መነሻ ገጽ - ሌሎች አምዶች - ማህበራዊ ጉዳዮች - ሴት - የሴቶች መበልጸግ ፋይዳ
Buy Valtrex Online Buy Albuterol inhaler Online Buy Prinivil Online
24 March 2013 ተጻፈ በ 

የሴቶች መበልጸግ ፋይዳ

‹‹ዓለም ላይ ካሉ ደሀ ማኅበረሰቦች ውስጥ 70 በመቶዎቹ ሴቶች ናቸው፡፡

እነዚህ ሴቶች ገቢ እንዲኖራቸውና ድህነትን እንዲቀርፉ ቢደረግ ከነቤተሰቦቻቸው የተሻለ ይመገባሉ፣ የተሻለ ይለብሳሉ፣ እንዲሁም በተሻለ መልኩ ቤተሰባቸውን መንከባከብ ይችላሉ፤›› ያሉት ላለፉት 25 ዓመታት ሴቶችን በኢኮኖሚ ስለማብቃትና ስለ ሥርዓተ ጾታ መንግሥታዊና መንግሥታዊ ባልሆኑ ድርጅቶች ውስጥ የጥናትና ምርምር ፕሮግራምን ሲመሩ፣ ሲያስተዳድሩና ሲቆጣጠሩ የቆዩት ወይዘሮ የውብዳር ኃይሉ ናቸው፡፡

ሴቶችን አስመልክቶ ለበርካታ ዓመታት ሲሠሩ የቆዩት የሥርዓተ ጾታ ባለሙያዋ እንዳብራሩት ከሆነ፣ የሴቶች ኢኮኖሚያዊ ብልጽግና ቤተሰባቸው ብሎም ያሉበት ማኅበረሰብ  የተሻሻለ፣ የተለወጠ፣ ያደገ ኑሮና ኢኮኖሚ እንዲኖረው ይረዳል፡፡

ወይዘሮ የውብዳር የሴቶች በኢኮኖሚ መበልጸግ ከድህነት ሊያወጣ ይችላል የሚለውን ጽንሰ ሐሳብ ያንጸባረቁት፣ ሴቶች በኢኮኖሚ በቅተው የሚቆጣጠሩት፣ የሚያስተዳድሩትና የሚያዙበት ንብረት ባለቤት መሆናቸው ከጤናና ከሌሎች ጉዳዮች አኳያ ሊያመጣ ስለሚችለው ለውጥ ሙያዊ ትንታኔያቸውን እንዲሰጡ በተጋበዙበት መድረክ ላይ ነበር፡፡

በመሆኑም ሴቶች አቅማቸው በደረጀ ቁጥር ጤናቸውን ለመጠበቅ (የቤተሰባቸውንም ጭምር) ወደ ሕክምና ተቋማት ሄደው አገልግሎቱንና መረጃን የማግኘት ተነሳሽነታቸውና ጥረታቸው እየጨመረ ይሄዳል፡፡ ይህ ከጤና አኳያ ሲሆን ከምግብ፣ ከትምህርትና ከሌሎች አስፈላጊ የኑሮ ሂደቶች ጋርም ቢያያዝ፣ ሴቶች የተሻለ ገቢ ኖሯቸው ኢኮኖሚያቸው ሲያድግ ከላይ የተጠቀሱት ነጥቦች በቤተሰባቸው ውስጥ ስለመሟላታቸው ማረጋገጫዎች ይሆናሉ፡፡

አብዛኛዎቹ ሴቶች ያመርታሉ፣ ቤተሰብ ይንከባከባሉ፣ ከቤተሰባቸው አባላት ውስጥ አንድ ሰው ቢታመም ከሥራ ቀርተው የሚያስታምሙት ሴቶች ናቸው፣ ምግብ ያበስላሉ፣ ምግቡን የተመጣጠነ የማድረግ ኃላፊነት ያለባቸው ሴቶቹ ናቸው፤ እንዲሁም ስለልጆችን ጤናና ስለልጆች መማር ኃላፊነት ያለባቸው ሴቶች እንደሆኑ ባለሙያዋ አስታውሰዋል፡፡ 

‹‹ብዙ ጊዜ ዋጋ ሲሰጥ የሚታየው የሚከፈልበት ሥራ እንጂ ሴቶቹ በቤታቸው ውስጥ የሚያደርጓቸው እንክብካቤዎችና ሌሎች ሁኔታዎች ከግንዛቤ ውስጥ አይገቡም፤›› ያሉት ወይዘሮ የውብዳር፣ ሴቷ ላይ የሚጣልባት የሥራ ጫና እየበዛ በሄደ ቁጥር የሴቷ ጤና እየተናጋና የቤተሰቧም ጤንነት አደጋ ውስጥ እየወደቀ የምታደርገውም አገልግሎት ሙሉ በሙሉ እየቆመ እንደሚሄድ አስረድተዋል፡፡

ከግብርና አቅጣጫ ሲታይ ደግሞ ሴቷ ግብርናን አስመልክቶ የምትሰጠው አገልግሎት 75 በመቶ ይደርሳል፡፡ ‹‹ቢሆንም ግን ሴቷ እንደገበሬ ታይታ አስፈላጊውን ድጋፍ አታገኝም፡፡ ይህ ሲሆን ደግሞ (እማወራ ከሆነች) በቂ ምርት አታገኝም፡፡ በቂ ምርት ካላገኘች ደግሞ ቤተሰቧን በትክክል መመገብ ስለሚሳናት ውጤቱ የቤተሰቧ ጤንነት በበሽታ መተካት ነው፣›› ብለዋል፡፡  
ሴቶች በኢኮኖሚ ሲበቁ ማንኛውንም የልማት ግብ ማሟላት ይቻላል የሚል ዕምነት ያላቸው የሥርዓተ ጾታ ባለሙያዋ፣ ሴት ገበሬዎች የተሻለ እንዲያመርቱ ቢደረግ ከ20-30 በመቶ ድረስ ምርታማነታቸው እንደሚጨምር ጥናቶች እንደሚጠቁሙ ጠቅሰዋል፡፡ ይህም በመሆኑ ደግሞ ከ2.5 እስከ 4 በመቶ የሚደርሱ የተራቡ ሰዎችን ቁጥር መቀነስ ይቻላል፡፡ እንዲሁም ከ12-17 በመቶ የሚደርሱና በድህነት የሚኖሩ ሰዎችን ቁጥርም እንደሚቀንስ አስረድተዋል፡፡

‹‹ይህ በመሆኑ ደግሞ ከ100-150 ሚሊዮን ሕዝብ መራቡ ይቀራል ማለት ነው፡፡ መራቡ ሲቀር ደግሞ የተሻለ ምግብና ጤንነት አጠባበቅ ከማከናወን አንስቶ የተሻለ ሕይወትን እስከመኖር ያስችላል፤›› ሲሉ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡

ሴት እጅ ውስጥ የገባ ገቢ ከ70 እስከ 90 በመቶ የሚሆነው ለቤተሰቧ ጤና፣ ለልጆቿ ትምህርትና ለቤተሰቧ መመገቢያ እንደሚውል ጥናቶችን ተመርኩዘው ያብራሩት ወይዘሮ የውብዳር፣ ሴቶችን ማብቃት ሲባል ገቢን ማስገኘትና የገቢ አቅምን መፍጠር ብቻ ሳይሆን፣ ሴቶች በራስ መተማመን ኖሯቸው የሚፈልጉትን ሁሉ በሚፈልጉት ጊዜና በሚፈልጉት አቅጣጫ ተንቀሳቅሰው ችግራቸውን መቅረፍም እንደሚያካተት አክለዋል፡፡