መነሻ ገጽ - ሌሎች አምዶች - ማህበራዊ ጉዳዮች - ወጣት - ኢትዮጵያዊው የዓለም ወጣት መሪዎች ተመራጩ
Buy Valtrex Online Buy Albuterol inhaler Online Buy Prinivil Online
10 April 2013 ተጻፈ በ 

ኢትዮጵያዊው የዓለም ወጣት መሪዎች ተመራጩ

በዓለም ኢኮኖሚ ፎረም ሥር የተለያዩ የፈጠራና የሙያ ባለቤቶች፣ ዓለም ላይ ታላቅ ተፅዕኖ መፍጠር የቻሉና ዕድሜያቸው ከ40 በታች የሆኑ ግለሰቦች የሚሰባሰቡበት  ‹‹ወጣት የዓለም መሪዎች›› (ያንግ ግሎባል ሊደርስ) የተሰኘ ቡድን አለ፡፡

  ቡድኑ የፎረሙን ‹‹ዓለምን ወደ ተሻለ ደረጃ ማድረስ›› የሚለውን ዓላማ ከሚያሳኩና የተለያየ ደረጃና አካሄድ ካላቸው 14 የተለያዩ ቡድኖች ውስጥ ይካተታል፡፡  በየጊዜው የላቀ አስተዋጽኦ፣ ግኝት ወይም ምርምር ያደረጉና ተፅዕኖ መፍጠር የቻሉ ግለሰቦች በየጊዜው ተወዳድረው ቡድኑን እንዲቀላቀሉ ይደረጋል፡፡

በያዝነው ዓመትም ለወጣት የዓለም መሪነት ከተመረጡት ከ70 አገሮች ከተወጣጡ 199 ወጣቶች መካከል  ኢትዮጵያዊው ዶክተር ሰለሞን አሰፋ ይገኝበታል፡፡ ከእነዚህም ውስጥ 19ኙ ከሰሃራ በታች ካሉ አፍሪካ አገሮች ሲመረጡ፣ 12ቱ ደግሞ ከመካከለኛው ምሥራቅና ሰሜን አፍሪካ የተውጣጡ ናቸው፡፡

   የ32 ዓመቱ ዶክተር ሰለሞን የፊዚክስ፣ የኮምፒውተር ሳይንስና የኤሌክትሪካል ኢንጂነሪንግ ባለሙያ ነው፡፡ ወጣቱ ዲግሪዎቹንና ማስተርሱን ከሠራበት አሜሪካ ከሚገኘው ከማሳቹሰትስ የቴክኖሎጂ ተቋም የዛሬ ዘጠኝ ዓመት ‹‹ኖቭል ፓሲቭ ኤንድ አክቲቭ ፎቶኒክ ክሪስታል ዲቫይዝስ ኦን ስሪ-ቪ ኤንድ ኤስአይ-ቤዝድ ፕላትፎርምስ›› በተሰኘው ምርምሩ ዶክተርነት  ተሰጥቶታል፡፡

ከነዶክተር ሰለሞን ጋር ከተመረጡ ወጣቶች መካከል የክሊንተን ፋውንዴሽን ቦርድ አባልና ለኤንቢሲ የአሜሪካ የዜና ተቋም ልዩ ዘጋቢ የሆነችው ቼልሲ ክሊንተንና የአይ አም ኤንጅል ፋውንዴሽን መሥራችና ከብላክ አይድ ፒስ የሙዚቃ ቡድን ጋር አብሮ በማቀንቀን የሚታወቀው ዊሊያም ጄምስ አዳምስ ወይም በቅፅል ስሙ ዊል አይ አም ይገኙበታል፡፡ ቀደም ብለው የቡድኑ አባል ለመሆን ብቁ ናቸው ተብለው ከተመረጡ ኢትዮጵያውያን መካከል ደግሞ የሶል ሬብልስ ጫማ አምራች ኩባንያ ዳይሬክተር የሆነችው ቤተልሔም ጥላሁንና የሳውዝ ዌስት ኢነርጂ ሊቀመንበርና ዋና ሥራ አስፈጻሚ የሆኑት አቶ ቴዎድሮስ አሸናፊ ይገኙበታል፡፡

ወጣቱን በወጣት የዓለም መሪዎች ስብስብ ውስጥ እንዲመረጥ ያደረገው ምርምሩ በኮምፒውተር ውስጥ የሚገኙት ቺፕሶች ላይ ያሉት የመዳብ ሽቦዎችን በትናንሽ ሲልከን ሰርኪዩት ተክቶ በኤሌክትሪክ ከሚንቀሳቀሱ ይልቅ በብርሃን እንዲሠሩ በማድረጉ ነው፡፡ እነዚህ ቺፕሶች የተገጠሙባቸው ኮምፒውተሮች እጅግ ፈጣንና በትንሽ የኤሌክትሪክ ኃይል የሚሠሩ ናቸው፡፡ ይህም ባሁኑ ጊዜ ጥቅም ላይ እየዋሉ ያሉት ኮምፒውተሮች ዶክተር ሰለሞን የሠራቸው ችፕሶች ቢገጠሙላቸው አሁን ካላቸው በ1000 ጊዜ የበለጠ ፍጥነት  ይኖራቸዋል ተብሏል፡፡

የዓለም ኢኮኖሚ ፎረም እ.ኤ.አ በ1971 ተመሥርቶ እንቅስቃሴ ከጀመረ ወዲህ ከዓለም የተውጣጡ 756 ወጣት ዓለም መሪዎች ስብስብ ይዟል፡፡ በየዓመቱ የ‹‹ወጣት ዓለም መሪዎች›› ቡድን ውስጥ ለመቀላቀል ከሚታጩ በርካታ ሰዎች ውስጥ በሥራ ስኬታማ የሆኑና ሌሎችን ማነቃቃት የሚያስችል ብቃት ያላቸው ግለሰቦች ብቻ ይመረጣሉ፡፡ መስፈርቱን ማሟላት የሚችሉ ሰዎችም በብዛት በመኖራቸው ከእጩዎቹ ውስጥ ነጥረው ማሸነፍ የሚችሉት በጣም ጥቂቱና እጅግ የላቀ ብቃት ያላቸው ብቻ በመሆናቸው ፉክክሩ ጠንካራ እንደሆነ በሒደቱ ያለፉና ሒደቱን የሚያውቁት ይመሰክራሉ፡፡

በኢኮኖሚክ ፎረሙ ላይ በተለያዩ ቡድኖች ተቧድነው የሚካተቱ ግለሰቦች የሚወያዩባቸው አርዕስተ ጉዳዮች የኢኮኖሚ ዕድገት፣ የአካባቢ ጥበቃ፣ ፋይናንስ፣ ጤናና ማኅበረሰባዊ ዕድገቶች እንደሆኑ ለመረዳት ተችሏል፡፡ እነርሱም የሚሰጧቸው ሐሳቦች ገንቢ በመሆናቸው የዓለም ታላላቅ ሰዎችና መሪዎች የሚሳተፉበት ዓመታዊው ፎረም ላይ ተገኝተው ያንጸባርቃሉ፡፡ የለውጥንም አቅጣጫ ያሳያሉ፡፡     

ዶክተር ሰለሞን ለከፍተኛ  ትምህርት ወደ አሜሪካ ከመሄዱ በፊት የመጀመሪያና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን ድል በትግልና አይሲኤስ በሚባሉ ትምህርት ቤቶች ውስጥ ተከታትሏል፡፡

ወጣቱ ከዚህ ቀደም ከታዲያስ ሜጋዚን ጋር ባደረገው ቃለ ምልልስ ኢትዮጵያ ውስጥ ባለው የሳይንስና ቴክኖሎጂ ዘርፍ ላይ ሰፊ ኢንቨስትመንት ሊኖር እንደሚገባና ይህም ለአገሪቷ ዕድገት ወሳኝ እንደሆነ ተናግሯል፡፡