መነሻ ገጽ - ፓለቲካ - የመኖሪያ ቤቶች እጥረትና አዲስ አበባውያን
Buy Valtrex Online Buy Albuterol inhaler Online Buy Prinivil Online
19 May 2013 ተጻፈ በ 

የመኖሪያ ቤቶች እጥረትና አዲስ አበባውያን

በአዲስ አበባ ከተማ ሥር ነቀል መፍትሔ ከሚያሻቸው ችግሮች አንዱ የመኖርያ ቤቶች እጥረት ነው፡፡ ላለፉት ዓመታት መኖሪያ ቤቶች በሚፈለገው መጠን ባለመገንባታቸው የከተማው ‹‹ውዝፍ›› የቤት ሥራ ሆኗል፡፡ 

በእርግጥ ኢሕአዴግ መራሹ መንግሥት ለመኖሪያ ቤቶች እጥረት ተጠያቂው የቀድሞውን ወታደራዊ መንግሥትን ቢያደርግም፣ ብዙዎች በኢሕአዴግ ላይ ጣታቸውን መቀሰራቸው አልቀረም፡፡

ኢሕአዴግ ወታደራዊውን መንግሥት ተጠያቂ የሚያደርገው በሚፈለገው ደረጃ የመኖሪያ ቤቶችን አልገነባም በሚል ነው፡፡ ይህ የኢሕአዴግ ክስ የማይዋጥላቸው ሰዎች ደግሞ ወታደራዊው መንግሥት ለነዋሪዎች እስከ 500 ካሬ ሜትር ድረስ መሬት ያቀርብ እንደነበር፣ ለቤት መሥሪያ የሚሆን ብድር የሚያቀርብ የገንዘብ ተቋም በማመቻቸቱና የቀድሞው የኪራይ ቤቶች አስተዳደር በተወሰነ ደረጃም ቢሆን ቤት የሚገነባ መሆኑን በመግለጽ ችግሩ የኢሕአዴግ እንደሆነ ይከራከራሉ፡፡

ኢሕአዴግ መራሹ መንግሥት ሥልጣን ከያዘበት 1983 ዓ.ም. ጀምሮ እስከ 1996 ዓ.ም. ድረስ ይህ ነው በሚባል ደረጃ በመኖሪያ ቤቶች ግንባታ ላይ እንዳልተሰማራ መከራከሪያቸውን ጨምረው ያቀርባሉ፡፡

ኢሕአዴግ ግን ይህንን አሜን ብሎ አይቀበልም፡፡ ከ1996 ዓ.ም. በፊት ባሉ ጊዜያት ለመኖርያ ቤቶች መሥሪያ ቦታ የሚያቀርብ መሆኑንና በደርግ ዘመን የነበረው የኪራይ ቤቶች አስተዳደር የተወሰኑ ቤቶችን ብቻ የሚያስተዳድር ተቋም እንደሆነ ተቃውሞውን ይሰነዝራል፡፡

ነገር ግን ዘግይቶም ቢሆን ኢሕአዴግ በ1996 ዓ.ም. የኮንዶሚኒየም ቤቶች ግንባታን ጀምሯል፡፡ በወቅቱ እነዚህን ቤቶች ለማግኘት የተመዘገቡ ሰዎች ቁጥር 453 ሺሕ ነበር፡፡ ይህንን ፕሮግራም የጀመረው በአቶ አርከበ ዕቁባይ ይመራ የነበረው የቀድሞ የአዲስ አበባ ጊዜያዊ አስተዳደር መሆኑ ይታወሳል፡፡ 

በወቅቱ የተቀረፀው ዕቅድ በየዓመቱ 1.2 ቢሊዮን ብር በመመደብ 50 ሺሕ ቤቶችን በየዓመቱ መገንባት ነበር፡፡ ይህ ዕቅድ ተግባራዊ ቢደረግ በዚህ ወቅት 450 ሺሕ ቤቶች ይገነቡ እንደነበር የቤቶች ኤጀንሲ መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡ ነገር ግን ይህ ዕቅድ በተለያዩ ፖለቲካዊና አስተዳደራዊ ችግሮች መቀጠል አልቻለም፡፡ በመሆኑም በአሁኑ ወቅት ተገንብተው ለተጠቃሚዎች የተላለፉት 110 ሺሕ ቤቶች ብቻ ናቸው፡፡ ይህ ባለመሳካቱም ከሦስት መቶ ሺሕ በላይ የሚሆኑ ቤት ፈላጊዎች ዘጠኝ ዓመት ሙሉ በመጠባበቅ ላይ ይገኛሉ፡፡ 

የመኖሪያ ቤት እጥረቱ ያሳሰበው መንግሥት በኮንዶሚኒየም ቤቶች ፕሮግራሙ ብቻ ችግሩን እንደማይወጣ ዘግይቶም ቢሆን የተረዳ መስሏል፡፡ ሰሞኑን እንደተገለጸው ከኮንዶሚኒየም (20/80) በተጨማሪ፣ ሌሎች ሦስት ፕሮግራሞችን አስተዋውቋል፡፡ በቅርቡም ምዝገባ እንደሚካሄድ አስታውቋል፡፡ አዲሶቹ ፕሮግራሞች 10/90፣ 40/60 እና የመኖሪያ ቤት ኅብረት ሥራ ማኅበራት ናቸው፡፡

10/90 እና 40/60 የሚባሉት ፕሮግራሞች ለከተማው አዲስ ቢሆኑም የመኖሪያ ቤት ኅብረት ሥራ ማኅበር ግን የሚታወቅ ፕሮግራም ነው፡፡

ቀደም ባሉት የአስተዳደር ወቅቶች በአዲስ አበባ ከተማ አምስት ሺሕ የመኖሪያ ቤቶች ኅብረት ሥራ ማኅበራት ተቋቁመዋል፡፡ እነዚህ ማኅበራት 97 ሺሕ አባላት ነበሩዋቸው፡፡ ነገር ግን ከተቋቋሙት ማኅበራቶች ውስጥ አብዛኞቹ በሕገወጥ መንገድ የተቋቋሙ፣ ሕገወጥ ጥቅም ለማግኘት ያሴሩና ተጠቃሚም የሆኑ አሉ በሚል ዕርምጃ ተወስዶባቸዋል፡፡

ዕርምጃው የተለያየ ቢሆንም ጭራሽ ለመኖሪያ ቤት ኅብረት ሥራ ማኅበራት መሬት ማቅረብም ተከልክሎ ቆይቷል፡፡ 

አስተዳደሩ አዲስ አዋጅ በማዘጋጀት የመኖሪያ ቤት ኅብረት ሥራ ማኅበራት ዳግም ነፍስ እንዲዘሩ አድርጓል፡፡ ነገር ግን አሁን እየተሰማ ያለው የነዋሪዎች ቅሬታ የኅብረት ሥራ ማኅበራት ለምን መቶ በመቶ ክፍያቸውን እንዲፈጽሙ ይገደዳሉ የሚል ነው፡፡ 

ምክንያቱም አሠራሩ ከፍተኛ ገቢ ላላቸው የኅብረተሰብ ክፍሎች ያዳላ ነው የሚል ነው መከራከሪያው፡፡ እነዚህ ወገኖች እንደሚሉት እየቆጠበ አቅም የሚፈጥር ማንኛውም ነዋሪ ከባንክ ጋር ተሳስሮ የራሱን መኖሪያ ቤት ሊገነባ እየቻለ፣ አስተዳደሩ ግን ይህንን ዕድል ሆን ብሎ አጥብቧል የሚል ነው፡፡ 

ከንቲባ ኩማ ደመቅሳ ለዚህ ቅሬታ ቀጥተኛ መልስ መስጠት አልፈለጉም፡፡ ከንቲባው በቅርቡ ለጋዜጠኞች እንደገለጹት ለዝቅተኛና መካከለኛ ገቢ ላለው የኅብረተሰብ ክፍል፣ መንግሥት ከፍተኛ ድጎማ አድርጎ 10/90 እና 20/80 የቤት ፕሮግራሞች ማቅረቡን ገልጸው፣ የተቀሩት 40/60 እና የመኖሪያ ቤት ኅብረት ሥራ ማኅበራት ፕሮግራሞች የተሻለ ገቢ ላላቸው ነዋሪዎች መቅረባቸውን ገልጸዋል፡፡ 

የከተማው አስተዳደር እነዚህን ፕሮግራሞች መጀመሩን ባስታወቀበት መድረክ ስድስት መቶ ሺሕ ተመዝጋቢዎች ሊኖሩ እንደሚችሉ ግምቱን ይፋ አድርጓል፡፡ በከተማው ውስጥ በአሁኑ ወቅት ከ500 ሺሕ ቤት በላይ እጥረት እንዳለ አመላካች መረጃ ነው ተብሎለታል፡፡ 

ነገር ግን ምዝገባው በሚካሄድባቸው 113 ወረዳዎች መጨናነቅ እንዳይፈጠር አስተዳደሩ 1.2 ሚሊዮን ቅጾች አሳትሟል፡፡ የ1,500 ኮምፒውተሮችና ዳታ ኢንኮደሮችን ግዥ ፈጽሞ ማሰራጨቱን ገልጿል፡፡ 

ላለፈው አንድ ዓመት ዝግጅት ሲደረግባቸው በቆዩት እነዚህ የቤት ፕሮግራሞች ተግባራዊ የሚያደርጉ አራት ሺሕ ሠራተኞች ሥልጠና ተሰጥቷቸዋል ተብሏል፡፡ 

የከተማውን ቁልፍ በቅርቡ ያስረክባል ተብሎ የሚጠበቀው የአቶ ኩማ ደመቅሳ አስተዳደር ባለፉት አምስት ዓመታት በቂ ልምድ አግኝቻለሁ በሚል ሕገወጦችን የሚያጠምድበት አሠራር መዘርጋቱን አስታውቋል፡፡

ብሔራዊ መረጃና ደኅንነት መረብ ኤጀንሲ ምዝገባ የሚካሄድበት ሶፍትዌር ሠርቶ ለአስተዳደሩ አስረክቧል፡፡ የተዘረጋው ወጥመድ አንድ ሰው በተለያዩ የቤት ፕሮግራሞች ምዝገባ ቢያካሂድ የሚታወቅበት አሠራር ነው ተብሏል፡፡ ባዮ ሜትሪክ እየተባለ የሚጠራው ይህ የምዝገባ አሠራር ሕገወጥ ጥቅም ለማግኘት የሚሞክሩትን ያጋልጣል ተብሏል፡፡ 

ለዚህ ሥራ የአዲስ አበባ አስተዳደር ለኤጀንሲው 11 ሚሊዮን ብር ክፍያ የፈጸመ ሲሆን፣ ይህንን ሥራ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በአማካሪነት ይሠራል፡፡ 

ከዚህ አዲስ ቴክኖሎጂ ያመለጠ ሕገወጥ ሰው በየማኅበረሰቡ በሚደረግ የማውጣጣት ሥራ ይጋለጣል የሚል መረጃ ተሰጥቷል፡፡ 

በእነዚህ የመኖሪያ ቤት ፕሮግራሞች ሕገወጥ ከሚባሉት ተግባራት መካከል፣ በራሱም ሆነ በትዳር አጋሩ መኖሪያ ቤት እያለው የተመዘገበ ሰው፣ ቀደም ሲል መኖሪያ ቤት ኖሮት ለሌላ ወገን ያስተላለፈ ሰው፣ ከአንድ ጊዜ በላይ የሚመዘገብ ከሆነ ትልቅ ጥፋት ተደርጎ ይመዘገባል፡፡ በዚህም ድርጊት ከበድ ያለ ቅጣት እንደሚጥል አስተዳደሩ አስጠንቅቋል፡፡ 

በእነዚህ የመኖሪያ ቤት ፕሮግራሞች የመንግሥት ሠራተኞች ልዩ ተጠቃሚ እንዲሆኑ ዕድሉ ተመቻችቶላቸዋል፡፡ የመንግሥት ሠራተኞች 20 በመቶ ቅድሚያ ይሰጣቸዋል ሲሉ የአዲስ አበባ ቤቶች ልማትና አስተዳደር ሥራ አስኪያጅ አቶ መስፍን መንግሥቱ ገልጸዋል፡፡ 

ቀደም ሲል ለሴቶች 30 በመቶ ቅድሚያ የተሰጠ በመሆኑ በተጠቃሚነት በኩል ሴቶችና የመንግሥት ሠራተኞች የአንበሳውን ድርሻ ይዘዋል፡፡

የመንግሥት ሠራተኞች ምዝገባ የሚያካሂዱት በ33 ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቶችና በሥራቸው በሚገኙ 177 ኤጀንሲዎች ውስጥ ነው፡፡

ምዝገባው የሚጀመረው በተለይ ለ10/90 እና ለ20/80 ቤቶች ፕሮግራም ተመዝጋቢዎች ከሰኔ 3 ቀን እስከ ሰኔ 21 ቀን 2005 ዓ.ም. ድረስ ይሆናል፡፡ በዚህ ጊዜ አዲስ ተመዝጋቢዎች ብቻ ሳይሆኑ ቀደም ሲል የኮንዶሚኒየም ቤት ለማግኘት የተመዘገቡ ሰዎችም በድጋሚ እንዲመዘገቡ ይጠበቃል፡፡ በድጋሚ ያልተመዘገበ ሰው በራሱ ፈቃድ ፕሮግራሙን እንደለቀቀ ይቆጠራል ተብሏል፡፡ 

እነዚህን መኖሪያ ቤቶች ማግኘት የሚፈልግ ሰው ገንዘብ መቆጠብ እንዳለበትና የሚቆጥበው ገንዘብ ዝቅተኛ ጣሪያ ተቀምጧል፡፡ ከዚህ በታች በሰንጠረዥ በዝርዝር ተቀምጧል፡፡ 

የቤት ዓይነት

አጠቃላይ የቤቱ ዋጋ

ወርኃዊ ቁጠባ

ተከፍሎ ማጠናቀቂያ ጊዜ

የ10/90

33 ሺሕ ብር

187 ብር

ከ2 – 3 ዓመት

የ20/80

ስቱዲዮ 61 ሺሕ ብር

ነባር 151 ብር

 

 

 

ለነባር 5 ዓመት

ለአዲስ 7 ዓመት

 

ባለ 1 መኝታ 126 ሺሕ 721 ብር

ነባር 247 ብር

አዲስ 196 ብር

 

ባለ 2 መኝታ 224 ሺሕ ብር

ነባር 561 ብር

አዲስ 401 ብር

 

ባለ 3 መኝታ 304 ሺሕ 215 ብር

ነባር 685 ብር

አዲስ 489 ብር

የ40/60

ባለ 1 መኝታ 162 ሺሕ 645 ብር

1 ሺሕ 33 ብር

 

እስከ 5 ዓመት

 

ባለ 2 መኝታ 250 ሺሕ ብር

1 ሺሕ 575 ብር

 

ባለ 3 መኝታ 386 ሺሕ 400 ብር

2,453 ብር

 

የቤት ዓይነት

አጠቃላይ ክፍያ

ቅድሚያ ክፍያ

 

የኅብረት ሥራ ማኅበራት

ባለ 1 መኝታ 210 ሺሕ

 

ከምዝገባ በፊት 50 በመቶ ዝግ አካውንት ማስገባት

ባለ 2 መኝታ 280 ሺሕ

ባለ 3 መኝታ 385 ሺሕ

እነዚህ ቤቶች ለተጠቃሚ የሚደርሱት በዕጣ ሲሆን ማንኛውም ቁጠባ የጀመረ ስሙ በዕጣው ውስጥ እንደሚካተት ተገልጿል፡፡ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በእነዚህ ፕሮግራሞች የነዋሪዎችን የመኖሪያ ቤት ፍላጎት አረካለሁ በሚል ቢንቀሳቀስም፣ ነዋሪዎች ይህ ፕሮግራም በምን ያህል ፍጥነት ተግባራዊ ይሆናል ሲሉ መጠየቃቸው አልቀረም፡፡ 

አስተዳደሩ ለ10/90 እስከ ሦስት ዓመት ጊዜ የሰጠ ሲሆን፣ ለ20/80 አዲስ ተመዝጋቢዎች በሰባት ዓመት ጊዜ ውስጥ፣ የነባር ተመዝጋቢዎች ፕሮግራምና የ40/60 ፕሮግራም በአምስት ዓመት ጊዜ ውስጥ እንደሚጠናቀቅ ገልጿል፡፡ ነዋሪዎች በዚህ ፕሮግራም የቤት ችግራቸው እንደሚፈታ ቢያልሙም፣ ፕሮግራሙ በዕቅዱ መሠረት ይተገበራል ወይ የሚለው ጥያቄ በሒደት የሚታይ ይሆናል፡፡