መነሻ ገጽ - ሌሎች አምዶች - ማህበራዊ ጉዳዮች - ጠለስ - የኤችአይቪ መከላከያ
Buy Valtrex Online Buy Albuterol inhaler Online Buy Prinivil Online
18 August 2013 ተጻፈ በ 

የኤችአይቪ መከላከያ

ራሳቸውን ላጋለጡ ወይስ ለተጋለጡ?

የሠርጉ ዕለት ሦስት አልያም አራት ሳምንታት ብቻ ቀርተውታል፡፡ ለሠርጉ ሁሉንም ዝግጅት አጠናቅቋል፡፡ ከወራት በፊት ደግሞ ከእጮኛው ጋር በመሆን የኤችአይቪ ምርመራ በማድረግ በደማቸው ውስጥ የቫይረሱን አለመኖር አረጋግጠዋል፡፡

ነገር ግን ለጋብቻ ዕለት በዓሉ ጥቂት ሳምንታት ሲቀሩ ከእጮኛው ጋር የጥንዶች የኤችአይቪ ምርመራ ወዳደረጉበት የየካቲት 12 ሆስፒታል የኤችአይቪ ምርመራ ማዕከል እንዲሔድ የግድ የሚለው ነገር ተፈጠረ፡፡

ከወራት በፊት ባደረገው ምርመራ ውጤቱ ኔጌቲቭ የነበረ ቢሆንም ለሠርጉ ጥቂት ቀናት ሲቀሩ ራሱን ለቫይረሱ ማጋለጡን ለጤና መኰንን ቅድስት እንግዳ ገለጸላት፡፡ ወጣቱ ወደ ማዕከሉ የሔደው በአስገድዶ መደፈር በሕክምና አገልግሎት ላይ በሚደርስ ድንገተኛ አደጋ ለቫይረሱ ተጋልጠዋል ተብሎ ለሚታመን ሴቶችና የሕክምና ባለሙያዎች እንዲሁም በተመሳሳይ ሁኔታ ለቫይረሱ ለተጋለጡ ሰዎች የሚሰጠውን የኤችአይቪ መከላከያ (Post Exposure Prophlaxis) ለመውሰድ ፈልጐ ነው፡፡ በመተግበር ላይ ያለው የጤና ጥበቃ የፀረ ኤችአይቪ መድኃኒት አጠቃቀም መመሪያ ግን ከተወሰኑ ሁኔታዎች ውጭ መድኃኒቱ ለማንም እንዳይሰጥ ይከለክላል፡፡ 

‹‹ከወራት በፊት እኛ ጋር ተመርምሮ ነፃ መሆኑን ገልጾ እውነቱን ለመሆኑ እንዳረጋግጥ ካርድ ሰጠኝ፡፡ በካርድ ቁጥሩ መሠረት ያወጣሁት ዶሴ እንዳለው ከሴት ጓደኛው ጋር አንድ ላይ መመርመራቸውንና ነፃ መሆናቸውን ያሳያል፤›› የምትለው ጤና መኰንን ቅድስት ዘወትር መመርያውን መሠረት አድርገው ቢሠሩም እንደዚህ ያለ አጣብቂኝ ውስጥ የሚከትታቸው አጋጣሚ መኖሩን ትናገራለች፡፡ 

ወጣቱ የቀድሞ ፍቅረኛው ከዓረብ አገር መጥታ ከእሷ ጋር ተገናኝቶ ሳያስበው ምንም ዓይነት ጥንቃቄ የሌለው ወሲብ መፈጸሙን፤ ለዓመታት ተለያይተው ስለቆዩ ስለ ልጅቷ የሚያውቀው አንዳች ነገር ባለመኖሩ ለቫይረሱ የመጋለጥ ዕድል እንዳለው ለጤና መኰንኗ ገልጾ ‹‹ድንገተኛ የፀረ ኤችአይቪ መድኃኒት እንድትሰጠው ተማፀናት፡፡ 

እንደ አሠራር በስሜታዊነት፣ በአልኮል አልያም በተመሳሳይ ምክንያት ለቫይረሱ ለሚጋለጡ ሰዎች መድኃኒት መስጠት ባይፈቀድም የዚህ ዓይነቱ አጋጣሚ ባለሙያዎችን ማስጨነቅና በተለያዩ ጥያቄዎች መወጠሩ አይቀርም፡፡

‹‹ለዚህ ልጅ መድኃኒቱን መስጠት ከአሠራር ውጭ ነው፤ ወንጀልም ነው፡፡ በሌላ በኩል ጥቅምና ጉዳትህን መዝነህ ለፈጸምከው ነገር ኃላፊነት መውሰድ አለብህ አይሰጥህም ሒድ ቢባል የሙሽራዋስ ሕይወት?››፡፡

በተመሳሳይ መልኩ በዘውዲቱ ሆስፒታል የኤችአይቪ ምርመራ ማዕከል የፀረ ኤችአይቪ ስፔሻሊስት የሆኑት ዶክተር አስቴር ሸዋአማረ የትምህርት ቤት ዩኒፎርም ለብሰው ከነደብተራቸው ወደ ማዕከሉ የኤችአይቪ መከላከያ መድኃኒት ፍለጋ የሚሔዱ የሁለተኛና የመጀመሪያ ደረጃ ተማሪዎች ጭምር እንደሚያጋጥሙ ይናገራሉ፡፡ 

‹‹በቅርብ አንድ የሁለተኛ ደረጃ ተማሪ ደብተሩን እንደያዘ ሰባተኛ አካባቢ ያለጥንቃቄ ከሴተኛ አዳሪ ጋር ወሲብ መፈፀሙን ነገረን፡፡ እኛ ጋር የመጣው ደግሞ የኤችአይቪ መከላከያ መድሃኒት ፈልጐ ነበር››

ዶክተር አስቴር እንደሚሉት፣ የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎችም በተመሳሳይ ምክንያት ወደ ማዕከሉ ይሔዳሉ፡፡ ነገር ግን ፀረ ኤችአይቪ መድኃኒትን ከመመርያ ውጭ ለማይገባቸውና ለማይፈቀድላቸው መስጠት የመድኃኒት ብክነትንና እጥረትን ያስከትላል፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ ሰዎች መድኃኒት አለ በማለት መጠንቀቅን ችላ እንዲሉ ሊያበረታታም ይችላል፡፡ 

መድኃኒቱን ለመስጠት መጀመሪያ ምርመራ ማድረግም ያስፈልጋል፡፡ ለቫይረሱ ተጋልጠዋል ተብሎ ከታመነ ብቻ ነው የሚሰጠው፡፡ መድኃኒቱ ከሁለት ሰዓት ውስጥ ቢሰጥ የሚመረጥ ይሆናል፡፡ ነገር ግን እስከ 72 ሰዓትም ሊሰጥ ይችላል፡፡ ነገር ግን 72 ሰዓት ካለፈ በኋላም እንዲሰጣቸው የሚጠይቁ አሉ፡፡ መድኃኒቱ ለአንድ ወር የሚወሰድ ሲሆን ከሦስት ወር በኋላ ዳግም ምርመራ ማድረግ የግድ ይላል፡፡ 

በተደጋጋሚ ወደማዕከሉ የኤችአይቪ መከላከያ መድኃኒት ፍለጋ ከሔዱ ወጣትና ታዳጊዎች ጋር ያደረጉትን ቆይታ በማስታወስ የወሲብ ፊልም፣ አልኮል፣ የቀን ላይ ፓርቲ በአንድም ይሁን በሌላ መንገድ ወጣቶቹ ራሳቸውን ለቫይረሱ እንዲያጋልጡ አስተዋጽኦ ማድረጋቸውን ይናገራሉ፡፡ ጤና መኰንን ቅድስት ደግሞ እነዚህ መድኃኒቱን ፈልገው የሚሔዱ ሰዎች መጀመሪያ ላይ ኮንዶም ተበጠሰብን፣ ፖዘቲቭ የሆነ ሰው የተጠቀመበት ስለት ወጋንና ሌሎች ተመሳሳይ ምክንያቶችን ቢሰጡም በመጨረሻ ጥንቃቄ በጐደለው ግንኙነት ለቫይረሱ መጋለጣቸውን እንደሚናገሩ ትገልጻለች፡፡ 

ወጣት ወይም ታዳጊዎች ብቻም ሳይሆኑ ብዙ ያውቃሉ የሚባሉም በተለያየ ምክንያት ራሳቸውን ለቫይረሱ አጋልጠው ፀረ ኤችአይቪ መድኃኒት ፍለጋ ወደ ማዕከሉ እንደሚሔዱ የምትናገረው ጤና መኮንኗ፣ በዚህ ረገድ የምታስተውላቸው ነገሮች ለረዥም ዓመታት ኤችአይቪ ላይ የተሠራው ሰፊ ሥራ ውጤት የት አለ? የሚል ጥያቄ ዘወትር ለራሷ እንድታነሳ እንደሚያስገድዳት ገልጻልናለች፡፡

‹‹በቅርቡ ሁለት የመጀመሪያ ዓመት የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች በአንድ ምሽት በአንድ ሰው መደፈራቸውን ገለጹልኝ፡፡ ከልጆቹ ጋር በደንብ ስንወያይ ግን ደፈረን ካሉት ሰው ጋር አብረው እየጠጡ ማምሸታቸውን ነገሩኝ፡፡ በነገሩ በተወሰነ መልኩ የእነሱም ፈቃድ የነበረበት ይመስላል፤›› የምትለው ጤና መኰንን ቅድስት፣ በተለያየ ምክንያት ራሱን ለቫይረሱ አጋልጦ ያለ አግባብ የኤችአይቪ መከላከያ መድኃኒት ፍለጋ ወደ ማዕከሉ የሚሔድ በሳምንት ቢያንስ አንድ ሰው እንደሚኖር ገልጻልናለች፡፡ 

ጤና መኰንን ቅድስትና ዶክተር አስቴር የባሕሪ ለውጥ እንዲመጣ ሰፊ ሥራ መሠራት እንዳለበት፣ እንዲሁም ትምህርት ቤቶችና ዩኒቨርሲቲዎች ላይ ትልቅ ትኩረት ማድረግ እንደሚያስፈልግ አሳስበዋል፡፡ 

ጉዳዩን በሚመለከት በጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ከሚመለከታቸው ባለሙያ መረጃ ለማግኘት ያደረግነው ጥረት የሕዝብ ግንኙነት ክፍል ብቻም ሳይሆን የቅርብ አለቃዬ ጉዳዩን ሊያሳውቀኝ ይገባል በሚል ምክንያት አልተሳካም፡፡