መነሻ ገጽ - ሌሎች አምዶች - ማህበራዊ ጉዳዮች - ሴት - አስገድዶ መድፈርና የሕክምና ማስረጃ
Buy Valtrex Online Buy Albuterol inhaler Online Buy Prinivil Online
18 August 2013 ተጻፈ በ 

አስገድዶ መድፈርና የሕክምና ማስረጃ

-60 በመቶ የሚሆኑ ኬዞች በማስረጃ እጥረት ይዘጋሉ

ቀደም ባሉት ዓመታት አንዲት ሴት አስገድዶ መድፈር ተፈጸመባት ሲባል ትኩረት የሚደረግበት የመጀመሪያ ጉዳይ የክብረ ንፅህና መገሰስና አለመገሰስ ነበር፡፡

የሴቷ ፈቃደኛ መሆን አለመሆን ጉዳይም አከራካሪ ነበር፡፡ ምንም እንኳ በሕግ የተቀመጠ ነገር ባይኖርም በአፈጻጸም ደረጃ ሴቷ ታግላለች፣ ቧጭራለች የሚሉ ጥያቄዎችን በማንሳት ሴቷ ፈቃደኛ አለመሆኗን ለመግለጽ ምን ያህል ሔዳለች የሚሉ ሐሳቦች ሲንፀባረቁም ይታያል፡፡ 

ከአስገድዶ መድፈር ጋር በተያያዘ የፈቃድ ጉዳይ ባደጉ አገሮችም ዛሬም ላይ አከራካሪ የሚሆንባቸው አጋጣሚዎች ጥቂት አይደሉም፡፡ ‹‹እምቢ›› አለማለት ‹‹እሺ›› ማለት ነው ወይ? በኃይልና ማስፈራራት አልያም በማስከር ወይም በማደንዘዝ ‹‹እምቢ›› እንዳትል ማድረግስ እንዴት ይታያል? የሚሉና መሰል ጥያቄዎች የሚነሱ ናቸው፡፡

ከአስገድዶ መድፈር ጋር በተያያዘ የሕክምና ምርመራ ውጤት አንድ ማስረጃ ነው፡፡ በአደጉ አገሮች በአስገድዶ መድፈር የተጠረጠሩ ግለሰቦች ምርመራ በፎረንሲክ ደረጃ በዲኤንኤ ውጤት አማካይነት ሲሆን የመቀጣት መጠንም በከፍተኛ ሁኔታ እየጨመረ ይገኛል፡፡ በኢትዮጵያስ የሕክምና ማስረጃ በምን ያህል ደረጃ ከአስገድዶ መደፈር ጋር በተያያዘ የፍትሕ ሒደትን እያገዘ ነው? ምርመራውስ በምን ደረጃ ላይ ይገኛል? 

በጋንዲ መታሰቢያ ሆስፒታል ውስጥ የሚገኘው የሴቶችና የሕፃናት የተቀናጀ እንክብካቤና ፍትሕ ማዕከል የድንገተኛ ሕክምና ንኡስ የሥራ ሒደት መሪ ዶክተር ስንታየሁ ታከለ አንደሚሉት፣ በሴቶች በኩል ከግንዛቤ ችግር፣ ሳምንታትና ወራት ያህል ከመቆየትና  ከመታጠብ የሕክምና ማስረጃዎችን የማጥፋት አጋጣሚ ቢኖርም ማዕከላቸው የሚያደርገው መሠረታዊ ምርመራ የፍትሕ ሥርዓቱን እያገዘ ነው፡፡

በፊት አንዲት ሴት ተደፈርኩ ስትል ሕክምና ለማግኘት የምትጠየቃቸው ነገሮች ነበሩ፡፡ አሁን ግን ምንም ዓይነት ማስረጃና መረጃ ሳትጠየቅ ነፃ ምርመራ እንደሚደረግላት ዶክተር ስንታየሁ ይናገራሉ፡፡ ‹‹አንድ ሴት በዚህ ቀን በዚህ ሁኔታ ተደፈርኩ ስትል በማሕፀኗ የወንድ ዘር መኖር አለመኖሩን እናያለን፡፡ ብልት አካባቢና ከማሕፀን ውጭ ጉዳት መኖርና አለመኖሩንም እንመረምራለን፡፡ የፎረንሲክ አቅማችን ውስን ባይሆንም ምራቅ ወስዶ ዲኤንኤ መመርመርም ይቻል ነበር፡፡ እኛ ግን እዚያ ላይ አልደረስንም፤›› ይላሉ፡፡

እሳቸው እንደሚያስረዱት፣ ሕይወት ያላቸው የወንድ ዘሮች መታየት ግንኙነት የተፈፀመበትን ጊዜ፣ ከማሕፀን ውጭ የሚደርስ መፋፋቅና ተጨማሪ ጉዳቶች ኃይል የተቀላቀለበት ግንኙነት መደረጉን ያሳያሉ፡፡ አጠቃላይ ሁኔታዎችን አጢኖና የቀረቡ ማስረጃዎችን አገናዝቦ የአስገድዶ መደፈር ወንጀል ተፈጽሟል አልተፈጸመም የሚለውን ማስቀመጥ የፍትሕ ባለሙያ ጉዳይ ይሆናል፡፡

ከንግግራቸው እንደተረዳነው፣ በምርመራ የወንዱ ዘር ለአካለ መጠን የደረሰ ሰው ነው ከማለት በዘለለ ተጠርጣሪው የሚገኝበትን የዕድሜ ክልል ማስቀመጥ አይቻልም፡፡ በሌላ በኩል ዓይንና አፍንጫ ላይ የሚደርሱ አካላዊ ጉዳቶችም በሕክምና ማስረጃው ላይ ይሰፍራሉ፡፡

ዶክተር ስንታየሁ ‹‹አሁን ባለው ሁኔታ መሠረታዊ አሠራሮች አሉን፤ ነገር ግን የሕክምና ማስረጃው ለፍትሕ ሒደት የሚኖረውን ዋጋ ለመጨመር የፎረንሲክ አቅማችንን መገንባት፣ ድጋፍ ለማግኘትና በጋራ ለመሥራት ፕሮፖዛል እያዘጋጀን ነው፤›› ብለዋል፡፡ 

ማዕከሉ ከተከፈተ አንድ ዓመት ሲሆነው ለ1 ሺሕ 43 ተጠቂዎች አገልግሎት ሰጥቷል፡፡ 50 ከመቶ የሚሆኑት ተጠቂዎች ከ18 ዓመት በታች ሲሆኑ 30 በመቶ የሚሆኑት ከ10 ዓመት በታች ናቸው፡፡ 

ቀደም ባሉት ዓመታት የሕክምና ማስረጃ በእንግሊዝኛ እየተጻፈ ለማስተርጐም ከመንገላታት አንስቶ የትርጉም ማዛባት ድረስ ችግር ያጋጥም እንደነበር በማስታወስ የሕክምና ማስረጃ በአማርኛ እንዲጻፍ መደረጉ የሕክምና ማስረጃዎች ለፍትሕ ሒደት የሚኖራቸውን እገዛ ከፍ እንዳደረገውም ያምናሉ፡፡

በማዕከሉ የሕክምና፣ የሥነ ልቦና፣ የማኅበራዊና የፍትሕ አገልግሎት በተቀናጀ መልኩ መሰጠቱ ከአስገድዶ መደፈር ጋር በተያያዘ በፍትሕ ተደራሽነት ላይ የሚያሳድረው አዎንታዊ ተፅእኖ ከፍተኛ ነው፡፡ የፍትሕ ማዕከሉ ገና አንድ ዓመቱ ቢሆንም በሒደት አቅሙን እየገነባ ሲሔድ የሴቶችና የሕፃናት የፍትሕ ማዕከላት በአስገድዶ መድፈር ወንጀል የፈፀሙ ሰዎች በመቀጣት መጠን እንደ ደቡብ አፍሪካና መሰል አገሮች ዘጠና በመቶ ወደማድረስ እንደሚሔድ ዶክተሩ ተስፋ ያደርጋሉ፡፡ 

የኢትዮጵያ ሕግ ባለሙያ ሴቶች ማኅበር ዳይሬክተሯ ወይዘሮ ዜናዬ ታደሰ እንደ ጅምር የማዕከሉ አስተዋጽኦ፣ የማዕከሉ መቋቋም ትርጉምም ትልቅ ቢሆንም ማዕከሉ አዲስ አበባ ውስጥ ለሚገኙ አሥር ክፍላተ ከተሞች ብቻ አገልግሎት የሚሰጥ ነው፡፡ ሆኖም ክልሎች ላይ ዛሬም ችግሮች መኖራቸውን ይናገራሉ፡፡ 

ይህ ማለት ዛሬም የተደፈሩ ሴቶች የሕክምና፣ የፍትሕና ማኅበራዊ አገልግሎት ለማግኘት የተለያዩ ቦታዎች መሔድ የግድ ይላቸዋል፡፡ አገልግሎቱ እዚያና እዚህ በተነጣጠለ መልኩ ስለሚሰጥ ማስረጃዎች ሊጠፉ ምስክሮች ተስፋ ሊቆርጡ ይችላሉ፡፡ የአስገድዶ መድፈር ወንጀል ተፈጸመ ሲባል ነገሩን ቀጥታ ከክብረ ንፅህና መገሰስ ጋር የማገናኘትና ለሐኪም ክብረ ንፅህና መገሰስ አለመገሰሱን አረጋግጡልን የሚል ጥያቄ ማቅረብ ዛሬም ሙሉ ለሙሉ አልቀረም፡፡

መሻሻሎች ቢኖሩም ከአስገድዶ መደፈር ጋር በተያያዘ የሴቷ መፍቀድንና አለመፍቀድን በሚመለከት ዛሬ ላይም ችግሮች መኖራቸውን ወይዘሮ ዜናዬ ይናገራሉ፡፡ ማኅበራቸው ከሁለት ዓመታት በፊት በአዲስ አበባ አንድ ክፍለ ከተማ ላይ ባደረገው አነስተኛ ጥናት መሠረት ሪፖርት ከተደረጉ የአስገድዶ መድፈር ኬዞች ስድሳ በመቶ የሚሆኑት ማስረጃ የላቸውም ተብሎ እንደሚዘጉ ገልጸዋል፡፡ ከዚህ ውስጥ አብላጫውን ቁጥር የሚይዘው ኬዝ ደግሞ የስም ማጥፋት ነው ተብሎ በወቅቱ ታምኗል፡፡

በፖሊስ ጣቢያዎች የሕፃናትና የሴቶች ዴስኮች እንዲኖሩ ማድረግን እንደ አንድ አዎንታዊ ዕርምጃ የሚያዩት ወይዘሮ ዜናዬ፣ ወንዶች አስገድዶ መደፈርን እንዴት ይረዱታል? የሚለው ነገርም ሊታይ እንደሚገባ ያምናሉ፡፡ ‹‹እንኳን ለአስገድዶ መድፈር ለሌሎችም ሴቶችን የሚመለከቱ የሕግ ጉዳዮች ሴት ባለሙያዎች አስፈላጊው ቦታ ላይ እንዲቀመጡ ዘወትር የምንጠይቀው ነገር ነው፤›› በማለት ከአስገድዶ መድፈር ጋር በተያያዘ የሕክምና ማስረጃዎች ሚዛን የሚደፉ ይሆኑ ዘንድ በሚመለከታቸው ተቋማት የፎረንሲክ አቅም ግንባታ ዋናው ሊተኮርበት የሚገባ ነገር እንደሆነ ይናገራሉ፡፡ የፍትሕ ሒደት ፍጥነትና በጀትም ሊታዩ የሚገቡ ነገሮች መሆናቸውን ይጠቁማሉ፡፡

ለረዥም ዓመታት ከአስገድዶ መድፈር ጋር በተያያዘ የሠሩና ስማቸው እንዲገለጽ ያልፈለጉ አንድ ባለሙያ፣ የተሠራውን ያህል በሰዎች አመለካከት ላይ ለውጥ እንዳልመጣ፤ በሕክምና፣ በፍትሕ፣ በማኅበራዊ አገልግሎት ዘርፍ ውስጥ ያሉ ባለሙያዎችም ከዚህ ውጭ አለመሆናቸውን ይናገራሉ፡፡ ‹‹ብዙ ተሠርቷል የመጣው ለውጥ ግን ጥቂት ነው፡፡ ከዓመታት በፊት ያወራነውን ደግመን ዛሬ ማውራት ለውጥ አለመምጣቱን በራሳችን ላይ ምስክር መሆን ነው፤›› ይላሉ፡፡

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሕግ ትምህርት ቤት ስማቸው እንዳይገለጽ የፈለጉ መምህርት ስለአስገድዶ መድፈር ሲወራ ዛሬም ተጠቂዎችን በአንድም ይሁን በሌላ መንገድ ተወቃሽና በተወሰነ መልኩ ተጠያቂ የማድረግ ነገር እንዳለ ይናገራሉ፡፡ በእኛ አገር ብቻ ሳይሆን በሌሎችም ጭምር አስገድዶ መድፈርን የሚመለከቱ ሕጐች የሴት ልጅን መብት፣ ካለፈቃዷ ያለመነካት መብቷን መጠበቅ ሳይሆን ንፅህናዋንና የማኅበረሰብን እሴት መሠረት ያደረጉ መሆናቸው ጥያቄ ውስጥ ሊገባ እንደሚገባ ያስረዳሉ፡፡ 

አስገድዶ መድፈር መያያዝ ያለበት ከሴት ካለፈቃድ መነካት፣ ከመብትና ከክብር ጋር ነው፡፡ በመጀመሪያ ደረጃ መታየት ያለበት የአንዲት ሴት ካለፈቃዷ ያለመነካት መብቷ ነው፡፡ አንዲት ሴት ካለፈቃዷ መነካቷን ለማረጋገጥ ወደኋላ ተመልሶ መታገሏን፣ መቧጨሯን ወይም የልብሷን መቀደድ ማየት አያስፈልግም፡፡ አልታገለችም ‹‹እምቢ›› አላለችም ማለትን ከፈቃደኝነት ጋር እኩል ማድረግ አይቻልም፡፡ ለምሳሌ ደፋሪው ቤተሰብሽን እገድላለሁ ብሎ ቢያስፈራራት ሴቷ እንዳትቃወመው፣ እንዳትከላከለው አድርጓታል ማለት ነው፡፡ ሕጉም ካልተከላከለችው ወይም ካልታገለችው ሳይሆን እንዳትከላከለው ካደረጋት የሚለውን ነገር ነው የሚያስቀምጠው፡፡  

አስገድዶ መደፈርን ከሴት ልጅ ያለፈቃዷ አለመነካት መብትና ደኅንነት ጋር አያይዞ ማየት የተደፈሩ ሴቶች ቤተሰባችን ይዋረዳል፣ ማኅበረሰቡ ለእኛ የሚኖረው አመለካከትም የወረደ ይሆናል ሳይሉ ወደ ፍትሕ አካል እንዲሔዱ፣ ክስ የሚመሠረትባቸው አስገድዶ ደፋሪዎች የጥፋተኝነት ውሳኔ እንዲጨምር እንደሚያደርግም ያስረዳሉ፡፡