መነሻ ገጽ - ሌሎች አምዶች - ማህበራዊ ጉዳዮች - ማህበራዊ - እርድና ዘመናዊነት
Buy Valtrex Online Buy Albuterol inhaler Online Buy Prinivil Online
08 September 2013 ተጻፈ በ 

እርድና ዘመናዊነት

ዓመት በዓል ሲመጣ ወቅቱን አሊያም ዕለቱን ‹‹በዓል በዓል ያሰኙታል ድምቀት ይሰጡታል›› ተብሎ ዶሮና በግ ተገዝቶ በየቤቱ ሲገቡና በየአካባቢው ለሽያጭ ቀርበውም ይታይል፡፡

ይህ ትዕይንት ለበርካታ በዓል አፍቃሪያን ትርጉም ያለውና ስሜት የሚሰጥ ነው፡፡ በግና ዶሮዎች በየቤቱ ሲጮሁ፣ ምግብና ውኃ መስጠት፣ የታሰሩበትን አካባቢ ሲያቆሽሹ ማፅዳትና እንቅስቃሴአቸውን መከታተል የብዙዎች የልጅነት ትዝታ ነው፡፡ 

ለዘመን መለወጫው እንቁጣጣሽና ለፋሲካ አብዛኛው የማኅበረሰብ ክፍል ዶሮ ያርዳል፡፡ ዶሮውን ለማሳረድ ወንድ ተፈልጎ (የሚያሳርዱት ሰዎች ክርስቲያን ከሆኑ አንገቱ ላይ ክር ያሰረ ሰው ቢሆን ይመርጣሉ) ላባውን ከሰውነቱ ለመንቀያ እንዲሆን ውኃ ፈልቶ፣ ታርዶ፣ ፈልቶ ከሚፋጀው ውኃ ጋር ታግሎ ላባውን ነቃቅሎ (ላባውን ከነቆዳው አውልቀው ለማይጥሉት)፣ ጭንቅላቱና እግሩ ተቆርጦ ተጥሎ፣ ገላው ላይ ያሉት ጸጉሮች እንዲራገፉ በእሳት ተለብልቦ፣ የተለበለበው ገላ በሽሮና በጨው ታሽቶ ታጥቦ ከታጠበ በኋላ ቆዳውን ከመላጥ ጀምሮ ሆድ ዕቃው እስኪራገፍ ድረስ ብልት በብልት ይገነጣጠላል፡፡ ይህ ከሆነ በኋላ ደግሞ የተበለተው የዶሮ ሥጋ በሎሚና በውሃ ለረዥም ሰዓት እየተዘፈዘፈ ይታጠባል፡፡ ስለበጉም ሲታሰብ እንደ ዶሮ የሚታጠብበት ረዥም ጊዜ ባይወስድም (ከጨጓራ፣ አንጀትና ሽንፍላ በስተቀር) ታርዶ፣ ተገፎ፣ ተበልቶ እስከሚመጣ ድረስ የሚወስደው ጊዜና ጉልበት አለው፡፡ 

እነዚህ የሥራ ሒደቶች ላለፉት በርካታ ዘመናት ባህል ሆነው ሲወርዱ ሲዋረዱ መጥተዋል፡፡ ነገሩ ምንም እንኳን አድካሚና ጊዜ የሚወስዱ ቢሆንም በርካቶች ግን አሁንም ይደሰቱበታል፡፡ ዶሮና በግ የማረዱ ግርግር፣ ከታረዱም በኋላ ለምግብነት የማይውሉ አካሎቻቸው ሲጣሉ የሚፈጥሩት ሽታና ሌሎች ምቾት የሚነሱ ነገሮች ሁሉ እንደ ችግር አይታዩም፡፡ ሁሉም የበዓል ወግ ነውና፡፡  

ለበዓል በግ ወይም ዶሮ ካልታረደ ምኑን በዓል ሆነው የሚሉ አሉ፡፡ ዘመን መለወጫን በተመለከተ ዶሮ መታረዱ ‹‹ያለፈውን ዘመን በሰላም ያሳለፈልን አምላክ መጪውንም ዘመን ሰላም ያድርግልን›› በሚል የምስጋና ስሜት እንደሆነ በብዙዎች ይስተዋላል፡፡ በዚህ የሚስማሙት የ55 ዓመቷ ወ/ሮ እፀገነት ‹‹ለበዓሉ ዶሮ ካላረድኩ በጣም ቅር ይለኛል፡፡ ምክንያቱም በዓሉ የራሱ ክብር አለው፡፡ በዕለቱ ዶሮም ሆነ በግ መታረዱ የበዓሉ ክብር መገለጫ ስለሆነ የግድ እንዲታረድ አደርጋለሁ፤›› ሲሉ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡ እኚህ እናት ልጆቻቸው ለበዓል የሚታረድ በግና ዶሮ ይኖራል ብለው ጠበቁም አልጠበቁም እርሳቸው ግን ‹‹መጪው ጊዜ ምን እንደሚፈጥር እርግጠኛ መሆን ስለማይቻል (ለበዓሉ ደም ካልፈሰሰ ከቤተሰባቸው ውስጥ አንዱ ችግር ይደርስበታል ብለው ስለሚፈሩ) የግድ አርዳለሁ፤›› ይላሉ፡፡ 

‹‹ወላጆቻችን ለበዓል የማረድን ባህልና እምነት በምን ምክንያት ተዋሕዷቸው እንዳወረሱን ባናውቅም እኔና በእኔ ዕድሜ ክልል ወይም ዕድሜያችን ከ40 በላይ ያለን ሰዎች ባህሉን ከነእምነቱ ይዘን ቀጥለናል፤›› ያሉት ወ/ሮ እፀገነት፣ ለበዓል ተብሎ የሚደረገው በግም ሆነ ዶሮ የማረድና የመበለት ልማድ ለመጪው ትውልድ መተላለፍ ይገባል ብለዋል፡፡ 

ይሁንና ለበዓል የማረድን ልማድ ከነጓዙ በቤት ውስጥ የሚኖረውን መተራመስ ጭምር የሚያስቀር ነገር አለ፡፡ ይህም የታረደ በግና ዶሮ ከቄራ፣ ከየልኳንዳ ቤቱና ከየሱፐር ማርኬቱ መግዛት ነው፡፡ እርግጥ ነው በዚህ መልኩ የሚገዙት የታረዱ በጎችና ዶሮዎች በበዓል ቤት ውስጥ ዶሮና በግ ሲጮኹ፣ ልጆች እነርሱን እያዩ ሲደሰቱ ማየትን ያስቀራሉ፡፡ 

የክርስትና እምነት ተከታይ የሆኑ ሰዎች በጎቻቸውን ወይም ዶሮዎቻቸውን የሚያርዱላቸው ሰዎች ጿሚና አንገታቸው ላይ ማተብ ያሰሩ ያ ካልሆነ ደግሞ የእምነቱ ተከታይ መሆን አለባቸው የሚል እምነት አለ፡፡ በዚህም ምክንያት የታረደን ዶሮ ከሱፐር ማርኬት ላለመግዛት ‹‹የእምነቱ ተከታይ አላረደውስ እንደሆነ›› የሚለው አንዱ ምክንያት ነው፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ደግሞ በዓሉ የሚከበረው የጾም ወቅት አልፎ ከሆነ ‹‹በጾም የታረደን እንዴት እንበላለን›› የሚለውም ሐሳብ የታረደን በግን ወይም ዶሮን ላለመግዛት ሌላው ምክንያት ይሆናል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ የታረዱ ዶሮዎችን ላለመግዛት ምክንያት ከሚሆኑት ነጥቦች የከፋ ስሜት ያለው ደግሞ ‹‹ታርደው ለሽያጭ የተዘጋጁት ዶሮዎች ከሞቱ በኋላ ቢሆንስ፣ ለመታረዳቸው የነበረው ምክንያት መታመማቸው የነበረ አለመሆኑን በምን ማወቅ ይቻላል እንዲሁም ታርደው ለሽያጭ የቀረቡት ዶሮዎች ሞተው ፍሪጅ ውስጥ የቆዩ ስለሆኑ እነርሱን እንዴት ለበዓል እናቀርባለን›› የሚሉት ጥያቄዎች በርካቶችን እንዳይገዙ ይከላከላሉ፡፡ 

ቢሆንም ግን ለበዓል ተብሎ ዶሮና በግ የማረድ ግርግሩን ማየት የማይፈልጉ፣ በማረድ ምክንያት የሚፈጠረው መቋሸሽ የሰለቻቸውና ይህን ለማየት ትዕግስቱ የሌላቸው የማረድ ልማዱ ቀርቶ ቀለል ባለ መንገድ ማሳለፍን ይመርጣሉ፡፡ እንዲህ በማሰባቸው ዶሮውን ከሱፐር ማርኬት በጉንም ከቄራ ወይም ከልኳንዳ ገዝተው ይጠቀማሉ፡፡ 

‹‹ለበዓልም ይሁን ለአዘቦት ቀን ዶሮና በግን የማረድ ትዕግሥትና ፍላጎት ያላቸው የራሳቸው ግቢ ያላቸውና በባህሉም ጠለቅ ያለ እምነት ያላቸው ናቸው፤›› የምትለው የ36 ዓመቷ ወ/ሮ በእምነት ናት፡፡ ወ/ሮ በእምነት የሦስት ልጆች እናት ናት፡፡ የምትኖረው ኮንዶሚኒየም በመሆኑ የአኗኗር ዘዬዋ በፊት ከነበረው የቀለለና የተቀየረ ነው፡፡ ቤተሰቦቿ ቤት ትኖር በነበረበት ጊዜ ለበዓል የሚደረገው ዝግጅት ቢያስደስታትም፣ አብዛኛው የበዓል ሥራ ጫና እሷ ላይ ይሆን ስለነበር በምን መልኩ እንደሆነ እርግጠኛ ባትሆንም ሁኔታዎችን እንዲቀየሩ ግን ትመኝ ነበር፡፡ ‹‹አሁን መልሱን አግኝቼዋለሁ›› የምትለው ወ/ሮ በእምነት፣ ለበዓልም ይሁን ለአዘቦት ቀን የታረደ ሲልም የተበለተን ዶሮ መግዛት ልማዷ አድርጋለች፡፡ የበግ ሥጋ መግዛት የምትፈልግ ከሆነም ከቄራ ወይም ከልኳንዳ ትገዛለች፡፡ ‹‹እኔ የምኖርበት ቤት ዶሮና በግ ልግዛ የምል ከሆነ የት አሳድራቸዋለሁ›› ብላ የምትጠይቀው በእምነት፣ የዶሮ ወይም የበግ ሥጋ ለመብል መቅረቡ እንጂ ቤት ውስጥ አርዶ መርመጥመጡ የተለየ ትርጉም እንደማይሰጣት ትናገራለች፡፡ 

ኮንዶሚኒየም ውስጥ የሚኖሩ ሰዎች የገዟቸውን ዶሮዎች የሚያሳድሩት ምግብ ማብሰያ ክፍል ውስጥ ሲሆን፣ በጎቹን ደግሞ በበር ዘግተው በረንዳው ላይ ሲልም መጸዳጃ ቤት ውስጥ ነው፡፡ ይህ ሆነ ማለት ደግሞ አንድ ጣራ ስር በግድግዳ ተለያይቶ ሰው፣ በግና ዶሮ በአንድ ላይ ያድራሉ ማለት ነው፡፡ በጉም ዶሮውም በየፊናቸው ይጮሃሉ፣ ይንደፋደፋሉ እንዲሁም ይንጓጓሉ፡፡ በጉ ያለበትን መፀዳጃ ቤትን መጠቀም የፈለገ በጉ በሩ ሥር ተኝቶ ከሆነ እንዲነሳ በሩን በጉልበት መግፋትና ውስጡም ከገቡ በኋላ ክፍሉን ሲጠቀሙ ከበጉ ጋር መፋጠጥ የግድ ነው፡፡ በበዓሉ ዕለት ዶሮውና በጉ ወደ መታረጃቸው ሲወሰዱ እነሱ ያቆሸሹትን ክፍሎች ማጽዳት የመጀመርያው ሥራ ነው፡፡ 

ወግን እንከተል ባህልን እናስቀጥል ከተባለ ይህ ተግባር 100 ሺሕ ለሆኑ የኮንዶሚኒየም ነዋሪዎች ተግባራዊ የሚሆን ሲሆን፣ በቀጣይም ባለቤት እንሆናለን ብለው ለተመዘገቡ 900 ሺሕና ከዚያ በላይ ለሆኑ ቤት ፈላጊዎችም ተግባራዊ የሚሆን ነው፡፡ ይህ መሆኑ የግል ግቢ ውስጥ ይደረግ የነበረ የአኗኗር ዘዬን ቀለል ባለ አኗኗር መተካቱ አይቀሬ ነው፡፡ ማረድን፣ ማጠብንና ማጨስን (ዳቦ በመድፋት የሚፈጠረውን) በተመለከተ የጋራ መጠቀሚያ የሆኑ ምድር ቤቶች ተዘጋጅተዋል፣ ይዘጋጃሉ፡፡ ቢሆንም ግን እነዚህ ቤቶች ሙሉ ለሙሉ የተዘጋጁበትን ዓላማ ትተው ለሌላ አገልግሎት የሚውሉበት ሰፊ አጋጣሚ አለ፡፡

ከአጋጣሚዎቹ ውስጥ የተወሰኑትን ለመጥቀስ ቤቶቹ ለዲኤስቲቪ ማሳያ፣ ለሱቅ፣ ለሱፐር ማርኬት፣ ለጂም፣ ለትምህርት ቤት፣ ለአትክልት ቤት፣ ለግለሰቦች መኖሪያ ቤትነትና ለሌላም አገልግሎቶች ሲውሉ ይስተዋላል፡፡ ይህ በመሆኑ የኮንዶሚኒየም ነዋሪዎች ካላቸው የቦታ ውስንነት አኳያ እንደልብ ዘና ብሎ ያለምንም መጨናነቅና ትርምስ የታረደ በግና ዶሮን  ወደ መግዛት መሸጋገሩ አይቀሬ ነው፡፡ ይህ ሲሆን ደግሞ በጉ ወይም ደሮው ለበዓል ተገዝቶ ሲመጣ የሚፈጠረው ስሜት፣ ጩኸቱ፣ መተረማመሱና አካባቢው መቆሸሹ ይቀራል፡፡ በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ መንገድ ኮንዶሚኒየም ውስጥ ያሉ ሰዎች ዘመናዊ አኗኗር እንዲኖራቸው ሁኔታው በማስገደዱ እርድን ጨምሮ ሌሎች የአኗኗር ዘዬዎች እየተቀየሩና እየቀለሉ ነው፡፡  

ዘመናዊነት ተንሰራፍቶ፣ የማረድ ባህልና ልማድ ወደ ጎን ተትቶ ጣጣቸው አልቆ ለሽያጭ ወደተዘጋጁ የበግና የዶሮ ስጋ መዞሩ አሁን ላይ ባሉ ወጣቶች ዘንድ ተመራጭ ያደርገዋል፡፡ በጉ ወይም ዶሮው ቤት ውስጥ ስለመታረዱ ደም ከመፍሰሱ ጋር የተገናኘ ስሜት ከሌለ በስተቀር፣ እየተፈጠረ ላለው የመኖሪያ ቦታ መጣበብም ነገሮችን እያቀለሉ መሄዱ አስገዳጅ ይሆናል፡፡ 

ባህሉና ልማዱ ቀለል ተደርጎ ተወስዶ ያለቀላቸውን ዶሮዎችና በጎች መግዛት እርዱ እቤት አልተከናወነም፣ የበጉ መልክ እንዲህ ነው፣ የዶሮው ድምድማቱ ድርብ ነው ወይም ነጠላ ነው፣ የዶሮው ቀለም ገብስማ፣ ቀይ ወይም ነጭ ነው ከማለት ውጪ ስጋው ላይ የሚፈጥረው ልዩነት አይኖርም፡፡ የሆነ ሆኖ አሁን ባለው አካሄድና የአኗኗር ሁኔታ የታረደ ዶሮን የሚያቀርቡ አካላት ጥራቱን፣ ደረጃውንና የደንበኞችን እምነት በጠበቀ መልኩ አቅርቦቱን ማስፋታቸው የግዢ ልምዱ እንዲዳብር አስተዋጽኦ ያደርጋል፡፡ ለውጡ አያስፈልገኝም የሚለው ደግሞ ያለው ቦታ ይስፋም ይጥበብም የሚፈልገውን በፈለገው ጊዜ እያረደ ይቀጥልበታል፡፡