መነሻ ገጽ - ሌሎች አምዶች - ማህበራዊ ጉዳዮች - ሴት - የአፍሪካ ኅብረት እናቶችን የመታደግ ዕርምጃ
Buy Valtrex Online Buy Albuterol inhaler Online Buy Prinivil Online
31 March 2013 ተጻፈ በ 

የአፍሪካ ኅብረት እናቶችን የመታደግ ዕርምጃ

‹‹አፍሪካ ከፍተኛ የእናቶችና የሕፃናት ሞት የሚመዘገብባት አህጉር ናት፡፡

በሌሎች በተለይም ባደጉ አገሮች ወሊድ እንደማንኛውም አካላዊ ክንውን፣ የሰው ልጅ ዘርን የመተካት ሒደት ተደርጎ ሲታይ በአህጉራችን ወሊድ ሕይወትን ለአደጋ ማጋለጥ ማለት ነው፤›› በማለት የአፍሪካ ኅብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር የሆኑት ዶክተር ዳላሚኒ ዙማ የእናቶች ሞት አስከፊነትን በማስመልከት ተናግረው ነበር፡፡

በአፍሪካ ሴቶች ከሀምሳ በመቶ በላይ የሚሆነውን የሕዝብ ቁጥር እንደሚሸፍኑ መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡ ይህን ያህሉን የሕዝብ ቁጥር መያዝ ብቻም ሳይሆን በተለያዩ ዘርፎች የሚያበረክቱት አስተዋጽኦም ከፍተኛ እንደሆነ ይታመናል፡፡

የእናት መሞት እንዲሁ እንደ አንድ ሰው ሞት ሊታይ እንደማይገባ የተናገሩት ሊቀመንበሯ፣ የእናቶች ሞትን ተከትሎ ብቻቸውን የሚቀሩ ጨቅላዎች በጤና ማደግ ለመቻላቸው ምንም መተማመኛ ባለመኖሩ፤ ያለ እናት እንክብካቤና ድጋፍ የጨቅላነታቸውን ጊዜ ማሳለፋቸው ቀጣይ ሕይወታቸው ላይ ጥላ ስለሚያጠላ የእናት ሞት የቤተሰብ ብሎም የኅብረተሰብ መጥፋት ማለት እንደሆነ ገልጸዋል፡፡

በአፍሪካ የእናቶች ሞትን ለመቀነስ በአህጉርና በአገሮች ደረጃ የተለያዩ ዕርምጃዎች ተወስደዋል፡፡ በዚህ ረገድ እ.ኤ.አ. 2009 ላይ የአፍሪካ ኅብረት በአዲስ አበባ ባደረገው መደበኛ ጉባኤው ላይ በአፍሪካ የእናቶች ሞት ቅነሳን የማፋጠን ካርማ (Campaign on accelerated maternal mortality reduction in Africa) ዘመቻን ይፋ አድርጎ ነበር፡፡ ዘመቻው በተባበሩት መንግሥታት የሥነ ሕዝብ ፈንድ (ዩኤንኤፍፒኤ) የሚደገፍ ነው፡፡ ካርማ ይፋ የተደረገው የአፍሪካ መሪዎች በተገኙበት መድረክ ላይ የራሳቸውን ድጋፍ አግኝቶ ቢሆንም ዘመቻውን ብሔራዊ አድርገው በአገራቸው ያስጀመሩ መሪዎች መጀመሪያ ላይ ጥቂት ብቻ ነበሩ፡፡

ኅብረቱ የእናቶችና የሕፃናትን ሞት በአህጉር ደረጃ ለመቀነስ ከወሰዳቸው ሌሎች ዕርምጃዎች ጋር ሲነፃፀር የሚመለከታቸውን አካላት የፖለቲካ ቁርጠኝነትና ድጋፍ በይበልጥ ማግኘቱ፤ ይህም ተጨማሪ ሀብትና ተሳትፎን ማስገኘቱን የተባበሩት መንግሥታት የሥነ ሕዝብ ፈንድ (ዩኤንኤፍፒኤ) አፍሪካ ቢሮ ቴክኒካል አማካሪ የሆኑት ዶክተር አኪናየለ ኤሪክ ዳያሮ ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡ ይህን የገለጹት ከአንድ ሳምንት በፊት ኡጋንዳ ላይ በተደረገውና ሪፖርተር በተጋበዘበት የካርማ አድቮኬሲ ወርክሾፕ ላይ ነበር፡፡ በዐውደ ጥናቱ ላይ ከምሥራቅና ደቡብ አፍሪካ የተለያዩ መገናኛ ብዙኅን ተጋብዘው ነበር፡፡

በአሁኑ ወቅት 37 የአፍሪካ አገሮች ካርማን በብሔራዊ ደረጃ አውጀዋል፡፡ በአፍሪካ ኅብረት የዘመቻውን ይፋ መሆን ተከትሎ ወዲያው ካርማን የጀመሩ አገሮች ስምንት ነበሩ፡፡ እነዚህን አገሮች ተከትለው 2010 ላይ ዘመቻውን ካወጁ አገሮች መካከል ኢትዮጵያ፣ ኬንያ፣ ኤርትራና ኡጋንዳ ይገኙበታል፡፡

ደቡብ አፍሪካ ጐራውን ዘግይተው ከተቀላቀሉ አገሮች መካከል የምትመደብ ነች፡፡  ዘመቻውን ይፋ ያደረገችው 2012 ላይ ነው፡፡ እንደ ሱዳን፣ ደቡብ ሱዳን፣ ሞሪሺየስ፣ ማሊ፣ ኮሞሮስና አይቮሪኮስት የመሳሰሉ አገሮችም እስከ አሁን ዘመቻውን የራሳቸው አድርገው ይፋ አላደረጉም፡፡ ካርማ የአፍሪካ አገሮች የጤና ሚኒስትሮችና መሪዎች በተገኙበት በአህጉር ደረጃ ድጋፍ ተሰጥቶት ይፋ ቢደረግም የመንግሥታት ዘመቻውን በብሔራዊ ደረጃ ይፋ ለማድረግ መዘግየት እንዴት ይታያል? የሚል ጥያቄ ለቴክኒካል አማካሪው አቅርበን ነበር፡፡

ከቀደሙት ዓመታት ጋር ሲነፃፀር 2012 ላይ ካርማን ይፋ ያደረገች አገር ደቡብ አፍሪካ ብቻ በመሆኗ የተቀዛቀዘውን ነገር ማፋጠን አስፈልጎ እንደነበር ይናገራሉ፡፡ በሌላ በኩል አገሮች ካርማን በይፋ ለማስጀመር የዘገዩበት የተለያዩ አገራዊ እውነታዎች መኖራቸውን የሚናገሩት ዶክተር ዳያሮ፣ ደቡብ አፍሪካን በምሳሌነት አንስተው አገሪቷ ዘመቻውን ቀደም ብላ 2010 ወይም 2011 ላይ መጀመር ያልቻለችው ወቅቱ የፕሬዚዳንት ለውጥ ያደረገችበት በመሆኑ እንደነበር አስታውሰዋል፡፡ በሌላ በኩል የአገሪቱ የጤና ፖሊሲ ዋና ትኩረት ኤችአይቪ ላይ ስለነበር ያም ተፅዕኖ አሳድሮ ነበር፡፡

በአሁኑ ወቅት ካርማን በብሔራዊ ደረጃ ይፋ ያላደረጉ አገሮች በጥቅሉ 17 ናቸው፡፡ ከእነዚህ መካከል 12ቱ በቅርብ ይፋ እንደሚያደርጉ ይጠበቃል፡፡ “በዚህ ስብሰባ ላይ የማዳጋስካርና ኮሞሮስ ተወካዮች ተገኝተዋል፡፡ እነዚህ አገሮችን ጨምሮ ሱዳንና ደቡብ ሱዳንን ያሉ የምሥራቅ አፍሪካ አገሮች ካርማን በብሔራዊ ደረጃ ይፋ ለማድረግ መንገድ ላይ ናቸው፡፡ ሶማሊያ እዚህ መስመር ላይ አይደለችም፤” ይላሉ፡፡

የካርማ ዒላማ በአገሮች እ.ኤ.አ 2015 ላይ የእናቶች ሞት 75 በመቶ እንዲቀንስ ነው፡፡ በአማካይ የአፍሪካ አገሮች 41 በመቶ የእናቶች ሞትን መቀነስ ችለዋል፡፡ እንደ ኤርትራ (73%) እና ኢኳቶሪያል ጊኒ (81%) መድረስ የቻሉ አገሮችም አሉ፡፡ እሳቸው እንዳሉት ይህን ውጤት ያስመዘገቡት ከሁሉም በላይ የወሊድ መቆጣጠሪያን፣ ተቋማዊ የወሊድ፣ የቅድመና ድህረ ወሊድ ክትትል አገልግሎትን በማረጋገጣቸው ነው፡፡

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሥነ ሕዝብ ፈንድ ኤክስኪዩቲቭ ዳይሬክተር በካርማ የ2013 ሪፖርት ላይ እንደተናገሩት፣ ምንም እንኳ በአህጉሪቱ የእናቶች ሞት በከፍተኛ ሁኔታ እየቀነሰ ቢሆንም የእናቶች ሞት አሁንም ትልቅ ተግዳሮት ነው፡፡ ከዓለም ሕዝብ 14 በመቶ የሚሆነው ሕዝብ መኖሪያ የሆነችው አፍሪካ በዓለም ከሚከሰቱ የእናቶች ሞት ከግማሽ በላይ የሚሆነው የሚመዘገብባት መሆኑ ትልቅ ተግዳሮት ነው፡፡

የቤተሰብ ምጣኔ አገልግሎት ተደራሽ አለመሆን፣ ዘመናዊ የወሊድ አገልግሎት አለመኖር፣ የቅድመና ድህረ ወሊድ ክትትል አለማድረግ በአህጉሪቱ ለእናቶች ሞት በቀዳሚነት የሚቀመጡ ነገሮች ናቸው፡፡ ዛሬም በአፍሪካ በቀን ከ450 በላይ የሚሆኑ ሴቶችና ልጃገረዶች በእርግዝና ወቅት በሚያጋጥም የጤና መታወክ አልያም በወሊድ ሕይወታቸው ያልፋል፡፡

የመንግሥታት በአፍሪካ አገሮች ካርማን በብሔራዊ ደረጃ ተግባራዊ ለማድረግ ፈቃደኛና ቁርጠኛ መሆንን ተከትሎ የእናቶችን ሞት በመቀነስ ረገድ ውጤቶች እየተመዘገቡ ነው፡፡ የጤና ተቋማት እየተጠናከሩ፣ የእናቶችን ሞት ለመቀነስ ለሚደረጉ እንቅስቃሴዎች የገንዘብ ዕርዳታ እየጨመረና በሕዝብ፣ በግልና በበጎ ፈቃደኛ ተቋማት መካከል አጋርነት እየተጠናከረ ነው፡፡

የካርማ የ2013 ሪፖርት እንደሚያሳየው፣ 92 በመቶ የሚሆኑ የአፍሪካ አገሮች የፖለቲካ ቁርጠኝነትን ለማፋጠን ዕርምጃዎችን ሲወስዱ 50 በመቶ የሚሆኑት የጤና አገልግሎት አሰጣጥ ሲስተማቸውን አጠናክረዋል፡፡ የአገልግሎት አሰጣጥን መገምገምና መቆጣጠር የሚያስችል ሥርዓትም ዘርግተዋል፡፡ የኤችአይቪ፣ የሥነ ተዋልዶ ጤናና የቤተሰብ ምጣኔ አገልግሎቶች በተቀናጀ መንገድ እንዲሰጡ መንገድ ተቀይሰዋል፡፡

17 በመቶ የሚሆኑት አገሮች ደግሞ ለእናቶችና ለሕፃናት የጤና አገልግሎት እንዲሁም ለሥነ ተዋልዶ ጤናና መብት የሚመድቡትን የገንዘብ መጠን ከፍ አድርገዋል፡፡ አሁንም እንደ ታንዛኒያ ያሉ አገሮች በቂ ገንዘብ እንዲመድቡ በሌላውም ዘርፍ ተገቢ ዕርምጃ እንዲወስዱ ዶክተር ዳያሮ ጥሪ አድርገዋል፡፡

የሰው ኃይልና የገንዘብ እጥረት፣ የጤና አገልግሎት አሰጣጥ የሚጠበቀውን ያህል አለመጠናከር፣ ደካማ የጤና መሠረተ ልማት፣ ውስን የወንዶች ተሳትፎ፣ ሃይማኖታዊና ባህላዊ ተፅዕኖዎች፣ የጤና ባለሙያዎች በከፍተኛ ሁኔታ ሥራ መልቀቅና የባለሙያዎች ብቃት ማነስ የካርማ ተግዳሮቶች ተብለው ከተቀመጡ የተወሰኑት ናቸው፡፡

ኢትዮጵያ የእናቶች ሞትን በመቀነስ ረገድ ጥሩ ውጤት ካስመዘገቡ አገሮች መካከል እንደምትጠቀስ ይናገራሉ፡፡ በኢትዮጵያ የእናቶችና ሕፃናትን ሞት ለመቀነስ የተለያዩ ዕርምጃዎች ተወስደዋል፡፡ የጤና ተቋማትን ማጠናከርና ተደራሽነታቸውን ማስፋት አንደኛው ዕርምጃ ሲሆን፣ የጤና ዘርፍ ልማት ፕላን (Health Sector Development Plan) በዚህ ረገድ የሚጠቀስ ሌላው እመርታ ነው፡፡

የኢትዮጵያ የ2011 የሥነ ሕዝብና ጤና ዳሰሳ እንደሚያሳየው፣ ዕድሜያቸው ከ15-49 በሆኑ ሴቶች 30 በመቶ የሚሆነው ሞት ከእርግዝና አልያም ከወሊድ ጋር በተያያዘ ምክንያት የሚከሰት ነው፡፡ ከመቶ ሺሕ ወሊድ ደግሞ 676 ሞት ይከሰታል፡፡ ይህ ጥናቱ ከመደረጉ በፊት በነበሩ ሰባት ዓመታት የተመዘገበ ነው፡፡