መነሻ ገጽ - ሌሎች አምዶች - ማህበራዊ ጉዳዮች - ወጣት - እጅ አልባዋ ስኬታማ
Buy Valtrex Online Buy Albuterol inhaler Online Buy Prinivil Online
03 April 2013 ተጻፈ በ 

እጅ አልባዋ ስኬታማ

ከ32 ዓመት በፊት አሪዞና በተሰኘችው የአሜሪካ ግዛት ውስጥ ሁለት እጅ ያልተፈጠረባት ሕፃን ትወለዳለች፡፡ ጄሲካ ኮክስ ቻምበሪለን፡፡

ጄሲካ ዕድሜዋ 32 እስኪደርስ ድረስ ከፊሊፒናውያን ወላጆቿ ታገኝ በነበረው ቋሚ ድጋፍና ማበረታቻ ታግዛ ሕልሟን ማሳካት ጽኑ ፍላጎት ነበራት፡፡ በቤተሰቦቿ ድጋፍ ብቻ ያልተገታው ፍላጎቷ ላይ የራሷን ጠንካራ ጥረቶችና ትጋቶች አክላበት በልጅነቷ ያቀደቻቸውንና ያለመቻቸውን ሁሉ ዕውን ለማድረግ በቅታለች፡፡

በዓለም የድንቃ ድንቅ መዝገብ ላይ ‹‹የመጀመሪያዋ እጅ አልባ ፓይለት›› በሚል ርእስ የሰፈረችው ጄሲካ አውሮፕላን ማብረር፣ የሙዚቃ መሣሪያ (ፒያኖ) መጫወት፣ መደነስ፣ መኪና መንዳትና ባለሁለት የጥቁር ቀበቶዎች (በቴኳንዶ) ስፖርተኛ የሆነች ባለትዳርና የሁለት ልጆች እናት ናት፡፡ በሥነ ልቦና ትምህርት የመጀመሪያ ዲግሪዋን የሠራችው ጄሲካ ህልሞቿን እውን አድርጋ የተለያዩ አገሮች እየዞረች ልምዷን እያካፈለች ትገኛለች፡፡ 

አሜሪካ የሚገኘው ሃንዲ ካፕድ ኢንተርናሽናል አማካይነት በ19 አገሮች እየዞረች ልምዷን እንድታካፍልና አቻ ወጣቶችን እንድታነቃቃ ባሰናዳው ትምህርታዊ ጉዞ አማካይነት ጄሲካ ለጥቂት ቀናት በኢትዮጵያ እንድትገኝ አድርጓታል፡፡ አዲስ አበባ በነበራት ቆይታም በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተገኝታ ለአካል ጉዳተኛ ተማሪዎች የማነቃቂያ ንግግር አድርጋ ልምዷንና ተሰጥኦዎቿን አካፍላለች፡፡

በፕሮግራሙም መሠረት ባለፈው ሰኞ መጋቢት 23 ቀን 2005 ዓ.ም. ጄሲካን ለመስማት ስድስት ኪሎ በሚገኘው የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ዋናው ግቢ ማንዴላ አዳራሽ ውስጥ ከአንድ ሺሕ በላይ ተማሪዎች ታድመው ነበር፡፡ እርሷም የተማሪዎቹን ጥያቄ ከመመለስና አስተያየታቸውንም ከመቀበል ባለፈ የሕይወት ውጣ ውረዷን አጋርታለች፡፡ በእግሮቿም ከምታከናውናቸው የዕለተ ተዕለት ተግባራት መካከልም የተወሰኑትን ለተማሪዎቹ በተግባር አሳይታለች፡፡

በኢትዮጵያ ስለሚገኙ አካል ጉዳተኛ ወጣቶች በተለይም ሴት ተማሪዎች የተወሰነ ግንዛቤ መጨበጧን የገለጸችው ጄሲካ፣ ሁኔታው ከአብዛኛው የታዳጊ አገሮች ጋር ተመሳሳይ እንደሆነ አስረድታለች፡፡ ጌሲካ በተለይ ከሪፖርተር ጋር ባደረገችው አጭር ቆይታ ለመረዳት እንደተቻለው፣ የስኬቷ መሠረት ተወልዳ ያደገችበት አገር ሥልጣኔና ምቹ ሁኔታ ሳይሆን፣ ከልጅነቷ ጀምሮ ሲንከባከቧትና ሲደግፏት የቆዩት ወላጆቿ እንደሆኑ ተናግራለች፡፡ ‹‹በእርግጥ እንደ አሜሪካ ባሉ ያደጉ አገሮች አካል ጉዳተኛ ሆኖ ተወልዶ ማደግ የራሱ የሆነ መልካም ዕድል ሊኖረው ይችላል፡፡ ቁም ነገሩ ግን የወላጆች ቁልፍ ድጋፍና የአካል ጉዳተኛው ግላዊ ተነሳሽነት ነው፣›› ስትል የወላጆቿን ያልተቋረጠ ድጋፍና የግል ጥረቷን አሳይታለች፡፡

የኢትዮጵያ አካል ጉዳተኛ ሴቶችን አስመልክታ ስትናገርም፣ አገሪቷ እያደገች ያለች በመሆኗ ለልጆቹ ሊሟሉ የሚገቡ በርካታ ነገሮች ባይሟሉላቸውም፣ ወላጆቻቸው ግን የሚጠበቅባቸውን ያህል ቢደግፏቸውና ልጆቹ ያለባቸውን ተፅዕኖ ሰብረው መውጣት ቢችሉ ማንም ያገኘውን ስኬት ማግኘት እንደሚችሉ ሐሳቧን ገልጻለች፡፡

በአዳራሹ ተገኝተው የጄሲካን የሕይወት ውጣ ውረድንና ስኬትን መጋራት ከቻሉ አካል ጉዳተኛ ተማሪዎች መካከል ሲስተር ሔለን ወልዱ አንዷ ነበረች፡፡ ከጊዜ በኋላ ባጋጠማት የመውደቅ አደጋ ሁለቱም እግሮቿ ሙሉ በሙሉ በመጎዳታቸው በክራንች ለመራመድ የተገደደችው ሲስተር ሔለን፣ የጄሲካ ስኬት ለእሷና ለመሰሎቿ ጥሩ የመንፈስ መነቃቃትን እንደሚፈጥር ተናግራለች፡፡

ሲስተር ሔለን የእግሮቿ ሕመም ወደ ወገቧ እየተሸጋገረ በመምጣቱ ከትምህርትም ሆነ ከሥራ ተገላ እንድትቀመጥ ቢነገራትም ምክሩን ወደ ጎን ጥላ ትምህርቷን ለማሻሻል እየተማረች ትገኛለች፡፡ ‹‹ሥልጣኔና ማኅበረሰባዊ ዕድገት የራሱ የሆነ አስተዋጽኦ አለው፡፡ ቢሆንም ደግሞ ግላዊ የመንፈስ ጥንካሬና የቅርብ ሰዎች ድጋፍ በጣም ወሳኝ እንደሆነ የጄሲካ የሕይወትና የሥራ ስኬት ያሳየናል፤›› ያለችው ይህች አካል ጉዳተኛ፣ ከራሷ የሕይወት ተሞክሮ አንጻር በእርሷና በጄሲካ መካከል ያለውን ተቀራራቢነትና ልዩነት ለማስረዳት ሞክራለች፡፡

በዕለቱ ተጋባዥ ከነበሩ ግለሰቦች መካከል እግሮቹን እንደ እጆቹ በመጠቀም የእንጨት ሥራ በመሥራት የሚታወቀው የአካል ጉዳተኛ አቶ ስንታየሁ ይገኝበታል፡፡ ግለሰቡ በየትኛውም የዓለም ክፍል የሚገኝ የአካል ጉዳተኛ ከሚገጥመው የተለያየ መልካም ዕድል ውጪ ሁሉም ነገር ተመሳሳይ እንደሆነ ገልጿል፡፡ እሱም መኪናና አውሮፕላን የመሞከር ዕድል ቢገጥመው በእግሮቹ ብቻ እንዳሻው ሊያሽከረክርና ሊያበር እንደሚችል በልበ ሙሉነት ተናግሯል፡፡

አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የተለያየ ጉዳት ደርሶባቸው ሙሉ አካል የሌላቸውን 347 አካል ጉዳተኛ ተማሪዎችን ያሰለጥናል፡፡ ይህንን የገለጹት የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት ዶክተር አድማሱ ፀጋዬ የጄሲካ የሕይወት ተሞክሮና የስኬት ምስጢር ለተማሪዎቹ የላቀ አስተዋጽኦ እንዳለው ተናግረዋል፡፡ በአሜሪካ ኤምባሲ ትብብር መድረኩ መሰናዳቱን የገለጹት ፕሬዚዳንቱ፣ የጄሲካን ልዩ ልዩ የስኬት ውጤቶችን ዘርዝረው ተማሪዎች ከትምህርታቸው ባሻገር በሌሎች የሙያና የዕውቀት ዘርፎች ቢሰማሩ ውጤታማ መሆን እንደሚችሉ አቅጣጫን ለማመላከት ሞክረዋል፡፡

ዶክተር አድማሱ በዩኒቨርሲቲው ማኅበረሰብ ስም የተዘጋጀውን የአገር ባህል ልብስ ስጦታ ለጄሲካ ያበረከቱላት ሲሆን፣ እሷም ስጦታው ከተጠቀለለበት ወረቀት ውስጥ በእግሮቿ ፈታታ አውጥታ ለታዳሚዎቹ አሳይታለች፡፡