መነሻ ገጽ - ፓለቲካ - እንደ ወረደ የቀረበው የዶ/ር መረራ ጉዲና መጽሐፍ
Buy Valtrex Online Buy Albuterol inhaler Online Buy Prinivil Online
28 August 2013 ተጻፈ በ 

እንደ ወረደ የቀረበው የዶ/ር መረራ ጉዲና መጽሐፍ

የ1966 አብዮትና የዘመነ ኢሕአዴግ የፖለቲካ ውጣ ውረድን አስመልክቶ  በአገሪቷ ውስጥ የሚገኙ የፖለቲካ ድርጅቶችን ታሪክ፣ እንዲሁም በአገሪቷ የተከሰቱ ዓበይት ፖለቲካዊ ክንዋኔዎችና አጋጣሚዎችን በሚመለከት በተለያዩ ጊዜያት የተለያዩ መጻሕፍት ሲታተሙ ተስተውሏል፡፡

ወደፊትም የሚቀጥል ነው፡፡ እስካሁን ድረስ የተለያዩ መጻሕፍት ያሳተሙ ምሥጋና ይገባቸዋል፡፡ ቢያንስ ኅብረተሰቡን ለውይይትና ለክርክር ባስ ሲልም ለብስጭት ይዳርጉታልና፡፡ ብዙዎቹ ከፖለቲካ ጋር የሚያያዙ መጻሕፍት በድፍረት ራስን ከተጠያቂነት በማሸሽ ሲጻፉ፣ በጣም በጣም ጥቂቶቹ ወይም ከአንድ እጅ ጣቶች የሚያንሱት ግን በሰከነ መንፈስ ተጽፈው ተነበዋል፡፡ እንዲያም ሆኖ ግን መጻሕፍቱ መቅረባቸው ይበል ያሰኛል፡፡ ምርትና ግርድን የመለየት ዋናው ሥራ የአንባቢያን መሆኑ እንደተጠበቀ ሆኖ፡፡ 

እስካሁን ተጽፈው የታተሙትና አንባቢያን ዘንድ የደረሱ መጻሕፍት ሁሉም ማለት ቢከብድም፣ አብዛኞዎቹ ግን የሥነ ጽሑፍ ሙያ ከሚፈልገው ዓውድ ውጭ ከመጻፍቸውም በላይ ስሜታዊነት  በርትቶ ይታይባቸዋል፡፡ ከህሊና ጋር ሙግት የተደረገባቸው እንደሆኑ ቢገለጽም፣ የህሊና ሙግቱ የተደረገው እንዴት እንደሆነ ግራ ያጋባል፡፡  እንዲህም ሆኖ ንባቡ ይቀጥላል፡፡

በዚህ የተነሳም አብዛኞቹ የጽሑፍ ዝግጅቶች የሚከተሉትን ሦስት ዓይነት አቀራረቦችን መሠረት ያደረጉ መሆናቸውን መረዳት ይቻላል፡፡ አንደኛው የፖለቲካ ድርጅቶችንና በአመራር ደረጃ የነበሩ ወይም ያሉ ግለሰቦችን ለማወደስ ብሎ የሚነሳ  ሲሆን፣ ሁለተኛው ዓይነት ደግሞ የድርጅቶቹ ወይም የግለሰቦች ጠላት ወይም ተቃዋሚ ሆኖ እነርሱን ለማንቋሸሽና ለማጥላላት የሚነሳ የሚቀርብ ነው፡፡ ሦስተኛውና የመጨረሻው ደግሞ ራስን በፖለቲካ ድርጅቶች ውስጥ ከተፈጠሩ ስህተቶችና አላስፈላጊ መጠላለፎች ከተጠያቂነት የማሸሽ አዝማሚያ የሚስተዋልባቸው ጭብጦችን ይዞ የሚነሳ መሆኑን ከሚታተሙትና ለገበያ እየቀረቡ ካሉት መጻሕፍት መረዳት ይቻላል፡፡ እዚህ ላይ በቀና መንፈስ ተነሳስተው የነበራቸውን ዕውቀትና ልምድ በሰከነ መንገድ ለማካፈል የተነሱት ተዘንግተው አይደለም፡፡ ያን ያህል ቁጥራቸው የተበራከቱ አይደለም እንጂ፡፡ በቅርቡ ለሕትመት የበቃውና ከፍተኛ አድናቆት ያተረፈው በእንግሊዝኛ ቋንቋ የተጻፈው የሕይወት ተፈራ “ታወር ኢን ዘ ስካይ” መጽሐፍ ለዚህ ተጠቃሽ ነው፡፡ 

በዚህም ማነፃፀሪያ መሠረት በቅርቡ ለሕትመት የቀረበውን በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካል ሳይንስና ዓለም አቀፍ ግነኙነት መምህርና ታዋቂው ፖለቲከኛ ዶ/ር  መረራ ጉዲና፣ “የኢትዮጵያ ፖለቲካ ምስቅልቅል ጉዞና የሕይወቴ ትዝታዎች ከኢትዮጵያ ተማሪዎች ንቅናቄ እስከ ኢሕአዴግ” የሚለውን አዲስ መጽሐፍ እንመለከታለን፡፡

ይህ አሥራ ሁለት ምዕራፎችና አንድ አባሪ (እኔ ሳልጽፈው ኢሕአዴግ ራሱ ጽፎና አዘጋጅቶ የላከው የሚሉት ደብዳቤ) የተካተቱበት ባለ 264 ገጽ መጽሐፍ፣ የጸሐፊውን የሕይወት ውጣ ውረድ በማሳየት ረገድ የተሳካለት ቢሆንም፣ የኢትዮጵያ የፖለቲካ ምስቅልቅ ግን በአጥጋቢ ሁኔታ የተተነተነበት አይመስልም፡፡ በተለይ እንደ ፖለቲካ ሳይንስ መምህርነታቸውና በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ ካላቸው ዘለግ ያለ ተሳትፎ አንፃር ለጉዳዩ ቅርበት ስላላቸው፣ እንዲሁም ደግሞ ታላላቅ በተባሉት የኢትዮጵያ ፖለቲካ ፓርቲዎች ውስጥ እንደ መሥራታቸው፣ የፖለቲካውን ትንታኔ በደንብ አልተወጡትም፡፡ ሌላው ፖለቲካውን በደንብ አልተወጡትም የሚባልበት ምክንያት ደግም የመጽሐፉ አብዛኛው ክፍል የልጅነት፣ የትምህርት ቤትና የአብዮቱ ዘመን ላይ ማተኮሩ ነው፡፡ አብዮቱና ዘመኑን በተመለከተ በርካታ መጻሕፍት ታትመው ለአንባቢያን ደርሰዋል፡፡ ስለዚህ ጸሐፊው ጉዳዩን በተወሰኑ ማብራሪያዎች ገልጸውት አልፈው አሁን ስላሉበት የፖለቲካ ምስቅልቅልና መደረግ ይኖርበታል ብለው የሚያምኑት አዲስ ነገር ካለ ቢያስነብቡን መልካም ነበር፡፡ ግን አልሆነም፡፡

ይህ የሚባልበት ዋነኛው ምክንያት ግን በመጽሐፉ መግቢያ ላይ ጸሐፊው እንደገለጹት፣ “በአጭሩ ይህ ጽሑፍ ዋነኛ ዓላማው የዛሬው ትውልድ፣ የእኛ ትውልድ ከሠራው ስህተተም ሆነ ከከፈለው መስዋዕትነት በመማር ሁላችንንም በእኩልነት የምታስተናግድ ዲሞክራሲያዊት ኢትዮጵያ እንድትፈጠር የበኩሉን ሚና እንዲጫወት ለመምከር ነው፤” ስለሚል ነው፡፡ ይህ ትውልድ ያለፈው ትውልድ የሠራውን ስህተት እንዳይደግም ለመምከር የግድ በየእስር ቤቱ የደረሰውን ሰውነት እስኪተለተል መገረፍን፣ እርግጫንና የዱላ መዓትን እንዲሁም ሞትን ደግሞ ደጋግሞ በመንገር ሳይሆን፣ በጊዜው የነበረውን የአገር ፍቅር ስሜት፣ የወጣቶችን ንቃትና አንባቢነትን የሚተርክ መሆን አለበት ተብሎ ስለሚታመን ነው፡፡ የዚያ ትውልድ የጀግንነት ውሎና የደረሰበት አሰቃቂ መከራ መነገሩ እንዳለ ሆኖ፣ አርቆ ካለማሰብ የተፈጸመው የእርስ በርስ መበላላት ዛሬም እንዳይደገም የችግሮችን መንስዔ ፈልፍሎ ማውጣት ጠቃሚ ነበር፡፡ ከዚህም በላይ መፍትሔን ማመላከትም የተሻለ ይሆን ነበር፡፡ 

የመረራ የሕይወት ጉዞ

ጸሐፊው በሕይወት ተፈትነው እዚህ የደረሱ እንደሆኑ ከመጽሐፉ መረዳት ይቻላል፡፡ በመጽሐፉም ከልጅነታቸው አምቦ አካባቢ በሚገኝ የቶኬ መንደር ከብት ጥበቃ (የራሳቸው ቃል ነው) እስከ አምቦ ከተማ ያደረጉትን የመጀመሪያ የሕይወትና የትምህርት ቤት ትግል እያስነበቡን፣ ለትምህርት ያላቸውን ጥረትና ታታሪነት እያደነቅንና በየመሀሉ የሚከቷቸውን የትረካ ማዋዣዎችን እየተከተልን እንሄዳለን፡፡ ለምሳሌ ገጽ 8 ላይ ከልጅነታቸው ጀምሮ ቄሶችን እንደሚጠሉ ይገልጹልናል፡፡ ለዚህም ዋነኛ ምክንያት በአባታቸው ሞት ምክንያት ለቄሶቹ የሚቀርበው በየዓመቱ በተዝካር ስም የሚደገሰው የሚያደርሰውን ቀውስና በወላጅ እናታቸው ላይ ይደርስ የነበረውን መንገላታት ይቃወሙ እንደነበር ያትታሉ፡፡ በተለይ ቄሶቹ የአባታቸው አምስተኛ ዓመት ተስካር ተደግሶ ሲወሰድላቸው ሌላ ሀብታም ሞተው ስለነበር ይኼንን ንቀው ባለመገኘታቸው የተዘጋጀውን ምግብና መጠጥ ለኔ ቢጤዎች መከፋፈሉን ያስረዳሉ፡፡ በቄሶቹ ተግባርም እናታቸው ተስፋ ቆርጠው ተስካር ማውጣት ማቆማቸውን ያትታሉ፡፡

ዶ/ር መረራ በመጽሐፉ እንደገለጹትና እንዳብራሩት በትምህርት ላይ የወሰዱት አቋም አስገራሚ ነው፡፡ በተለያዩ ጊዜያት የደረሰባቸውን ፈታኝ ሁኔታዎች በማለፍ እዚህ ለመድረስ ያደረጉት ጥረትና ትጋት የሚደነቅና ምሳሌም ሊሆን የሚችል ነው፡፡  ከገጠራማዋ ቶኬ መንደር እስከ ኔዘርላንድስ ድረስ የዘለቀው የትምህርት ሕይወታቸው  በመጀመሪያዎቹ ክፍል ላይ በሰፊው አቅርበውታል፡፡ አሁንም ድረስ ለትምህርት ያላቸው ከፍተኛ ክብርና ትጋት በበጎ ጎኑ ሊወሳ የሚችል ትልቅ ተግባር ነው፡፡ ይህ ለዚህ ዘመን ትውልድም ሆነ ለመጪው ትልቅ ትምህርት እንደሚሆን ይታሰባል፡፡

መረራና ምስቅልቅሉ የወጣው የፖለቲካ ጉዞ 

ገና አምቦ የከፍተኛ ሁለተኛ ደረጃ ተማሪ ሳሉ ሳብ መለስ ሲያደርጋቸው የነበረው የፖለቲካና የፍትሕ ጥያቄ በኋላ ጠቅልለው ወደ ፖለቲካ እንዲገቡ እንዳስገደዳቸው ገልጸዋል፡፡ በዚህ የተነሳም የተለያዩ የፖለቲካ ፓርቲዎች ውስጥ እየገቡ ተሳትፈዋል፡፡ ያስመዘገቡትንም ውጤት በመጽሐፉ ውስጥ በዝርዝር ይገልጻሉ፡፡ በተለይ የኢትዮጵያ ተቃዋሚዎች ተጠናክረው መሥራት እንዳቃታቸው፣ ዋናው መሰናክልም ተቃዋሚ ፓርቲዎች እርስ በእርስ የሚያደርጉት ሽኩቻ መሆኑንም ይገልጻሉ፡፡ ለዚህ የሚሰጡት ትንታኔም በገጽ 178 ላይ እንዲህ ሰፍሯል፡፡

 “… ከኢሕአዴግ ስውር እጆች በተጨማሪ የአገራችንን ፖለቲካ በቀላሉ እንዳይወጣ ያደረጉት ሦስት መሠረታዊ ችግሮች እንዳሉ ነው፡፡ እነዚህን የታሪክ ፈተናዎች በሚሆን መንገድ ካላለፍን የኢትዮጵያ ፖለቲካ ካለህበት እርገጥ የሚወጣ አይመስለኝም፤” በማለት ሦስት ምክንያቶችን በዝርዝር ያስቀምጣሉ፡፡ እነርሱም ከሌላው  በተሻለ ኢትዮጵያዊ እኔ ነኝ የሚሉ በተለያዩ ሁለት ጫፎች የፖለቲካ ፓርቲዎች መቋቋም፣ የተቃዋሚ ፖለቲካ መሪዎች ግለሰባዊ ጠብ ፓርቲውን እስከ ማፍረስ ማድረሱንና ከኢትዮጵያ ውጭ በሚኖሩ (በተለይ በሰሜን አሜሪካ) ኢትዮጵያውያን ላይ ከፍተኛ እምነት መጣል መሆኑን ይዘረዝራሉ፡፡ 

እዚህ ላይ መነሳት ያለበት ጉዳይ ግን ጸሐፊው በተለያዩ ወቅቶች የተለያዩ የፖለቲካ ፓርቲዎች አባልና አመራር ሆነው መሥራታቸው ይታወሳል፡፡ ያለፉበትን የፖለቲካ፣ የቀለም ትምህርትና የዕውቀት ችግሮችን ነቅሶ ከማውጣትና አሁንም ቢሆን እንደ ማንኛውም ግለሰብ ችግሮቹን ከመዘርዘር ባለፈ መፍትሔ አይጠቁምም፡፡ ይኼ ደግሞ የብዙዎች የፖለቲካ ፓርቲ መሪዎች፣ ድርጅቶችና ግለሰቦች መሠረታዊ ችግር ነው፡፡ እየተፈጠረ ያለውን ችግር ከሥር ከመሠረቱ ማወቅ እጅግ ጠቃሚና  አስፈላጊ ቢሆንም፣ ችግሩ ይኼ ነው ብሎ ማለፍና ለዚህ ችግር ይኼ መፍትሔ ቢበጅለት ብሎ አማራጭ ማቅረብ ለየቅል ናቸው፡፡ በመጽሐፉ የችግሮቹ ዝርዝር ውስጥ እንደ መፍትሔ የተሰነዘረ ሐሳብ ባለመኖሩ ይኼንን ለማለት ያስገድዳል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም አሁን በአመራር ደረጃ በማገልገል ላይ የሚገኙበት መድረክም ቢሆን ይህ ሥጋት እንዳለበት እንዲህ በማለት በገጽ 180 ላይ ይጠቁማሉ፡፡ “ዛሬ ከተሳካለት መድረክ የሚጥረው እንደዚያ ዓይነት ክፍፍል እንዳይደገም ነው፤” ይላሉ፡፡

ዶ/ር መረራ በተለይ በዩኒቨርሲቲ ተማሪነት ዘመናቸው መኢሶንን እንዴት እንደተቀላቀሉ ጥርት አድርገው አይናገሩም፡፡ በመኢሶን ውስጥ የነበረውን እንቅስቃሴ፣ ከኢሕአፓ ጋር የተፈጠረውን ቅራኔ፣ መኢሶን እንዴት ደርግን እንደተጠጋና እንደተለየ ለዚህ ዘመን ትውልድ በሚገባው መንገድ አልተነተኑትም፡፡ ያዝ ለቀቅ እያደረጉ ቀድሞ ከሚተዋወቋቸው ሰዎች ጋር የሚያወሩ ነው የሚመስሉት፡፡ ይህ ያለማብራራት ችግር ብዙ ቦታ በስፋት ይስተዋላል፡፡ በተለይ በፖለቲካ ትንተናቸው አንድ ነገር ጀምረው ሳይጨርሱ ሌላ ገጠመኝ ያመጡና በግድ ነው ወደነበሩበት የሚመለሱት፡፡ ይህንንም ሲያደርጉ ቀጥለው እንደሚመለሱበት የሚዘረዝሩት ብዙ ቦታ ላይ ይገኛል፡፡ 

መረራና የኦሮሞ ፖለቲካ

ሌላው ጸሐፊው በስፋት ያነሱት ጉዳይ ስለ ኦሮሚያ ነፃነት፣ ስለ ኦነግና  ኦሮሚያ ላይ ደረሱ ስለተባሉ ግፎች፣ በደሎችና ጭቆናዎች ነው፡፡ እነዚህን ከመመልከታችን በፊት ግን ጸሐፊው ኦሮሞ የሚለውን ቃል በተከለከለ መንገድ በመጽሐፉ ውስጥ ሲጠቀሙ ይታያል፡፡ ለምሳሌ (ገጽ 9 እና 35) ጸሐፊው ኦሮሞ በመሆናቸው ብቻ የብሔረሰቡን ስም የብሔረሰቡ ተወላጆች በማይፈልጉት ስያሜ መጠቀማቸው ለምን ያሰኛል፡፡ ከእኔ ወዲያ ኦሮሞ ስለሌለ እንደፈለግኩ እጽፈዋለሁ ያሉም ያስመስልባቸዋል፡፡ ለዚህም እንደ ምክንያት የሚቀርብ አለ፡፡ ሌላውን ሁሉ ትተን በቅርቡ እሳቸው የሚያስተምሩበት የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ፕሬስ የሚያሳትማቸው ቆየት ያሉ የታሪክና የተለያዩ መጻሕፍት እንኳን በተጻፉበት ዘመን አገልግሎት ላይ ይውሉ የነበሩትን ስያሜዎች ቀይሮዋቸዋል፡፡ አሁን ቅቡልነት ባለው ስያሜ የአርትኦት ሥራ ሠርቶ ለሕዝብ እያቀረበ ባለበት ሁኔታ፣ እርሳቸው ግን ያንን ቃል እንደ ወረደ መጠቀማቸው በመጽሐፋቸው ውስጥ በተደጋጋሚ እንደገለጹት፣ የግትርነት ፀባያቸው ማሳያ የሆነ ይመስላል፡፡ እወክለዋለሁ የሚሉትን ብሔር በአደባባይ ሰድቦ ለሰዳቢ እንደመስጠት ከመቆጠሩም በላይ፣ ይህን የተለየ መብት ማን ሰጣቸው የሚል ጥያቄም ያጭራል፡፡

የኦሮሞ ጥያቄዎችን በተመለከተ ጥያቄዎቹን ለመመለስ በተለያዩ ወቅቶች ስለተሠሩና ስለታቀዱ ዕቅዶች እያብራሩ አሁን ያለበት ደረጃ ላይ መደረሱን ያወጉናል፡፡ አሁን የደረሰበት የትግልም ሆነ የመብት ጥያቄ በዝርዝርና በጥልቀት አልተቀመጠም፡፡ ሆኖም ግን የራሳቸውን ግላዊ አተያይ ያስቀምጣሉ፡፡ ከዚህ ጉዳይ ጋር ተያይዞ መነሳት ያለበት ጉዳይ ጸሐፊው እንደሚገልጹት በአሁኑ ወቅት፣ “በእኔ እምነት የመጀመሪያውን የትግል ምዕራፍ ጨርሰን ሁለተኛውና የመጨረሻው የትግል ምዕራፍ ውስጥ ገብተናል፤” የሚል ሐሳብ አለ፡፡ ጥያቄው ግን የመጀመሪያው ምዕራፍ ላይ ተነስተው የነበሩ የኦሮሞ መሠረታዊ መብቶችና ጥያቄዎች ተመልሰዋል ወይ? ቀደም ብለው ስለ ኦሮሚያ መገንጠል ሲሠሩ የነበሩ ድርጅቶች አሁን መገንጠል አያዋጣም እያሉ ከሌሎች ኅብረ ብሔራዊ ፓርቲዎች ጋር ጥምረት በሚያደርጉበት ጊዜ የመጀመሪያው ምዕራፍ ተመልሷል ማለት ይቻላል ወይ? አሁንም የመገንጠል ጥያቄ የሚያነሱ ፓርቲዎች እያሉ እንዴት ነው የመጀመሪያው ምዕራፍ የተጠናቀቀው? ወዘተ የሚሉ ጥያቄዎች ይነሳሉ፡፡ እነዚህ ጥያቄዎች ሳይመለሱ ወደ ሁለተኛውና ወደ መጨረሻው ምዕራፍ ተሸጋግረናል ማለትስ ምን ማለት ነው? ምክንያቱም እነዚህ ጉዳዮች ዛሬም አከራካሪ ናቸው፡፡ ሌላው ከዚሁ ጉዳይ ጋር ተያይዞ የሚነሳው ጥያቄ ደግሞ የኦሮሞ ትግል ወደ ሁለተኛውና ወደ መጨረሻው ምዕራፍ ተሸጋግሯል ሲባል ሁለተኛው ምዕራፍ ምንድን ነው? ከየት ተነስቶ ነው እዚህ የደረሰው? በሁለተኛውና በመጨረሻው ምዕራፍ የሚሠራው ምንድን ነው? የመሳሰሉት መልስ የሚሹ ጥያቄዎች ናቸው፡፡ ምላሽ የሌላቸው ጥያቄዎች ደግሞ መጽሐፉን ጎደሎ ያደርጉታል፡፡

መረራና የቃላት ግድፈቶቻቸው

የዶ/ር መረራን ንግግር ለብዙ ጊዜ ያዳመጠ ሰው የእሳቸውን የንግግር ለዛና የአብሻቂነት ባህሪ ያስታውሳል፡፡ ዶ/ር መራራ ኮርኳሪ ቃላትን እየተጠቀሙ ተከራካሪዎቻቸውን በማናደድም ይታወቃሉ፡፡ ያው የአነጋገራቸው ስልት በጽሑፋቸውም ላይ በሰፊው ይንፀባረቃል፡፡ በጣም አስገራሚው ጉዳይ ግን ስለ ቃላት አጠቃቀማቸው ለአንዲት ደቂቃም ቢሆን ቆም ብለው ያሰቡ አይመስሉም፡፡ ኧረ እንዲያውም የመጽሐፉ ረቂቅ የታተመ ነው የሚመስለው፡፡ እጅግ በርከት ያሉ የቃላት ስህተቶችና ግድፈቶች መጽሐፍ ውስጥ ተስተውለዋል፡፡ ለአብነት ያህል እነዚህን እንመልከት፡፡ ገጽ 63 “ተካ ትሉ የሚባል የደርግ አባል በማግስቱ መጣ፡፡” እንግዲህ “ትሉ” “ቱሉ” መባል ነበረበት፡፡  በዚሁ መጽሐፍ ላይ በሌላ ቦታ “ተካ ቱሉ” ብለው ይጠራሉ፡፡ እንዲህ ዓይነት ስህተት ለአንባቢያን ካለመጨነቅ በተጨማሪ የተጻፈበትን ቋንቋ ጉዳዬ ካለማለትም ይመነጫል፡፡  ሌላ አብነት ገጽ 110 “በዛ ጣቢያ ዓይኖቹ በድብደባ ብዛት የታወሩበት ልጅና የእግር ጣቶች በድብደባ ሙሉ በሙሉ የተቆራረጡበት  ልጅ…. በቀረው የሕይወት ዘመናቸው አንዱ ቆማጣ ሌላው ዓይነ ስውር ሆኖ ሊኖር ነው፡፡ የተቆመጠው ልጅ ሽንት ቤት የሚወሰደው የሚመለሰው በድጋፍ ነው፡፡” እዚህ አንቀጽ ውስጥ እንግዲህ የምንመለከተው አላስፈላጊ ቃላት መጠቀማቸውን ነው፡፡ አሁን በወቅቱ በነበረው የፖለቲካ ልዩነት ይገረፍ የነበረን ሰው “ቆማጣ” እያሉ መጥራት ለእርሳቸውስ ቢሆን እንደምን ቀለላቸው? ይህ ለፖለቲከኛ ትልቅ ስህተት ነው፡፡ በዚህ ዘመን የአካል ጉዳተኞች በጉዳታቸው ዓይነት የሚጠሩባቸው ስያሜዎች አሉ፡፡ አንድ አብነት ለመጨመር በገጽ 69 ላይ እንዲህ የሚል ስህተት ይገኛል፡፡ “ይዞታችንን ለማጠናከር መኢሶን ውስጥ የነበርነው የኦሮሞ ልሎች የኦሮሞ ብሔር ዲሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ኦብዲን) የሚባል ድርጅት ፈጠርን” “ልሎች” የሚለው ልጆች መሆኑ ነው፡፡

እነዚህን በምሳሌነት ለማንሳት እንጂ መጽሐፉ በቃላት ስህተት መታጨቁንና አንድም እንኳን የእርማት ሥራ አለመሠራቱን ማስተዋል ይቻላል፡፡ ከመጀመሪያው የምህፃረ ቃላት መረጃ ጀምሮ እስከ መጨረሻው ገጽ ድረስ ይህንን መታዘብ ይቻላል፡፡ የመጽሐፉ የጀርባ ሽፋን ላይ የሰፈረውን መረጃ ስናይ እንደነግጣለን፡፡ “የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ አጠናቋል…” የሚል የተዛባ መረጃ፡፡ መጽሐፉ ለሁለተኛ ጊዜ የሚታተም ከሆነ ቢታሰብበት መልካም ነው፡፡ የቃላትና የሰዋሰው ስህተቶች በመጽሐፉ ውስጥ ከዚህ ቀደም በሌሎች ጻሕፍት ባልታየ ሁኔታ ክብረ ወሰን ሰብረዋል፡፡ እሳቸው ሦስት መጻሐፍት በእንግሊዝኛ ቋንቋ ሲያሳትሙ ይህ ችግር ፈጽሞ አልታየም፡፡ አሁን ለምን? የአርትኦትና የፊደል ለቀማ ሥራ የሚያከናውኑ በርካታ ባለሙያዎች ባሉበት አገር ውስጥ እንዲህ ዓይነቱ መዝረክረክ ለሥነ ጽሑፍ ጨርሶ አይፈቀድም፡፡

ለምን ሕይወት ተፈራን?

በመጽሐፉ ገጽ 68 ላይ ጸሐፊው የ “ታወር ኢን ዘ ስካይ” ደራሲ የሆነችውን ሕይወት ተፈራን ያነሳሉ፡፡ የሚያነሷትም በደግ አይመስልም፡፡ “እሳት የላሰች ኢሕአፓ መጣች” የሚል ሪፖርት በዩኒቨርሲቲው የመኢሶን ኃላፊ በመሆናቸው ይደርሳቸው እንደነበር ያወሳሉ፡፡ ከዚህ ተነስተው በአጭሩ የሚገልጹት አለ፡፡ ዋናው ግን በአሁኑ ጊዜ ከሁለቱም ወገን ያልሆነ በቅን ልቦና ላይ የተመሠረተ መጽሐፍ ያሳተመችውን ጸሐፊ፣ “በዩኒቨርሲቲ የመሳሳሚያ ገንዳ (Kissing Pool) የሚባለው አካባቢ ከአብዮቱ በፊት ኮከብ ሆና ሳያት ስለነበር….” ብለው ይገልጻሉ፡፡ የሕይወት ተፈራን ስም በዚህ መንገድ ማንሳቱ ጥቅሙ ምንድ ነው? ወይስ አሁንም የመኢሶንና የኢሕአፓ በጠላትነት መፈላለግ አላቆመም ያሰኛል፡፡ በሌላ በኩል ይህቺ ጸሐፊ ለዶ/ር መረራ መጽሐፍ ግብዓት ሊሆኑ የሚችሉ አስገራሚ ክስተቶችን ጽፋ፣ እሳቸው ግን በማጣቀሻነት ለማየት የፈለጉት ሌሎች ሁለት መጻሕፍትን ነው፡፡ ቢያንስ ከእሷ መጽሐፍ መጥቀስ ካልፈለጉ እሷ በሚገባ  የተረከችውን የወጣትነት የዩኒቨርሲቲ ጉዳይ መጥቀሱ ፋይዳው ምንድን ነው? የዶ/ር መረራ መጽሐፍ በውስጡ ብዙ ነገሮች ታጭቀውበታል፡፡ የሚያደናቅፉ የቃላትና የአገባብ ስህተቶች ባይኖሩበት ኖሮ በደንብ ሊነበብ ይችል ነበር፡፡ ከነችግሮቹም ቢሆን የሚያስተላልፈው መልዕክት አለው፡፡ ነገር ግን ከአንድ ታዋቂ ፖለቲከኛና የዩኒቨርሲቲ መምህር ያውም የረጂም ጊዜ ልምድ ካለው መረራ ጋር ሲታይ መጽሐፉ ብዙ ይቀረዋል፡፡ እንደ ወረደ ከሚጻፍ ይልቅ በተደራጀ ሁኔታ ፍሰቱን ጠብቆ ቢጻፍ ደረጃውን ጠብቆ ለአንባብያን ይደርስ ነበር፡፡