መነሻ ገጽ - ሌሎች አምዶች - ማህበራዊ ጉዳዮች - ማህበራዊ - የድንኳኖች ባዛር በሸማቾች ዓይን
Buy Valtrex Online Buy Albuterol inhaler Online Buy Prinivil Online
08 September 2013 ተጻፈ በ 

የድንኳኖች ባዛር በሸማቾች ዓይን

በምሕረተ ሥላሴ መኰንን

በመዲናችን አዲስ አበባ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በተለይም ዐውደ ዓመትን አስታከው ብቅ ብቅ የሚሉ የመገበያያ ድንኳኖች ተበራክተዋል፡፡

እነዚህ ድንኳኖች በአብዛኛው ኅብረተሰብ ዘንድ ባዛር በመባል ይታወቃሉ፡፡ በከተማዋ የተለያዩ ስፍራዎች የሚጣሉት ድንኳኖች ውስጥ የእጅ ቦርሳ፣ ቀበቶ፣ ጫማና አልባሳት ከመሳሰሉት ጐን ለጐን ከሰል ማንደጃና ጀበናን የመሰሉ የቤት ቁሳቁሶች ይገኙበታል፡፡ 

በዓል በዓል የሚሸቱ ምግቦች እንዲሁም አረቄና ጠጅም ለገዢው እነሆ ይላሉ፡፡ ብዙውን ጊዜ በባህላዊ ሙዚቃ፣ በተደረደሩ አገልግሎችና በአገር ባህል ልብሶች ይታጀባሉ፡፡ 

ቁጥራቸው በርከት ያሉ ሰዎች በዕቅድም ይሁን በአጋጣሚ ያስፈልገናል ያሉትን ሲገዙ ይስተዋላሉ፡፡ ዞር ዞር እያሉ የሚመለከቱ ታዳሚዎችም አይታጡም፡፡ ስለ ገበያ ቦታው፣ ስለሚቀርቡት ሸቀጦች በተያያዥም ስለ ጠቅላላ የግብይት ሥርዓቱ የተለያዩ ሸማቾች ያላቸውን ሐሳብ ገልጸውልናል፡፡ 

ቦሌ ድልድይ አካባቢ ባለው ባዛር ውስጥ የገንዘብ ቦርሳ ለመግዛት ከሻጭ ጋር በዋጋ ሲደራደሩ የነበሩት የ40 ዓመቱ አቶ ወንድምአገኝ መርሻ በአጋጣሚ ለሕክምና ወደ ቦሌ መጥተው ባዛሩን እንዳዩትና በድንኳኖቹ ውስጥ ሌላ ገበያ ላይ በቀላሉ የማያገኙትን እንዳገኙ ገልጸዋል፡፡ ከበዓል ጋር ተያያዥነት ያለው ሙዚቃ ሲከፈት በጣም ደስ እንደሚላቸው በተጨማሪም ከተማዋን ሞቅ ደመቅ እንደሚያደርጋት ተናግረዋል፡፡ 

በእነዚህ ባዛሮች ከቁሳቁሶች ጐን ለጐን ደረቅ ምግቦች አልፎ አልፎም እንጀራ በወጥ ይገኛል፡፡ በሚቀርቡት ምግቦች ዙሪያ ስማቸውን ለመግለጽ ፈቃደኛ ያልሆኑት የ35 ዓመት የባንክ ሠራተኛ ‹‹በጊዜ እጥረት ምክንያት በቤት ውስጥ ማዘጋጀት ያልቻልናቸው ምግቦች መቅረባቸው መልካም ነው፤›› ሲሉ በምሕንድስና ሥራ ላይ የተሰማሩት አቶ ግርማ ይመኑ ደግሞ ምግቦቹ የኅብረተሰቡን ጤና ከመጠበቅ አኳያ የታሰበባቸው ስለመሆናቸው እርግጠኛ ለመሆን እንደሚያስቸግር ጠቁመዋል፡፡ 

የማኔጅመንት ተማሪ ለሆነው የ24 ዓመቱ በሽር ዑመር ከኢትዮጵያ ሱማሌ ክልል ለመጣውና በአማርኛ የሚካሄደው ግብይት አያስቸግርም ወይ በሚል ለቀረበለት ጥያቄ ‹‹በመጀመሪያ የተለያየ ዕቃ መኖሩ ገዢውን ያበረታታል፡፡ በእኔ በኩል ጥቂት አማርኛ ስለምችል መገበያየት አያስቸግረኝም፡፡ አንዳንዴም በሰውነት እንቅስቃሴ ከሻጮች ጋር መግባባት ይቻላል፤›› ብሏል፡፡ 

የድንኳን ገበያው ካሉባቸው አካባቢዎች አንዱ በሆነው ካዛንቺስ ከምሳ በኋላ ቡና ለመጠጣት ጎራ ያሉት በቂርቆስ ክፍለ ከተማ የከተማ አስተዳደር ሠራተኛ የሆኑት አቶ ያሬድ ዓለማየሁና አቶ በኃይሉ አስፋው እንዳሉት ያለ ብዙ ግርግርና ግፊያ የተለያዩ ነገሮች በአንድ ቦታ መገኘታቸው ደስ ያሰኛል፡፡ በባዛሩ ላይ የሚያስፈልጉዋቸውን ነገር ግን በቤታቸው የሌሏቸውን ዕቃዎች እንደሚያስታውሳቸው ገልጸዋል፡፡ 

በዚሁ አካባቢ ያገኘናቸው የ35 ዓመቷ ወይዘሮ ፀሐይ ወልደ ሰንበት በበኩላቸው የገበያው ሁኔታው ጥቃቅንና አነስተኛ ንግድ ላይ የተሰማሩ ሠራተኞችን ከማበረታታት አኳያ እንደሚያዩት፣ በዓልን አስቀድመው ስለሚመጡም አስፈላጊ ነገሮችን ለመግዛት በጉጉት ጠብቀው ከሥራ ባልደረቦቻቸው ጋር እንደሚመጡ ተናግረዋል፡፡ 

አራት ኪሎ አካባቢ በሚገኙት ድንኳኖች ያገኘነው አቶ ዳንኤል መላ በበኩሉ በአጋጣሚ ያየው ዕቃ ቢኖርም ባዛሩን ምክንያት አድርጎ እንዳልመጣ ነግሮናል፡፡ የመንገድ ላይ ባዛሮቹም በተለይም በዋና ዋና የእግረኛ መንገድ ላይ መሆናቸው አካባቢውን እንደሚጨናነቁና አንድ አንዴም ለአደጋ እንደሚጋብዙ ይናገራል፡፡ 

ከቋንቋ ትምህርት ቤት ወደ ቤት ባለ ጉዞ ላይ ወደ ባዛሩ ጎራ ያሉት ወጣት ሸማቾች ወይዘሪት ዘይባ አሚንና ወይዘሪት ሠናይት ምንዳዬ ናቸው፡፡ በኢትዮጵያውያን የተሠሩ ምርቶችን ከማስተዋወቅ አንጻር ባዛሩ መልካም ቢሆንም ከአገርም ይሁን ከዓመት በዓል ጋር ያልተያያዙና ሀገርኛ ያልሆኑ ሙዚቃዎችን መክፈቱ አስፈላጊነቱ አይታየንም ብለዋል፡፡ ቦሌ ድልድይ አካባቢ ያገኘናቸው ወይዘሮ የዛብየለሽ አታሌ ግን ‹‹ሙዚቃው ለጥቂት ቀናት እስከሆነ ድረስ ያደምቃል እንጂ ብዙም አያስቸግርም፤›› ብለዋል፡፡ 

ካዛንቺስ በሚገኙት ድንኳኖች ሹራብ ሲገዛ ያገኘነው ባለትዳርና የአንድ ልጅ አባት የሆነው መምህር ከፍያለው አሰፋ ‹‹ባዛሩ መንገድ ዳር መሆኑ ለሚተላለፈውና ገዢ ላልሆነው ኅብረተሰብ በተጨማሪም በአካባቢው በሥራ ላይ ላሉ ሰዎች ሊያስቸግር ይችላል፡፡ በድንኳኑ ውስጥ በሻጮች መካከል ያለው የእርስ በርስ ትስስር ግን ይበል ያሰኛል፤›› ብሏል፡፡ 

ከባለቤታቸው ከወይዘሮ ስንዱ ደሳለኝና ከሦስት ዓመት ልጃቸው ጋር ያገኘናቸው አቶ ታገሰ አደራው ደግሞ ከባዛሩ በፊት ከደንበኛቸው ቅቤ ለመግዛት እንደመጡ ነገሩን፡፡ አያይዘውም ምናልባት ብዙ ዓይነት ሸቀጦች በአንድ ቦታ መገኘታቸው ገዢውን አጓግተው ካለው አቅም በላይ እንዲሸምት አይገፋፉም ወይ ስንላቸው፤ ‹‹ለምን ተብሎ? እንደየሰው ይለያያል፣ ደግሞም የሚያስፈልገንን ነገርና የኪሳችንን አቅም መፈተሽ የየግል ድርሻንም ነው፤›› ሲሉ ባለቤታቸው በበኩላቸው በድንኳኖቹ ውስጥ ያሉ አንድ ዓይነት ዕቃዎች በተመሳሳይ ዋጋ መሸጣቸውና ሸማቹ ለበዓል የሚፈልገው መቅረቡ መልካም ነው ብለዋል፡፡ አያይዘውም ምንም ባይገዛ እንኳን መጐብኘቱ ብቻ ከበዓል ጋር ተያይዞ የሚታወስ ጥሩ ትዝታ ጥሎ ያልፋል ሲሉ አጫውተውናል፡፡