መነሻ ገጽ - ሌሎች አምዶች - ማህበራዊ ጉዳዮች - ፌርማታ - ‹‹ውበት ሲለካ. . .!››
Buy Valtrex Online Buy Albuterol inhaler Online Buy Prinivil Online
28 August 2013 ተጻፈ በ 

‹‹ውበት ሲለካ. . .!››

የውሻው ጅራት

 በኦዬሻ ቱሽክሎ የተተረከ

በጌታቸው በጣም ይበደሉ የነበሩ አንድ አህያና አንድ ውሻ ጠፍተው ወደ ሌላ ቦታ ሄደው ለመኖር በማሰብ ከቤታቸው ወጥተው ሄዱ፡፡

ከአንድ ለምለም ስፍራ በደረሱም ጊዜ አህያው እስኪጠግብ ስለበላ ማናፋት አማረውና ውሻውን ‹‹ማናፋት እችላለሁ?›› ብሎ ጠየቀው፡፡

ውሻውም ‹‹ተው! ጅብ የሰማ እንደሆን መጥቶ ይበላሃል፤›› ቢለውም አህያው ከጥጋቡ የተነሳ ራሱን መግዛት ተስኖት ሶስት ወይም አራት ጊዜያት አናፋ፡፡

በዚህ ጊዜ ውሻው ‹‹እንግዲያው አንተ ማናፋት ካማረህ እኔ ተደብቄ የሚሆነውን አያለሁ፤›› ብሎ ከአንድ አለት ላይ ወጥቶ ምን እንደሚከሰት መከታተል ጀመረ፡፡ ጅቡም የአህያውን ማናፋት ሰምቶ በመምጣት ገድሎት ሥጋውን ከአለቱ ስር አስቀመጠ፡፡

ትኩሱን ሥጋ ያየውም ውሻ ምራቁን ማዝረክረክ ጀመረ፡፡ በዚህ ጊዜ የውሻው ምራቅ ጠብ ያለበት ጅብ ቀና ብሎ ሲመለከት ውሻውን አየው፡፡ ከዚያም ጅቡ ውሻው ከተደበቀበት ወርዶ የአህያውን ቆዳ እንዲገፍ አዘዘው፡፡

ውሻውም ካለበት ቦታ ወርዶ አህያውን ከገፈፈው በኋላ የአህያውን ልብ ሲያይ መታገስ ስላልቻለና በመጎምዠት አፉን ምራቅ ስለሞላው የአህያውን ልብ ለቀም አድርጎ ዋጠው፡፡ ጅቡም የአህያው ሙሉ አካላት እንዳለ ሊፈትሽ ሲመጣ ልቡን ያጣውና ውሻውን ‹‹ልቡ የታለ?›› ብሎ ሲጠይቀው ውሻውም ‹‹አህያው ልብ የለውም፡፡ ልብማ ቢኖረው ኖሮ እያናፋ አንተን ባልጠራህ ነበር፤›› ብሎ መለሰለት፡፡

በዚህ ጊዜ ውሻው ጅቡ ሊገድለው እንደፈለገ ስለገባው መሮጥ ጀመረ፡፡ ጅቡም ውሻውን እያሳደደው ሲከተለው ውሻው አንድ እሾሃማ አጥር አጠገብ ሲደርስ እሾሁን ጠምዞ ወደ አጥሩ ውስጥ ገባ፡፡ ሰውነቱ በሙሉ ወደ አጥሩ ውስጥ ሲገባ ጅራቱ ብቻ ውጪ ስለቀረ ጅቡ ለቀም አድርጎ ቆረጠው፡፡ እሾሃማው አጥር የውሻው ጌታ ግቢ ነበር፡፡ ጅቡም በኩራት ‹‹ብታመልጠኝም ጅራትህን ቆርጨዋለሁ፤›› አለው፡፡ ውሻው ግን በጅቡ ስቆበት ‹‹ጌታዬ የሚተኛው በቁርበት ላይ በመሆኑ እኔም አጠገቡ ነው የምተኛውና እኛ ውሾች እንደተለመደው በጅራታችን አመድ ስለምናቦን እኔም ጌታዬ ላይ አመድ እንዳላቦንበት ሰሞኑን ጅራቴን ልቆርጥ አቅጄ ስለነበረ ብዙም የጀግንነት ስሜት አይሰማህ፡፡ እኔም ልቆርጠው ነበርና፤›› አለው ይባላል፡፡

-‹‹የኢትዮጵያ ተረቶች ከደቡብ ኦሞ››

**************

ብዙ ቀንዳም አለ

ጥርስ እንጎቻ ሁኖ፣ አብሮ እየበላ፣

ልቡን ሸፍጥ ሞልቶት፣ በቁም የሚያተላ፡፡

ብዙ ቀንዳም አለ

ፍቅርን አንተርሶ

በእሾሀማ እጆቹ፣ አናትን ደባብሶ፣

መርዝን የሚቀባ፣ በማር ወዝ ለውሶ፡፡

ብዙ ቀንዳም አለ

አሸሸ ገዳሜ ዘጭ እምቧ፣ ዘጭ እምቧ፣

እያለ አምቧችሮ፣ ከአፈር የሚያስገባ፡፡

ብዙ ቀንዳም አለ

የሰው ሥጋ ለብሶ፣ የሰይጣን ተምሳሌት፣

ጮቤ የሚረግጥ፣ ደም ያለቀሱ ዕለት!

    28/01/2013

ማስታወሻነቱ፡- በሰው እንጀራ ለምትገቡ ሁሉ!

-አዜብ ዮሴፍ ‹‹የመካን እርግማን›› (2003)

*******************

የሰመመን እግር ኳስ

በእግር ኳስ ፍቅር ልባቸው የተቃጠለው አንድሩና ስቲቭ መንግሥተ ሰማያት የእግር ኳስ ውድድር ስለመኖሩ ዕድል አብዝተው ይወያዩ ነበር፡፡ የእግር ኳስ ውድድር መንግሥተ ሰማያት ውስጥ ካልተካሄደ መንግሥተ ሰማያትን ገነት ለማለት የማይቻል በመሆኑ ቢተማመኑም ስፖርቱ ለመኖሩ እርግጠኛ ስላልነበሩ ከሁለቱ ቀድሞ የሞተ ፈጥኖ በመመለሰ በመንግሥተ ሰማያት የእግር ኳስ ውድድር መኖር ወይም አለመኖሩን ለጓደኛው እንዲያሳውቅ ተስማሙ፡፡ ብዙም ሳይቆዩም አንድሩን አውቶቡስ ገጭቶ ገደለው፡፡ 

በሞተ በማግስቱ ስቲቭ ተኝቶ ሳለ አንድሩን በሰመመን የስፖርት ትጥቅ እንዳጠለቀ አየው፡፡ የእግር ኳስ መጫወቻ ታኬታ ጫማ ማድረጉንም ወዲያውኑ ተገነዘበ፡፡ ‹‹አሃ! የእግር ኳስ ጨዋታ አለ ማለት ነዋ!›› ብሎም አልጋው ጫፍ ላይ ተቀመጠ፡፡ 

‹‹አዎን፤ ሆኖም ቀድሜ ጥሩውን ዜና ልንገርህ ወይስ መጥፎውን?›› በማለት መንፈሱ ጠየቀው፡፡ 

‹‹ኧረ ጥሩውን አስቀድምልኝ›› ስለ ስቲቭ ፈጥኖ፡፡ 

‹‹እንግዲያው፣ እኛ ዘንድ ድንቅ የሆነ የእግር ኳስ ሜዳና ምርጥ ተጫዋቾች አሉ፡፡ መላዕክቱም የእግር ኳስ ውድድር ማየት በጣም ይወዳሉ›› በማለት አብራራለት፡፡ 

‹‹ድንቅ ዜና ነው ያሰማኸኝ፡፡ መጥፎው ዜና ታዲያ ምኑ ነው?››

‹‹መጥፎው ዜናማ የማስታወቂያ መለጠፊያው ሠሌዳ ላይ ለእሑድ ውድድር ከሚሰለፉት ተጫዋቾች ዝርዝር ውስጥ ስምህን ማየቴ ነው፡፡››

-አረፈዓይኔ ሐጐስ ‹‹የስኮትላንዳውያን ቀልዶች›› (2005)

*******************

የክንዴ ቅንጭብ ታሪክ

ስድስት ኪሎ ካምፓስ ነው የደረሰኝ፡፡ ስድስት ኪሎ መመደቤ ለኔ ልዩ ትርጉም አለው፡፡ ስድስት ኪሎ መመደቤን የተለየ ትርጉም የምሰጠው በሦስት ምክንያቶች ነው፡፡ አንደኛ ለቤተሰቤ ስድስተኛ ልጅ ነኝ፡፡ ስድስተኛ ልጅ ሆኜ ስወለድ ዓመተ ምሕረቱ 66 ነበር፡፡ በጣም የሚገርመው የሰውነት ክብደቴ ስድሳ ኪሎ መሆኑን ብናገር ማን ያምናል? ይኼን ከስድስት ቁጥር ጋር ያለኝን ቁርኝት የሰማ ልጅ ‹‹የስድስት ስድሳ ስድስት ነቢይ አንተ ሳትሆን አትቀርም!›› ብሎ ሊያሳቅቀኝ ሞክሯል፡፡ 

ስድስት ኪሎ ካምፓስ ደረስኩ፡፡ ዩኒቨርሲቲው በር ላይ ስደርስ በሩ አናት ላይ የተቀመጠውን የአንበሳ ምስል እያየሁ ማልቀስ ዳዳኝ፡፡ እንደኔ ወደ ዩኒቨርሲቲው በመግባት ላይ የነበረ ልጅ ለእንባ መነሳሳቴን አይቶ ምን እንደሆንኩ ይጠይቀኝ ጀመር፡፡ 

‹‹በሩ ላይ ምስል የቆመለትን አንበሳ ሳይሞት በፊት ታውቀዋለህ እንዴ? ምስሉን እያየህ የምታለቃቅሰው?›› ብሎ ጠየቀኝ፡፡ 

ሳግ ባፈነው ድምፅ ‹‹እዚህ ዩኒቨርሲቲ ለመግባት የከፈልኩት መስዋዕትነትና ያሳለፍኩት አበሳ ትዝ ብሎኝ ነው!›› ስለው ልጁ ጤነኛነቴን ተጠራጠረ መሰል በቆምኩበት ጥሎኝ ሔደ፡፡ 

አንበሳ ሲያይ ያለፈ አበሳውን ለመጀመሪያ ጊዜ ያስታወሰ ሰው እኔ ሳልሆን አልቀርም፡፡ ሰው መቼም የከፈለው መስዋዕትነት እንደሁኔታው ይለያያል፡፡ እኔም አፍንጫዬን በኩራዝ ጭስ ወዳጠቆርኩለት ዩኒቨርሲቲ ስገባ ማልቀስ ይነሰኝ?

ወደ ዩኒቨርሲቲው ቅጥር ዘለቅኩ …

የሚያስፈልገውን የምዝገባ ጣጣ ከጨረስኩ በኋላ ዶርም ተቀበልኩ፡፡ የደረሰኝ ዶርም ቁጥር 13 ነው፡፡ እኔ ምንም ባይመስለኝም ዶርም ቁጥር 13 አብሮኝ የተመደበ አንድ የአዲሳባ ልጅ ግን ሲያለቃቅስ ነበር፡፡ ልጁ ዶርም ቁጥር 13 መመደቡን እንደ ጥሩ ገድ ያየው አልመሰለኝም፡፡ (እንደሚታወቀው 13 ቁጥር በፈረንጆች ገደ ቢስ ተብሎ ይታመንበታል፡፡) 

‹‹እዚህ ዶርም ተመድቤ መባረሬ አይቀርም!›› እያለ ሲነጫነጭ ሳየው ገረመኝ፡፡ 13 ቁጥር ሟርተኛ ቁጥር መሆኑን እየነገረ ሲበጠብጠን ዋለ፡፡ የሰው ዕጣ ፈንታና ቁጥርን ምን እንደሚያገናኘው እንጃ! በአዲስ አበባ ያሉ ሎተሪ አዟሪዎች እንደነገሩኝ በቅድሚያ የሚጨርሱት ‹‹19››፣ ‹‹12›› ቁጥር እና ‹‹21›› ቁጥር መነሻና መድረሻው የሆኑ የሎተሪ ትኬቶችን ነው፡፡ ይኼ ለምን ይሆናል ብዬ አንድ የሎተሪ አዟሪን ጠይቄው፤ ዝነኛ ታቦቶች የሚውሉበት ቀን በመሆኑ እንደሆነ ገልጾልኝ በወቅቱ አስገርሞኛል፡፡ ብሔራዊ ሎተሪን ብሆን ሎተሪውን ሁሉ በእነዚህ ቁጥሮች ስብጥር ነበር የምሞላው እያልኩ አስባለሁ፡፡

ሌላኛው የዶርም ተጋሪዬ ግን ዶርም ቁጥር 13 መመደቡ ምንም ሳይመስለው ከአልጋው ላይ ተጋድሞ መጽሐፍ ሲያነብ ሳየው ትንሽ ተረጋጋሁ፡፡ ወዲያውም ጠጋ አልኩና ምን መጽሐፍ እንደሚያነብ ጠየቅኩት፡፡

‹‹የብላቴን ጌታ ወልደ ጊዮርጊስ ከሥራ በኋላ የተሰኘ የእንቆቅልሽ መጽሐፍ ነው የማነበው!›› አለኝ፡፡ 

‹‹እንቆቅልሽ?›› አልኩ በመገረም እና ጆሮዬን በመጠራጠር፡፡ 

‹‹አዎ እንቆቅልሽ፡፡ አየህ በእንቆቅልሾች ውስጥ የቋንቋ እና የሕይወት ምስጢራት ተቀምጠዋል፡፡ ለኔ ደግሞ ከልጅነቴ ጀምሮ እንቆቅልሽ መጫወት ሆቢዬ ነው፡፡ መቼም ሆቢዬ ውኃ መዋኘት፣ ፊልም ማየት በሚባልበት ሀገር እንደዚህ ማለቴ ሳይገርምህ አልቀረም?›› አለኝ፡፡ (ከያዘው መጽሐፍ ላይ አንብቦ እንቆቅልሽ የሚለው ቃል እንቁላል ያለህ ወይም እንቁላል ያለሽ ከሚለው ሐረግ የመጣ መሆኑንም ነግሮኛል፡፡)

በርግጥም ገረመኝ፡፡ እንቆቅልሽ መጫወት ሆቢው የሆነ ሰው ሳገኝ በሕይወቴ የመጀመሪያዬ ነው፡፡ የመጨረሻዬ እንደሚሆንም እገምታለሁ፡፡ በእርግጥ ልጁ ሐቀኛ ይመስላል፡፡ ‹‹መርሐቤቴ›› ተወልዶ ‹‹የበረዶ ሸርተቴ›› ሆቢዬ ነው ከሚል ዘላባጅ ይሻላል፡፡ 

*************

ኬንያውያኑ አንድ ሚስት ለማግባት ተፈራረሙ

አንዲቷን ያፈቀሩ ሁለት ኬንያውያን ሁለቱም ባል ሆነው ከእርሷ ጋር በስምምነት ለመኖር ተፈራረሙ፡፡

ከአራት ዓመት ላላነሰ ጊዜ ከሁለቱም ጋር ግንኙነት እንደነበራት የተነገረላት ስሟ ያልተጠቀሰ ኬንያዊት ሁለቱንም በየተራ እያስተናገደች ለመኖርም ተስማምታለች፡፡ 

ሁለቱ ወንዶች በሚስታቸው አማካይነት ላይጣሉ እንዲሁም በየተራ ከእሷ ጋር ለመኖር በሕጋዊ መንገድ ተፈራርመዋል፡፡ 

የመንትዮች እናት እንደሆነች የተነገረላት ሚስት የቀድሞ ባሏ ሞቷል፡፡ አሁን ካገባቻቸው ሁለት ወንዶች አንዱን መምረጥ ስላቃታትም ከሁለቱም ጋር በሰላም ለመኖር ተስማምታለች፡፡ የኬንያ ኮሚዩኒቲ ፖሊሲን ጠቅሶ ዴይሊ ኔሽን እንደዘገበው፣ ሁለቱ ወንዶች ከሴቷ፤ ሴቷም ከወንዶቹ ተለያይተው መኖር እንደማይችሉ ተናግረዋል፡፡ 

ያደረጉት የፊርማ ስምምነት በቤት ውስጥ የሚኖራቸውን ፈረቃ፣ መከባበር እንዲሁም ሴቲቷ ስትወልድ የሚወለዱትን ልጆች በእኩል ማሳደግን ይጨምራል፡፡