መነሻ ገጽ - ሌሎች አምዶች - ማህበራዊ ጉዳዮች - ሴት - የራቀ የጋራ ድምፅ
Buy Valtrex Online Buy Albuterol inhaler Online Buy Prinivil Online

የበጎ አድራጎትና ማኅበራት አዋጅ ከወጣ በኋላ ኢትዮጵያዊ ሆነው ከመብትና ከውትወታ (advocacy) ጋር የተያያዙ ጉዳዮች ላይ ለመሥራት የወሰኑ ድርጅቶች የተለያዩ ችግሮችን ተጋፍጠዋል፡፡

አጋጣሚው ችግር ብቻም ሳይሆን ለዓመታት ያልታዩ አቅጣጫዎች እንዲታዩና ዕድል እንዲሆኑ መንገድ ጠርጓል የሚል አስተያየትም ይሰነዘራል፡፡

በሴቶች መብትና የፖሊሲ ውትወታ ላይ የሚሠሩ ድርጅቶች በየትኛው መስመር ላይ እየተጓዙ ነው? የአዋጁን መውጣት ተከትሎ ምን ዓይነት ተግዳሮቶችን እየተጋፈጡ፤ ምን ዓይነት ዕድሎችንስ መጠቀም እየቻሉ ነው? 

እ.ኤ.አ በ2004 ሕጋዊ ዕውቅና ካገኘ ጀምሮ የኢትዮጵያ የሴቶች ማኅበራት ቅንጅትን (NEWA) በዳይሬክተርነት የመሩት ወይዘሮ ሳባ ገብረ መድህን የሴቶች የጋራ ድምጽ ለመሆን በ13 ድርጅቶች አባልነት የተመሠረተው ኔትወርክ በአዋጁ መውጫ ዋዜማ ላይ አባል ድርጅቶቹን ቁጥር 42 አድርሶ እንደነበር ያስታውሳሉ፡፡ አዋጁ ከወጣ በኋላ ግን የሴቶች መብትና ውትወታ ላይ ይሰሩ የነበሩ በርካታ አባል ድርጅቶቻቸው አቅምና አቅጣጫቸውን አገናዝበው የኢትዮጵያ ኗሪዎች ሆነው በመመዝገባቸው ከመብት ጋር በተያያዘ ለመሥራት የወሰኑት አሥር ብቻ ነበሩ፡፡ ከእነሱም እንደ ኢትዮጵያ ሴት ጋዜጠኞች ማኅበር (EMWA) ያሉት በድጋሚ የአቅጣጫ ለውጥ በማድረጋቸው በአሁኑ ወቅት ስምንት ብቻ ሊቀሩ የግድ ሆኗል፡፡ 

ኔትወርኩ ራሱም መብት ላይ ለመሥራት መወሰኑን የሚናገሩት ወይዘሮ ሳባ ኔትወርኮች ኢትዮጵያዊና የኢትዮጵያ ኗሪዎች ሆነው የተመዘገቡ ድርጅቶችን በአንድ ጥላ ሥር አድርገው መቀጠል እንደማይችሉ በመመሪያ በመቀመጡ ኔትወርኩ መብት ላይ የሚሠሩትን ብቻ ይዞ ሲቀጥል ቀሪዎቹ አባል ድርጅቶች እንዲሁ ከሚበተኑ ተብሎ የኢትዮጵያ ሴቶች በጎ አድራጎት ማኅበራት ኅብረትን (UEWCA) መመስረትን ይገልጻሉ፡፡ ኅብረቱ ዛሬ ላይ ወደ 40 የሚሆኑ አባል ድርጅቶች አሉት፡፡

‹‹አዋጁ ሴቶች ላይ እንዲሁም የሴቶች መብቶች ላይ የሚሠሩ ድርጅቶችን በቁጥር፣ በአቅምና በአባላት ቁጥር ከፋፍሏል፡፡ ጥንካሬና ኅብረት ተከፋፈለ፡፡ አብዛኞቹ ድርጅቶች መብት ላይ ይሠሩ ስለነበር ጥንካሬአቸው ተበትኗል፡፡ ለምሳሌ ኔትወርኩ በሰው ኃይል፣ በአሻራ በሁሉም ረገድ ሲሶውን ይዞ ነው የቀጠለው፡፡ ቁጥርም አቅም በመቀነሱ ለሴቶች አጀንዳ ይሰጥ የነበረው ትኩረትም ቀንሷል›› የሚሉት ወይዘሮ ሳባ በአቅጣጫ ለውጥ የታዩ ዕድሎችም መኖራቸውንም ይናገራሉ፡፡ 

የመብትና የፖሊሲ ውትወታ ጉዳዮች ገንዘብ ብቻም ሳይሆን የሕዝብ ድጋፍን፣ የሰዎች በጉዳዩ ማመንን የሚጠይቅ መሆኑ የሚያጠራጥር አይደለም፡፡ የሰዎች በነገሩ ማመን የገንዘብ ድጋፍ ማድረግ ባይችሉ ጊዜያቸውን አልያም ዕውቀታቸውን ላመኑበት ዓላማ እንዲያውሉ የግድ ይላል፡፡ ነገር ግን በሴቶች መብት ላይ ይሠሩ የነበሩ ድርጅቶች ቀደም ሲል በአገር ውስጥ ሕዝባዊ ድጋፍን እንዲሁም በጎ ፍቃደኝነትን ማስፋት ላይ አለመሥራታቸው ከአዋጁ መውጣት በኋላ ለችግር እንዳጋለጣቸው ወይዘሮ ሳባ ያምናሉ፡፡ ለማኅበራቱ የሚሰጠው የሽግግር ጊዜ እንዲረዝም የነበረው ጥያቄ በጎ ፍቃደኝነትን በሚመለከት ኅብረተሰቡ ላይ የተወሰነ ሥራ ለመስራት በማሰብ ነበር፡፡

በተለያየ መንገድ ከአገር ውስጥ ገቢ ለማሰባሰብ፤ በአገር ውስጥ በበጎ ፍቃደኝነት ላይ እንዲሰሩ መገደዳቸውን እንደ አንድ አዎንታዊ ገጽታ ይመለከቱታል፡፡ ‹‹ምክንያቱም በተለይም የመብት ጥያቄ ሕዝባዊ ድጋፍ ይፈልጋል፡፡ ከገንዘብ ውጭ የሕዝብ ድጋፍ ያስፈልገናል፡፡ የሚያቆመን ገንዘብ ብቻም ሳይሆን የሕዝብ ድጋፍም ነው›› 

በአገር ውስጥ በተለያዩ ዘዴዎች ውስጥ ገንዘብ ማሰባሰብ ችለዋል፡፡ የተወሰኑ የውጭ አገር ገቢዎች እንደ አገር ውስጥ መቆጠራቸውም ጠቅሟቸዋል፡፡ ነገር ግን በዚህ መልኩ መቀጠል ስለማይቻል ዘላቂ ገቢ ማግኘት ይቻል ዘንድ የሴቶች ማዕከል ለመገንባት በማሰብ ከሁለት ዓመታት በፊት ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር መሬት ተረክበዋል፡፡ ለግንባታው ወደ 47 ሚሊዮን ብር ገደማ ያስፈልጋል፡፡ ይህ አሁን ባላቸው አቅም ከባድ ቢሆንም ባላቸው ገንዘብ የግንባታው መጀመር ግድ እንደሆነ ታምኗል፡፡ ምንም እንኳ የከተማው አስተዳደር በመልካም ፍቃድ ከሊዝ ነፃ መሬቱን ቢሰጣቸውም በአሠራር ችግር እስካሁን ወደ ግንባታ መግባት አለመቻላቸው ተገቢ አለመሆኑ ይሰማቸዋል፡፡

በጎ ፍቃደኝነት ባልተስፋፋበት መንግሥታዊ ላልሆኑ ድርጅቶች የገንዘብ ድጋፍ ማድረግም ባልተለመደበት ሁኔታ ውስጥ በአገር ውስጥ ገንዘብ ማሰባሰብ የሴቶች መብት ላይ መሥራት ለወሰኑ ድርጅቶች ቀላል ነው ወይ? ለሚለው ጥያቄ ‹‹በጣም አስቸጋሪ ነው፡፡ ብዙዎቹ ድጋፍ ስንጠይቃቸው እናንተ ስጡን እንጂ ደግሞ ለኤንጂኦ ገንዘብ ይሰጣል እንዴ ብለው ይጠይቃሉ፡፡ የአዋጁን መውጣት ቢያውቁም ተፅዕኖው ምን ድረስ እንደሆነ አይረዱም፡፡ በሌላ በኩል ድጋፍ ለማድረግ ቢወስኑ እንኳ ለሚታይ ነገር ድጋፍ ማድረግን ይመርጣሉ፡፡ እኛ የምንሠራው መብት ላይ በመሆኑ ብዙው ሥራችን ከሰዎች አመለካከት ለውጥ ጋር የተያያዘ ነው፡፡ ለውጡ ደግሞ ሒደት ነው፡፡ ሰው ደግሞ መብት፣ ጥቃት ላይ ነው የምንሠራው ስንል ነገሩ ይርቅበታል›› ነበር መልሳቸው፡፡  

በኔትወርኩ ሥር ከነበሩ ድርጅት የሴቶች መብት ላይ ለመሥራት ከወሰኑት መካከል የኢትዮጵያ ሴቶች ደራሲያን፣ የአማራ ክልል፣ የድሬዳዋ፣ የዳሎቻ የውኃ ልማት፣ የአካል ጉዳተኛ፣ የጋምቤላ ሴቶች ማኅበራት ይጠቀሳሉ፡፡ የሴቶች መብት ላይ ሰፊ ሥራ ሲሰራ የነበረው የኢትዮጵያ ሕግ ባለሙያ ሴቶች ማኅበር (EWLA) እንዲሁም ሌላ አንድ ድርጅት አዋጁን ለማስፈጸም በወጣ መመሪያ ምክንያት ኔትወርኩንም ሆነ የኢትዮጵያ ሴቶች በጎ አድራጎት ማኅበራት ኅብረትንም መቀላቀል አልቻሉም፡፡ ‹‹ይህ ተቀባይነት የሌለው ነገር ነው፡፡ ለእኛ አሳማኝ ባለመሆኑ አሁንም እየተከራከርን ነው›› ይላሉ ዳይሬክተሯ፡፡

ከቀድሞ ጋር ሲነፃፀር ሥራቸው እጅግ ውስን ሊሆን የግድ ሆኗል፡፡ ስለዚህ እየሠሩ ያሉት የሴቶች ጥቃትና ማኅበራዊ ተጠያቂነት ላይ ነው፡፡ ‹‹ዓላማውን በማሰብ እንጂ ያሉት ተግዳሮቶች በጣም ከባድ ናቸው፡፡ ግን በተመቻቸ ሁኔታ ውስጥ፣ የውጭ ድጋፍ ሲኖር ብቻም ሳይሆን የሴቶች መብት ላይ መሠራት እንዳለበት እናምናለን፡፡ አሁንም ሊያሠራን የሚችል ከባቢን የመፍጠር ኃላፊነት አለብን›› 

በአሁኑ ወቅት ምንም እንኳ የኢትዮጵያ ሴቶች በጎ አድራጎት ማኅበራት ኅብረትን እንደ ኔትወርኩ አካል አድርጎ ማየት ባይቻልም በጋራ እየሠሩ ይገኛሉ፡፡ ሴቶችን በሚመለከት ጉዳይ ከአገልግሎት ከድጋፍ ጋር በተያያዘ ኅብረቱ ሲሠራ፤ ከመብትና ከፖሊሲ ጋር በተያያዘ ኔትወርኩ ይንቀሳቀሳል፡፡ በዚህ ረገድ ወደ አረብ አገር የሚሄዱ ሴቶች ጉዳይ በጋራ እየሠሩባቸው ካሉ ጉዳዮች አንዱ ነው፡፡ ወደ ዓረብ አገር ከሚሄዱ ሴቶች ጋር በተያያዘ እየደረሰ ያለውን ችግር በማስመልከት ‹‹የሕገወጥ ዝውውሩ መስመር በጣም ጠንካራ ችግሩን ለመፍታት እየተሰራ ያለው ሥራ ግን ያን ያህል ጠንካራ አይደለም፡፡ ችግሩን ለመፍታት ትልቅ የፖለቲካ ውሳኔና ፈቃድ ያስፈልጋል›› ይላሉ ወይዘሮ ሳባ፡፡