መነሻ ገጽ - ሌሎች አምዶች - ማህበራዊ ጉዳዮች - ጠለስ - ብርታት
Buy Valtrex Online Buy Albuterol inhaler Online Buy Prinivil Online

ይኖር በነበረበት ቢሾፍቱ ከተማ ከሠፈራቸው አቅራቢያ ወደሚገኝ አንድ ጤና ጣቢያ በመሔድ ምርመራ ለማድረግ የሞከረው ገና የአሥራ ሦስት ዓመት ታዳጊ እያለ ነበር፡፡

ነገሩን በተወሰነ መልኩ አስገራሚ የሚያደርገው ሕፃኑ ዕርምጃውን የወሰደው እንደዛሬው ስለ ኤችአይቪ በቂ መረጃ በሰዎች ዘንድ ባልነበረበት፣ ሰዎች መመርመርን ብዙም በማይደፍሩበት፣ ቫይረሱ በደማቸው ውስጥ የሚገኝ ሰዎች በግልጽ ይገለሉ በነበረበት ጊዜ መሆኑ ነው፡፡

በዕድሜና በሕይወት ልምድ ሰፊ ተሞክሮ ያላቸው አዋቂዎች እንኳን የኤችአይቪ ምርመራ ለማድረግ ሲያስቡ በፍርኃት ሲሸበቡ የታዳጊው ሕፃኑ ስለኤችአይቪ ከማወቅ አልፎ ለመመርመር መፈለግ ሠራተኞቹን አስገረመ፣ አስደነገጠም፡፡ ያ ታዳጊ ዛሬ የ22 ዓመት ወጣት ነው፡፡

ዛሬ ላይ ቆሞ ምርመራ ለማድረግ ወደ ጤና ማዕከሉ የሔደበትን ጊዜ ወደኋላ ተመልሶ በማየት ባለሙያዎቹ ያሳዩት አቀራረብና የሰጡት ምላሽ ትክክል እንዳልነበር ይናገራል፡፡ በመጀመሪያ ሌላ አዋቂ ይዞ ካልሆነ በስተቀር መመርመር እንደማይችል ነገሩት፡፡ ይህ ሐሳቡን እንዲቀይር አላደረገውም፡፡ በማግሥቱ አያቱን ይዞ ወደ ጤና ጣቢያው አመራ፡፡ ባለሙያዎቹ አያትየው አያት ስለመሆናቸው ከቀበሌ አስጽፈው እንዲመጡ ከመንገር ውጭ ይህ ነው ብለው በግልጽ ባላስቀመጡት ምክንያት ለሁለተኛ ጊዜ ታዳጊውን ሳይመረመር ወደ ቤቱ ላኩት፡፡ ሁኔታው አበሳጨው፣ አሳዘነውም፡፡ ከዚያ በላይ ገፍቶ መሔድ ስለማይችል የኤችአይቪ ምርመራ የማድረግ ሙከራው በዚያው ተገታ፡፡

የአሥራ ሦስት ዓመቱን ታዳጊ ምርመራ ለማድረግ ያነሳሳው ያስፈራውስ ጉዳይ ምን ነበር? ወላጅ እናቱ በ1994፣ አባቱን ደግሞ በ1996 ዓ.ም. አልጋ ላይ ከዋሉ በኋላ ሞተዋል፡፡ በጨቅላ ዕድሜው እንደ አዋቂ አባቱን አስታሟል፡፡ የእናት የአባቱን ረዥም ጊዜ ታመው ማለፍ፣ የታናሽ ወንድሙን ገና በሕፃንነት መሞት ማስተዋሉና ወላጆቹ ታመው በነበሩበት ወቅት የሰማቸውና ብዙም ያልተረዳቸው አንዳንድ ነገሮች ለመመርመር እንዲያስብ እንዳስገደዱት ያስታውሳል፡፡ ከዚህ ውጭ የማንም ግፊት አልነበረም ለመመርመሩ፡፡ ስለ ኤችአይቪ እንዲህ እንዲህ ነው ተብሎ በግልጽ የሰማው ነገር ባይኖርም ነገሮችን በጥልቀት ለማስተዋል፣ ለመገመትና ትርጉም ለመስጠት ይሞክር ነበር፡፡

ወላጆቹ አካል ላይ ያስተዋላቸውን ለውጦች እሱ ላይ ይታዩ እንደሆነ ብሎ የተከታተለበት ጊዜ መኖሩን በሚገባ ያስታውሳል፡፡ ለብቻው ሔዶ ለመመርመር የሞከረው አባቱ በሞተ በዓመቱ ነበር፡፡ ሙከራው አልተሳካም፡፡ በቀጣዩ ዓመት መጨረሻ ላይ ሰርተፍኬት ለመቀበል ትምህርት ቤት በተገኘበት ወቅት ራሱን ስቶ ቢሾፍቱ ሆስፒታል ገባ፡፡ በዚያ አጋጣሚ በተደረገለት ምርመራ ኤችአይቪ ፖዘቲቭ መሆኑ ታወቀ፡፡ ‹‹ወደ አንድ ወር ገደማ ነው ሆስፒታል የተኛሁት በጣም ደክሜ ነበር፡፡ ሰውነቴ ቆስሎ ፀጉሬ ሁሉ ሳስቶ ነበር፡፡ በዚያ ወቅት ዛሬ ላይ ሆኜ ሳስበው ልመረመር በሔድኩበት አጋጣሚ ተመርምሬ ራሴን አውቄ ቢሆን ኖሮ ጥሩ ነበር፡፡ ፀረ ኤችአይቪ መድኃኒትም በጊዜ እጀምር ነበር፤›› ይላል፡፡ ብዙ ግን አይቆጭም፡፡

ከኤችአይቪ ጋር በተያያዘ ሕፃናት የሚመረመሩበት፣ ቫይረሱ በደማቸው ውስጥ ቢገኝ የሚነገርበት እንዲሁም ወላጆቻቸው እንኳ ፖዘቲቭ ሲሆኑ ይህን እውነት እንዴትና መቼ ነው ማወቅ ያለባቸው የሚለውን የሚመለከት የተለየ አካሔድ ቢኖርም ባለሙያዎች ሁሌም ልጆች ራሳቸውን የሚያደርጉትን ጥረት ማገዝ እንደሚገባቸው ይሰማዋል፡፡ 

ወላጆችን ማስታመም በመጨረሻም ማጣት ከባድ ነው፡፡ እንደ እሱ ላለ ሕፃን ደግሞ ነገሩ ይበልጥ ይከብዳል፡፡ እሱ እንደሚለው ግን ሁሉንም ነገር ተቀብሎ እንደ ልጅ እየደነገጠ ሳይሆን ተረጋግቶ መኖር ቀጥሎ ነበር፡፡ ነገር ግን አልፎ አልፎም ቢሆን ለምን ፖዘቲቭ ሆንኩ? እንደ ልጅ በመቦረቅ በመዝለል ፋንታ በፈታኝ ሁኔታ ለምን እንዳልፍ ሆነ? የሚሉ ጥያቄዎችን ለራሱ በማንሳት የተጨነቀና ያዘነባቸው ጊዜያት ነበሩ፡፡ ዛሬ ላይ ሆኖ ሲያየው የሆነውን ነገር ሁሉ ጥሩ የሕይወት ተሞክሮ ያለው አዋቂ ሊቀበለው በሚችልበት ደረጃ ተቀብሎ እንደነበር ይናገራል፡፡

‹‹የአሥራ ሁለት ዓመት ሕፃን ሆኜ ምንም እንኳ ሠርቼ ገንዘብ አመጣ የነበረ ባይሆንም ሙሉ በሙሉ ቤት የማስተዳድረው እኔ ነበርኩ፡፡ እንደ አዋቂ ብዙ ኃላፊነት ነበረብኝ›› በማለት ያለፈበት የሕይወት መስመር የግድ አጠንክሮት እንዳወጣው ይናገራል፡፡

ጊዜ ጊዜን እየወለደ አፍላዎቹ የዕድሜው ጊዜያት ላይ ኤችአይቪ ፖዘቲቭ መሆኑ እንደ አዲስ ይረብሸው ጀመር፡፡ ትምህርት ቤት፣ ከትምህርት ቤት ውጭም ከጓደኞቹ ጋር ሆኖ በሚያደርጋቸው ነገሮች ሁሌም አንድ ቦታ ላይ እሱን የሚገድበው ነገር መኖሩ ያበሳጨው ያዘ፡፡ ወጣትነትና የጓደኛ ግፊት በአንድ በኩል የጤናው እውነት ደግሞ በሌላ በኩል ዕለት በዕለት ይፈትኑት ጀመር፡፡

‹‹ፈታኝ ነገሮች ያጋጥሙኝ ጀመር፡፡ በጣም ከሚያውቀኝ አንድ ጓደኛዬ ውጭ ስለጤናዬ ማንም አያውቅም፡፡ አንዳንድ ዝግጅቶች ላይ በእኔ ዕድሜ ያሉ ወጣት ሴቶች ጋር ቀርቤ ሳወራ አደገኛ አዝማሚያዎችን አስተውል ነበር፡፡ በእነዚያ አጋጣሚዎች ራሴን ተቆጣጥሬ ማለፍ ችያለሁ፡፡ በሌላ በኩል አጋጣሚዎቹ ስለወጣቶች እንድጠይቅ ያደርጉኛል፡፡››

የሃያ ሁለት ዓመቱ ወጣት ባለፈው ዓመት በኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ዲፕሎማውን የያዘ ሲሆን፣ ዘውዲቱ ሆስፒታል ውስጥ በሚገኘው የኤችአይቪ ምርመራ ማዕከል ውስጥ በመሥራት ላይ ይገኛል፡፡ በተለይም እሱ በሚገኝበት የዕድሜ ክልል ላይ የሚገኙ ወጣቶች ለምርመራ ወደ ማዕከሉ ሲሔዱ ከእሱ ሕይወት እንዲማሩ፣ ኤችአይቪ ምንም አይደለም ተብሎ የሚታይ ባለመሆኑ ራሳቸውን እንዲጠብቁ ልምዱን ያካፍላል፡፡