መነሻ ገጽ - ሌሎች አምዶች - ማህበራዊ ጉዳዮች - ምን እየሰሩ ነው? - የቀርከሃው ትሩፋቶች
Buy Valtrex Online Buy Albuterol inhaler Online Buy Prinivil Online
20 March 2013 ተጻፈ በ 

የቀርከሃው ትሩፋቶች

አቶ አዳነ በርሔ የአዲል ኢንዱስትሪያል ባለቤትና ሥራ አስኪያጅ ናቸው፡፡ ከአዲስ አበባ ንግድ ሥራ ኮሌጅ በሒሳብ መዝገብ አያያዝ በዲፕሎማ ተመርቀዋል፡፡

በትምህርት ላይ እያሉ ቢዝነስ ውስጥ እንደነበሩ ይናገራሉ፡፡ በቀርከሃ የሚመረቱ የተለያዩ ምርቶችን በኢንዱስትሪ ደረጃ በማቋቋምም በቀዳሚነት ይጠቀሳሉ፡፡ ከቀርከሃ የሚመረት ጣውላ፣ ስቴክኒ፣ ከሰል፣ ምንጣፍና ተያያዥ ምርቶች በማምረት ለአገር ውስጥና ለውጭ ገበያ ያቀርባሉ፡፡ ከ10 ሚሊዮን ብር በላይ ካፒታል የሚንቀሳቀሰው ኩባንያቸው ወደፊትም ብዙ ራዕይ እንዳለው አቶ አዳነ ይገልጻሉ፡፡ ስላላቸው እንቅስቃሴና ዳዊት ታዬ አነጋግሯቸዋል፡፡  

ሪፖርተር፡- ወደንግድ ሥራ እንዴት ገቡ?

አቶ አዳነ፡- ልጅ ሆኜ ነው የጀመርኩት ማለት እችላለሁ፡፡ ተማሪም ሆኜ ከቤተሰብ ጋር እሠራ ነበር፡፡ ራሴን የመቻል ፍላጐቱ የነበረኝ ለመሻሻል ሳይሆን ለምዝናናበት ነበር፡፡ ከጓደኞቼ የተሻለ ገንዘብ የምይዘው እኔ ነበርኩ፡፡ አባቴ መርካቶ የፕላስቲክና የብረት በርሜል ይሸጥ ነበር፡፡ እሱ ጋ ተጠግቼ ለእሱ ዕቃ አቅራቢም ሆኜ በመሥራት ጭምር የራሴ የሆነ ገንዘብ የምለውን መያዝ ቻልኩ፡፡ በዚህ ምክንያት ተማሪ እያለሁ መኪና መግዛት ችያለሁ፡፡

ሪፖርተር፡- ኢንዱስትሪ ወደማቋቋም እንዴት ገቡ?

አቶ አዳነ፡- በደርግ ጊዜ ሥራ ልሥራ ብለህ ብትነሳ እንዲህ በቀላሉ ፈቃድ አታገኝም፡፡ ዝግ የኢኮኖሚ ፖሊሲ ነበር፡፡ ለማደግ ገደብ ነበረብህ፡፡ በዚያን ወቅት ዕድሜህ ብቻ ነው የሚያድገው፡፡ ገንዘብህ አያድግም፡፡ ምክንያቱም የገንዘብህ የዕድገት መጠን አንድ ቦታ ላይ ይቆማል፡፡ ካፒታልህን ማሳደግም ኩነኔ ነበር፡፡ ከዚህ አንጻር ፈቃድ ለማግኘት ከባድ ስለነበር አንድ ፈቃድ ያለው ምሁር ሥራውን መቀጠል ስላልቻለ ቢዝነሱን መሸጥ ይፈልጋልና ትገዙት እንደሁ ብለው ወዳጆቻችን አማከሩን፤ በዚህ አጋጣሚ ፈቃደኛ ሆንን፡፡ እኔ እንዲያውም በጣም ጉጉ ሆንኩኝ፡፡ ምክንያቱም የጐጆ ኢንዱስትሪ ሒደት ፍላጐቱም ስሜቱም ስለነበረኝ፣ ወዲያውኑ ወሰንን፡፡ ሰውዬውን እንዲያገናኙን አድርገን ተስማምተንም ፈቃዱን ገዛነው፡፡

ሪፖርተር፡- በወቅቱ ፈቃዱን የሸጡላችሁ ሰው በዚያ ፈቃድ ሥራውን ጀምረው ነበር? ፈቃዱ ምን ዓይነት ሥራ ነበር የሚያሠራችሁ?

አቶ አዳነ፡- በራሳቸው መንገድ ፈቃዱን አውጥተው ሥራውን ጀምረውት ነበር፡፡ እኛ በ1978 ነበር የገዛነው፡፡ በዚህ መንገድ ሥራውን ጀመርን፡፡ በዚያን ወቅት እንዲህ ላሉ ኢንዱስትሪዎች የሚፈልጉትን የውጭ ምንዛሪ በኮታ ያገኙ ነበር፡፡ ባለፈቃዱም መደብ ነበረው ተራ ጠብቆ የውጭ ምንዛሪ ያገኛል፡፡ በየሦስት ወሩ ዕቃ የሚመጣበት 5 ሺሕ ዶላር ይፈቀድ ነበር፡፡ አፈቃቀዱም በንግድ ሚኒስቴር በኩል በኮታ የምትወስደው ነው፡፡ ፈቃዱን ስንገዛው አንድ የንግድ ምልክት ነበር ያለው፡፡ ‹‹ፍላወር ኪንግ ባለአንድ ዘንቢል›› የሚል ሰንደል ምርት ነው፡፡ በዚሁ ስያሜ የተመረተውንም ሰንደል ገበያ ውስጥ ይዘን ገባን፡፡ ሕትመቱ እንዲሻሻል አደረግሁ፡፡ ለጊዜው ሰንደሉ ላይ በኢትዮጵያ የተመረተ የሚል አልነበረበትም፡፡ እንዲባልም አይፈለግም ነበር፡፡  

ሪፖርተር፡- ምክንያቱ?

አቶ አዳነ፡- ያኔ የአገር ውስጥ ምርት በፍላጐትና በአቅርቦት መካከል መራራቅ ስለነበር ነው፡፡ በዚህም ምክንያት የተመረተው ሁሉ ይሸጣል፡፡ ጥራት አለው የለውም የሚባል ነገር የለም፡፡ ስለጥራት አይታሰብም፡፡ ብዙ ኢንዱስትሪ የለም፡፡ ተወዳዳሪ የለም፡፡ በጥቅሉ የነበርንበት ሥርዓት ለውድድርና ለጥራት የሚጋብዝ አልነበረም፡፡ አመለካከታችንና ስነልቦናችን የተገዛበት ጊዜ ስለሆነ የማንኛውም ምርት ጥገኞች ነን፡፡ ጥራት ከኢንዱስትሪ ጋር ያለውን ተያያዥነት አናውቀውም፡፡ ዝም ብለህ ማምረት ነው፡፡ ስታመርት ደግሞ በቅድሚያ ገንዘብ ተቀብለህ ነው የምትሸጠው፡፡ ምርቱን ሰጥተኸው ሳይሆን ገንዘቡን ሰጥቶህ ነው ሸቀጡን የምትሰጠው፡፡

ሪፖርተር፡- ገበያው ላይ አቅርቦትና ፍላጐት ስለሌለ ነው ወይስ ሌላ ምክንያት ስለነበር ነው እንዲህ ዓይነቱን መንገድ የምትከተሉት?

አቶ አዳነ፡- በዚያ ሥርዓት ውስጥ እኮ ሁሉም የሚያደርገው ነው፡፡ ፍላጐት ሁልጊዜ አለ፡፡ አቅርቦቱ ግን ፍላጐቱን አይመጥንም፡፡ ምክንያቱም በማንኛውም ሥርዓት ውስጥ ሕዝብ ያድጋል ይዋለዳል ራሱን ይችላል፡፡ ፍላጐቱም የዚያኑ ያህል ይጨምራል፡፡ ይህ ሒደት ነው፡፡ ስለዚህ መሠረተ ልማቱም ሆነ የምርት አቅርቦቱ የዚያኑ ያህል ካላደገ በፍላጐትና በአቅርቦት መካከል መራራቁ ከዕለት ወደ ዕለት እየሰፋ ነው የሚሄደው፡፡ በወቅቱም ይህ ክፍተት ሰፊ ስለሆነ ጥራት የሚባለውን ነገር ሳታስብ የቻልከውን እያመረትክ፤ ትሸጣለህ፡፡ ስለ ጥራት የሚጨነቅ አልነበረም፡፡

ሪፖርተር፡- ስለዚህ በወቅቱ የምታመርቱትን ትሸጣላችሁ እንጂ የገበያ ችግር አልነበረም ማለት ነው?

አቶ አዳነ፡- አዎ! የቻልነውን እንሠራለን፡፡ ሰንደሉን እያመረትን እንሸጣለን፡፡ ግን የምርት ብዛት አልነበረንም፡፡ ሰንደሉን እንዲያመርቱ የቀጠርናቸው 45 ሴቶች ነበሩ፡፡ ለእነዚህ ሴቶች በጠቅላላ እንከፍል የነበረው አምስት ሺሕ ብር አይሞላም፡፡ እውነት ለመናገር 70 ብር ደመወዝ እየከፈልን እያሠራን እንኳን ይህንን ሥራ ለመሥራት ብዙ ሰው ይመጣል፡፡ በ70 ብር ደመወዝ ሠራተኛ እንቀጥራለን ብለን ማስታወቂያ ስናወጣ 300 እና 400 ሰው ይመጣል፡፡ ሥራ ፈላጊው ብዙ ነበር፡፡

ሪፖርተር፡- ከእዝ ኢኮኖሚ ወደ ነፃ ገበያ ሥርዓት በኋላ የሥራ እንቅስቃሴያችሁን እንዴት ቀጠላችሁ?

አቶ አዳነ፡- የመንግሥት ለውጥ መጣ፡፡ ለውጡ አንዱ ኢኮኖሚውን መለወጥ ነው፡፡ ሒደቱን መለወጥ ነው፡፡ ተለወጠ፡፡ እርግጥ መጨረሻ አካባቢ ቅይጥ ኢኮኖሚ የሚል ነገር መጥቶ ነበር፡፡ በቅይጥ ኢኮኖሚው ውስጥ አንዱ ዕቅድ ካፒታልህን ማሳደግ ነው፡፡ ይህም ማለት ከነበረህ ቁመት አሥር ሴንቲ ሜትር ተጨምሮልሃል እንደማለት ነው እንጂ ሙሉ ለሙሉ እንድትሠራ የሚያደርግህ አይደለም፡፡ ክፍት አልነበረም፡፡ የቅይጥ ኢኮኖሚው መፈቀድ ጋር ተያይዞ የግሉ ክፍለ ኢኮኖሚ ሒደት ማደግ አለበት በሚለው ጭብጥ ዙሪያ በወቅቱ ውይይት ተደርጐ ነበር፡፡ እኛም ተጋብዘን እንድንወያይበት ተፈልጐ ነበር፡፡ ነገሩ እንግዳ ነገር ሆነብን፡፡ ሐሳብም ለመስጠት ፈራን፡፡ ምክንያቱም ዝግ በሆነ ሥርዓት ውስጥ ስለነፃ ኢኮኖሚ ማውራት ትንሽ ድፍረት ይጠይቃል፡፡

ኢንዱስትሪ በሌለበት ስለነፃ ገበያና ውድድር ማውራትም ከባድ ሆኖ ታይቶን ነበር፡፡ በኋላ ላይ ግን ለውጡ መጣና ነፃ ገበያ ሥርዓት ተፈቀደ፡፡ ተወዳዳሪነት ተከተለ፡፡ ጥራት የሚለውም ነገር መጣ፡፡ አሁን ቃሉንም ተግባሩንም ወደመተግበር ገባን፡፡ ነፃ ኢኮኖሚ ሥርዓት ውስጥ የሚያዋጣው በጥራት ማምረትና ተወዳሪ ሆኖ ለገበያ መቅረብ ነው፡፡ እስከዚያ ድረስ እኛ ውድድር አናውቅም፡፡ ያመረትነው ምርት ሁሉ ይሸጣል፡፡ ምንም ብናመርት እንሸጥ ነበርና ምንም ችግር አልነበረብንም፡፡ ለውጡ ግን ምርታችንን ከጥራት ጋር እንድናያያዝ አደረገን፡፡ እንዲያውም የሰንደሉን ሽታ ራሳችን ስናሸተው ይሸት ነበር ወይ? ወደሚለው ጥያቄ እስከመጠየቅ ደረስን፡፡ በመሃል ግን ገበያው በሌሎች የሰንደል ምርቶች ተጥለቀለቀ፡፡ የእኛን የሚያየውም ጠፋ፡፡ እንደቀድሞው መሸጥ ሳንችል ቀረን፡፡ ሥራውንም አቆምን፡፡ 

ሪፖርተር፡- ይህ ያልታሰበ ነገር ሲገጥማችሁ ምን ዓይነት ውሳኔ ወሰናችሁ?

አቶ አዳነ፡- ከዚያ በኋላ ለአሥር ወር ያህል የሰንደል ማምረቻው ሥራ አቆመ፡፡ ግን ደመወዝ እንከፍላለን፡፡ ይህንን እያደረግን በሥራችን ለመቀጠል ምን ማድረግ አለብን የሚለውን ወሳኝ ጉዳይ ማየት አስፈለገን፡፡ ገበያው ምን ይፈልጋል? እንዴት ማምረት አለብን? ሥራችንን እንዴት ቀጣይ ማድረግ እንችላለን? ብለን ማሻሻል እንደሚኖርብን ወሰንን፡፡ ምርቱን፣ መጠቅለያውን፣ የሽታውን ዓይነት ተወዳዳሪ እንዲሆን ማድረግ፣ የምርት ዓይነቶችን ማብዛት እንደሚያስፈልግ ተገነዘብን ምርቶቻችን ካልተሻሻሉና የጥራት ቁጥጥር አድርገን ለውጥ ካላመጣን አደጋ መሆኑን ተገነዘብን፡፡ ከዚህ ጐን ለጐንም መንግሥት ለመልሶ ማቋቋሚያ የውጭ ምንዛሪ ለአነስተኛ የጐጆና ሌሎች ኢንዱስትሪዎች በደንብ እየሰጠ ነበርና አጋጣሚውን ተጠቀምንበት፡፡ ወደማሻሻሉ ገባን፡፡

ለውጥ መጣ፡፡ ማደግ አስፈላጊ መሆኑን አየን፡፡ ተወዳዳሪ ሆንን፡፡ በዚህ ልምድ ሌሎችንም ምርቶች ማሳደግ ስለሚያስፈልግ መንቀሳቀስ ጀመርን፡፡ የውጭ ጉዞ ጭምር አድርገን ልምድ ቀሰምን፡፡ በቢዝነስ ዓለም መንቀሳቀስ ትምህርት ነው፡፡ ዕውቀት ነው፡፡ ወደ ውጭ ሄዶ ማየት ትምህርት ነው፡፡ ይህንንም እንቅስቃሴ በመጀመራችን ወደውጭ ሔደን የአመራረት ስልታቸውን በመመልከት እነሱ የጐደላቸውን እኛ አሟልተን በመቅረብ ጥሩ ተወዳዳሪ አደረገን፡፡ ምርቱ ላይ ምን መለወጥ እችላለሁ ብለህ ነው የምትገባው እንጂ እሱ ያመረተውን ኮፒ አድርገህ አይደለም፡፡ ከዚህ አንጻር የተሻለ እያመረትን ሄድን፡፡  

ሪፖርተር፡- ለውጥ አመጣን ተወዳዳሪ መሆን ቻልን ስትሉ ምን ዓይነት ለውጦችን አድርጋችሁ ነው?

አቶ አዳነ፡- ዛሬ ወደኋላ ተመልሰን ስናየው የሚገርመንን ነገር ልንገርህ፡፡ አንድ ለሰንደል የምትሆነውን ስንጥር (ስቲክ) አንድ ሴት ቢላዋ ይዛ ቀርከሃውን እየሰነጣጠቀች እና እየሰነጣጠረች በእጅዋ ነበር የምትሠራው፡፡ እያንዳንዷ ስቲክ በቢላዋ ተፍቃ ነበር የምትሠራው፡፡ ይህንን መለወጥ አንዱ ሥራችን ነበር፡፡ በኋላ ላይ ግን ብዛት ጥራት መኖር አለበት ብለን ወደማሽን ቀየርነው፡፡ ማሽኑን እዚህ ለማሠራት ብዙ ባለሙያዎችን አማክሬ ነበር፡፡ ባለመቻሉ ሄጄ ማሽኑን ገዛሁ፡፡ በዚህ ጉዞዬ ግን የቀርከሃ ገነትን ተመልክቻለሁ፡፡ ታይዋን የቀርከሃ ትልቅ ገነት ነው ቢባል ማጋነን አይደለም፡፡ እዚያ ሆኜ የእኛን ሥራ ሳስብ ገረመኝ፡፡ በእጃቸው ቀርከሃ እየሰነጣጠቁ ስቲክ እያደረጉ ሰንደል ሲሠሩ የነበሩና በዚህም መንገድ ተሠርቶ ይኖር እንደነበር ሳስበው አሁንም ይገርመኛል፡፡

ሪፖርተር፡- ስለዚህ ዛሬ ቀርከሃን ግብዓት በማድረግ የገነቡት ኢንዱስትሪ ዋነኛ መነሻ ይሄ ጉዞዬ ነው ብለው ያስባሉ?

አቶ አዳነ፡- ልክ ነው ለዛሬው ሥራዬ መነሻ የታይዋን ጉዞዬ ነው፡፡ ጉዞ ዕውቀት ነው ያልኩት ለዚህ ነው፡፡ ታይዋን ያየሁት ነገር ቀርከሃ ብዙ የልማት ሥራዎች ሊሠራበት የሚችል መሆኑን ነው፡፡ ስቲኩ በማሽን ነው የሚሠራው፣ ሰንደሉ መጋረጃው ስቲክኒውና ሌሎችም ምርቶች የሚሠሩት በማሽን ነው፡፡ እዚያ ሆኜ ወዲያው የወሰንኩት መጀመሪያ ስቲኪን ማምረት አለብን፡፡ ስቲክኒውን ስናመርትም ለውጥ ባለው መንገድ መሆን እንዳለበትም ተገነዘብኩ፡፡ የሰንደሉም የአመራረት ሒደት ዘመናዊ እንዲሆን ሠራን፡፡

ሪፖርተር፡- ቀርከሃን ግብዓት ወዳደረገ ኢንዱስትሪ እንዴት ልትገቡ ቻላችሁ?

አቶ አዳነ፡- በደረጃ የሆነ ነው፡፡ በሒደት የመጣነው፡፡ አጠቃላይ ነገሩ ሒደት እንጂ የሐሳብ ምንጭ አይደለም፡፡ ሰንደል የሚሠራው ከቀርከሃ ነው፡፡ እዚህም በቢላ እየተሰነጠቀ የሚሠራው ስቲክ በቀርከሃ ነው፡፡ ስለዚህ የቴክኖሎጂ ቀመስ የሆነው የሥራ ሒደት ከታይዋን ተቀስሞ መጣ፡፡ አብሮ ስቴክኒ በማምረት በጥሩ ሁኔታ በነጠላ አሽጐ ለሆቴሎች ማቅረብ ተቻለ፡፡ ስቴክኒ በነጠላ አሽጐ ማቅረብ ለጤና ዋስትና ነው፡፡ በተለይ በህንድ ከተወሰነ ደረጃ በላይ ያሉ ሆቴሎች ቁጥጥር ከሚደረግባቸው ወይም ማሟላት ከሚገባቸው ነገሮች ውስጥ አንዱ በነጠላ የታሸገ ስቴክኒ ከሚሸጡት ምግብ ጋር ማቅረብ አለባቸው፡፡ አለበለዚያ ሆቴሉ ይታሸጋል፡፡ በነጠላ ያልታሸገ ስቴክኒ ማቅረብ አይቻልም፡፡ እኛ አገር በሒደት ሊመጣ ይችላል፡፡ እንዲህ ዓይነቱ ጥንቃቄ የተሞላበት አሠራር ለተመጋቢ ዋስትና ነው፡፡

ዛሬ ብዙ ተላላፊ በሽታዎች አሉ፡፡ ስለዚህ ነፃ የሆነና የታሸገ ስቴክኒና በካፕ ተደርጐ ከሚቀርብልህ ስቲክኒ ልዩነት አለው፡፡ ብዙ ጊዜ በካፕ የሚቀርብልህ ምቹ አይደለም፡፡ ከቦታ ቦታ ስታዘዋውረው ሊፈስ ይችላል፡፡ ከመሬት ላይ ተለቅሞ ተመልሶ ካፕ ውስጥ እንዲገባ ሊደረግ ይችላል፡፡ ይሄ ያጋጥማል፡፡ ስለዚህ ዓለም ወደተሻለና ጤናማ ወደሆነ አሠራር እየተሸጋገረ በመሆኑ የእኛም መንገድ ይህ መሆን አለበት፡፡

ሪፖርተር፡- እናንተ በስቴክኒ ምርቶቻችሁ የምትታወቁ ቢሆንም አሁንም ከውጭ የሚገቡ የስቴክኒ ምርቶች አሉ፡፡ የስቴክኒ ማምረቻ ጥሬ ዕቃ ቀርከሃ ከሆነና ይህም ምርት እንደልብ ካለ ከውጭ ለምን ይገባል አስፈላጊ ነው?

አቶ አዳነ፡- በነጠላ የታሸገ ስቴክኒ አይገባም፡፡ በነጠላ የታሸገ ስቴክኒ እኛ ጋ ብቻ ነው ያለው፡፡ ምክንያቱም አትመን የምንሰጠው በሆቴልና በሌላው አድራሻ ስም ነው፡፡ ሆቴሎች በሙሉ ከእኛ ነው የሚወስዱት፡፡ በካፕ ያለው ለምን ይገባል የሚለው ጥያቄ አግባብ ነው፡፡ እኛም በእርግጥ በሙሉ አቅም ትኩረት ሰጥተን ለገበያ አላቀረብንም፡፡

ሪፖርተር፡- ምክንያታችሁ ምንድነው?

አቶ አዳነ፡- ማሸጊያ ነው፡፡ እኛ አገር የጐደለን ነገር የማሸጊያ ኢንዱስትሪዎች አለመስፋፋቱ ነው፡፡ ሌሎቹ እየቀደሙን ያለው የመጠቅለያና የማሸጊያ ቴክኖሎጂያቸውን ማሳደጋቸው ነው፡፡ በሁሉም ዘርፍ ያለ ችግር ነው፡፡ እኛ መጠቅለያውን በአግባቡ ተወዳዳሪ በሚያደርገን ዋጋና ጥራት ብናገኝ እናቀርባለን፡፡ በነገራችን ላይ በራሳችን ምልክት ራሳችን ኃላፊነት ወስደን ለየት ያለ መጠቅለያ ጠንከር ባለ ፕላስቲክ አድርገን ስቴክኒውን እናቀርባለን፡፡

ሪፖርተር፡- በካፕ ማለትዎ ነው?

አቶ አዳነ፡- በካፑም ስናቀርብ ቆይተናል፡፡ ግን የፒፒሲ ፋብሪካዎች ካፑን የሚያቀርቡልን ዋጋ ከስቴክኒው በላይ ሆነ፡፡ ከውጭ ከሚገባው ምርት ጋር ተወዳዳሪ ሊሆን የሚችል የጥራት ደረጃ ያለው ምርት የላቸውም፡፡ ይህ በሆነበት ሁኔታ ዋጋቸው ከፍተኛ ነው፡፡ ምክንያቱም ጥሬ ዕቃውን ከውጭ ነው የሚያስገቡትና እነሱ ላይም መፍረድ ይከብዳል፡፡ በነገርህ ላይ በነጠላ ካሸግን የምናቀርበው ስቴክኒ ለእኛ ብዙ ጠቀሜታ ይሰጠናል ብዬ አይደለም፡፡ ቴክኖሎጂው በመግባቱ በብሔራዊ ደረጃ ትርፌ ነው፡፡ ይህ በነጋዴ አስተሳሰብ ተቀባይነት ላይኖረው ይችላል፡፡ ለእኔ ግን ቴክኖሎጂው ገብቶ ሆቴሎች በዚህ በመጠቀማቸው ትልቅ ዕርካታ ይሰጠኛል፡፡ አሁን ባለው አቅማችን በቢሊዮን የሚቆጠር ስቴክኒዎች ማምረት እንችላለን፡፡ አሁን ለገበያ የምናቀርበው ምርት በአነስተኛ አቅም የሚሠራ ስለሆነ ተጨማሪ ምርቶችን በማመረት የአገር ፍላጐትን ለመሙላት እንሠራለን፡፡ 

ሪፖርተር፡- በኢንዱስትሪያችሁ ከቀርከሃ አምስት ዓይነት ምርቶችን እያመረታችሁ ነው፡፡ ወደ እንዲህ ዓይነት የምርት ሒደት እንዴት ገባችሁ?

አቶ አዳነ፡- በፋብሪካችን አምስቱም ማምረቻዎች የሚጠቀሙት አንድ የቀርከሃ ዘንግ ነው፡፡ የመጀመሪያው ክፍል ለጣውላ ለሚውል ይሄዳል፡፡ ቀጥሎ ለመጋረጃ ይሄዳል፡፡ ከዚህ የሚተርፈው ደግሞ ለሰንደል ማምረቻ ይውላል፡፡ ከዚህ ውጭ ያለው ደግሞ ስቴክኒ ይመረትበታል፡፡ በመጨረሻ ላይ ብናኙና ቁርጥራጩ ደግሞ ከስሎ ለከሰልና ለሰንደል ምርታችን በተጨማሪ እንደጥሬ ዕቃ ይውላል፡፡ ስለዚህ አንዱዋ የቀርከሃ ዘንግ በዚህ መንገድ ለእያንዳንዱ ምርት ሒደት ተከፋፍላ መሠራቷ ግብዓቱ ፈጠራቸው እንጂ እኛ የግድ የተለያዩ ፋብሪካዎች ሆነው መያዛችን አይደለም፡፡ አንዱ የቀርከሃ ዘንግ የፈጠራቸው ናቸው፡፡ ለምሳሌ የመጨረሻው የከሰል ምርታችን ግድ ሆኖብን የፈጠርነው ነው እንጂ በእኛ አስተሳሰብ የፈጠርነው አይደለም፡፡  

ሪፖርተር፡- ግድ ሆኖ የተፈጠረነው ያሉት ለምንድን ነው?

አቶ አዳነ፡- ግድ ያደረገው ተረፈ ምርቱ ግቢውን እየሞላ ስላስቸገረን ነው፡፡ ተረፈ ምርቱን የሚወስዱልን ነበሩ፡ በመሃል አቆሙ፡፡ ይህ ተረፈ ምርት የሚወስድብን ቦታ በመስፋቱ በቃ ከሰል ማምረት አለብን ወደሚለው ሐሳብ ገባን፡፡ ሐሳቡ እንደመጣልን ጥናት ይካሄድ ሳይባል ቀጥታ ዕርምጃ ተወሰደ፡፡ ምክንያቱም ለምርቱ የሚያስፈልገው ዋናው ግብዓት ወጪ የለውም፡፡ ስለዚህ የማምረቻ መሣሪያውን አፈላልገን ገዛን፡፡ ከሰሉ ምን ያህል ይሸጣል፣ የት ይሸጣል የሚለው ጥያቄ የለም፡፡ ለአንዲት ነገር ብቻ መልስ ሰጥቷል፡፡ ለአካባቢ ጥበቃ በሚኖረው አስተዋጽኦ በፋብሪካው ደን መቆረጥን እንዲቆም እናደርጋለን፡፡ ሕገወጥ ከሰል ማክሰልንና የደን ጭፍጨፋን ይገድብልናል፡፡

ኢትዮጵያ ውስጥ የቀርከሃ ከሰል አጥጋቢ ሆኖ ከተገኘ ከግብርና ሚኒስቴር ጋር በመተባበር አንድም ደን ለከሰል እንዳይቆረጥ የሚለውን ጥብቅ ዕርምጃ ይወሰድ የሚለውን ድምፅ አሰምተን ልናቆም እንችላለን፡፡ ስለዚህ ለኢንሻይሮሜንት ትልቅ አስተዋጽኦ አለው፡፡ ሁለተኛው ደግሞ በኢንዱስትሪ የምናመርተው የቀርከሃ ከሰል ካርቦን ሞኖክሳይዱ ዝቅተኛ ነው፡፡ ጪስ አልባ ነው፡፡ እኛ በር ዘግታችሁ ከሰሉን አንድዱ ማለታችን አይደለም፡፡ እሱም ቢሆን ይገላል፡፡ እንደዚያኛው ከሰል ግን ጭስ ኖሮት ካርቦንሞኖኦክሳይድ ኖሮት አደጋ ያደርሳል ተብሎ አይታሰብም፡፡ በጐረቤት አገሮች እንዲህ ላለው ከሰል ምርት የገበያ ፍላጐት በጣም ከፍተኛ ነው፡፡ ምርቱን ከጀመርን በኋላ ሳናስተዋውቅ ነው ወደ ገበያ የገባነው፡፡ እንዲህ ዓይነቱ የከሰል ምርት አሁንም የውጭ ገበያ አለው ወደመካከለኛው ምሥራቅ ልከናል፡፡ አሁንም ገበያው ቢኖርም መድፈር ነው የተቸገርነው፡፡

ሪፖርተር፡- ለመድፈር ለምን ፈራችሁ?

አቶ አዳነ፡- ምክንያቱም ጥያቄው በጣም ብዙ ነው፡፡ በጣም ብዙ ቶን ማምረት አለብን፡፡

ሪፖርተር፡- በዚህ ደረጃ ለማምረት አቅም መፍጠር አይቻልም?

አቶ አዳነ፡- ቦታም አቅምም አቅርቦትም ያስፈልጋል፡፡ መዘጋጀት ያስፈልጋል፡፡ የውጭ ገበያ ለመግባት ደግሞ የከሰል ገበያ ቀጣይነት አለው፡፡ የአገር ውስጥ ገበያንም አይተነዋል፡፡

ሪፖርተር፡- በአገር ውስጥ ያለው የምርቱ ተቀባይነት ምን ያህል ነው?

አቶ አዳነ፡- በአገር ውስጥ ገበያ እስካሁን ያመረትነው ስቶክ ከሌለን፤ መጋዘን ውስጥ የማይቀመጥ ከሆነ ፍላጐቱ እንዳለ ትረዳለህ፡፡ ምርቶቻችን አይቀመጡም፡፡

ሪፖርተር፡- በኢንዱስትሪ የሚመረተው ከሰል በተለምዶ ከሚታወቀው ከሰል በዋጋ ደረጃ ያለው ልዩነት ምን ያህል ይሆናል?

አቶ አዳነ፡- በተለምዶ ከምናውቀው ከሰል ይረክሳል ብዬ ብናገር ማጋነን አይደለም፡፡ በጣም ይረክሳል፡፡ ሌሎች ጥቅሞችም አሉ፡፡ ለምሳሌ በተለምዶ የምናውቀውን ከሰል ገዝተህ ለማስቀመጥ ያስቸግራል፡፡ ለሱ ብቻ የሚሆን ቦታ ካላዘጋጀህ ብዙ ነገር ያበላሽብሃል፡፡ እኛ የምናመርተው ከሰል በቪላ ቤትህ ጓዳ በማንኛውም ቦታ ሼልፍ ላይ ልታስቀምጠው ትችላለህ፡፡ ብናኝ የለውም፣ አካባቢውን አያበላሽም፡፡ ውዳቂ የለውም፡፡ ሙሉ ለሙሉ አክስለህ የምትጠቀምበት ነው፡፡ ለረዥም ጊዜ ትጠቀምበታለህ ሌላው ቀርቶ የማሸጊያ ማዳበሪያውን ለሌላ አገልግሎት ልትጠቀምበት ትችላለህ፡፡

ሪፖርተር፡- ከቀርከሃ ግብዓትነት ለመጠቀም የሚመረቱ በርካታ ምርቶች ቢኖሩም በኢትዮጵያ ውስጥ የቀርከሃ ኢንዱስትሪ እጅግ ውስን ነው፡፡ እናንተ በዘርፉ ከመቆየታችሁ አንጻር ዘርፉን አሁን ከሚገኝበት ደረጃ ከፍ ለማድረግ ምን አቅዳችኋል? ከዚህ በኋላስ ምን ትሠራላችሁ?

አቶ አዳነ፡- የቀርከሃን ምርት በዓለም ከፍተኛ ደረጃ ያደረሰችው ቻይና ናት፡፡ ምክንያቱም በታሪክ አጋጣሚ የቀርከሃ ምርት ስለነበራትና ራሳቸውንም ለማኖር ከአምስት ሺሕ ዓመት በፊት ለምግብ፣ ለቤትና ድልድይ፣ ለጦር መሣርያ ጭምር በቀርከሃ ይጠቀሙበት ነበር፡፡ ወደኋላ መለስ ብለን ስናይ ወረቀት ሳይቀር ከቀርከሃ የተሠራ ነው፡፡ ስለዚህ እኛም አሁን ዓለም የደረሰበትን የቀርከሃ ቴክኖሎጂ ተከታትለን መድረስ ነው፡፡ ፓናል ያመርታሉ እኛም ፓናል እናመርታለን፡፡ ወረቀት ያመርታሉ፣ እኛም ወረቀት ወደማምረት መግባት ዓላማችን ነው፡፡ ኢትዮጵያ በቀርከሃ የሚመረቱ ምርቶችን ለማምረት አቅሙ አላት፡፡ ሀብቱም ስላላት ከአካባቢ ጥበቃው ጋር አስተሳስረህ ዓለም የደረሰበት ደረጃ ማድረስ ነው፡፡ ብዙ ጊዜ ሥራችንን ከአካባቢ ጥበቃ ጋር የምናያይዘው፣ መሪ ዓላማችንም ከዚህ ሐሳብ ጋር የተጣመረ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- በዓለም አቀፍ ደረጃ በቀርከሃ የሚመረቱ ምርቶች ከፍተኛ ተቀባይነት እያገኙና ለአገልግሎት እየዋሉ ብዙ ጥቅም እያስገኙም ነው፡፡ በኢትዮጵያ ከቀርከሃ የሚመረቱ ምርቶችን ምን ያህል ተቀባይነት አላቸው? የተገልጋዩ አስተያየት ምን ይመስላል?

አቶ አዳነ፡- እንደአምራች ግንዛቤው ያላቸው ሰዎች በሙሉ ምርቶቻችንን ይቀበላሉ፡፡ አይደለም ግንዛቤው ያላቸው ሰዎች ያዩ ሰዎች ግንዛቤውን ይፈጥሩና ሁሉም ይቀበሉታል፡፡ ገና የሚያረካ ምርት አላቀረብንም፣ ለማስተዋወቅ አልበቃንም፡፡ ሰው በባህላዊ መንገድ እያመረተ ነው፡፡ እነሱም እያስተዋወቁ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ኢትዮጵያ በቀርከሃ ምርትዋ በአፍሪካ ቀዳሚ ነች ይባላል፣ አንድ ሚሊዮን ሔክታር ቀርከሃ እንዳለም ይነገራል፡፡ ይህንን ያህል ሀብት እያለ ከዘርፉ ተጠቃሚ ሆናለች ማለት ይቻላል?

አቶ አዳነ፡- የቀርከሃ ሀብት አለ ብሎ ለኅብረተሰቡ ግንዛቤ ለመስጠት በርግጥ በአፍሪካ አንደኛ ነች፡፡ በተለይ የቆላ ቀርከሃ ሰፊ ሽፋን አለው፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ አንድ ሚሊዮን ሔክታር ቀርከሃ አለ ይባላል፡፡ የተመዘገበውም ያልተመዘገበም ሊኖር ይችላል፡፡ ይህ እ.ኤ.አ. በ2000 የተጠና ነው፡፡ ማሻ ላይ በሁለት ዓመት ልዩነት ሄጄ ያየሁትን ልንገርህ፣ በማሻ አካባቢ ያለው ቀርከሃ አበባ ያወጣል ይረግፋል፡፡ እንደገና ይተካል፡፡ ነገር ግን ቀርከሃን ካልተጠቀምንበት እየጠፋ ነው የሚሄደው፡፡ በአንድ ወቅት የቤኒሻንጉልንም የቀርከሃ ምርት አይቻለሁ፡፡

ፊት ለፊቱ ስለሚቆረጥ እየተጠቀጠቀ ነው የሚሄደው፡፡ ምርቱ እንዲበዛ መቆረጥ ያስፈልጋል፡፡ ለምሳሌ የደን ሀብትን መቁረጥ ሕገወጥ ነው ይባላል፡፡ በቀርከሃ ግን ተቃራኒ ነው፡፡ ቀርከሃን መቁረጥ ሕጋዊ ነው፡፡ ይመከራል፡፡ በሦስት ዓመት ስለሚደርስ ቆርጠህ ማገዶም ቢሆን ማድረግ አለብህ፡፡ በዚህ መንገድ ልማቱን ትጠብቃለህ፡፡ ታበዛዋለህ፡፡ የሳር ዘር ነውና እየፈላ ነው፡፡ ቤኒሻንጉል ውስጥ ያለውን ዘልቀን ስንገባ መሃሉ ባዶ ነው፡፡ ካልተጠቀምክበት ይጠፋል፡፡ ከዚህ አንጻር እንደተጠናው ጥናት አንድ ሚሊዮን ሔክታር የሚሆን ቀርከሃ አለን ወይ? ልትል ትችላለህ፡፡ ቻይናዎች የቀርከሃ ሀብታቸው እየጨመረ የሄደው እየቆረጡ ስለሚጠቀሙበት ነው፡፡ እኛ አልተጠቀምንበትም፡፡ ምን ያህል ተጠቅመንበታል የሚለውን ብናሰላ 0.01 በመቶ አይሆንም፡፡ እርግጥ የቀርከሃ ሀብት ያለበት አካባቢ በኢንዱስትሪ ምርት ሒደት ውስጥ ለማስገባት ገበሬው ግንዛቤ ያስፈልገዋል፡፡ ጋባዥ መሆን አለበት የሚል እምነት አለኝ፡፡

በየአካባቢዎቹ ወረዳና ቀበሌ ድረስ ያሉ ባለሥልጣናት የቀርከሃን ምርት ለማሳደግ ከፍተኛ ኃላፊነት አለባቸው፡፡ በከፍተኛ ኃላፊነት ደረጃ ላይ የሚታየው ፍላጐት እንደተጠበቀ ሆኖ ወደታች ስትወርድ ጉድለት አለ፡፡ ታች ድረስ አይተነዋል፡፡ ሥራ ለመሥራት ብለን ከስረን የተመለስንበት ሁኔታ አለ፡፡    

ሪፖርተር፡- በቀርከሃ ለመጠቀም ታች ባሉ አመራሮች ተፈጠረ የምትሉት ችግር ምንድን ነው?

አቶ አዳነ፡- ብዙ ችግሮች አሉ፡፡ ዝቅተኛ አመራር ደረጃ ክፍተት አለ፡፡ የገበሬው አንገት ላይ የቆሙት እነሱ ናቸው፡፡ ይህ ጉዳይ መታረም አለበት፡፡ አንድ ወቅት ወደባሌ ሔደን ገበሬን የሚጠቅም ፕሮጀክት ተቀርጾ ይህም በውል ተደግፎ ለመሥራት ያቀድነው ሥራ ታች ባሉ አመራሮች ተደናቅፏል፡፡ ገበሬው ሸጦ እንዳይጠቀም ተደርጓል፡፡ ምክንያቱ ግን ግልጽ አይደለም፤ ይህ መታረም አለበት፡፡ የቀርከሃ ጠቀሜታ በግልጽ መታወቅ አለበት፡፡ ገበሬው ስለሚጠቀምበት ለአካባቢ እንክብካቤም ወሳኝ በመሆኑ ጭምር ታች ያሉ አመራሮች አመለካከታቸው ሊቀየር ይገባል፡፡