መነሻ ገጽ - ፓለቲካ - በታላቁ የህዳሴ ግድብ ላይ የተደመጠው ባእድ ድምፅ
Buy Valtrex Online Buy Albuterol inhaler Online Buy Prinivil Online
10 March 2013 ተጻፈ በ 

በታላቁ የህዳሴ ግድብ ላይ የተደመጠው ባእድ ድምፅ

‹‹ኢትዮጵያ እየገነባች ያለችው ታላቁ የህዳሴ ግድብ ከ70 ቢሊዮን ሜትሪክ ኪዩብ በላይ ውኃ የማጠራቀም አቅም የሚኖረውና ከሱዳን ድንበር 12 ኪሎ ሜትር ርቀት፣ በ700 ሜትር ከፍታ (አልቲትዩድ) ላይ የሚገነባ ነው፡፡

ይህ ግድብ በማንኛውም ምክንያት የመፍረስ አደጋ ቢገጥመው ሱዳን ሙሉ በሙሉ ትጠፋለች፡፡ ከዚህ አልፎም በግብፅ የአስዋን ግድብ ላይ ተጨማሪ ጉዳት ሊያደርስ ይችላል፡፡››

‹‹በዚህ የህዳሴ ግድብ በዋናነት የምትጐዳው ግብፅ ነች፡፡ ምክንያቱም ግብፅ ከሌሎቹ የዓባይ ተፋሰስ አገሮች ጋር ስትነፃፀር ሌላ ምንም ዓይነት የውኃ አማራጭ የሌላት አገር ነች፡፡ ከሱዳን ድንበር 12 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የሚገነባው ይህ የኃይል ማመንጫ ግድብ ሊኖረው ከሚችለው ኢኮኖሚያዊ ጥቅም ይልቅ ፖለቲካዊ ትንኮሳው ያመዝናል፡፡ እናም በግብፅና በሱዳን ብሔራዊ ደኅንነት ላይ የተጋረጠ ሥጋት ነው፡፡››

ከላይ የተቀመጠውን መልዕክት የያዘው ድምፅ የተሰማው ከአሥሩ የዓባይ ተፋሰስ አገሮች አይደለም፡፡ ድምፁ ከሳምንት በፊት ከተፋሰሱ አገሮች ውጭ 11ኛ ሆና ብቅ ካለችውና ለተፋሰሱ ባዕድ ከሆነችው የሳዑዲ ዓረቢያ ምክትል የመከላከያ ሚኒስትር አንደበት የወጣ ነው፡፡

ምክትል ሚኒስትሩ ልዑል ካሊድ ቢን ሡልጣን ድምፃቸውን ያሰሙት ከቀናት በፊት በግብፅ ካይሮ ከተማ በተካሄደው የዓረብ የውኃ ምክር ቤት ዓመታዊ ስብሰባ ላይ ተገኝተው ነው፡፡ ምክትል የመከላከያ ሚኒስትሩ በዚህ ብቻ አላበቁም ቀጥለዋል፡፡ ‹‹ይህ ግድብ ተጠናቀቀ ማለት ኢትዮጵያ እያንዳንዷን የውኃ ጠብታ በቁጥጥሯ ሥር ማድረግ ቻለች ማለት ነው፡፡ ይህ ደግሞ አሳሳቢ ነው፡፡ በመሆኑም አሁን ባለው ደረጃም ሆነ ወደፊት ሊፈጥር የሚችለውን አደጋ አሳንሰን ልንመለከተው አይገባም፤›› ብለዋል፡፡

የህዳሴው ግድብ የሌሎች አገሮችን በተለይም በግብፅና በሱዳን ላይ ሊያስከትል የሚችለው ጉዳት አለመኖሩን ለማሳየት በኢትዮጵያ ሐሳብ አመንጪነት ከሦስቱ አገሮች የተውጣጡ እንዲሁም ዓለም አቀፍ ገለልተኛ ባለሙያዎች የተካተቱበት የቴክኒክ ኮሚቴ በግድቡና ግድቡ ሊፈጥር ስለሚችለው ተፅዕኖ ጥናት እያካሄዱ ባለበት ወቅት፣ የተደመጠው የሳዑዲ ምክትል የመከላከያ ሚኒስትር ድምፅ የኢትዮጵያ መንግሥትን እንዲሁም ኢትዮጵያውያንን ያስደነገጠ፣ ያስገረመና ጥያቄዎችን ያስነሳ ነው፡፡

በተለይም ከኢትዮጵያ ጋር ዘመናትን ያስቆጠረ ታሪካዊ ግንኙነት ካላት፣ በአንፃራዊ መልኩም ኢኮኖሚያዊ ቁርኝትን ከፈጠረችና በማጠናከር ላይ ከምትገኘው ሳዑዲ ዓረቢያ ከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣን መሰንዘሩ የኢትዮጵያ መንግሥትና ሕዝብን አስደንግጧል፡፡ የሳዑዲ ዓረቢያ ባለሥልጣን ለምን በዚህ ወቅት ተናገሩ? የሚሉ መሠረታዊ ጥያቄ ኢትዮጵያውያን እንዲጠይቁ ተገደዋል፡፡

ጥያቄያቸውም እስካሁን ምላሽ ያላገኘ እንቆቅልሽ ሆኗል፡፡ በተለይም የልዑሉ ንግግር በእርግጥ የመንግሥታቸው አቋም ነው ወይ? የሚለው የኢትዮጵያ መንግሥት ትኩረት ሆኗል፡፡ ይህንን ጥያቄ ለመመለስ የኢትዮጵያ መንግሥት በአዲስ አበባ የሚገኙትን የሳዑዲ ዓረቢያ አምባሳደር ግልጽ ማብራሪያ ከመጠየቁም ባሻገር፣ የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ከኢትዮጵያ ጋር በተያያዘ ግልጽና እርግጠኛ የሆነውን የሳዑዲ መንግሥት የፖለቲካ አቋም በራሱ መንገድ ማወቅ ተቋማዊ ኃላፊቱ በመሆኑ ቀጣይ ተልዕኮው እንደሚሆን መገመት ይቻላል፡፡

የሳዑዲ ዓረቢያና የኢትዮጵያ ግንኙነት
ሳዑዲ ዓረቢያ ጥልቅ በሆነና ረጅም ዓመታትን ባስቆጠረው ሃይማኖታዊ ታሪክ ራሷን ከኢትዮጵያ ጋር ያቆራኘች አገር ነች፡፡ የሁለቱ አገሮች ታሪካዊ ግንኙነት የሚጀምረው የነብዩ መሐመድ ተከታዮች የሆኑ ሳዑዲ ዓረቢያዊያን በአገራቸው የደረሰባቸውን እንግልት ሸሽተው በስደት ወደ ኢትዮጵያ ከገቡበትና መልካም አቀባበል ካደረጉላቸው የወቅቱ የኢትዮጵያ ንጉሥ፣ ንጉሥ አርማህ ዘመን ነው፡፡ በዚህ ታሪካዊ መሠረት ላይ የተገነባው የሳዑዲ ዓረቢያና ኢትዮጵያ ግንኙነት በመንግሥት መለዋወጥ እንኳን ተሸርሽሮ አያውቅም፡፡

በተለይም ደግሞ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ሳዑዲ ዓረቢያ የራሷን የምግብ ደህንነት ለማረጋገጥ ስትል ባለሀብቶቿ ቅርብ በሆኑት የምሥራቅ አፍሪካ አገሮች ላይ በግብርና አሰማርታለች፡፡ በዓመት ከስምንት ቢሊዮን ዶላር በላይ ገንዘብ ለግብርና ዘርፉ በመደጐም ጥቂት በግብርና የተሰማሩ ባለሀብቶች ሳውዲ ዓረቢያን ሲቀልቡ ቢኖሩም፣ እያደገ በመጣው የሕዝብ ቁጥርና በሚታረስ መሬት መጠን አለመጣጣም ሳዑዲ ተጨማሪ የእህል ግዥ ውስጥ እንድትገባ አድርጓታል፡፡

ለዚህ ነው ሰፊ ያልታረሰ መሬት ባላቸው የምሥራቅ አፍሪካ አገሮች ላይ ትኩረት ያደረገችው፡፡ የሳዑዲ ፍላጐት ለምሥራቅ አፍሪካ አገሮች የግብርና ዕድገት አስተዋጽኦ ያለው በመሆኑ ሳዑዲን ከእነዚህ አገሮች የሚያገናኘው  የመጀመርያው ስብሰባ እ.ኤ.አ በ2009 በአዲስ አበባ ተካሄደ፡፡ በዚህ ወቅትም በሰባት የሳዑዲ ዓረቢያ ሚኒስትሮች መሪነት ከ500 በላይ የአገሪቱ ባለሀብቶች ወደ አዲስ አበባ በመምጣት በአዲስ አበባ ከተገኙት የምሥራቅ አፍሪካ መሪዎች ጋር ተወያይተው መግባባት ላይ ደርሰዋል፡፡ ከዚህ ስብሰባ በኋላም የሁለቱ አገሮች ኢኮኖሚያዊ ትስስር እየተጠናከረ መጥቷል፡፡

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን የተለያዩ የሳዑዲ ዓረቢያ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች አክራሪ የእስልምና እምነትን በኢትዮጵያ ለማስረጽ እየተጉ ነው በማለት ከኢትዮጵያ መንግሥት በኩል ወቀሳ እየተሰነዘረ ነው፡፡ በተጨማሪም ኢትዮጵያ በአገሪቱ ውስጥ የሚገኙ በሳዑዲ ዓረቢያ የገንዘብ ድጋፍ የተመሠረቱ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶችን ዘግታለች፡፡ የኢትዮጵያ መንግሥት በአክራሪነትና በተያያዥ እንቅስቃሴዎች ተሳትፈዋል ያላቸውን ኢትዮጵያውያን ሙስሊሞችን በሕግ የመጠየቅ ሒደት ውስጥ ሲሆን፣ ጉዳዩ በሳዑዲ ዓረቢያ መንግሥትና በኢትዮጵያ ግንኙነት ላይ ስለፈጠረው አሉታዊ ተፅዕኖ በእርግጠኝነት ማለት የሚቻል ነገር የለም፡፡

በሚኒስትር ደረጃ የነበሩት አቶ ጁነዲን ሳዶና ባለቤታቸው ተሳትፈውበታል በተባለው ሕገወጥ ተግባር ላይ በአዲስ አበባ የሚገኘው የሳዑዲ ዓረቢያ ኤምባሲ እጁ አለበት ቢባልም፣ የኢትዮጵያ መንግሥት ግን ከሳዑዲ ጋር ስላለው ግንኙነት ሲል በኤምባሲው ላይ የወሰደው ዕርምጃም ሆነ የተለየ አቋም አልታየም፡፡ የኢትዮጵያና ሳዑዲ ዓረቢያ ግንኙነት በእነዚህ ጠቅለል ባሉ የሁለት አገሮች የግንኙነት ገጽታ ላይ በመንተራስም አገሮቹ በመልካም ግንኙነት ላይ ያሉ ናቸው ማለት ይቻላል፡፡

ሳዑዲ - ግብፅ
ሳዑዲ ዓረቢያና ግብፅ በዓረቡ ዓለም ውስጥ ወሳኝ ከሚባሉት አገሮች ዋነኞቹ ናቸው፡፡ ከፍተኛ የሕዝብ ቁጥር ግብፅን ለዓረቡ ዓለም የበላይነት ያበቃት ሲሆን፣ ሳዑዲ ዓረቢያ ደግሞ ከኃያላኑ የአውሮፓ አገሮች ጋር ያላት ጥብቅ ወዳጅነት በዓረቡ ዓለም ወሳኝ ተደርጋ እንድትታይ አስችሏታል፡፡ እጅግ በርካታ ዘመናትን ያስቆጠረው የግብፅና የሳዑዲ ግንኙነት ግን በመልካም መሠረትና ወዳጅነት ላይ የተገነባ ነው ከማለት ይልቅ በአለመግባባትና በጦርነት የታጀበ ነበር ማለት ይቻላል፡፡

በ19ኛው ክፍለ ዘመን ከ1811 እስከ 1818 የግብፅ ገዥ የነበሩት ኢብራሂሞቪች በኤምሬትስ ኦፍ ደሪያህ (የሳዑዲ የቀድሞ መጠሪያ) ላይ በከፈቱት ዘመቻ ሔጃዝና ነጅድ የተባሉ ግዛቶችን በመቆጣጠር የተጠናቀቀ ሲሆን፣ ይህም የመጀመርያዋን ሳዑዲ ዓረቢያን ህልውና ያሳጣ መሆኑን ታሪክ ያስታውሰዋል፡፡ በግብፁ ፕሬዚዳንት ጋማል አብድል ናስር ወቅትም ቢሆን፣ ሁለቱ አገሮች በዓረቡ ዓለም ተደማጭነትንና የበላይነትን ለማግኘት ደክመዋል፡፡ በሰሜን የመን የነበረው የእርስ በርስ ጦርነት የሁለቱ አገሮች እጅ የነበረበት በመሆኑ፣ በወቅቱ በየመን የነበረው መንግሥት የሳዑዲ ዓረቢያ ‹‹ቅምጥ›› ነው የሚለው የግብፅ አቋም የብጥብጡ መነሻ ነበር፡፡

የሁለቱ አገሮች ፍጥጫና በዓረቡ ዓለም ላይ የበላይነትን ለመቆናጠጥ የሚደረገው ፉክክር በዚህ ብቻ የተወሰነ አልነበረም፡፡ ከጋማል አብዱል ናስር በኋላ ወደ ሥልጣን የመጡት አንዋር ሳዳት ለእስራኤል የተለየ የፖለቲካ አመለካከት ማሳየት መጀመራቸውና ከእስራኤል ጋር ሰላምን በማውረድ ግብፅ የመጀመርያዋ የዓረብ አገር እንድትሆን ማድረጋቸው ከሳዑዲ በኩል ከፍተኛ ትችትና ተቃርኖ ገጥሟቸዋል፡፡

ፕሬዚዳንት ሆስኒ ሙባረክ ወደ ሥልጣን ከመጡ በኋላ ሁለቱ አገሮች የተሻለ ወዳጅነት ያሳዩ ቢመስሉም ውስጥ ውስጡን ግን በዓረቡ ዓለም ላይ የሚያደርጉት ፉክክር በግልጽ ይታይ ነበር፡፡ ፕሬዚዳንት ሙባረክ የተከተሉት ፖለቲካ ግብፅን ከምዕራባውያኑ አገሮች በተለይም ከአሜሪካ ጋር ያወዳጀ በመሆኑና ይህ የፖለቲካ አካሄድ ደግሞ ለዓመታት በሳዑዲ በኩል የተተገበረ በመሆኑ፣ ለመግባባታቸው ምንጭ የምዕራባውያኑ ተፅዕኖ ሊሆን እንደሚችል መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡ የውስጥ ፉክክሩ ግን እንዳለ ነበር፡፡ ይህንን ፍንትው አድርጐ ያሳየው ወደ ሥልጣን መምጣታቸውን ተከትሎ ፕሬዚዳንት ኦባማ የመጀመርያ የዓረብ አገሮች ጉብኝታቸውን በግብፅ ማድረጋቸው ነበር፡፡ የሳዑዲ ዓረቢያ መንግሥት ፕሬዚዳንት ኦባማ የመጀመርያ ጉብኝታቸውን በግብፅ ማድረጋቸውን በግልጽ የተቸ ሲሆን፣ የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መሥርያ ቤትም የሳዑዲ መንግሥት ቅያሜን ለማለዘብ በፕሬዚዳንት ኦባማ የተመራ ከፍተኛ የመንግሥት ልዑክ ከግብፅ ቆይታ በኋላ ወደ ሳዑዲ እንዲያመራ መደረጉን መረጃዎች ያስረዳሉ፡፡

እ.ኤ.አ በ2011 በግብፅ የተካሄደውን ሕዝባዊ አመፅ ክፉኛ በመቃወም የፕሬዚዳንት ሙባረክ ወዳጅ መሆኗን ሳዑዲ የገለጸች ቢሆንም፣ ውጤቱ ግን በተቃራኒው በመሆኑ የፕሬዚዳንት ሙባረክ ዘመን ተጠናቆ የሁለቱ አገሮች ግንኙነት እንደ አዲስ ተጀምሯል፡፡

ባለፈው ዓመት ሚያዝያ ወር ላይ ግብፃውያን በካይሮ በሚገኘው የሳዑዲ ኤምባሲ ላይ ተቃውሞ ማካሄዳቸውን ተከትሎ ሳዑዲ ኤምባሲዋን በመዝጋት አምባሳደሯን ወደ አገር መመለሷ የሚታወስ የቅርብ ጊዜ እውነት ነው፡፡ የዚህ ጠብ መነሻ አህመድ አል ጊዛዊ የተባለው የግብፅ የሕግ ባለሙያ የሳዑዲውን ንጉሥ ስም አጥፍቷል በሚል ወደ ሳዑዲ ዓረቢያ በገባበት ወቅት በመያዙ ሲሆን፣ ሳዑዲ ግን ግለሰቡ የተያዘው ሕገወጥ ዕፅ ወደ ሳዑዲ ዓረቢያ ለማሳለፍ ሲሞክር ነው በማለት ቀጥታዋለች፡፡ ፕሬዚዳንት መሐመድ ሙርሲ ወደ ሥልጣን ከመጡ በኋላም ቢሆን የሁለቱ አገሮች ውዝግብ እንደቀጠለ ነው፡፡ ሳዑዲ በግዛቷ የሚገኙ ግብፃውያን ሠራተኞችን ከሥራ መቀነስ መጀመሯን መረጃዎች ያስረዳሉ፡፡

ይሁን እንጂ በአሁኑ ወቅት መጠነኛ መለሳለስ እየታየ ነው፡፡ ሳዑዲ ዓረቢያም ኤምባሲዋን በካይሮ መልሳ ከፍታለች፡፡ ለማሳየት እንደተሞከረው  ከግብፅ የተሻለ ሳዑዲ ዓረቢያ ከኢትዮጵያ ጋር ፖለቲካዊ ግንኙነት መሥርታለች ማለት ይቻላል፡፡ ልዑል ካሊድ ቢን ሡልጣን በቅርቡ በግብፅ ያስተላለፉትን ኢትዮጵያን ያስቆጣ ንግግር አስመልክቶም በውጭ ጉዳይ ሚኒስትሯ በኩል ይህ የመንግሥቷ አቋም አለመሆኑን አስረድታለች፡፡

ልዑል ካሊድ ቢን ሡልጣን ማን ናቸው?
ልዑል ካሊድ ቢን ሡልጣን 64 ዓመታቸው ሲሆን፣ የተወለዱት ከቀድሞው የሳዑዲ ዓረቢያ ልዑል ሡልጣን ቢን አብድላዚዝ ነው፡፡ ልዑል ካሊድ ሳዑዲ ከሚገኘው ንጉሥ ፉአድ ዩኒቨርሲቲ ከተመረቁ በኋላ በአገራቸው የወታደራዊ ሳይንስ ትምህርት በሮያል ወታደራዊ አካዳሚ ተከታትለዋል፡፡ በመቀጠል በአሜሪካ ካንሳስ ግዛት ተጨማሪ የውትድርና ትምህርት ሲቀስሙ፣ እንዲሁም ከአላባማ ኤር ዋር ኮሌጅም ተመርቀዋል፡፡ በመቀጥልም ኡበርን ከተባለ ዩኒቨርሲቲ የማስተርስ ዲግሪያቸውን በፖለቲካ ሳይንስ ይዘዋል፡፡

በርካታ ዓመታትን በሳዑዲ ዓረቢያ መከላከያ ሠራዊት ውስጥ ያሳለፉት ልዑል ካሊድ በዚህ ቆይታቸው ወቅት የሳዑዲ የሚሳይል አባት የሚል ዕውቅና እስከማግኘት ደርሰዋል፡፡ ኢራቅ ኩዌትን በወረረችበት የመጀመርያው የፐርሺያ ባህረ ሰላጤ ጦርነት ወቅት የአሜሪካና ሳዑዲ ዓረቢያ ጥምር ጦር ኮማንደር በመሆን ከአሜሪካው ጀነራል ኖርማን ሽዋርክዞፍ ጋር ጦርነቱን መርተዋል፡፡

ልዑል ካሊድ ለረዥም ዓመታት በጦሩ ውስጥ ካገለገሉ በኋላ ሠራዊቱን በመልቀቅ በግል ንግድ ውስጥ ገብተዋል፡፡ ከተሠማሩባቸው የንግድ ዓይነቶች ውጭ መገናኛ ብዙኅንን የመቆጣጠር ልዩ ፍቅር ስለነበራቸው ሁለት ታዋቂ በዓረብኛ የሚታሙ ጋዜጦችን የገዙ ሲሆን፣ አል ሃያት የተባለው በእንግሊዝ አገር የሚታተመው በዓረቡ ዓለም ታዋቂ የሆነው ጋዜጣ አሁንም በእሳቸው ይዞታ ሥር ይገኛል፡፡

ከሡልጣን ቢን አብዱላዚዝ የተወለዱት ልዑል ካሊድ የአባታቸውን እግር የመከተል አባዜ የተጠናወታቸውና ለዚህም ማንኛውንም ዋጋ እንደሚከፍሉ ይነገርላቸዋል፡፡ አባታቸው የሳዑዲ ዓረቢያ ንጉሥ ለመሆን ዕጩ ከነበሩ የልዑል ቤተሰቦች መካከል በዕድሜ አነስተኛው ሰው ነበሩ፡፡ በተለያዩ የመንግሥት ከፍተኛ ኃላፊነቶች ያገለገሉት አባታቸው በመጨረሻዎቹ ዕድሜያቸው የሳዑዲ መከላከያ ሚኒስትርና ሁለተኛው የሳዑዲ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ለመሆን ችለዋል፡፡ ለንግሥና የተቀቡ የሳዑዲ ልዑል መሆን ደረጃም ደርሰው ነበር፡፡ እ.ኤ.አ በ2011 ግን በካንሰር በሽታ ሞተዋል፡፡

በመከላከያ ሠራዊቱ ቆይታቸው ልዩ ከበሬታና ከምዕራባውያን በተለይም ከአሜሪካ ጋር ወዳጅ የነበሩት ልዑል ሡልጣን እስልምናን በተለያዩ አገሮች ለማስፋፋት በግላቸው ከፍተኛ ሀብት ይመድቡ እንደነበር ታሪካቸው ያስረዳል፡፡ ኢትዮጵያ፣ ጂቡቲና ሶማሊያ እስልምናን ለማስፋፋት ሀብታቸውን ካፈሰሱባቸው አገሮች መካከል እንደሚገኙም መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡

የልዑል ካሊድ አባት የነበሩት ልዑል ሡልጣን ቢን አብዱላዚዝ በሕይወት በነበሩባቸው ዓመታት የፈጸሟቸው በርካታ ተግባራት በሳዑዲ ዓረቢያውያን ዘንድ ዝናን አትርፎላቸዋል፡፡ ልዑል ሡልጣን በሳዑዲ መንግሥት ውስጥ ከነበሩዋቸው ከፍተኛ ኃላፊነቶች በተጨማሪ በግላቸው በተለያዩ የበጐ አድራጐት መስኮች ከመሳተፍ ባለፈ በስማቸውም የተለያዩ የበጐ አድራጎት ድርጅቶችን መሥርተዋል፡፡ ከእነዚህ መካከል ልዑል ሡልጣን ቢን አብዱላዚዝ ዓለም አቀፍ የውኃ የሽልማት ድርጅት (ኢንተርናሽናል ወተር ፕራይዝ) አንዱ ነው፡፡ ይህ ተቋም የዓለም አገሮች በሚጋሯቸው የውኃ ሀብቶች ሳቢያ ግጭት ውስጥ እንዳይገቡ የተለያዩ አማራጭ የውኃ አጠቃቀም ሐሳቦችን፣ እንዲሁም በዚህ ዙሪያ የሚነሱ ግጭቶችን ለማስወገድ ሳይንሳዊ መፍትሔዎችን ለሚያቀርቡ ተመራማሪዎች የገንዘብ ድጋፍና ሽልማት በየዓመቱ የሚሰጥ ነው፡፡ ውኃ ፈጣሪ ለሰው ልጆች ከለገሳቸው ሀብቶች መካከል ድንቅ የሆነ ነው የሚሉት ልዑል ሡልጣን ይህ ልዩ የተፈጥሮ ሀብት የግጭት መፍለቂያ ሊሆን አይገባም የሚል እምነትም አላቸው፡፡ ይህና ሌሎች በጐ ተግባራቶቻቸውም በሳዑዲ ዓረቢያ የንግሥና ተዋረድ ወስጥ ከሚገኙ የንጉሡ ቤተሰቦች መካከል ለንግሥና የተቀቡ በዕድሜ ወጣቱ ልዑል እንዲሆኑ አብቅቷቸዋል፡፡

ልጃቸው ልዑል ካሊድ ጦሩን ተሰናብተው ከተሰማሩበት የንግድ ሥራ በድጋሚ ወደ ሠራዊቱ እ.ኤ.አ በ2001 ተመልሰዋል፡፡ በዚህ ወቅት የሳዑዲ መከላከያ ሚኒስቴር ረዳትና የአየር ኃይሉ አዛዥ በመሆን ተሹመዋል፡፡ የአባታቸውን እግር የመከተል ልምድ ያላቸው ልዑል ካሊድ በጦሩ ውስጥ በድጋሚ ከተመለሱ በኋላ በአጭር ዓመታት ውስጥ የሠራዊቱ ምክትል ሚኒስትርና የአየር ኃይል አዛዥ በመሆን ሥልጣናቸውን አደራጅተዋል፡፡

በአሁኑ ወቅት አባታቸው ጥለዋቸው ያለፏቸውን የበጐ አድራጐት ደርጅቶችንም በመምራት ላይ ይገኛሉ፡፡ በአባታቸው መስመር በመጓዝ በአጭር ጊዜ የተቀቡ ልዑል በመሆን የንግሥና መስመር ውስጥ መግባት የሚፈልጉት ልዑል ካሊድ እነዚህን የበጐ አድራጐት ድርጅቶች አጠናክሮ በመያዝ መራመድ አቋራጭ መንገድ መሆኑን አጥብቀው እንደሚያምኑ በማህደራቸው የሚገኙ ጽሑፎች ያስረዳሉ፡፡

ነገር ግን ልዑል ካሊድ በመንግሥት ሥልጣናቸው ከሚፈጽሟቸው ተልዕኮዎች ጐን ለጐን የግል ፍላጐታቸውን ለማሟላት የማይፈነቅሉት ድንጋይ እንደሌለና ችኩል እንደሆኑም ይነገራል፡፡ ለአብነት ያህል እ.ኤ.አ በ2009 በየመን የሚገኘውን የአልቃይዳ አሸባሪ ክንፍ እንዲመቱ ተልዕኮ በመውሰድ የአየር ድብደባ በመፈጸም ውጤት ቢያስመዘግቡም፣ በዚህ ተልዕኮ ውስጥ ግን ንፁኃን የየመን ዜጐች የተኙበትን ሆስፒታል በመደብደብ የበርካቶችን ሕይወት አጥፍተዋል፡፡ በዚህ ኃላፊነት የጐደለው ተግባር ዓለም አቀፍ ወቀሳን ያተረፉት ልዑል ካሊድ በፈጸሙት ተግባር ከመፀፀት ይልቅ የተለያዩ ምክንያቶችን ይሰነዝሩ ነበር፡፡ ‹‹የየመን መንግሥት የሆስፒታሉ አካባቢ የአልቃይዳ ክንፍ መቀመጫ ነው ብሎ በመልቀቁ ድብደባው እንዲፈጸም ወስኛለሁ፡፡ ስህተቱ የተፈጸመው ትክክለኛ ያልሆኑ የጦር መሣርያዎችን በመጠቀማችንና የአሜሪካ መንግሥትም ትክክለኛ መረጃ ሊያደርሰን ስላልቻለ ነው፡፡ ከባድ የጦር ጥቃት በመፈጸምና የሳዑዲ ዓረቢያ የጦር አቅምን በማሳየት የአልቃይዳ ክንፍ የሆኑት የየመን አማፂያን ከየመን መንግሥት ጋር እርቅ እንዲፈጥሩ ማድረግ የመንግሥቴ አቋም በመሆኑ ነው፤›› የሚሉ የተዛቡ አስተያየቶችን በመስጠት ግራ ሲያጋቡና ራሳቸውን እንዲሁም መንግሥታቸውን ለበለጠ ወቀሳ መዳረጋቸው የቅርብ ታሪክ ነው፡፡

በቅርቡ በቱርክ ኢስታንቡል ከተማ ላይ በተካሄደ 16ኛው የዓለም የውኃ ስብሰባ ላይ የተገኙት ልዑል ካሊድ ያደረጉት ንግግርና ከሳምንት በፊት ደግሞ በካይሮ ግብፅ ተገኝተው የጦርነት ይዘት ያለውንና በኢትዮጵያ፣ በግብፅና በሱዳን መካከል የዓባይ ውኃን በተመለከተ ውጥረትን የበለጠ የሚያፋፍመው ንግግር ሲነፃፀሩ፣ የልዑሉ አቋም ምን እንደሆነ ከማስረዳት ይልቅ ከፍተኛ የሐሳብ ግጭት ያለባቸው ለማለት ያስደፍራል፡፡

‹‹ስለውኃ ተፈጥሯዊ እውነት አንድ ነገር በመናገር ይህን ስብሰባ መልካም መንፈስ እንዳላብሰው ይፈቀድልኝ፡፡ በየትኛውም ዓለም በሚገኙ የተለያዩ ባህላዊ እሴት ባላቸው ማኅበረሰቦችና እምነት ተከታዮች ዘንድ ውኃ ቅዱስና ንፁህ ነው፡፡ ከሰው ልጆች ታሪካዊ አመጣጥ ጀምሮ ሰዎች ውኃ መንፈሳዊ ሕይወትን የማንፃት ኃይል ያለው የንፅህና ምንጭ መሆኑን ይገነዘባሉ፡፡ ፈጣሪ በልዩ ባህሪው ውኃን ልዩ አድርጐ ባርኮታል፡፡ የውኃ ሞሎኪውሎች ውህደት፣ የውኃ የመጨረሻ መቀዝቀዣ (ፍሪዚንግ) እና መፍያ (ቦይሊንግ) ዲግሪዎች ልዩነት፣ ውኃ ከፈሳሽነት ወደ ጠጣርነት የመቀየር ባህሪው ከሌሎች ልዩ ያደርጉታል፤›› በማለት በመንፈሳዊና በሳይንሳዊ ትንታኔ ንግግራቸውን ጀምረዋል፡፡

ቀጥለውም፣ ‹‹በአሁኑ ወቅት ዓለማችን ከውኃ ጋር በተያያዙ ሁለት ጥያቄዎች ተወጥራለች፡፡ በአንድ በኩል የውኃ እጥረትና ከዚህ ጋር የተያያዘው በምግብ ራስን የመቻል ጥያቄ ነው፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ የሕዝቦች ንፁህ የመጠጥ ውኃ የማግኘት መብት ነው፡፡ እነዚህን ሁለት ፍላጐቶች ሚዛናዊ በሆነ መንገድ ማርካታ ካልቻልን ውጥረቱ የግጭት መነሻ እንዲሆን ፈቀድን ማለት ነው፤›› በማለት ስብሰባው በተሻሉ ተጨባጭ የመፍትሔ ሐሳቦች ላይ እንዲያተኩር ጠይቀዋል፡፡

የልዑሉ ንግግር የማን ነው?
ከላይ የተዘረዘሩትን የኢትዮጵያና የሳዑዲ እንዲሁም የግብፅና የሳዑዲ ታሪካዊ ግንኙነቶች ቀጥሎም ምክትል የመከላከያ ሚኒስትሩ ሰብዕናና የሥልጣን ፍላጐትን አስመልክቶ ከቀረቡ ሀተታዎች በመነሳት የልዑሉ ሰሞነኛ ንግግር ሙሉ ለሙሉ የሳዑዲ ዓረቢያ አቋም ነው ወይስ የግል ሐሳብ? ወይም የተለመደ የአፍ ወለምታ? የሚለውን ጥያቄ ለመመለስ መደንደርደርያ ሊሆን ይችላል፡፡ ስማቸውን መጥቀስ ያልፈለጉ አንድ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ መምህር ልዑሉ በቅርቡ የሰጡት አስተያየት መንግሥታቸውን ይወክላል ለማለት በቂ አይደለም ይላሉ፡፡

ሳዑዲ ዓረቢያ በዓረቡ ዓለም እንዲኖራት የምትሻው የበላይነት ዘወትር ከግብፅ መንግሥት የከፋ ተቃርኖ የሚገጥመውና ወደፊትም በዚሁ መልኩ የሚቀጥል እንደሆነ የሚናገሩት ባለሙያው፣ የዓረቡ ዓለምን ከምዕራባውያንና ክርስትናን ከሚከተሉ አገሮች የማወዳጀት ፍላጐት ካለው የሳዑዲ መንግሥት የመነጨ ነው ብሎ መደምደም ከባድ ነው ይላሉ፡፡ ምክትል የመከላከያ ሚኒስትሩ ያደረጉትን ንግግር ተከትሎ በሳዑዲ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በኩል የተገለጸው በቂ ነው ባይባልም፣ ምላሹ በራሱ ግብፅ የዓባይ ተፋሰስን አስመልክቶ ካላት ፍላጎት ጋር የሚጋጭ በመሆኑ የሳዑዲ አቋም ነው ማለት አይቻልም በማለት ያስረዳሉ፡፡

አቶ ተፈራ በየነ በውኃና ኢነርጂ ሚኒስቴር የድንበር ዘለል ወንዞች ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተርና በዓባይ ጉዳይ ላይ የኢትዮጵያ ተደራዳሪም ናቸው፡፡ በዚህ ሳምንት በተካሄደው የ‹‹ናይል ዲስኮርስ›› ስብሰባ ላይ በዓባይ ተፋሰስ አገሮች በኩል ስላሉ አስተሳሰቦች ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡ የተፋሰሱ ስድስት አገሮች በተፋሰሱ ዙሪያ በትብብር የሚሠሩበትን ማዕቀፍ ቢፈርሙም ግብፅና ሱዳን ይህንን ስምምነት ከዚህ በኋላ ይፈርማሉ ብሎ መጠበቅ ከባድ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡ በአሁኑ ወቅት በተለይ በግብፅ በኩል የተያዘው አቋም የተለያዩ መንገዶችን በመጠቀም የትብብር ስምምነቱን በማደናቀፍ የኢትዮጵያን አካሄድ ማጨናገፍ ነው ብለዋል፡፡ በቅርቡ ከሳዑዲ መንግሥት ባለሥልጣናት ባልተለመደ ሁኔታ ከተደመጠው የልዑል ካሊድ አስደንጋጭ ንግግር ጀርባም የግብፅ እጅ ሊኖር ይችላል ብለዋል፡፡

ኢትዮጵያ የህዳሴ ግድቡን ከመጀመሯ በፊት ወይም በዓባይ ዙሪያ በተፋሰሱ አገሮች የጠረጴዛ ውይይት ከመጀመሩ በፊት የነበረው የግብፅ ፖሊሲ ኢትዮጵያ ማንኛውንም ዓይነት የገንዘብ ድጋፍ ከአበዳሪ ዓለም አቀፍ ድርጅቶች እንዳታገኝ ተፅዕኖ መፍጠር እንደነበር የሚያስታውሱት የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲው መምህር፣ የሰሞኑ የሳዑዲው ልዑል ንግግርም ከዚህ የግብፅ የቀድሞ ተግባር ጋር ተመሳሳይ ነው ማለት እንደሚቻል ገልጸዋል፡፡

ግብፅ በሳዑዲው ባለሥልጣን በኩል ያስደመጠችው ድምፅ በአንድ ድንጋይ ሁለት ወፍ እንደመምታት ነው የሚሉት ደግሞ ሌላው የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ምሁር ናቸው፡፡ በዓለም አቀፍ ሕግ ተመራቂ የሆኑትና በዚህ ዙሪያም ከፍተኛ ልምድ ያካበቱት እኚህ ምሁር፣ ከሕግ አንፃር በመመልከት የሳዑዲው ልዑል ንግግር ከኢትዮጵያ ውጭ ሌላ ጉዳይ ላይም አነጣጥሯል ይላሉ፡፡ ንግግሩ የሚመለከታት ሌላዋ አገር ሱዳን መሆኗን የሚናገሩት መምህሩ፣ ሱዳን ኢትዮጵያ በዓባይ ላይ በምትገነባው የኃይል ማመንጫ እያሳየች ያለችው አቋም ከግብፅ አንፃር ሲመነዘር እጅግ ለዘብተኛ ነው፡፡ ይህ ደግሞ ለግብፅ ከፍተኛ ሥጋት ነው ይላሉ፡፡ ሱዳን ለዘብተኛ ከመሆኗ ባሻገርም በኢትዮጵያ መንግሥት የፖለቲካ ተፅዕኖ ሥር የመውደቅ አዝማሚያ እየታየባት ነው፡፡ ይህንንም ለህዳሴው ግድብ ግንባታ በምታደርገው ድጋፍ መግለጽ ይቻላል፡፡ ይህ ትልቅ የግብፅ ሥጋት ነው በማለት ያብራራሉ፡፡

እስካሁን የግብፅ ትልቁ መከራከሪያ የቅኝ ግዛት ስምምነቱ እንዲከበርላት መሆኑን የሚያስረዱት ምሁሩ፣ ይህም የውኃ ድርሻዋ እንዳይነካባት የምታደርገው ትግል ነው ብለዋል፡፡ የሱዳን ለዘብተኛ አቋም ተለውጦ የትብብር ስምምነቱን ልትቀበል ትችላለች የሚል ሥጋት በግብፅ በኩል መኖሩን የሚያስረዱት እኚህ መምህር፣ ሱዳን የሌሎቹን የተፋሰስ አገሮች ስምምነት ትቀላቀለች ማለት የቅኝ ግዛቱን መከራከሪያ ውድቅ ያደርገዋል ብለዋል፡፡ ምክንያቱም የቅኝ ግዛቱ ስምምነት አካል አንዷ ሱዳን በመሆኗ ነው ይላሉ፡፡

በመሆኑም ሱዳንን ለማንቃት በዓረቡ ዓለም ተሰሚነት ያላትን ሳዑዲ ዓረቢያን መጠቀም አንዱ መፍትሔ ከመሆኑ ባሻገር በኢትዮጵያ ላይም ሽብርን መንዛት ነው ብለዋል፡፡ በመፍትሔ ሐሳብነትም ኢትዮጵያ የግብፅን ብቻ ሳይሆን የሌሎች አገሮችን ፖለቲካዊ አቋም በዓባይ ዙሪያ ምን እንደሆነ ለመረዳት መሞከርና ራሷን ለመፍትሔ ማዘጋጀት ይገባታል ሲሉ ይመክራሉ፡፡ በተጨማሪም የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የውኃ ኮንቬንሽንን መፈረም ተገቢ ነው ይላሉ፡፡