መነሻ ገጽ - ሌሎች አምዶች - ማህበራዊ ጉዳዮች - ጠለስ - እውነታን መቀበል
Buy Valtrex Online Buy Albuterol inhaler Online Buy Prinivil Online

ትዳር የመሠረተችው ከአሥራ ሁለት ዓመታት በፊት ነበር፡፡ ያደገችው አዲስ አበባ ኳስ ሜዳ እየተባለ ከሚጠራው አካባቢ የነበረ ቢሆንም፣ አብዛኛውን ጊዜ በገጠሪቱ የአገሪቷ ክፍል እንደሚሰማው ትዳር የመሠረተችው በፍላጐቷና ተጓዳኟን መርጣ ሳይሆን ተጠልፋ ነበር፡፡

መውለዷን ተከትሎ ሰውነቷ መቀነስ ከቀድሞ በተለየ መልኩ ይዳከም ጀመር፡፡ ‹‹የኑሮ አለመመቸት መንገላታት ይመስለኝ ነበር፡፡ ሰውነቴ መቀነስ ቀጠለ፡፡ የቤት ውስጥ ሥራ ለመሥራት እንኳ አቅም አጣ ጀመር፤›› በማለት የኤችአይቪ ምርመራ ከማድረጓ በፊት የነበረችበትን ሁኔታ ታስታውሳለች፡፡ ዕድሜዋ በሃያዎቹ መጨረሻ እንደሚገኝ ብትናገርም ሁኔታዋ ማንም አይቷት ምናልባትም በሣላሳዎቹ መጨረሻ እንደምትሆን ቢገምት እንዴት አያስብልም፡፡ ገጽታዋን ጨምሮ ሁለንተናዋ በሃያዎቹ ውስጥ ያለች ስለመሆኗ አይናገርም፡፡

ባደረገችው የኤችአይቪ ምርመራ ቫይረሱ በደሟ ወስጥ መኖሩን አወቀች፡፡ ኤችአይቪ ፖዘቲቭ እሆናለሁ የሚል ምንም ዓይነት ግምት ስላልነበራት እውነቱን ስትሰማ ራሷን ስታ ነበር፡፡ ቀስ በቀስ ራሷን እየገዛች ብትሄድም እንዴት ልያዝ ቻልኩ? ለምን? በሚሉ በቀላሉ መልስ ልታገኝላቸው ምናልባትም መልስ በሌላቸው ጥያቄዎች ራሷን አስጨነቀች፡፡

እውነቱን ቀድማ የነገረችው ለእህቶቿ ሲሆን፣ ለባለቤቷም መናገር እንዳለባት አምና የጤናዋን እውነት ነገረችው፡፡ ‹‹ምንም ምንም ሳይል ጥሎኝ ሄደ፣ እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ ለዓመታት ስለሱ ምንም ሰምቼ አላውቅም ነበር፡፡ ቫይረሱ በደሟ ውስጥ ከምትገኝ ሌላ ሴት ጋር አብሮ እንደሚኖር ሰምቻለሁ፡፡››

መለወጥ የማይቻልን እውነታ ተቀብሎ መኖር መልካም መሆኑ ግዴታ እንጂ ምርጫም እንዳልሆነ አከራካሪ አይደለም፡፡ በተለይም ቫይረሱ በደማቸው ውስጥ የሚገኝ ሰዎች እንዴት ባለ አጋጣሚ ተያዝኩ? በምን ተያዝኩ? በሚሉ ዓይነት ጥያቄዎች ራሳቸውን እንደሚጎዱ፤ ይህ ከፍተኛ የሥነ ልቦና ቀውስ ውስጥ እንደሚከታቸው ሪፖርተር በተደጋጋሚ ያነጋገራቸው ቫይረሱ በደማቸው ውስጥ የሚገኝ ሰዎች በተለያየ ጊዜ ተሞክሯቸውን አካፍለዋል፡፡ ለብዙዎቹ እውነታውን መቀበል በቀጣይ ሕይወታቸው ላይ እንዲያተኩሩና ከመቼውም በላይ ራሳቸውን አውቀውና ጤናቸውን ተጠብቀው እንዲኖሩ መሠረት ሆኗቸዋል፡፡

በመጨረሻ የጤናዋን እውነታ የኤችአይቪ ቫይረስ በደሟ ውስጥ መኖሩን እንዴት አምና እንደተቀበለች ጠየቅናት? የቤተሰቦቿ ድጋፍ ትልቅ ነገር እንደነበር አትዘነጋም፡፡ ወዲያው ስትነግራቸው ቢደነግጡም በምንም መልኩ አላገለሏትም፣ ሕክምናዋን እንድትቀጥል ነበር የነገሯት፡፡ እንዳሏት አደረገች፣ ‹‹ሆስፒታል ስሄድ ብዙ ቫይረሱ በደማቸው ውስጥ የሚገኝ ሰዎችን አገኘሁ፡፡ ስለራሳቸው የነገሩኝ ነበሩ፡፡ ስለእነሱ ጠንካራ መሆን የጤናቸውን ሁኔታ ስመለከት ተሰፋ መቁረጥ እንደሌለብኝ፣ ይበልጥ ደግሞ ለልጄ ራሴን በጤና ማኖር እንዳለብኝ አመንኩ፤›› በማለት እንደ እሷ ቫይረሱ በደማቸው ውስጥ ከሚገኝ ሰዎች ፖዘቲቭ ሆኖ ስለመኖር መስማቷ ሕይወቷን እንደቀየረው ታስታውሳለች፡፡

በኤችአይቪ የምክር አገልግሎት ባለሙያ የተሰጣትን ምክር፤ የቤተሰቦቿን የሞራል ድጋፍ ዋጋ ባታሳጣም ፖዘቲቭ ከሆነ ሰው ራስን አውቆ መኖር ምን ማለት እንደሆነ መስማት የተለየ እንደሆነ ታምናለች፡፡

ራሷን ከማወቋ በፊት ስለኤችአይቪ የተወሰነ ነገር ታውቅ እንደነበር ስትነግረን የምታውቀው ምን እንደነበር ጠየቅናት፡፡ የምታውቀው ኤችአይቪ በግንኙነት እንደሚተላለፍና ፖዘቲቭ ከሆኑ መኖር እንደማይቻል ነበር፡፡ ይህ ‹‹ለቫይረሱ የተጋለጥኩት በባለቤቴ ምክንያት ነው፡፡ ከዚህ ወዲያ ዕድሜዬ በጣት የተቆጠረ ነው፤›› ብላ እንድታምንና እንድትረበሽ  አድርጓት ነበር፡፡ ራሷን እስከመሳትም ያደረሳት ይኼው ነበር፡፡

ልጇ ዛሬ አሥር ዓመት ሆኗታል፡፡ የአራተኛ ክፍል ተማሪ ነች፡፡ እናቷም የሚኖሩት ከእሷ ጋር ነው፡፡ ቤተሰቧን የምታስተዳድረው ጌጣጌጥና ልብስ በተለያዩ አካባቢዎች እያዞረች በመሸጥ ነው፡፡ በተለይም እሷ ራሷን ባወቀችበት ወቅት ቫይረሱ በደማቸው ውስጥ የሚገኝ ሰዎች ከተለያዩ ድርጅቶች ዕርዳታና ድጋፍ ያገኙ የነበረ ቢሆንም፣ ‹‹ተረጂ መሆን የሰዎችን እጅ መጠበቅ ይበልጥ ይጐዳኛል፤›› በማለት ወደ አንድም ድርጅት አልሄደችም፡፡ የመረጠችው በላቧ ኑሮዋን ማሸነፍ ነበር፡፡ ከዓመታት በኋላ ግን ያልገመተችው አጋጣሚ ቫይረሱ በደማቸው ወስጥ ለሚገኝ ሰዎች ማኅበራዊ ድጋፍ ወደሚያደርገው ኦሳ ድርጅት እንድትሄድ አስገደዳት፡፡

ትወስድ በነበረው ፀረ ኤችአይቪ መድኃኒት የጐንዮሽ ጠንቅ ምክንያት ሰውነቷ ያብጥ ጀመር፡፡ ደሟም ይረጋ እንደነበር በባለሙያዎች እንደተነገራት ታስታውሳለች፡፡ ሕመሟ በርትቶ ቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል ለረዥም ጊዜ ተኝታ ነበር፡፡ በዚያ ወቅት የታዘዘላት መድኃኒት በእሷ አቅም የሚሞከር አልነበረም፡፡

‹‹ምርጫ አልነበረኝም፣ መድኃኒቱን እንዲገዛልኝ ወደ ድርጅቱ ዕርዳታ ፈልጌ ሄድኩኝ፡፡ በሺዎች የሚቆጠር ገንዘብ አውጥተው መድኃኒቱን ገዙልኝ፡፡ የቤት ለቤት ተንከባካቢም ቀጥረውልኝ ነበር፤›› በማለት እዚያ ድርጅት ሄዳ ቫይረሱ በደማቸው ውስጥ ከሚገኝ ሌሎች ሰዎች ጋር መገናኘቷም በብዙ መልኩ እንደጠቀማት ትናገራለች፡፡ እሷ እንዳለችው በዚያ ከእሷ አልፎ ሕይወታቸው ብዙዎችን የሚያስተምር ቫይረሱ በደማቸው ውስጥ የሚገኝ ሰዎች ይገኛሉ፡፡

‹‹አቅሜ በፈቀደ እየለፋሁ ልጄን እያሳደግኩኝ ነው፡፡ ቢሆንም ለልጄ አሁንም ላደርግ ያልቻልኳቸው ነገሮች ብዙ ናቸው፡፡ የመንግሥት ትምህርት ቤት ፍለጋ ልጄ ሩቅ መንገድ እየሄደች ነው የምትማረው፡፡ ብችል ልጄ እንዲያ እንዳትደክም ተርባ እንዳትውል ባደርግ ደስ ይለኛል፡፡ ብድር ወስጄ በተደጋጋሚ ንግድ ብሞክርም እንዳሰብኩት አዋጭ አልሆነም፡፡ ቢሆንም አሁንም መነሻ ነገር ባገኝ በደንብ መንቀሳቀስ እንደምችል እርግጠኛ ነኝ፡፡››