መነሻ ገጽ - ሌሎች አምዶች - ማህበራዊ ጉዳዮች - ጠለስ - ‹‹የቤት ሥራ››
Buy Valtrex Online Buy Albuterol inhaler Online Buy Prinivil Online

ባለፉት ዓመታት ኤችአይኢን በሚመለከት በተለያዩ መንግሥታዊና መንግሥታዊ ባልሆኑ ተቋማት አዎንታዊ ተፅዕኖ ማሳደር የቻሉ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራዎች ተሠርተዋል፡፡

እነዚህ ሥራዎች የቫይረሱ የሥርጭት መጠን እንዲቀንስ፣ አዳዲስ ኢንፌክሽኖች እንዲቀንሱ፣ ከእናት ወደ ልጅ የቫይረሱ የመተላለፍ ዕድል እንዲቀንስ፣ በቫይረሱ ሕይወታቸውን የሚያጡ ሰዎች እንዳይኖሩና ከኤችአይቪ ጋር በተያያዘ መገለልና አድሎ እንዲቀር አስችለዋል፡፡ 

ነገር ግን ዛሬም ሊተኮርባቸውና ብዙ ሊሠራባቸው የሚገባ የቤት ሥራ የሚሆኑ ጉዳዮች መኖራቸውን ባለሙያዎች ይናገራሉ፡፡ የባሕሪ ለውጥ አለመምጣት፣ በግልፅ ባይሆንም በተዘዋዋሪ ማግለል ውስጥ መኖር፣ ዛሬም ለኑሮ አጋሮቻቸው እንኳ የቫይረሱን በደማቸው ውስጥ መኖር መናገር የማይፈቅዱ ጥቂቶች አለመሆን፣ ዛሬም አስገዳጅ ሁኔታ እስካልመጣ ድረስ የኤችአይቪ ምርመራ ለማድረግ የማይፈቅዱ ብዙዎች መሆን እንደ ችግር የሚታይ ነው፡፡ 

በሌላ በኩል ለኤችአይቪ መከላከልና መቆጣጠር ይለቀቁ የነበሩ ዓለም አቀፍ ፈንዶች እያጠሩ መምጣት፣ የበጀት እጥረት፣ ከቀድሞ ጋር ሲነፃፀር በመገናኛ ብዙኀን እንዲሁም በተለያዩ መድረኮች ስለኤችአይቪ ብዙ አለመባሉ ኤችአይቪን በመዋጋት ረገድ እየተደረገ ያለው እንቅስቃሴ ላይ ጥላ አያጠላም ወይ? የሚል ሥጋት በብዙዎች ዘንድ ፈጥሯል፡፡ 

ይኸው ሥጋት በተንፀባረቀበት አንድ መድረክ ላይ የፌደራል ኤችአይቪ/ኤድስ መከላከያና መቆጣጠሪያ ጽሕፈት ቤት ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ አቶ መስቀሌ ቢራ፣ ሥጋቱ ተገቢ መሆኑን ነገር ግን የሚመለከታቸው ተቋማት በይበልጥ ተጋላጭ የሆኑ ክፍሎች ላይ የማተኮር አካሄድ እየተከተሉ በመሆናቸው እንጂ ዛሬም በመንግሥታዊም ሆነ መንግሥታዊ ባልሆኑ ተቋማት ለኤችአይቪ የሚሰጠው ትኩረት እንደቀድሞው መሆኑን አስረድተዋል፡፡ 

ተመርምሮ ራስን ማወቅ የኤችአይቪን ሥርጭት በመዋጋት ረገድ የመጀመሪያው ዕርምጃ ነው፡፡ ሰዎች በፈቃደኝነት ላይ የተመሠረተ የኤችአይቪ ምርመራ እንዲያደርጉ በሚመለከታቸው አካላት ከማስታወቂያ ጀምሮ በተለያዩ ጊዜያት ተንቀሳቃሽ የምርመራ ማዕከላትን በተለያዩ ቦታዎች በማኖር ሰዎች ተመርምረው ራሳቸውን እንዲያውቁ ሁኔታዎች ይመቻቻሉ፡፡ ነገር ግን ዛሬም የጤናቸው ሁኔታ ግድ እስካላለ አሊያም ምርመራውን እንዲያደርጉ የግድ የሚል ነገር እስካልመጣ የኤችአይቪ ምርመራ ማድረግ ለምን ያስፈልጋል? የሚል ጥያቄ የሚያነሱ ብዙዎች ናቸው፡፡ ራስን ቀድሞ ማወቅ ሌሎችን ከመጠበቅ የራሳቸውን ቀጣይ ጤና ከመታደግም አንጻር ጠቀሜታው ብዙ መሆኑን ባይክዱም፣ መመርመር የሚያሳድረውን የሥነልቦና ጫና እንዲሁም ፖዘቲቭ ሆነው ቢገኙ እውነቱን መቀበል ቀላል አለመሆንን በማንሳት በአቋማቸው መፅናትን ይመርጣሉ፡፡ 

ከጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ያገኘነው የዘንድሮ የዘጠኝ ወር ሪፖርት እንደሚያሳየው፣ በተጠቀሰው ጊዜ ውስጥ በአገሪቱ በፈቃደኝነት ላይ የተመሠረተ የኤችአይቪ ምርመራ ያደረጉ ሰዎች ቁጥር 8,490,991 ነው፡፡ የአምናው ሲታይ ደግሞ ከአንድ ሚሊዮን በላይ እንደነበር በዓመታዊው ሪፖርት ላይ ተመልክቷል፡፡ 

ሰዎች በፈቃደኝነት የኤችአይቪ ምርመራ እንዲያደርጉ የተለያየ የቅስቀሳ ዘመቻ ከማድረግ ይልቅ ተጋላጭ ናቸው ተብሎ የሚታመን ቡድኖችን ለይቶ እንዲመረመሩ ማድረግ ላይ በማተኮር የአቅጣጫ ለውጥ መደረጉን ከጤና ጥበቃ ያገኘነው መረጃ ያሳያል፡፡ ቀደም ባሉት ዓመታት ሁሌም ጳጉሜን አምስት ቀን ሰዎች ምርመራ እንዲያደርጉ ቅስቀሳ ይደረግ የነበረ ቢሆንም አሁን ግን ተጋላጭ ቡድኖች ላይ ወደማተኮር ተሒዷል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ መመርመር ላይ ብቻም ሳይሆን በምርመራ ራስን ከማወቅ በኋላስ መሆን መደረግ ያለበት ምንድን ነው የሚለው ነገር ላይ ትኩረት ተሰጥቷል፡፡ 

ተንቀሳቃሽ የምርመራ አገልግለት የሚሰጡ ጊዜያዊ ጣቢያዎችን በመክፈት ነጻ የኤችአይቪ ምርመራ ከሚሰጡ ተቋማት መካከል የኤችአይቪ ማኅበራዊ አገልግሎት ድርጅት (ኦሳ) አንዱ ነው፡፡ ሰዎች እንደቀድሞ ራሳቸውን ለማወቅ ምርመራ ያደርጋሉን? አገልግሎቱን በሚመለከትስ ድርጅቱ ያደረገው ለውጥ አለወይ? የሚሉ ጥያቄዎችን በድርጅቱ የምክር አገልግሎት ባለሙያ ለሆኑት አቶ ቢራቱ ፈይሳ አንስተን ነበር፡፡ 

‹‹እንደ ቀድሞ ባይሆንም ሰዎች ዛሬም በፈቃደኝነት ራሳቸውን ለማወቅ ምርመራ ያደርጋሉ፡፡ በእርግጥ እዚህ ላይ በትኩረት ሊታይ የሚገባ ነገር አለ፡፡ በተደጋጋሚ የሚመረመሩ ሰዎችም ቁጥር ጥቂት የሚባል ላይሆን ይችላል፡፡ እኛ ግን የስትራቴጂ ለውጥ አድርገናል፡፡ ለቫይረሱ ተጋላጭ ናቸው የምንላቸውን ነው ምርመራ እንዲያደርጉ ለይተን እየተንቀሳቀስን ያለነው፡፡ ለምሳሌ ባል ፖዘቲቭ ቢሆን ሚስትና ልጆችም እንዲመረመሩ እናደርጋለን፡፡ እንዲህ እንዲህ እያልን በተለያየ መልኩ ተጋላጭ የሆኑ ቡድኖች ላይ እናተኩራለን፤›› በማለት መልሰዋል፡፡

ራሳቸውን ለማወቅ ወደ ተለያዩ ጤና ተቋማት ከሚሄዱ ሰዎች መካከል ቀደም ሲልም ተደጋጋሚ ምርመራ ያደረጉ ሰዎች በመኖራቸው ይህን ያህል ሰዎች ራሳቸውን ለማወቅ ምርመራ አደረጉ ሲባል በተደጋጋሚ የሚመረመሩ ሰዎች መኖራቸው ከግምት ውስጥ ሊገባ ያስፈልጋል፡፡ በሌላ በኩል በምርመራ ማዕከሎች የኤችአይቪ ምርመራ የሚያደርጉ ሰዎች ቁጥር ከበፊቱ ጋር ሲነጻጸር እየጨመረ ለመሆኑ ሰፊ ጥናት ካልተደረገ በቀር በምልከታ ወይም በውስን ጥናት የሚመረመሩ ሰዎች ቁጥር ቀነሰ ማለት አስቸጋሪ ይሆናል፡፡ ምክንያቱም የኤችአይቪ ምርመራ የሚሰጥባቸው ማዕከላት ቁጥር ጨምሯልና፡፡

እንደ አቶ ቢራቱ አገላለጽ፣ ‹‹ቀደም ሲል ወደ አንድ ጣቢያ ለምርመራ ሊሄዱ ይችሉ የነበሩ ሰዎች አሁን ሰፊ ምርጫ ስለሚኖራቸው ወደ ተለያየ ቦታ ሊሄዱ ይችላሉ፡፡››