መነሻ ገጽ - ሌሎች አምዶች - ማህበራዊ ጉዳዮች - ፌርማታ - ቻይናውያኑ በአሸንዳ
Buy Valtrex Online Buy Albuterol inhaler Online Buy Prinivil Online
04 September 2013 ተጻፈ በ 

ቻይናውያኑ በአሸንዳ

ከነሐሴ 15-21/2005 ዓ.ም. በተከበረው የአሸንዳ በዓል ቻይናውያን ቆነጃጅት ከመገኘታቸውም በላይ የከተማዋን ልጃገረዶች ተቀላቅለው በመቐለ ከተማ ዐውራ ጎዳና ላይ የወጡት የአሸንዳን ባህላዊ አልባሳት ተላብሰው ነበር:: (ፎቶ በጨለ መቐለ)

ቀታሊዬ እሱ ነው

በልቡ መራዕይ፣ የኔን ልብ ሐትቶ፣

ውበትን እንደ ሰ’ል፣ ከውስጥ ውስጤ አቃብቶ፡፡

በሃሳብ ስባዝቅ፣ ወኔዬ ሲላሽቅ፣

ትዝታ አስደምሞኝ፣ እንባዬ ሲል ቡልቅ፡፡

በአራት መንታ ሲወርድ፣ ሳግ እንደ ሙዚቃ፤

ከውስጥ እያጀበው፣

እሱ ነው ቀታሊ…

አይቶኝ እንዳላየ፣ ረግጦኝ ያለፈው፡፡

ብታገኙኝ እንኳን፣ ከመሬት ወድቄ፣

ሥጋዬ ከአጥንቴ፣ ተላቆ ደቅቄ፡፡

እሱ እንደሁ አእምሩ፣ ሌላ አትወንጅሉ፣

ቀታሊዬ እንደሆን፣ ሰዎች ልብ በሉ፡፡

3/7/93

መፍቻ      ቀተለ በግእዙ ገደለ 

     ሐተተ በግእዙ አብራራ

     መራዕይ በግእዙ መነጽር

     አእመረ በግእዙ አወቀ ማለት ነው፡፡

-አዜብ ዮሴፍ “የመካን እርግማን” (2003)

***********

 

 

እንካስላንቲያ

በፊደል! ምን አለህ በፊደል?

በዕውቀት ኃያል በትር ድንቁርናን ግደል፡፡

 

በቅመራ!ምን አለህ በቅመራ?

ማለቂያ የለውም የትምህርት አዝመራ፡፡

 

በያንሳል!ምን አለህ በያንሳል?

ዕውቀት ሲመነምን ዕድገት ይኮስሳል፡፡

 

በልቆ!ምን አለህ በልቆ? 

የሳይንስ ባሕር አያልቅም ተጠልቆ፡፡

 

በቅርስ! ምን አለህ በቅርስ?  

- ኃይለመለኮት መዋዕል “እንካስላንቲያ” (2005) 

*****************

የ50 ዓመቱ “ሕልም አለኝ”

እኤአ በ1963 ማርቲን ሉተር ኪንግ የመራውና ስድስት ዋና የሚባሉ የሰብአዊ መብት ተከራካሪ ድርጅቶች የተሳተፉበት ሰልፍ በዋሽንግተን ዲ.ሲ ተካሂዶ ነበር፡፡

የሰልፉ ዓላማ የፌዴራሉ መንግሥት በደቡባዊ አሜሪካ የሚገኙ የሰብአዊ መብት ታጋዮችንና ጥቁሮችን መብት ለመጠበቅ የታየበትን ድክመት መተቸትና ጉዳዩ ትኩረት እንዲሰጠው ማድረግ ነበር፡፡ ከፕሬዚዳንት ኬኔዲ ጽሕፈት ቤት ሰልፍ እንዳይካሄድ ግፊት ቢደረግም፣ የነሐሴ 28 ቀን 1963 ዓ.ም. ሰልፉ ግን ሊደረግ በቅቷል፡፡

እንደ ማልኮልም ኤክስ ያሉ፣ ጥቁሮች በዓመጽ መታገል አለባቸው ብለው የሚያምኑ አፍቃሪ አሜሪካውያንን ጨምሮ ብዙዎች ሰልፉ “ተራ ትርዒት” እንደሚሆን ቢተነብዩም ውጤቱ ግን የተለየ ነበር፡፡ በሰልፉ ላይ ከሩብ ሚሊዮን በላይ የተለያየ የቆዳ ቀለም እና ዘር ያላቸው ሰዎች የተገኙ ሲሆን በወቅቱ ይህ ቁጥር በዋሽንግተን ታሪክ ከታዩ ሰልፎች ሁሉ ከፍተኛው ነበር፡፡

በሰልፉ ማብቂያ ላይ ማርቲን ሉተር ኪንግ በስፋት የሚታወቅበትንና “ሕልም አለኝ” (I Have A Dream) ያለበትን ንግግሩን አድርጓል፡፡ ኪንግ የዚህን ንግግሩን አብዛኛውን ክፍል ያደረገው ወረቀት ላይ ካሰፈረው ውጪ ነበር፡፡ ከሁሉም ተናጋሪዎች መጨረሻ ወደ መድረኩ የወጣው ወጣት ያደረገው ንግግር ከፍራንክሊ ዴላኖ ሩዝቬልት እና የአብርሃም ሊንከን የጌቲስበርግ ንግግር ጋር በአሜሪካ ታሪክ ከታዩ ሦስት ታላላቅ ንግግሮች አንዱ ሆኖ ተመዝግቧል፡፡ የኪንግ ባለቤት ኮሬታ ስኮት ኪንግ ይህንን ንግግር ያደረገበትን ሰዓት ስታስታውስ “ለአፍታ ያህል መንግሥተ ሰማይ የታየን ያህል ተሰምቶን ነበር” ብላለች፡፡ እውነትም ብዙዎች በኪንግ ሕልም ውስጥ ተስፋን ማየት ችለው ነበር፡፡ 

ወዳጆቼ ሆይ፣ እላችኋለሁ፤ ምንም እንኳ ዛሬም ሆነ ነገ የምንጋፈጣቸው ቢኖሩም አሁንም ሕልም አለኝ፡፡

ሕልም አለኝ - አንድ ቀን የቀድሞ የባሪያ አሳዳሪዎችና የቀድሞ ባሪያዎች ልጆች  በወንድማማችነት ጠረን ጴዛ ዙሪያ በአንድነት ይቀመጣሉ፡፡

ሕልም አለኝ - አንድ ቀን በጭቆና ሙቀት የተጠመቀችው የሚሲሲፒ ክልል እንኳ ወደ ነፃነት ፍትሕ ምንጭነት ትለወጣለች፡፡

ሕልም አለኝ - አንድ ቀን አራቱ ትንንሽ ልጆቼ በቆዳቸው ቀለም ሳይሆን በባሕሪያቸው ይዘት የሚዳኙበት አገር ውስጥ ይኖራሉ፡፡

ሕልም አለኝ - አንድ ቀን ሸለቆው ሁሉ ከፍ ይላል፣ ተራራውና ኮረብታውም ሁሉ ዝቅ ይላል፣ ጠማማውም ይቃናል፣ ሥርጓጉጡም ሜዳ ይሆናል፡፡…

በዚህ እምነት ከተስፋ መቁረጥ ተራራ የተሰፋን ዕለት ፈልፍለን ማውጣት እንችላለን፡፡ ….

-አዲስ ተስፋ “ተምሳሌቶቹ” (2004) 

************

 

ተፈጥሮ ድል መንሻ

ቡናው ተለቅሞ፤ ተፈልፍሎ፤ ተሽጦ፤ ተጭኖ ካለቀ በሁዋላ ሱጴ ቦሮ ባይመታትም ለወትሮ አንበጣ እንደዋለበት ማሳ ጭር ትላለች፡፡ የተሸመጠጠው የቡና ዛፍ የተጋጠ አጥንት መስሎ ቆሞ ሲቀር - አቧራው ሲነሳ - ኑሮ ትሰክንና ሱጴ ቦሮ ማዛጋት ፥ ማንቀላፋት ትጀምር ነበር፡፡ ድርቁ የባሰ መልክ ሰጥቶአት የሚያዛጋ ባዶ መቃብር አስመስሎአታል፡፡

ከስር መሬቱ እንደረመጥ ያቃጥላታል፡፡ ከላይ የአየሩ ወበቅ እንደ እሳት ላንቃ ይጋረፋል፡፡ ሳር ቅጠሉ ደርቋል፡፡ ዛፎቹ ከሰል መስለዋል፡፡ ወፎቹ ተሰደዋል፡፡ ጐዳናቸው አንድ ሁለት ተብሎ የሚቆጠር በሞትና በሕይወት መካከል የሚንገዳገዱ፤ ጣእረ ሞት የሚመስሉ የቤት እንስሳት፤ መጠለያና መኖ አጥተው በየሜዳው በቁም ያንቀላፋሉ፡፡ እረኞቻቸውም እንደእነርሱ አጥንታቸው ወጥቶ፤ ፊታቸው ገርጥቶ፤ ሆዳቸው እንደከበሮ ተነፍቶ፤ ዓይናቸው ጐድጉዶ፤ እግሮቻቸው ቀጥኖ - የያዙትን ዘንግ መስለው - እንደሌላው ጊዜ በዋሽንት አይጫወቱም -  ከወንዝ ወዲህና ወዲያ ማዶ ሆነው የእረኛ ዘፈን አይቀባበሉም፡፡

እንደ ወንዞቹ ደርቀው፤ እንደ ከብቶቹ ከስተው በዝምታ የተፈጥሮን ልግስና ይጠባበቃሉ - በትእግስት፡፡ በተስፋ የእግዜሩን ምሕረትና ቸርነት ይጠባበቃሉ - ሌላ የሚያደርስላቸው ኃይል አያውቁምና! ጉልበት ያለው ጐረምሳ እንደ ወፎቹ በጊዜ አገር ለቅቆ ወጥቷል - የዕለት ጉርስ ፍለጋ፡፡ አዝማሪዎች መሲንቆቻቸውን በባሕር እጣን ማሟሸትና መቃኘት ከተው ቆይተዋል፡፡ ዘፈን የለም፡፡ ብር የለም፡፡ ጠጅ የለም፡፡

ከጠላ ቤቱ ደጅ የቆርቆሮ ጣሳ አይታይም፡፡ ከጠጅ ቤቱ ደጅ አምቡላ አይሸትም፡፡ ንቦች አይታዩም፡፡ እነርሱም ከአገር ወጥተዋል፡፡ በየዛፉ ላይ የተሰቀሉት የማር ቀፎዎች ጭር ብለዋል፡፡ በዕድሜ የገፉ ገበሬዎች በየደጃቸው እግርና እጃቸውን አጣምረው ከተፈጥሮ ጋር ያሸልባሉ - ያንቀላፋሉ - ያዛጋሉ፡፡ የሞት ፍርዱን የሚጠባበቅ እስረኛ ይመስላሉ፡፡ ተፈጥሮ ፊቷን አዙራባቸዋለች፡፡ የእግዜር  ቸርነት ብቻ ነበር ተስፋቸው፡፡ ሁሉም ወደ ሰማይ አንጋጠው የእግዜሩን ቸርነት ይጠባበቃሉ፡፡

ሀዲስ ብቻ ነበር ፊቱን ወደ ምድሪቷ አዙሮ የሚያስበው - ተፈጥሮ የሰው ልጅ ተገዢ እንጂ የበላይ አይደለችም - ሰው ተፈጥሮን ድል ማድረግ አለበት - ተፈጥሮ ድል የምትሆንበት መሳሪያ እውቀት ነው - የእውቀት ምንጩ ትምህርት ቤት ነው - እጅ- የሰው  እጅ- ድል የማይነሳው ምን ነገር አለ? ተፈጥሮ ራሷ ለጠንካራ እጅ ምስጢሯን ትገልጣለች፡፡ ተፈጥሮ የሰውን ልጅ እንዲታገል እንጂ እንድትገዛው አልነበረም የተፈጠረችው - ግን ምስጢሩዋን ለማወቅ የሰው ልጅ ጥበብ ያስፈልገዋል፡፡ ምስጢሩዋን እንደነፈገችው ነው፡፡ ተፈጥሮ የእግዜርን ቦታ በመውሰድ በሰው ዘንድ ልትመለክ ትፈልጋለች፡፡

ተመልካለችም - ግዙፍነትዋ - ምስጢሩዋ - በሰው ያላት ኃይል፡፡ ተፈጥሮ የምትመካው በሰው ልጅ ድንቁርና ነው - ከድንቁርና ሌላ መሳሪያ የላትም፡፡ ሀዲስ የተፈጥሮን ንፉግነትና ወላዋይነት ድል ለማድረግ አስቀድሞ በወሰደው እርምጃ መሠረት ባስቆፈራቸው ሦስት የውኃ ጉድጓዶች ብዙ ሰዎች ሲጠቀሙ በማየቱ ቢደሰትም፤ ብዙ የውኃ ጉድጓዶ በየቦታው ቢቆፈሩ፤ የእልቄ ወንዝ ቢገደብ - የገባ ወንዝ ለኤሌክትሪክ ኃይል መስጫ እንዲውል ቢደረግ፤ ተፈጥሮን በመግራት የሰው ልጅ ባርያ ለማድረግ የሚቻል መሆኑን ቢያጤንም፤ ተፈጥሮን ድል መንሳት የመጀመርያ እርምጃ  ትምህርት ቤቶችን ማስፋፋት አስፈላጊ እንደሆነ በበለጠ ተገነዘበ፡፡ አዲሱ ትምህርት ቤት ሊሰጥ  የሚችለው ጥቅም በይበልጥ በአእምሮው ውስጥ ጉልህ ሆኖ ታየው፡፡

እጆቹ  ከመጠን በላይ ይንቀጠቀጡ ጀመር፡፡ የትምህርት ቤቱ ሥራ ተፈጽሞ ከሥራ ላይ የሚልበት ቀን ናፈቀው - አጓጓው፡፡ ዓይኖቹ እንባ አቀረሩ፡፡ ተፈጥሮ እንደ እንቅፋት ከፊቱ ላይ መጥታ በመደንቀሯ ረገማት፡፡ እንደ ሸርሙጣ ለኃይለኛው ብቻ የምታደላ በመሆኗ ጠላት፡፡ ተፈጥሮን ድል ለማድረግ የእጅ ኃይል - የሰለጠነ እጅ የሚሠራው ተአምር - ብቻ እንደሆነ በይበልጥ አመነ፡፡ ኢትዮጵያ በምህላ ወደሰማይ የዘረጋቻቸውን እጆች ወደ ምድሪቱ እንድትመልስ ተመኘ፡፡ የጀመረው የእጅ ጉዞ በትምህርት ቤቱ ሥራ ብቻ ከአፎቱ ተመልሶ እንደማይዝግ አመነ፡፡ አሳቡ አንሰራራ…

-በዓሉ ግርማ “የህሊና ደወል” (2005) 

*******************

የአውሮፓ ወንዶች በ110 ዓመታት 11 ሴንቲ ሜትር ኡደት

ኤ ኤፍ ፒ እንደ አውሮፓ አቆጣጠር በሴፕቴምበር ሁለት, 2013 ያወጣው መረጃ በ1970 ዎቹ እና በ1980ዎቹ መሀከል ባሉት ዓመታት አውሮፓ ወንዶች 11 ሴንቲ ሜትር መጨረሻውን ገለጹ፡፡  

ጥናቱ በቀጥታ ያተኮረው እድሜያቸው እስከ 21 በደረሰ ወንድ አውሮፓውያን  ላይ ሲሆን ይህ መረጃም ወታደራዊና የሕክምና መዝገቦችን ያጣቀሰ ነው፡፡

በደቡብ አውሮፓ ነዋሪ የሆኑት ወንዶች መጀመሪያውና በሁለተኛው የዓለም ጦርነቶች መሀከል ከፍተኛ የቁመት እድገት አሳይተዋል፡፡ በአንጻሩ ደግሞ በሰሜን አውሮፓ ባሉ ወንዶች ላይ እድገቱ እየጨመረ የመጣው ከሁለተዓው የዓለም ጦርነት በኋላ ነው፡፡

የአውስትራሊያ ናሽናል ዩኒቨርስቲ እና የአስ የኢስ ኤስ ኤክስ ዩኒቨርስቲ ኢኮኖሚስት ቲምቲ ሀተን ይህን ለውጥ “ተአምራዊ” ብለውታል፡፡

የቁመት ለውጡን ከበሽታ ነጻ እየሆነ ከመጣው ዓለም፣ ከትምህርትና፣ ከገቢ መጠን መጨመር እንዲሁም ያነሰ የቤተሰብ ቁጥር ካለው ጥቅም ጋርም አጣቅሰውታል፡፡

በተጨማሪም በኦክስፎድ ዩኒቨርሲቲ ፕሬስ ላይ የታተመው የኦክስፎርድ ኢኮኖሚክ ፔፐር እንዳወጣው መረጃ ከሆነ በ1980 ጥናት ከተካሄደባቸው 15 አገራት መካከል የጀርመን ወንዶች እጅግ በጣም ረጃጅም ሆነው ተገኝተዋል፡፡ ቁመታቸውም ወደ 1.83 ሜትር ማለትም ስድስት ጫማ ደርሷል፡፡ በተቃኒው የፖቹጋል ወንዶች በጣም አጫጭሮች የነበሩ ሲሆን ቁመታቸው 1.73 ሜትር ወይንም አምስት ጫማ ከስምንት ኢንች ይደርሳል፡፡

ሌሎች በርካታ ተያያዥ ጥናቶች እንደሚጠቁሙት ከሆነ የአውሮፓ ወንዶች በቁመት መጨመር ረገድ አፍሪካውያንን፣ ላቲን አሜካውያንን እንዱሁም ሰሜን እስያውያንን አጥፈዋል፡፡ ይህ ንጽጽር የሚጠቁመው መረጃ የከተማ መስፋፋት አያይዞም የጤና ዘብ መድኃኒቶችና ተቋማት በተስፋፉበት (የተስፋፉበትን) ጊዜ ነው፡፡