀል፣ ሕይወትና ሞት እንዲሁም የስደት ሕይወት በስምንት ክፍል የተከተበው ‹‹የአሲምባ ፍቅር›› ያስነብበናል፡፡

በያኔው አጠራር በትግራይ ጠቅላይ ግዛት በአጋሜ አውራጃ በዛላ አንበሳ ወረዳ ጥርቀ በሚባል ሥፍራ የተወለደው አቶ ካሕሳይ በ1960ዎቹ መጨረሻና በሰባዎቹ መጀመርያ ዓመታት ለዲሞክራሲና ለፍትሕ ሲታገሉ የነበሩ ጓዶችን ታሪክ እንደወረደ ተርኮታል፡፡

በትግሉ ወቅት አያሌ ጓዶች ለተበደሉና ፍትሕ ላጡ ወገኖቻቸው ተቆርቁረውና በዓላማቸው ፀንተው ሕይወታቸውን ሰውተዋል፡፡ የትግል ጉዳይ ሆኖ አንዳንዶች በዕጣ ፈንታ ወይም በአጋጣሚ ተርፈው ሰላማዊ ኑሯቸውን ቀጥለዋል፡፡ አቶ ካሕሳይ በሕይወት ተርፈው ዛሬ ላይ በወቅቱ የነበረውን የኢሕአሠ/ኢሕአፓ ትግልና መስዋዕትነት ድክመትና ጥንካሬ በመጽሐፍ ከትበው ካሰፈሩ ሰዎች አንዱ ነው፡፡

አቶ ካሕሳይ በ‹‹አሲምባ ፍቅር›› መጽሐፉ በትግል ወቅት በቀጥታ የተካፈለበትን ሥራውን፣ ያገኛቸውን ታጋዮች ታሪክና በወቅቱ የተፈፀሙ ሆነው ሲነገሩ የሰማቸውንና ለማጣራት የቻለውን እንዲሁም አስፈላጊ ሁነቶችን ለማካተት ጥሯል፡፡ በሠራዊቱ ውስጥና በተለያዩ ቁልፍ የትግል ሒደቶች ላይ ልዩ ቦታ አላቸው ብለው የገመታቸውን ወቅቶችና ሰዎችንም በታሪኩ ጉልህ ስፍራ ሰጥቷቸዋል፡፡

ፀሐፊው ዛሬ ሰላም ከሰፈነ፣ አሲምባ የኢሕአሠ ምሽግነቱም ካከተመ በኋላ በወቅቱ ለፍትሕ፣ ለርትዕና ለዴሞክራሲ ብዙ ጓዶች መስዋዕትነት የከፈሉበትን ሐሳብ የጠነሰሱበትን የአሲምባን ተራራ ከአሜሪካ ቆይታቸው በኋላ ጐብኝተዋል፡፡ በጉብኝታቸው አካባቢው መልማቱን መንገድ መግባቱን፣ ውኃ መገደቡን፣ ትምህርት ቤት መሠራቱን አይተዋል፡፡ እነዚህና ሌሎችም የኢሕአፓ/ኢሕአሠ የሦስት ዓመት የትግል ጊዜያት ከፀሐፊው ሕይወት ጋር እየተጣመረ በ‹‹አሲምባ ፍቅር›› ይተረካል፡፡

መታሰቢያነቱ በገጠርም ሆነ በከተማ ለሕዝብና ለአገር ሲሉ የሕይወት መስዋዕትነት ለከፈሉ የኢሕአፓ/ኢሕአሠ ሰማዕታት ያደረገው የ‹‹አሲምባ ፍቅር›› ቀጣይ ክፍል ሁለት ይኖረዋል፡፡