መነሻ ገጽ - ሌሎች አምዶች - ማህበራዊ ጉዳዮች - ማህበራዊ - የእጅ ሙያን ያስከበረ ስኬት
Buy Valtrex Online Buy Albuterol inhaler Online Buy Prinivil Online
10 April 2013 ተጻፈ በ 

የእጅ ሙያን ያስከበረ ስኬት

በማለዳ ፍንትው ብላ በወጣችው ጮራ የታጀበው የወጣቶቹ ሽርጉድ በአካባቢው አንዳች የተለየ መርሐ ግብር ለማሰናዳት ታስቦ እንደሆነ የሚያስገነዝብ ነው፡፡

በትንሿ ከተማ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት አጥር ጥግ በተከፈተላቸው ኢንተርኔት ካፌ አማካይነት በአካባቢው መሰባሰብና ስለ ሥራዎቻቸው መመካከሩን ልማድ ያደረጉት የአካባቢው ወጣቶች ዛሬም የእጅ ሥራዎቻቸውን በይፋ ለሕዝብ ለማቅረብና ገበያውን ለመሳብ ሲሉ ይህንን የመንገድ ዳር አድምቀውታል፡፡ በየሠለጠኑበት የእጅ ሙያ ያዘጋጇቸውን ቁሳቁሶች በወግ በወጉ በመደርደር፣ በማሰማመርና ዋጋ በመለጠፍ ጭምር የመርሐ ግብሩን በይፋ መከፈት ለሚጠባበቀው እንግዳ የዓይን ማረፊያ እንቅስቃሴያቸውን እያጧጧፉት ነው፡፡

ከአዲስ አበባ 156 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በምትገኘው የጋርባ ጉራቻ ወረዳ ላለፉት ጥቂት ዓመታት በወጣቶች የሙያ ሥልጠና ዘርፉ ላይ ትኩረቱን አድርጎ የሚንቀሳቀሰው የኮርያ ዓለም አቀፍ በጎ ፈቃደኞች ማኅበር (Korea International Volunteers Organization) በአካባቢው ያለውን የወጣቶችን ችግር ከመቅረፉ አንፃርና ወጣቶቹ በጥቃቅንና አነስተኛ የገቢ ማስገኛ ሥራዎች ተሠማርተው ሥራ ፈጣሪ የሚሆኑበትን ዕድል እያመቻቸ እንደሚገኝ የድርጅቱ የኢትዮጵያ ሥራ አስኪያጅ አቶ ሚኪያስ ግርማ ይገልፃሉ፡፡ ድርጅቱ በአካባቢው የከፈተው የሙያ ማሠልጠኛ ማዕከል በ10+1 እና በ10+2 ትምህርታቸውን መከታተልና ወደ ዩኒቨርሲቲዎች ማምራት ያልቻሉትን ወጣቶች በእንጨት ሥራ፣ በብረታ ብረት፣ በኮምፒዩተርና በልብስ ስፌት ሙያዎች እያሠለጠነ ይገኛል፡፡ በመጀመርያው ዙር ያሠለጠናቸውን 76 ተማሪዎችም በዚህ ዕለት ከሠሯቸው ሥራዎች ጋር ለከተማው ኅብረተሰብ ማስተዋወቁ አስፈላጊ ሆኖ በመገኘቱ ይህ መርሐ ግብር መሰናዳቱን አቶ ሚኪያስ ይገልጻሉ፡፡

ተፈራ ተካልኝ በብረት ሥራ የሠለጠነ ባለሙያና የወጣቶቹ ተወካይ ነው፡፡ ከአንድ ዓመት በፊት የነበረበትን ተስፋ አስቆራጭ ሕይወት በማስታወስ ዛሬ የሚሰማውን ደስታ ለመግለጽ ይሞክራል፡፡ “እዚህ አካባቢ ትምህርት ከተባለ መምህርነት አልያም የመንግሥት ሠራተኛ ለመሆን እንጂ እንዲህ ዓይነቱን የሙያ ሥልጠና ለመማር ከሆነ ትርጉም አልነበረውም፤” ሲል ዛሬ ማዕከሉ በቀሰመው ዕውቀት በእጆቹ ጥበብ የሠራቸውን ሥራዎች እየጠቆመ የትምህርትን ቁም ነገር ያብራራል፡፡ እሱም ሆነ መሰሎቹ ከቤተሰቦቻቸው የሚደርስባቸውን የሥነ ልቦና ጫና ለመቋቋም ሲሉ ወደ ሙያ ትምህርት ቤቱ እንኳ ሲሄዱ የመማርያ ደብተሮቻቸውን ደብቀውና ሰው አየኝ አላየኝ በሚል ሁኔታ ተምረው ይመለሱ እንደነበርና ዛሬ ላይ ግን የእጆቻቸውን ጥበብ ይዘው በሰው ፊት ሲቀርቡ በፋጹም ልበ ሙሉነት መሆኑንም ይገልጻል፡፡

ሙለታ ረጋሣና ረጋሣ ኢቲቻ የ23 እና የ24 ዓመት ወጣቶች ናቸው፡፡ በዚህ “ተስፋችን በእጃችን” በተሰኘው የተማሪዎች ምረቃና የሥራ ማስተዋወቂያ ፕሮግራም ላይ ሲታደሙ አንድም እንደ ተተኪ ተማሪነታቸው የተመራቂዎችን ሥነ ልቦና በመገንዘብ ከቤተሰብና ከአካባቢው ማኅበረሰብ የሚመጣውን ጫና ለመቋቋም እንደሚረዳቸው በማሰብ ሲሆን፣ በሌላ በኩል ደግሞ ከእነሱ በላይ ያሉ ተማሪዎች የሠሯቸውን ሥራዎች በማየት እነሱ ምን የተለየ ነገር ሊሠሩ እንደሚችሉ ለመገመትም ነው፡፡ ሁለቱም በልብስ ስፌት ሙያ የሚሠለጥኑ እንደመሆናቸው ዓይኖቻቸው በተማሪዎቹ ተሠርተው ለዕይታ በበቁት ናሙናዎች ላይ ነበር፡፡ በአገሪቱ እያደገ የመጣውን የፋሽን ኢንዱስትሪ በአቅማቸው ልክ በመገንዘብ ነበር ይህንን ሙያ ለመማር መወሰናቸውን ለሪፖርተር የገለጹት፡፡ “ከዚህ በመነሳት ነገ በትላልቅ የልብስ ፋብሪካዎችና የዲዛይን ተቋማት መሥራት እንደምንችል እንገምታለን፤” ሲሉ የጋራ ተስፋቸውን በጋራ ይገልጻሉ፡፡

ወይዘሪት ሕይወት ዳዊት ላለፉት ሁለት ዓመታት በኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ (አይቲ) የትምህርት ዘርፍ ተማሪዎችን እያሠለጠነች ነው፡፡ የድርጅቱ በአካባቢው መንቀሳቀስ እሷን ጨምሮ ለሌሎችም ወጣቶች የሥራ ዕድል እንደፈጠረላቸው በመግለጽ ለሠልጣኝ ተማሪዎችም ብሩህ ተስፋ መፈንጠቅ እንደቻለ ትናገራለች፡፡ “እነዚህ ተማሪዎች ወደ ማሠልጠኛ ተቋሙ ከመግባታቸው በፊት ሞራላቸው የወደቀና በዚህ መልኩ ተምሮ ውጤታማ መሆን እንደሚቻል ለማመን የከበዳቸው ነበር፤” የምትለው መምህርት፣ ከትምህርቱ በኋላ ግን ተስፋቸው ለምልሞና ከወዲሁም በአንዳንድ መሥሪያ ቤቶች ውስጥ ተቀጥሮ የመሥራት ዕድሉን ማግኘታቸው እጅግ የሚያስደስት አጋጣሚ እንደሆነም ጨምራ ገልጻለች፡፡ “በአካባቢው ያለውን የወጣቶችን ችግር በቅርበት እንደመገንዘቤ በሌላ ተቋማት ተቀጥሮ ከመሥራት የማውቃትን ጥቂት ነገር ላስተላልፍላቸው ብዬ እየደከምኩ ብሆንም አሁን በማየው ነገር ግን በጣም እረካለሁ፤” ስትልም አስተያየቷን ትቋጫለች፡፡

የማሠልጠኛ ተቋሙ ዳይሬክተር አቶ ዓለማየሁ ኡርጌ ትምህርት ቤቱ ለአካባቢው ወጣቶች መልካም ዕድል የፈጠረ መሆኑንና ከወጣት ተማሪዎችም ባሻገር በአካባቢው ለሚገኙ ከአንድ ሺሕ በላይ የገጠር ነዋሪዎች በፀሐይ ኃይል የሚሠራ የመብራት አገልግሎት መገኘቱም ልዩ ዕድል መሆኑን ይናገራሉ፡፡ በአራት የማሠልጠኛ ክፍሎች እስከ 100 የሚደርሱ ተማሪዎችን በስድስት ወርና በአንድ ዓመት የሥልጠና ጊዜ የሚቀበለው ተቋም በአቅም ውስንነት ምክንያት እንጂ ከዚህም በላይ ቁጥር ሊቀበል የሚችልበት ዕድል መኖሩን ጠቁመው፣ በሒደት ድርጅቱ ከሚኖረው የማስፋፊያና የማጎልበቻ ዕቅድ ጋር በተቀናጀ መልኩ የሠልጣኙን ቁጥር ማሳደግና የትምህርት ክፍሎቹንም ቁጥር በተወሰነ ደረጃ ማብዛት እንደሚቻል ያመለክታሉ፡፡

አቶ ፈቃዱ ቱሉ የዞኑ የቴክኒክና ሙያ ተቋማት ተጠሪ በበኩላቸው በወረዳውና በዞኑ ያለው የወጣቶች ችግር ዘርፈ ብዙ መሆኑን ጠቅሰው መንግሥታዊ ያልሆኑ ተቋማት የራሳቸው ሚና እንደሚኖራቸው ይገልጻሉ፡፡ በተለይ በአካባቢው ስለ ሙያና ቴክኒክ ትምህርት (ሥልጠና) ያለው የተንሸዋረረ አመለካከት በተማሪዎች ሥነ ልቦና ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ የሚፈጥር መሆኑን ጠቅሰው፣ በጎ አድራጊዎች ከሥልጠናው ጎን ለጎን የግንዛቤ ማስጨበጫ ፕሮግራሞችንም ሊያዘጋጁ እንደሚገባ ይጠቁማሉ፡፡ በዞኑ በኩል ወደ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት የገቡና በቀለም ትምህርቶች እየሠለጠኑ የሚገኙ ተማሪዎች ልምዳቸውን ለሙያ ተማሪዎች እንዲያካፍሉና የትምህርትን አጠቃላይ ቁም ነገር በቀለሙም ሆነ በሙያው ውስጥ በተግባር በመገንዘብ የበታችነት ስሜቱ እንዳያይልና የአገርን ሁለንተናዊ ችግር ለመፍታት ሁሉም የራሱ ድርሻ እንደሚኖረው ለመማማር የሚያስችል እንቅስቃሴ መኖሩንም ይገልጻሉ፡፡

“አሁንማ በኩራት እኖራለሁ ምንም የሚያስጨንቀኝ ነገር የለም፤” የሚለው ተፈራ ተስፋውን በእጆቹ እንደጨበጠ ሲናገር የደስታ ሲቃ እየተናነቀው ነው፡፡ ትናንት አንገቱን ደፍቶና ተደብቆ ይቀስመው የነበረው የእጅ ሙያ ዛሬ ለዓይኑ ሞገስ የሆኑ በሮች፣ መስኮቶችን ሌሎችንም የብረት ውጤቶችን በማየት አንገቱን ቀና ያደርጋል፡፡ “ትምህርት ሊባል አይችልም” ሲሉት የነበሩትን ቤተሰቦቹንና የአካባቢውን ነዋሪዎች “ትምህርት ማለት የቀሰሙትን በተግባር ላይ ማዋል ነው፤” በሚል ምላሽ የተሳሳተ አመለካከታቸውን ለማቃናት ዕድል ማግኘቱንም ይገልጻል፡፡

ከተለያዩ የእንጨትና የብረት ውጤቶች በተጨማሪ ከትንሿ የመኪና ጎማ ማቆምያ (ታኮ) ጀምሮ እስከ ትልልቁ አልጋና ቁምሣጥን ድረስ በሥልጠናው የፈበረኩት ወጣቶች የገበያው ሁኔታ እንደሚያሳስባቸውና ለመሥሪያና ለንግድ የሚሆን ቦታንም ማግኘት ቀሪ የቤት ሥራቸው እንደሆነ ይናገራሉ፡፡ የከተማው አስተዳደር በመሥሪያና በንግድ ቦታ ማዘጋጀቱ ላይ መልካም ምላሽ እንደሚሰጣቸው መረዳታቸው ጊዜያዊ እፎይታ ቢሆናቸውም፡፡ እንደ አዲስ አበባ ባሉ ትልልቅ ከተሞች ውስጥ በዘመናዊ ማሽኖች የተገጣጠሙ የቤትና የቢሮ ዕቃዎችን እንዲሁም አልባሳትን መሸመት የሚቀናው የአካባቢው ኅብረተሰብ፣ ለዚህ የወጣቶቹ ጭንቀት ተግባራዊ ምላሽ ሊሰጣቸው እንደሚገባ አቶ ቡልቻ ሮቢ የተባሉ የአካባቢው ነዋሪ ያሳስባሉ፡፡