መነሻ ገጽ - ስፖርት - የዋሊያዎቹ ስኬትና 72 ሰዓት የቀረው ፍልሚያ
Buy Valtrex Online Buy Albuterol inhaler Online Buy Prinivil Online
04 September 2013 ተጻፈ በ 

የዋሊያዎቹ ስኬትና 72 ሰዓት የቀረው ፍልሚያ

ምዕራብ አፍሪካዊቷ ኮንጎ ብራዛቪል፣ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ለ2014 የዓለም ዋንጫ ማጣሪያና ለመጨረሻው የደርሶ መልስ ግጥሚያ የሚያበቃውን ጨዋታ ለማስተናገድ 72 ሰዓት ጊዜ ብቻ ቀርቷታል፡፡

ሁለቱ ተፋላሚዎች ማዕከላዊ አፍሪካ ሪፐብሊክና ኢትዮጵያ ቅዳሜ ጳጉሜን 2 ቀን 2005 ዓ.ም. የሚያደርጉት ግጥሚያ በተለይ ለዋሊያዎቹ ወሳኝ ነው፡፡

ለማጣሪያ ማጣሪያው ከሶማሊያ ጋር ጂቡቲ ላይ አንድ ብሎ የጀመረው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በጊዜ ሒደት እየተጠናከረ መጥቶ ለ2014 የዓለም ዋንጫ ማጣሪያ ከታላላቆቹ የእግር ኳስ አገሮች አንዳቸውን ለመፈተን የተዘጋጀ ይመስላል፡፡ ቡድኑ በቢጫ ካርድ ምክንያት የተቀነሰበት ሦስት ነጥብ ባይኖር ኖሮ፣ ዋሊያዎቹም ሆኑ የእግር ኳሱ ቤተሰብ ዕለተ ቅዳሜ በጉጉት ‹‹ባልተጠበቀ›› ነበር በሚል የተፈጠረው ቁጭት እስካሁን እንዳለ ነው፡፡

ለሦስት አሠርታት ያህል ከዓለምም ሆነ አህጉር አቀፍ ውድድሮች ርቆ የቆየው ብሔራዊ ቡድን አሁን ለሚገኝበት ደረጃ ሊደርስ የቻለው በአጋጣሚና በዕድል እንደሆነ የሚያምኑ ቢኖርም፣ ጥረት ካልታከለበት ዕድል ብቻውን የትም እንደማያደርስ የሚከራከሩ በዚያው መጠን በርካታ ናቸው፡፡ የቡድኑ አሠልጣኝ አቶ ሰውነት ቢሻው በ‹‹ዕድል ነው›› ለሚሉ አስተያየት ሰጪዎች፣ ምንም እንኳ አባባሉ ከሙያ አኳያ ሚዛን ‹‹ይደፋል፣ አይደፋም›› የሚለው እንደተጠበቀ፣ ከቁብ እንደማይቆጥሩት ጭምር ደጋግመው ይናገራሉ፡፡ ‹‹ይልቁንስ›› ይላሉ አሠልጣኙ፣ ‹‹በእግር ኳሱ እንዴት ለውጥ ማምጣት እንደምንችል ያገኘነው መስመር ተመልሶ እንዳይጠፋብን ብንሠራ›› ይላሉ፡፡ 

ውጤቱን በተመለከተ አሠልጣኙ፣ የእግር ኳሱ ቤተሰብ ለሚጠብቀው መከፈል ያለበት መስዋዕትነት ሁሉ ተከፍሎ ሙሉ ሦስት ነጥብ ለማግኘት እንደሚጫወቱ፣ ለዚያ ደግሞ በተጨዋቾቻቸው ሙሉ እምነት እንዳላቸው ያስረዳሉ፡፡ 

በቢጫ ካርድ ምክንያት የዓለም አቀፍ እግር ኳስ ማኅበር (ፊፋ)፣ ከኢትዮጵያ ቡድን ላይ ሦስት ነጥብ መቀነሱን ይፋ ካደረገበት ዕለት ጀምሮ፣ የእግር ኳሱ ቤተሰብ በአገሪቱ ከጫፍ እስከ ጫፍ ‹‹እንዴት›› በሚል ጥያቄ ማንሳቱ ይታወሳል፡፡ ተከትሎም ተጠናቀቀ የተባለው የዋሊያዎቹ የምድብ ማጣሪያ የመጨረሻው ጨዋታ እንደገና በጉጉት እንዲጠበቅ ሆነ፡፡

በሁኔታው በእጅጉ ከተበሳጩ የእግር ኳስ ቤተሰብ መካከል ወሰንሰገድ መርሻ አንዱ ነው፡፡ ወሰንሰገድ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ለዝግጅት ወደመረጣት አዳማ ከተማ ባለፈው ሳምንት አምርቶ የልጆቹን ዝግጅትና አጠቃላይ ሥነ ልቦና ምን እንደሚመስል ተመልክቶ ከተመለሰ በኋላ ተስፋው መለምለሙን ይናገራል፡፡ 

እንደ ወሰንሰገድ ሁሉ ሌሎችም አንጋፋ የእግር ኳስ ተመልካቾች ብሔራዊ ቡድኑ ከማዕከላዊ አፍሪካ ሪፐብሊክ ጋር በሚያደርገው ግጥማያ አራት ወሳኝ ጉዳዮችን ታሳቢ አድርጎ መጫወት እንዳለበት በመጠቆም የሚናገሩ አሉ፡፡ ከፍተኛ የሆነ የሥነ ልቦና ዝግጅት፣ የተጠናና የተደራጀ የኳስ ቁጥጥር፣ የባለጋራ ቡድንን ደካማ ጎን በሚገባ ማወቅና ብልጠት ናቸው፡፡ 

የሥነ ልቦና ዝግጅቱ፣ ይህንን ጨዋታ ለማሸነፍ የራስ መተማመንን ከፍ እንደሚያደርግ የሚናገሩት አስተያየት ሰጪዎቹ፣ ‹‹በተደራጀ ሁኔታ በኳስ ቁጥጥር መብለጥ፣ ለተቃራኒ ቡድን ጥቃት አያጋልጥም፡፡ የተቃራኒ ቡድንን ደካማ ጎን በፍጥነት ማወቅ ለውጤት ጠቃሚ ነው፡፡ ብልጠት ደግሞ የበላይነትን ለማጎልበት ይረዳል›› ይላሉ፡፡

ከዚህ ጋር ‹‹ዲሲፕሊን ለውድድር የማይቀርብ ወሳኙ ቁልፍ ነገር ነው›› የሚሉት አስተያየት ሰጪዎቹ፣ በተረጋጋ ሁኔታ ጨዋታውን ተቆጣጥሮ ውድድሩን መወጣት ከተቻለ በቢጫ ካርዱ ምክንያት ብሔራዊ ቡድኑ ያመለጠው ድል በቀላሉ እንደሚገኝ ጭምር ያስረዳሉ፡፡ 

ሌላው የአዲስ አበባ የአየር ጠባይና መልክዓ ምድራዊ አቀማመጥ ለስፖርተኞች ፈታኝ እንደሆነ የሚናገሩት ደግሞ በአዳማ ዩኒቨርሲቲ ስፖርት ሳይንስ ቴክኖሎጂ የሥነ ምግብ ሙያተኛ የሆኑት አቶ ተስፋዬ ብርሃኔ ናቸው፡፡

አቶ ተስፋዬ፣ ‹‹በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ›› እንዲሉ፣ ስፖርተኞቻችንን በአመጋገብ፣ በልምምድና በዕረፍት ሳቢያ ሳይንሳዊ ትግበራዎች ስለሚያጥራቸው በውጤታማነታቸው ላይ ተፅእኖ ሲያሳድር መቆየቱን ይናገራሉ፡፡ 

ይህንን የቆየ ልማዳዊ ተግባር በመበጠስ፣ የብሔራዊ እግር ኳስ ቡድን አባላትን የሥነ ምግብ ሥርዓት በመቀየር ላይ የሚገኙት ሙያተኛው፣ ስለሦስቱ መርሆዎች ማለትም ልምምድ፣ አመጋገብና ዕረፍት አስፈላጊነት ብቻ ሳይሆን ስለሚያመጡት አዎንታዊ ተፅእኖ ያስረዳሉ፡፡ 

ሙያተኛው ወደ ኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ከመምጣታቸው አስቀድሞ ተጨዋቾቹ ሁሉም እንደሚያውቀው ሙሉ ዘጠና ደቂቃ የመጫወት ብቃት ያልነበራቸው ናቸው፡፡ ይኼ ችግር ደግሞ ሦስቱ መርሆዎች ልምምድ፣ አመጋገብና በቂ ዕረፍት ተሟልተው አለመተግበራቸውን በምክንያትነት ያነሳሉ፡፡

ስለዚህ የሚሉት ሙያተኛው፣ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ተጨዋቾች የቆየውን የአመጋገብ ሥርዓታቸውን ለመለወጥና በአመጋገብ ሥርዓቱ እምነት እንዲኖራቸው ለማድረግ አስቸጋሪ ሆኖባቸው እንደነበር ጭምር ያስረዳሉ፡፡

ዋናውና ትልቁ ችግር የሚሉት አቶ ተስፋዬ፣ በአገሪቱ ከሥጋ ጀምሮ በርካታ ገንዘብ ወጥቶባቸው ለምግብነት የሚውሉ የምግብ ዓይነቶችን መመገብ የአቅም መለያ ተደርጎ የቆየበትና በአጠቃላይ የአገሪቱ የአመጋገብ ባህል የፈጠረው ተፅእኖ እንደሆነም ይናገራሉ፡፡ 

እግር ኳስ ተጨዋችን ጨምሮ ስፖርተኞች በዋናነት የሚያስፈልጓቸው በከፍተኛ ደረጃ ኃይል ሰጪ የሆኑ ምግቦችን ነው፡፡ እነዚህ ምግቦች ደግሞ በቀላል ወጪ የሚገኙት እንደ ማር፣ ዳቦ፣ ሩዝ፣ ሙዝ፣ ወተትና የወተት ተዋፅኦ ማግኘት እንደሚቻል ያስረዳሉ፡፡

ሙያተኛው የተጨዋቾቹን የአመጋገብ ሥርዓት ለመለወጥ ብሔራዊ ቡድኑን ከተቀላቀሉበት ጀምሮ አስቸጋሪ ሆኖባቸው የቆየው ስፖርተኞች በምንም ተአምር እንጀራና ሥጋን አዘውትረው እንዳይመገቡ ለማድረግ የሄዱበት መንገድ ነው፡፡ 

ከብዙ ውጣ ውረድና በጊዜ ሒደት ተጨዋቾቹ የአመጋገብ ሥርዓታቸውን ጠብቀው በመመገባቸው፣ ከልምምድ በኋላ በቂ ዕረፍት በማድረጋቸው ያገኙት ጥቅም እየተረዱት በመምጣታቸው በአሁኑ ወቅት ችግሩ ሙሉ በሙሉም ባይሆን ጥሩ ለውጥ እየተመለከቱ መምጣታቸውን ያስረዳሉ፡፡ 

በዚህም ቀድሞ ዘጠና ደቂቃ ተሯሩጦ መጫወት የማይችለው ተጨዋች በአሁኑ ወቅት፣ ሁሉም የብሔራዊ ቡድን ተጨዋቾች ሜዳ ላይ ሮጠው እንደማይጠግቡም ይናገራሉ፡፡ 

ሙያተኛው፣ ከእንግዲህ ከብሔራዊ ቡድኑ ጀምሮ ለአንድ ቡድን አንድ አሠልጣኘ እንደሚያስፈልገው ሁሉ የሥነ ምግብ ሙያተኛ ቢኖረው እንደሚበጅም ያስረዳሉ፡፡ ምክንያቱም ስፖርተኞች ሰባ ከመቶው ኃይል ሰጪ ምግቦችን ማግኘት ካልቻሉ የሚጠበቀውን ውጤት ማግኘት እንደማይቻል የሚናገሩት ሙያተኛው፣ ከዚሁ ጋር መታየት የሚገባው ደግሞ እያንዳንዱ ስፖርተኛ መመገብ ያለበት በሚመዝነው መጠን ቢሆን እንደሚመረጥ ጭምር ይናገራሉ፡፡ 

ሙያተኛው በገለጹት መሠረት እንጀራና ሥጋ በአገሪቱ ከተጨዋቾች ጀምሮ የተለመደ ምግብ ነው፡፡ ይህንኑ የአመጋገብ ሥርዓት ተጨዋቾቹ አስወግደዋል ማለት ይቻላልን? ለሚለው ሙያተኛው፣ ሥጋ እንደየሁኔታው አልፎ አልፎ ያውም በተመጠነ ሁኔታ እንዲመገቡ እንደሚደረግ፣ ነገር ግን እንጀራ ሙሉ ለሙሉ ባይባልም መመገብ እንዳቆሙ ተናግረዋል፡፡ 

ለስፖርተኞቹ እየቀረበ ያለውን ምግብ በተመለከተ አቶ ተስፋዬ፣ ፓስታ፣ ሩዝና ዳቦ፣ የመሳሰሉት ሲሆኑ ዳቦው የስንዴው ስሮች (ፋይበር) ሳይወጣ ቢቻል ገጠር ውስጥ እንደሚጋገረው ጥቁር ዳቦና የመሳሰሉት ስለመሆናቸውም ይናገራሉ፡፡ 

የአመጋገብ ሥርዓትን ለመለወጥ ዕድሜ ተፅእኖ አይኖረውም ወይ? ለሚለው የሥነ ምግብ ሙያተኛው፣ ያን ያህል ችግር እንደሌለው እንዲያውም የታዳጊዎች ጨጓራ የሚያገኘውን በሙሉ ቶሎ ቶሎ የመፍጨት አቅም ስላለው ከሁሉም የምግብ ዘሮች ቢመገቡ እንደሚመረጥ፣ ነገር ግን እያደጉ ሲሔዱ በተለይ ለስፖርተኞች የተስተካከለ የአመጋገብ ሥርዓት መከተል ከጤናም አኳያ ይመረጣል ይላሉ፡፡ 

አንድ ሰው ከአንድ ሰዓት በላይ ጠንካራ ልምምድ ካደረገ ንፁሕ ውኃ ብቻ ከመውሰድ ውኃውን በማርና ጨው ጋር አዋሕዶ ለስፖርተኛው ቢሰጥ የተሻለ እንደሚሆን የሚናገሩት ሙያተኛውና ጥቅማቸው ስፖርተኛው ያወጣውን ኃይል (ካሎሪ) በቀላሉ የሚተኩ ናቸው፡፡ ከተቻለ ከልምምድ በፊትና በኋላ መውሰድ ያለባቸውን ምግቦች መጥኖ ማቅረብ በተለይ ለእግር ኳስ ተጨዋች የግድ አስፈላጊ ነው ይላሉ፡፡ 

ወተትና የወተት ተዋፅኦ ከሆኑት ውስጥ ለስፖርተኛ ጠቃሚ ተብሎ የሚወሰደው፣ ብዙ ወጪ ከሚያስወጡት ወተትና እርጎ ይልቅ በሊትር እስከ 25 ብር የሚጠይቀውን አጓት ነው፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ሙዝም እንደዚሁ ስፖርተኞች ቢመገቡ የተሟላ አቅም ይኖራቸዋል፡፡

የብሔራዊ ቡድኑ የሥነ ምግብ ባለሙያ አቶ ተስፋዬ ብርሃኔ በኮንጎ ብራዛቪል ቡድኑ ምን ዓይነት ምግብ ሊቀርብለት እንደሚገባ ቀድመው ለማጥናት፣ እንዲሁም የአገሪቱን አየር ጠባይና ሌሎች ተያያዥ የሆኑ ነገሮችን ምን እንደሚመስሉ ለማወቅ በትናንትና ዕለት ከቡድኑ መሪ አቶ አፈወርቅ አየለ ጋር ወደ ስፍራው አምርተዋል፡፡ 

ከዚያ በፊት ግን በአዳማና አዲስ አበባ የአየር ጠባይ መካከል ስለሚኖረው ልዩነትና አንድነት እንዲሁም የአዳማው ከኮንጎ ብራዛቪሉ ጋር ያለውን ተዛማጅነት እንዲያስረዱን ጠይቀናቸው ነበር፡፡ 

ሙያተኛው ‹‹የኢትዮጵያ ቡድን ወሳኙን ጨዋታ የሚያደርግባት ኮንጎ ብራዛቪል ሞቃታማ የአየር ጠባይ ባለቤት ነች፡፡ ለእንደዚህ ዓይነቱ ተመጣጣኝ አየር ጠባይ ደግሞ ከአዳማ የተሻለ ማግኘት አይቻልም፡፡ አዳማ እንደሚታወቀው ከአዲስ አበባ ይልቅ የተሟላ ኦክስጅንና ቀይ የደም ሴል ተጨዋቾቹ በበቂ ሁኔታ እንዲኖራቸው ምቹ ስፍራ ነው፡፡ አዲስ አበባ ግን ቀዝቃዛ በመሆኑ ለኮንጎ ብራዛቪል የሚመጥን ኦክስጅንና ቀይ የደም ሴል ማግኘት አያስችልም፡፡ ስለሆነም አዳማን ለዝግጅት የመረጠው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ወደ ኮንጎ ብራዛቪል የሚያመራው በአዳማ የያዘውን ኦክስጅንና ቀይ የደም ሴል ከውስጡ ሳያወጣ ነው፡፡ የተሻለ ተጠቃሚ እንደሚያደርገውም እምነት አለኝ›› ሲሉ ይገልጹታል፡፡ 

ትልቁ ነገር የሚሉት ሙያተኛው ለዚህ ብቻ ሳይሆን፣ በዘላቂነት በአገሪቱ ያለውን የተፈጥሮ ስጦታ ከአመጋገብ ጋር በማዋሐድ ውጤታማ መሆን እንደሚቻል ነው የሚያስገነዝቡት፡፡ 

በመጨረሻም ሙያተኛው በአገሪቱ ከክለቦች ጀምሮ ውጤታማ ለመሆን በተለይ ክለቦች በየዓመቱ ለተጨዋቾችና ለአሠልጣኝ ከ500 እስከ 600 ሺሕ ብርና ከዚያም በላይ ያወጣሉ፡፡ ነገር ግን የወጪያቸውን ያህል ውጤታማ አይደሉም፡፡ ለዚህ መፍትሔው ደግሞ ሦስቱን የውጤታማነት መርሆዎች ልምምድ፣ የአመጋገብ ሥርዓትና በቂ ዕረፍት የሚባሉትን አሟልተው ስለማይሔዱ ነው፡፡ በሳይንሱም ከሦስቱ አንዱ ከጎደለ በምንም ተአምር ወደሚፈልጉት ግብ መድረስ እንደማይችሉ ጭምር ያስረዳሉ፡፡

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን የአመጋገብ ሥርዓቱን መለወጥ ይችል ዘንድ፣ ስፖርት ኮሚሽን ከትምህርት ሚኒስቴር ጋር በመነጋገር ባዘጋጁት ማዕቀፍ መሠረት እሳቸው፣ በመልካም ፈቃደኝነት እንዲያገለግሉ ተመርጠው የመጡ ስለመሆኑም ሙያተኛው አስረድተዋል፡፡