መነሻ ገጽ - ሌሎች አምዶች - ማህበራዊ ጉዳዮች - ማህበራዊ - ሥውሩ ረሃብ የሚያስከፍለው ዋጋ
Buy Valtrex Online Buy Albuterol inhaler Online Buy Prinivil Online
25 August 2013 ተጻፈ በ 

ሥውሩ ረሃብ የሚያስከፍለው ዋጋ

ሐምሌ 2005 ዓ.ም. እንደገባ ነው፡፡ በሰሜን ሸዋ ከደብረ ብርሃን 20 ኪሎ ሜትር ርቃ በምትገኘው ቀይት፤ የቀይት መጀመርያ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪዎች የሪፖርት ካርዳቸውን ለመውሰድ በቅጥር ግቢው ተሰብስበዋል፡፡

አብዛኞቹ ተማሪዎች ፊታቸው የበለዘና የነጣ ከንፈራቸውም የደረቀ ነበር፡፡ ውነታቸው የሞላ ቁመታቸውም ዘለግ ያሉ ተማሪዎችን ብናይም አብዛኞቹ ሴቶችና ወንዶች ሕፃናት ተማሪዎች ግን ጫጨት ያሉ ነበሩ፡፡ ዕድሜያቸውን ከጠየቅናቸው ውስጥ 11፣ 14 … በማለት የገለፁልን ከተናገሩት ዕድሜ ጋር የተመጣጠነ ቁመት ያልነበራቸው ናቸው፡፡ በአጠቃላይም አብዛኞቹ ተማሪዎች መጐሳቆል ይታይባቸዋል፡፡

በግቢው ውስጥ የሪፖርት ካርድ ለማደል ከተሰባሰቡ መምህራን ውስጥ ከደብረ ብርሃን ቀይት እየተመላለሰች የምታስተምር መምህርትን ተማሪዎቹ ለምንድን ነው ሰውነታቸው የጫጨው፣ ፊታቸውስ የተጐሳቆለው ስንል ጠየቅናት፡፡ ‹‹አብዛኞቹ ልጆች ምግብ በደንብ አይበሉም፡፡ ትምህርት ቤት ሲመጡ አሹቅ (ተቆልቶ የተቀቀለ ባቄላ) ይዘው ነው የሚመጡት፡፡ በዚህ ላይ አብዛኞቹ የገበሬ ልጆች ስለሆኑ የሥራ ጫና ይበዛባቸዋል፡፡ የአካባቢው ውርጭና ከርቀት ተጉዘው መማር ልጆቹ እንደ ዕድሜያቸው እንዳያድጉ አድርጓቸዋል›› አለችን፡፡

አመዳይ (ከፍተኛ ውርጭ) በሚያጠቃት ቀይት የሚመረተው ዋና ሰብል ባቄላ እና ገብስ ነው፡፡ አልፎ አልፎ ደግሞ አተር፣ ስንዴና ምስር ይመረታሉ፡፡ አርሶ አደሩ በአብዛኛው ለምግብነት የሚያውለው ደግሞ ባቄላውንና ገብሱን ነው፡፡ የገብስ እንጀራ ወይም ጥረሾ (ድርቅ ያለ ቂጣ) እንጀራውን ለማራስ ያህል በሚሠራ ‹‹ወጥ›› እንዲሁም ቆሎና የባቄላ አሹቅ መደበኛ ምግቦቻቸው ናቸው፡፡ በአካባቢው ላይ መንግሥታዊና መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ኅብረተሰቡ አትክልት አምርቶ እንዲመገብና እንዲሸጥ ጥረት እያደረጉ ቢሆንም፣ አብዛኛው ኅብረተሰብ አትክልት ወደመመገቡ አያዘነብልም፡፡ በመሆኑም አካባቢው ላይ የሚኖሩት ሕፃናትና አዋቂዎች ምግባቸው በአብዛኛው እንደአካባቢው የአመጋገብ ባህል በሁለቱ ላይ የተወሰነ ነው፡፡ 

በአካባቢው ላይ ያነጋገርናቸው የአካባቢ ጥበቃ ባለሙያ ‹‹አሹቅ ማቆያ፣ ረሃብ ማስታገሻ እንጂ መደበኛ ምግብ አይደለም፡፡  ነዋሪዎቹ ልጆቻቸውን አሹቅ የሚያስይዙት የምግብ ዝግጅቱ ላይ ያላቸው ግንዛቤ አናሳ ስለሆነ ነው፤›› ብለውናል፡፡ 

ካመረቱት ምርት ላይ ለምግባቸው የሚሆነውን አስቀርተው የተረፈውን የሚሸጡ አብዛኞቹ አርሶ አደሮች ለራሳቸውም ሆነ ለልጆቻቸው በተደጋጋሚ የሚመገቡት እንደየአካባቢው የአመጋገብና የአኗኗር፣ እንዲሁም እንደሚበቅለው የሰብልና የተክል ዓይነት የተለያየ ቢሆንም የተወሰነ የምግብ ዓይነት ብቻ ነው፡፡ ካለቡት ወተት፣ ከናጡት ቅቤ፣ ከቆረጡት ማር፣ ካደለቡት በግና ፍየል፣ ከሰበሰቡት እንቁላል ጥቂቱን እንኳን ለቤተሰብ ፍጆታ ሳያስቀሩ አውጥተው ሲሸጡ ማየቱ የተለመደ ነው፡፡ በከተማም ቢሆን የተመጣጠነ ወይም የንጥረ ነገር ይዘቱ የተጠበቀ ምግብ ማግኘት ከዕውቀት አልያም ከአቅም ማነስ ጋር ተያይዞ ለአብዛኛው ኢትዮጵያዊ የተሳካ አይደለም፡፡ ምግብ ሆድን ከመሙላት፣ ረሃብን ከማስታገስና አምሮትን ከመቁረጥ ባለፈ ፋይዳው እምብዛም አይታወቅም፡፡ በመሆኑም አገሬው የሚመገበው ምግብ የተመጣጠነ ይሁን አይሁን አያውቀውም፡፡ ዋጋም አይሰጠውም፡፡ የሥውር ረሃብ ወይም የተመጣጠነ ምግብ እጥረት ተጠቂም ነው፡፡ ይህ መሆኑ ደግሞ በኢትዮጵያ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ዕድገት ላይ ተፅእኖ ፈጥሯል፡፡ ዋጋ እያስከፈለም ነው፡፡ 

በቅርቡ ይፋ የሆነውና ሕፃናት የተመጣጠነ ምግብ ባለማግኘታቸው ምክንያት ኢትዮጵያ በማኅበራዊውና በኢኮኖሚያዊው ዘርፍ እየተጋፈጠችው ያለውን ተፅእኖ አስመልክቶ የተደረገው የዳሰሳ ጥናት የሚያሳየውም፣ የተመጣጠነ ምግብ ሳያገኝ ያደገ ሕፃን በትምህርትና በሥራ ዘመኑ ውጤታማ ስለማይሆን በአገሪቱ ላይ የሚፈጠረው ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ቀውስ ከባድ መሆኑን ነው፡፡ 

በኢትዮጵያ ጤናና ሥነ ምግብ ምርምር ኢንስቲትዩት እና በጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ተጠንቶ ይፋ የሆነው ጥናት እንደሚያሳየው በኢትዮጵያ ከአምስት ሕፃናት ሁለቱ የቀነጨሩ (Stunted) ወይም በተመጣጠነ ምግብ እጥረት ምክንያት ቁመታቸው ከዕድሜያቸው ጋር ሲነፃፀር ዓለም አቀፉ የጤና ድርጅት ካስቀመጠው መጠን በታች ናቸው፡፡ በኢትዮጵያ 28 በመቶ የሚሆነው የሕፃናት ሞት የሚከሰተውም ከተመጣጠነ ምግብ እጥረት ጋር በተያያዘ ነው፡፡ ከተመጣጠነ ምግብ እጥረት ጋር ተያይዞ በሕፃናት ላይ የሚከሰተው ሞትም የኢትዮጵያን አምራች ዜጋ 8 በመቶ ቀንሶታል፡፡ 

ሕፃናት አንድ ዓመት እስኪሞላቸው ድረስ በሚያጋጥማቸው የተመጣጠነ ምግብ እጥረት ምክንያት የሚከሰት ሕመሞችን ለማከም አገሪቷ ለጤና ከምትመድበው 44 በመቶ ያህሉን ይወስዳል፡፡ 

ከትምህርት ጋር በተያያዘም 16 በመቶ የሚሆነው የመጀመርያ ደረጃ ትምህርትን መድገም ከመቀንጨር ጋር የተያያዘ ነው፡፡ የቀነጨሩ ተማሪዎች ጤናማ አስተዳደግ ካላቸው ጋር በትምህርት ሲነፃፀሩ 1.1 ዓመት ወደኋላ የቀሩ ናቸው፡፡   

67 በመቶ የሚሆነው የኢትዮጵያ አምራች ዜጋ ማለትም ዕድሜው ከ15 እስከ 64 ዓመት የሚሆነው ሕዝብ በልጅነቱ ማለትም ከአምስት ዓመት በታች በነበረበት ወቅት በተመጣጠነ ምግብ እጥረት በመጐዳቱ የቀነጨረ ነው፡፡ 

ኢትዮጵያ ከሕፃናት የተመጣጠነ ምግብ እጥረት ጋር ተያይዘው የሚመጡ አሉታዊ ተፅእኖዎችን ለመጋፈጥ በዓመት 55.5 ቢሊዮን ብር የሚገመት ታወጣለች፡፡ ይህም ከአገሪቱ ኢኮኖሚ እኤአ በ2009 ከነበረው (ከጠቅላላ አገር ውስጥ ምርት አኳያ) 16.5 በመቶ ያህሉ ጋር ይመጣጠናል፡፡

በኢትዮጵያ ጤናና ሥነ ምግብ ምርምር ኢንስቲትዩት የምግብ ሳይንስና ኒውትሪሽን ምርምር ዳይሬክቶሬት ውስጥ ተመራማሪ የሆኑት አቶ ቢንያም ተስፋዬ እንደሚሉት ‹‹መቀንጨር›› ከፅንስ ጀምሮ ሊከሰት የሚችል የተመጣጠነ ምግብ እጥረት ውጤት ነው፡፡ በእርግዝና ወቅት ብቻ ሳይሆን ልጅ ከተወለደ በኋላ ባሉት የመጀመርያ ሁለት ዓመታት ውስጥ በተመጣጠነ ምግብ እጥረት ከተጐዳ ይቀነጭራል፡፡ በአጠቃላይ ከፅንስ ጀምሮ እስከ ሁለት ዓመት ድረስ ያሉት አንድ ሺሕ ቀናት ለሰው ልጅ አካላዊና አእምሯዊ ዕድገት ወሳኝ ጊዜያት ናቸው፡፡ በእነዚህ ጊዜያት የተመጣጠነ ምግብ አግኝቶ ያላደገ ሕፃን የትምህርት ውጤታማነቱ ይቀንሳል፣ የፈጠራ ችሎታው አናሳ ነው፡፡ ጤናው በየምክንያቱ ይታወካል፣ በሥራ ዘመኑ ውጤታማነቱ በምግብ እጥረት ካልተጐዳው አንፃር ሲወዳደር ዝቅተኛ፣ ጉልበት በሚጠይቁ ሥራዎች ላይ ያለው ምርታማነትም አነስተኛ ይሆናል፡፡ በአጠቃላይም የአእምሮና የአካል ዕድገት ውስንነት ይኖርበታል፡፡ ይህ ደግሞ ግለሰቡን ብቻ ሳይሆን አገሪቱንም ዋጋ ያስከፍላል፡፡ በመሆኑም ለሰው ልጅ ዕድገት መሠረት ከሚጣልበት ከፅንስ ጀምሮ ሕፃናት የተመጣጠነ ምግብ እንዲያገኙ መሥራትና መቀንጨርን ከኢትዮጵያ መቀነስ ግድ ይላል፡፡ 

ከተመጣጠነ ምግብ እጥረት ጋር ተያይዞ ኢትዮጵያና ሕዝቦቿ እየከፈሉት ያለውን ዋጋ ለመቀነስ በቅርቡ በአገር ደረጃ ብሔራዊ የሥነ ምግብ ፕሮግራም ይፋ ሆኗል፡፡ ፕሮግራሙ ሕፃናት የተመጣጠነ ምግብ አግኝተው እንዲያድጉ ለማስቻል ያሉ ሒደቶችን ሁሉ ያካተተ ነው፡፡

ከነዚህም ሕዝቡ በብዛት የሚጠቀማቸውን ምግቦች በንጥረ ነገር ማበልፀግ (fortification) ይገኝበታል፡፡ ስንዴና ዘይት በቅድሚያ በንጥረ ነገር ለማበልፀግ የተመረጡ ሲሆን፣ ማንኛውም የምግብ ዘይት ከውጭ ሲገባም በንጥረ ነገር የበለፀገ እንዲሆን የሚያስገድድ ሕግ ለማውጣትም ታስቧል፡፡ አገር ውስጥ የሚመረቱ የዘይት ዓይነቶችም በንጥረ ነገር እንዲበለጽጉ ለማድረግ ታቅዷል፡፡ 

በመንግሥት ደረጃ የታቀደውም የግብርና ምርቶች ንጥረ ነገር ይዘታቸው የተጠበቀ እንዲሆን፣ የአመጋገብ ሥርዓት እንዲስተካከልና ኅብረተሰቡ ላይ የግንዛቤ ሥራ ለመሥራት ነው፡፡