መነሻ ገጽ - ፓለቲካ - የከሸፈው የ‹‹መክሸፍ›› ውይይት
Buy Valtrex Online Buy Albuterol inhaler Online Buy Prinivil Online
13 February 2013 ተጻፈ በ 

የከሸፈው የ‹‹መክሸፍ›› ውይይት

እሑድ የካቲት 3 ቀን 2005 ዓ.ም. ማለዳ የብሔራዊ ቴአትር አዳራሽ በታዳሚዎች ሞልቶ ነበር፡፡ ታዳሚዎቹ በቦታውና በሰዓቱ የተገኙት ግን ቴአትር ለመመልከት አልነበረም፡፡

በአወዛጋቢው የፕሮፌሰር መስፍን ወልደ ማርያም ‹‹መክሸፍ እንደ ኢትዮጵያ ታሪክ›› መጽሐፍ ላይ ይደረጋል በተባለው ሞቅ ያለ ክርክር ለመታደም ነበር፡፡

ውይይቱ የተዘጋጀው በሰማያዊ ፓርቲ ሲሆን እጅግ አብዛኛው ሰው የተሳበው ደግሞ ቀደም ብሎ በተለፈፈው ማስታወቂያ እንደተነገረው ምሁራን በውይይቱ ላይ ይገኛሉ በማለት ነበር፡፡ በተለይ ቅዳሜ የካቲት 2 ቀን 2005 ዓ.ም. የ‹‹አዲስ አድማስ›› ጋዜጣ ዕትም የፊት ገጽ ላይ ዲያቆን ዳንኤል ክብረት፣ ሰለሞን ተሰማ፣ አስራት አብርሃም፣ ብርሃኑ ደቦጭ፣ ስብሃት ነጋ፣ ተመስገን ደሳለኝ፣ ዓለማየሁ ገላጋይ፣ ፕሮፌሰር ገብሩ ታረቀ፣ ዶ/ር ያዕቆብ ኃይለ ማርያም፣ ዶክተር ሽመልስ ተክለ ፃዲቅና ፕሮፌሰር አንድሪያስ እሸቴ በውይይቱ መድረክ ተገኝተው በመጽሐፉ ላይ ያላቸውን ሐሳብ እንደሚያቀርቡ፣ ደራሲው ፕሮፌሰር መስፍን ወልደ ማርያምም ስለ መጽሐፉ የሚቀርቡ ማንኛውንም አስተያየቶችንና ጥያቄዎችን እንደሚያስተናግዱና ምላሽ እንደሚሰጡ ተገልጾ ነበር፡፡

በፕሮግራሙ መግቢያ ላይ የመክፈቻ ንግግር ያደረገው አርቲስት ደበበ እሸቱ ግልጽ ውይይት ማድረግ ያለውን ጠቀሜታ ከዘረዘረ በኋላ በማስታወቂያው ከተገለጹት ሰዎች መካከል ከጉዳዩ ጋር የራቀ ግንኙነት ያላቸውን ሰለሞን ተሰማንና አስራት አብርሃምን ለግምገማ ወደ መድረኩ ሲጠራ ሌሎቹ ሰዎች ለምን እንዳልተገኙ እንኳን ለመግለጽ አልሞከረም፡፡ እርግጥ በአዳራሹ ውስጥ ብርሃኑ ደቦጭ፣ ተመስገን ደሳለኝ፣ ዓለማየሁ ገላጋይና ዶ/ር ያዕቆብ ኃይለ ማርያም የተገኙ ቢሆንም አስተያየት (በመጽሐፍ ላይ አይደለም) የሰጡት ዶ/ር ያዕቆብ ብቻ ናቸው፡፡ አቶ ብርሃኑ ደቦጭ አስተያየታቸውን ለመስጠት ሲሞክሩ ከታች በሚገለጽ ምክንያት አልተፈቀደላቸውም፡፡

የመጽሐፍ ግምገማ ነበር?
ሰለሞን ተሰማ የአዲስ ጉዳይ መጽሔት ዓምደኛ ነው፡፡ አስራት አብርሃም ደግሞ የአረና የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊና ‹‹ከአገር በስተጀርባ›› የተሰኘ መጽሐፍ ደራሲ ነው፡፡ ሁለቱ ግለሰቦች የፕሮፌሰር መስፍንን መጽሐፍ ለመገምገም እያንዳንዳቸው በተሰጡዋቸው 15 ደቂቃዎች ውስጥ ለታዳሚው መጽሐፉን ለማሳየት ያደረጉት ጥረት ከመድረኩ ይሁንታን አላሰጣቸውም፡፡

አስራት አብርሃም በመጽሐፉ ላይ ያለውን ጠቅለል ያለ አስተያየት ሲያስቀምጥ ኢትዮጵያ ውስጥ ባለውና በመጽሐፉ ላይ በተገለጸው የመክሸፍ ታሪክ እንደሚስማማ፣ ስም ጠቅሶ መውቀስ ያልተለመደ ባህል ቢሆንም መጽሐፉ ያን በማድረጉ እንደሚስማማ፣ ስለ ጣሊያን ወረራ በፎቶግራፍ የተደገፈው እውነታ አዲስ ዕውቀት እንደፈጠረበት፣ ሥልጣን እንዴት እንደሚያዝ ሥርዓት የሌለ መሆኑን በመጽሐፉ ላይ በደንብ መገለጹን፣ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ባለው የኢትዮጵያ ታሪክ ሥልጣን የሚያዘው ሕገ መንግሥቱን ባዘጋጀው አካል እንጂ በሌላ እንዳይሆን የኢትዮጵያ ሕገ መንግሥቶች ማድረጋቸውን በማጣቀስ ገልጿል፡፡ አስራት የመጸሐፉ ድክመት በማለት ሦስት ነገሮችን አስቀምጧል፡፡ አንደኛው የኢትዮጵያ ሕዝቦች አርበኞችን አልገደሉም ሥርዓቱ እንጂ የሚል ነው፡፡ ሁለተኛው በመጽሐፉ የተገለጸው የአፄ ሚኒሊክና የአፄ ዮሐንስ ግንኙነት እንዲሁም ስኬትና ድክመት በተጋነነ ሁኔታ ለአፄ ምኒልክ ያደላ ነው የሚል ነው፡፡ ሦስተኛው ፕሮፌሰር መስፍን ነጮችን በጠቅላላ መውቀሳቸው አግባብ አይደለም የሚል ነው፡፡

ሰለሞን ተሰማ በመጽሐፉ ላይ ያለውን ጠቅለል ያለ አስተያየት ሲያስቀምጥ ግዕዝ፣ እንግሊዝኛና ፈረንሳይኛ የሕዝብ ቋንቋ እንዳልሆኑ መጠቀሱን መጽሐፉ በባንዳ፣ በስደተኛና በአርበኛ ላይ እንደሚያተኩር፣ ሥልጣን እንዴት ይገራል? የሚለውን ጥያቄ ለመመለስ እንደሚጥርና ቄሳራዊ ምሁራን ላይ ትችት እንደሚሰነዝር በመጠቆም ነው፡፡ ሰለሞን የመጽሐፉ ድክመት ብሎ ያስቀመጠው ፕሮፌሰር መስፍን ለናሙና የወሰዷቸውን ጽሑፎች ሲሆን ተጨማሪ ንባቦችን ቢያደርጉ ኖሮ የተሻለ እንደነበር በመግለጽ፣ ዕውቀትና እውነት ላይ የቀረበውም ገለጻ ያልተጠናቀቀ መሆኑን አስረድቷል፡፡

የውይይት ሒደቱ
አርቲስት ደበበ እሸቱ ውይይቱን በዲሞክራሲያዊ መንገድ እንደሚመራ በተደጋጋሚ ሲገልጽ ነበር፡፡ ይሁንና በአዳራሹ ለውይይቱ ከፍተኛ አስተዋጽኦ በማድረግ የተለያዩ ዕይታዎችን ሊሰጡ የሚችሉ ታዳሚዎች ባሉበት ‹‹መጽሐፉን አላነበብኩም››፣ ‹‹መጽሐፉን ከዚህ እንደወጣሁ አነበዋለሁ›› በማለት ንግግራቸውን የጀመሩ ዕድል የተሰጣቸው ሰዎች ከመጽሐፉ እጅግ ርቀው የማይገናኝ አጀንዳ ሲያጣርሱ ደበበ እሸቱ ምላሹ ዝምታ ነበር፡፡ እውነት ነው የጋዜጣ አምደኛው አቶ ታዲዮስ ታንቱ መጽሐፉን አለማንበባቸውን ገልጸው በአስራት ተባለ በማለት ሲሰጡ የነበረውን አስተያየት ትክክል አለመሆኑን በመግለጽ ደበበ አስቁሞአቸዋል፡፡

በዚህ መሀል አቶ ብርሃኑ ደቦጭ እንዲናገሩ ማይክራፎኑ ሲሰጣቸው ምንም ዓይነት ፈቃድ ሳይሰጥ በማስታወቂያ ላይ ስማቸው ለምን እንደወጣ እንዳልገባቸው በመግለጽ ቅሬታ ያላቸው መሆኑንና በውይይቱ ላይ ማይክራፎኑ የተሰጣቸውም እጃቸውን ሳያወጡ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡ አርቲስት ደበበ በሰለሞን ተሰማ እጅ አውጥቷል ተብሎ በስህተት ስለተነገረው ዕድል መስጠቱን ገልጾላቸዋል፡፡ ይሁንና አቶ ብርሃኑ በአጋጣሚ ዕድሉን ካገኘሁ በመጽሐፉ ላይ ያለኝን አስተያት ልስጥ ሲሉ ደበበ ወደ ታዳሚው በመዞር ‹‹ይናገር ወይ?›› ብሎ የተቃውሞ ድምፅ በማነሳሳት አቶ ብርሃኑ እንዳይናገሩ በመከልከል ውይይቱን ዓላማውን እንዲስት አድርጓል፡፡ አርቲስት ደበበ በውይይቱ አስተያየት በሰጡ ሰዎች አቶ ብርሃኑ እንዳይናገሩ የተደረገው ስህተት እንደሆነ አስተያየት ቢሰጠውም ይህን ለማረም ያደረገው ጥረት አልነበረም፡፡ ዕውቁ የሙዚቃ ባለሙያ ሰርፀ ፍሬስብሃት በማስታወቂያው ላይ የተገለጹት ሰዎች ለምን አልመጡም የሚል ጥያቄ ሲያቀርብ የደበበ ምላሽ ‹‹እንቢ ብለው ነው›› ከሚል ውጪ እንቢ ያሉት ማስታወቂያው ከተነገረ በኋላ ነው ወይስ በፊት? የሚለውን አልመለሰም፡፡
እዚያው መድረክ ላይ ለነበሩትና ሳይነገራቸው ውይይቱ ላይ አቅራቢ መሆናቸውን ከሚዲያ መስማታቸውን ለገለጹት አቶ ብርሃኑም ይቅርታ ለመጠየቅ አልተሞከረም፡፡

  ለተጠራው ውይይት መነሻ የሆነው 238 ገጾችን በያዘው ‹‹መክሸፍ እንደ ኢትዮጵያ ታሪክ›› መጽሐፍ እጅግ በርካታ ቁም ነገሮች የተነሱና ጥቂት የማይባሉ አወዛጋቢ ነገሮች የተካተቱ ሲሆን፣ በውይይቱ ላይ የተነሱት ግን የኢትዮጵያ ሕዝብ አርበኞችን ይገድላል ወይስ አይገድልም? ከአፄ ምኒልክና ከአፄ ዮሐንስ ብዙ የተሳሳተው ማነው? የሚሉት ሁለት አንኳር ጥያቄዎች ናቸው፡፡

የውይይቱ አድማስ የጠበበው ሁለቱ ገምጋሚዎች ስለ መጽሐፉ እጅግ ቁንፅል ነገር በማቅረባቸው ነው፡፡ አስተያየት ሰጪዎቹ በቂ ዝግጅት አለመደረጉን ሲገልጹላቸው ሰለሞንም ሆነ አስራት የመከላከል ሚና ነበር የነበራቸው ሁለቱም አቅራቢዎች፣ ከዚህ በላይ እንዲዘጋጁ አስተባባሪዎቹ እንዳልነገሯቸው በመግለጽ በቂ ዝግጅት ያላደረጉት ሌሎቹ ምሁራን በስፋት እንደሚናገሩ በመጠበቅ እንደሆነ ሲናገሩም ተደምጠዋል፡፡ አርቲስት ደበበ እሸቱ በበኩሉ አቅራቢዎቹን እንዲህ ተናገሩ እንዲያ አትናገሩ ማለት እንደማይችል ለማስረዳት ሞክሯል፡፡

አንድ ተሳታፊ በመጽሐፉ ገጽ 105 ላይ ‹‹ብሪታንያ አፄ ቴዎድሮስን ስትወጋ የደጃዝማች ካሣን (በኋላ አፄ ዮሐንስ) ሙሉ ትብብር አግኝታ ነው፤ ይህ የደጃዝማች ካሣ (አፄ ዮሐንስ) ከውጭ ጠላት ጋር ተባብሮ ወገንን ማስጠቃት በዚያ አካባቢ የተለመደ ነበር፤›› በሚል መቀመጡን በመጥቀስ ‹‹በዚያ አካባቢ›› የሚለው አነጋገር ትግራይን እንደሚያመለክት በመጠቆም ፕሮፌሰሩን ለምን እንደዚያ እንዳሉ ጠይቋቸዋል፡፡

ዶ/ር በድሉ ዋቅጅራና ዶ/ር ያዕቆብ ኃይለ ማርያም በመጽሐፉ ውስጥ የተካተቱትን ነገሮች በመጠቆም የሚቀሩ ነገሮች መኖራቸውን አመልክተዋል፡፡ ዶ/ር በድሉ በተለይ በሕዝቡ ሚና ላይ ከመክሸፍ ጋር በተገናኘ የተገለጹት ነገሮች በቂ ትንታኔ እንዳልቀረበባቸው ሲገልጹ፣ ዶ/ር ያዕቆብ በበኩላቸው ጣሊያን በኢትዮጵያ ላይ ላስከተለችው ጉዳት ኢትዮጵያ የተሰጣት የካሳ ክፍያ ለቆቃ መገንቢያ ስድስት ሚሊዮን ዶላር ብቻ እንደነበር፣ በአንፃሩ ሊቢያ እጅግ ላነሰ ጉዳት 45 ቢሊዮን ዶላር የካሳ ክፍያ መውሰዷን አንስተው፣ ጣሊያን ያደረሰችውን ጉዳት የመተንተን ሥራው ገና እንደሚቀረው አስተያየታቸውን ገልጸዋል፡፡

የፕሮፌሰር መስፍን አስተያየት
ፕሮፌሰር መስፍን ወልደማርያም በፕሮግራሙ መዝጊያ ላይ ለተጠየቁት ጥያቄዎች መልስ እንዲሰጡና የራሳቸውን አስተያየት እንዲያቀርቡ ዕድል ሲሰጣቸው መጽሐፉ ለምን አሁን ታተመ በሚል ለቀረበላቸው ጥያቄ ሲመልሱ፣ መጽሐፉ ለሕትመት ዝግጁ የነበረው በደርግ ጊዜ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

በመጽሐፉ ላይ ትችት የተሰነዘረባቸው ምሁራን መሞታቸውና መታመማቸው ወይም አገር ውስጥ አለመሆናቸውን በመጥቀስ የሚቀርበውን ትችት አስመልክተው ፕሮፌሰሩ ሲናገሩ፣ ‹‹የሰዎቹ መሞት ለመጽሐፉ እርባና የለውም፡፡ የጻፉት የኢትዮጵያን ታሪክና ሕዝብ ስለሆነ ይመለከተናል፤›› ብለዋል፡፡

‹‹ብዙ የአፍሪካ አገሮች ከኋላ ተነስተው እየቀደሙን ነው፡፡ ለምንድን ነው የምንጫጨውና የማናድገው?›› ሲሉ የሚጠይቁት ፕሮፌሰር መስፍን፣ መጽሐፉን በዚህ ጭብጥ መጻፋቸውን ያመለክታሉ፡፡

ሌላኛው የመጽሐፉ ጭብጥ በኢትዮጵያ ታሪክ ላይ የምንወያየው በእምነት ወይስ በዕውቀት ዙሪያ መሆኑ ያለው ወሳኝነት ላይ መሆኑንም ያብራራሉ፡፡

በዶ/ር በድሉ፣ በዶ/ር ያዕቆብና በሌሎችም አስተያየት ሰጪዎች ያልተሟሉ ነገሮች መኖራቸውን በተመለከተ የተገለጸውን እንደሚያምኑበት በመግለጽ ፕሮፌሰር መስፍን፤ ‹‹ማስፋፋቱን ለሌሎች ሰጥቻለሁ፡፡ እኔ ጥያቄዎችን ነው ያነሳሁት፡፡ እያንዳንዱ ጥያቄ ፒኤችዲ የሚያሠራ ነው፤›› ብለዋል፡፡

ፕሮፌሰር መስፍን መክሸፍን በተመለከተ ያልከሸፈ ነገር ዕድሜ ልካቸውን ሲፈልጉ መኖራቸውን ገልጸዋል፡፡ ‹‹ያልከሸፈ ነገር ለማግኘት ሞከርኩ፣ ጣርኩ፡፡ ከጥንት ጀምሮ እስካሁን ድረስ ያልከሸፈ ያገኘሁት አንድ ነገር የኢትዮጵያ ሕዝብ የውጭ ጠላት ሲመጣ ለንብረቱም ሆነ ለሕይወቱ ሳይሳሳ ወጠቶ የሚመክት መሆኑን ብቻ ነው፤›› ብለዋል፡፡  

አርበኛን የገደሉት ሥርዓቶቻችን እንጂ እኛ ሕዝቦች አይደለንም በሚል ለቀረበው አስተያየት ፕሮፌሰር ሲመልሱ፣ ‹‹እንደ ኢትዮጵያ አርበኞቹን የገለደ ሕዝብ የለም፡፡ እንደ ሕዝብ ሥርዓቶቹ አርበኞቻችንን ሲገድሉ ምን ተቃውሞ አሰማን?›› ብለዋል፡፡

ገጽ 105 ላይ ስላለው ‹‹እዚህ አካባቢ የተለመደ ነው›› በማለት ለጻፉት መልስ ሲሰጡ፣ ‹‹እኔም እንደ አንተ ትግሬ ነኝ፡፡ ልዩነታችን አንተ ትግሬ ሆነህ ስላነበብከው፣ እኔ ደግሞ ኢትዮጵያዊ ሆኜ ስላነበብኩት ነው፤›› በማለት ምላሽ ሰጥተዋል፡፡

ከተሳታፊዎች የተሰነዘሩት አብዛኛዎቹ አስተያየቶች በሰለሞንና በአስራት እንዲመለሱ በመደረጉ፣ ጸሐፊው ፕሮፌሰር መስፍን ግን ለጥቂት ደቂቃዎች ከተናገሩ በኋላ እንዲያቆሙ ተደርጓል፡፡

የተሳታፊዎች አስተያየት
ሪፖርተር በውይይቱ ከተሳተፉ ሰዎች የተለያዩ አስተያየቶች ለመሰብሰብ የሞከረ ሲሆን፣ ‹‹በአንድ ፓርቲ ለምን ተዘጋጀ?›› ከሚል ‹‹መበጥበጡን የማያቆም ፕሮፌሰር›› እስከሚል ተቃውሞ እንዲሁም፣ ‹‹በጤና ያቆያቸው!›› ከሚል ምኞት እስከ ‹‹ፕሮፌሰር መስፍን ግለሰብ ሳይሆኑ ተቋም ናቸው›› ድረስ በሁለት ተቃራኒ ጽንፎች ላይ የቆሙ አስተያየቶች ከተሳታፊዎች ተሰምቷል፡፡

አርቲስት ደበበ እሸቱ መድረኩን በሚገባ መርቶታል ወይስ አልመራውም የሚለውም ሌላው የመከራከሪያ ጉዳይ ነበር፡፡ አንድ አስተያየት ሰጪ አርቲስት ደበበ አቶ ብርሃኑ ደቦጭ ይናገር አይናገር በማለት ወደ ተሳታፊው ጥያቄውን መወርወሩን በማስታወስ፣ ‹‹ቅንጅት ጥያቄዎችን ሁሉ ወደ ሕዝቡ በመውሰድና ከሕዝቡ አመራር በመጠየቅ ድሉን የቀለበሰበት ስህተት አሁንም እንዳልተስተካከለ የደበበን የዕለቱን አካሄድ በማየት መናገር ይቻላል፤›› ብለዋል፡፡

ፕሮፌሰር መስፍን በመጽሐፋቸው ለምኒልክ ከመጠን ያለፈ ቸር ሲሆኑ ለዮሐንስ ከመጠን ያለፈ የማጣጣል ሥራ መሥራታቸውን የጠቆመ አንድ አስተያየት ሰጪ፣ በቅርብ ዓመታት ምኒልክን የሚያጣጥሉና ዮሐንስን የሚያሞግሱ መጻሕፍት በገበያ ላይ መዋላቸው የፕሮፌሰሩን አቀራረብ ‹‹መልስ በመስጠት›› እና ‹‹ልክ በማስገባት›› ስሜት እንዲዋጥ ያደረገ እንደሆነባቸው ገልጿል፡፡ የቀደሙት ሥራዎችም ሆነ የፕሮፌሰሩ መጽሐፍ አንዳቸውን በማሞገስ ሌላኛውን በማንቋሸሽ ላይ ቢያተኩሩም፣ የሁለቱም መሪዎች ስኬትና ድክመት መሀል ላይ መሆኑን የሚያሳዩ ሥራዎች ሊቀርቡ እንደሚገባ አስተያየት ሰጪው ሐሳብ አቅርቧል፡፡

ፕሮፌሰር መስፍን በመጽሐፋቸው ሕግና ሥርዓት፣ አስተዳደር፣ እንደ ጋሪና ሠረገላ ያሉ የሰውና የዕቃ ማመላለሻዎች፣ መገበያያ ገንዘብ፣ የሕንፃ ሥራ፣ የመስኖ ሥራ፣ የመንገድና የድልድይ ሥራ፣ ትምህርትና ምርምር፣ አዲስ ሐሳብ፣ ጽሑፍን ማራባት፣ ጤና ጥበቃ፣ የእጅ ጥበብ፣ እርሻና ከብት እርባታ ኢትዮጵያ ውስጥ ለመክሸፋቸው ያቀረቡት ምክንያት የተወሰነ ነጥብ ቢኖረውም፣ አብዛኛው ገለጻ ግራ የሚያጋባ እንደሆነባት ያነሳችው አንዲት አስተያየት ሰጪ፣ በመድረኩ ሁሉም አስተያየት ሰጪዎች በደፈናው ኢትዮጵያ ስለመክሸፏ ያለ ጥያቄ ከፕሮፌሰሩ ጋር መስማማታቸው እንደደነቃት ገልጻለች፡፡

በመጽሐፉ ገጽ 49 ላይ ‹‹የታሪክ እውነት ከኑሮ ትግል ጋር የተወሳሰበ ስለሆነና የታሪክ ባለሙያውም ከዚህ የኑሮ ትግል ውጪ የሆነ ታዛቢ ስላልሆነ ሚዛኑና ግምቱ የራሱን እምነት ያንፀባርቃል፤ ለዚህ ነው ታሪኩን ከማንበብህ በፊት የታሪክ ጸሐፊውን ታሪክ አጥና የሚባለው፤›› የሚል ሐሳብ ሰፍሮ ይገኛል፡፡ አንድ አስተያየት ሰጪ የመጽሐፉን ጭብጥ ከፕሮፌሰሩ ሰብዕና ለይቶ ማየት እንደሚያስቸግር፣ ፕሮፌሰሩ ደግሞ በአገር ግንባታ ፕሮጀክት በመዋጣቸው ሌላውን ሐሳብ አራማጅ ሁሉ በጠባብነት እንደሚፈርጁ፣ ከዚህ መጽሐፍ በፊት በጻፏቸው ሌሎች መጻሕፍትና በኖሩት ኑሮ እንደሚታወቅ ጠቁሟል፡፡ አስተያየት ሰጪው፣ ‹‹ለዚህ ነው በመጽሐፉ ላይ አንድ ጸሐፊ ከእሳቸው ጋር ሲስማማ አሞግሰውት የሚቃረን ነገር ሲጽፍ ደግሞ እንዲህ ብሎ አበላሸው ማለት ያበዙት፡፡ በፖለቲካው መድረክ ብዙ በመቆየታቸውና ለውጥ ባለማምጣታቸው የተሰማቸው ብስጭት በጣም ጥልቅ ሆኗል፡፡ ትልልቅና የተከበሩ ምሁራንን ‹‹አልገባውም››፣ ‹‹ሳይመረምር››፣ ‹‹በነጮች ተፅዕኖ ሥር ሆኖ›› ማለት ያበዙ ሲሆን፣ እንደ ፕሮፌሰር ዶናልድ ሌቪንና ስቬን ሩቢንሰንን ደግሞ ልካቸውን እንዲያውቁ ማድረጋቸውን በመግለጽ በታሪክ ዘርፍ ባለሙያነታቸው የማይታወቁት ፕሮፌሰር መስፍን፣ ከእኔ በተሻለ ኢትዮጵያን የሚያውቅ የለም ወደማለት መሸጋገራቸውን ግን መጽሐፉ ያሳያል፤›› ሲሉም አክለዋል፡፡

በደርግ ጊዜ መጽሐፉ ለሕትመት ደርሶ የነበረ ቢሆንም በሳንሱር መቅረቱን ፕሮፌሰሩ መናገራቸውን ያስታወሰች አንዲት አስተያየት ሰጪ፣ ‹‹ታዲያ ኢሕአዴግ ሥልጣን ላይ ከወጣ በኋላ ባሉት 22 ዓመታት ፕሮፌሰሩ ያን ሁሉ መጽሐፍ ሲያወጡ ይህ ረቂቅ የት ነበር?›› ብላለች፡፡

ፕሮፌሰሩ እንደተለመደው አወዛጋቢ ነገሮችን በመጽሐፉ ማካተታቸውን ያስታወሰው ሌላ አስተያየት ሰጪ ከገጽ 67 እስከ ገጽ 73 ድረስ የተቀመጡትን ወሳኝ ጥያቄዎች ጨምሮ ከኢትዮጵያ ታሪክ ጋር በተያያዘ የተቀመጡ አሳማኝ ትንታኔዎች በውዝግቦቹ ተጋርደው እንዳይቀሩ ያለውን ሥጋት ገልጿል፡፡ አስተያየት ሰጪው በተለይ ፕሮፌሰሩ የውጭ አገር ዜጎች ሆነው የኢትዮጵያን ታሪክ የሚጽፉ ሰዎች ላይ ያነሱት ነጥብ በጥርጣሬ ሊታይ ቢገባውም ፕሮፌሰሩ ሊወቀሱበት እንደማይገባ ግን ይመክራል፡፡ ‹‹በአገር ውስጥ ሊቃውንትም ላይ የተሰነዘረው ትችት መታየት ያለበት ትችቱ እውነት ከመሆኑና ካለመሆኑ አንፃር ነው፡፡ ለምሳሌ በድንበርና በካርታ ዙሪያ ላይ በፕሮፌሰር ታደሰና በፕሮፌሰር መርዕድ ላይ አስተያየት ለመስጠት ፕሮፌሰር መስፍን የሙያ ብቃት አላቸው፡፡ ይህ ጉዳዩን ለመመርመር ቢያንስ መነሻ ነጥብ ይሆናል፤›› ሲሉ አስተያየት ሰጪው አክለዋል፡፡