Skip to main content
x

ክቡር ሚኒስትሩ ከአማካሪያቸው ጋር እያወሩ ነው

- አንድ መሪ ምን ዓይነት ችሎታ ሊኖረው እንደሚገባ፣ ስለጊዜ አጠቃቀሙ፣ ስለትጋት ምናምን በአግባቡ ሳያውቅ እንዴት መሪ ሊሆን ይችላል የሚል ጥያቄ ነው ሕዝቡ የጠየቀው፡፡ - ሌላስ ምን ይላል? - ባለሥልጣናቱ የሕዝብ አገልጋይ ሳይሆኑ በሕዝቡ ተገልጋይ መሆናቸው ተጋለጠ እየተባለ ነው፡፡ - የእኛ ሕዝብ ሁሌም ነገር ማወሳሰብ ይወዳል፡፡ - ደግሞ ከፓርላማ ጋር ሥራ ተቆጣጥራችሁ ትረካከባላችሁ ተብሏል አሉ፡፡ - ምን ችግር አለው? - በሚቀጥለው ዓመት ከፓርላማው ጋር የሥራ ኮንትራት ልትፈራረሙ ነው ተብሏል፡፡ - ስንትና ስንት ውል የምፈራረምና በፊርማዬ የታወቅኩ ሚኒስትር አይደለሁ እንዴ? - ይህችኛዋ ግን ትንሽ የምታስቸግር ይመስለኛል፡፡ - እኔን ብዙ አታውቀኝም ማለት ነው? እኔ እኮ በቢሊዮን ገንዘብ የሚያወጡ ፕሮጀክቶችን የተፈራረምኩ ሰው ነኝ፡፡ - ታዲያ የቢሊዮን ገንዘብ ፕሮጀክቶቹ አንዳቸውም ተግባራዊ መሆን አልቻሉም፡፡ - ቀስ እያሉ ይሠራሉ፣ ምን ፕሮጀክት ማራዘም እኮ የተለመደ ነው፡፡ - ለማንኛውም ይኼን ኮንትራት የሚፈርሙ ከሆነ፣ በዚያው አንድ ነገር መከታተል አይርሱ? - ምን? - የሥራ ማስታወቂያ!

ክቡር ሚኒስትሩ ከስብሰባ በኋላ የሻይ ዕረፍት ላይ ከሌላ ሚኒስትር ጋር እያወሩ ነው

ከጠዋት ጀምሮ ስብሰባው ላይ እያንቀላፉ እኮ ነው፡፡ ለምን አንከባበርም? ይኸው ፎቶ አንስቼዎታለሁ፡፡ ማሸለብ ብርቅ ነው? ኧረ ሙሉ ስብሰባውን ነው የተኙት፡፡ አሁን አንተ ንቁ ነኝ እያልክ ነው? እኔማ ስብሰባው የእርስዎን መሥሪያ ቤት ስለሚመለከት ብዙ አስተያየት ይሰጣሉ ብዬ ጠብቄ ነበር፡፡ ስማ እኔ ተኝቼ ሳይሆን እያሰላሰልኩ ነበር፡፡ ኪኪኪ… ምን ያስቅሃል? ለማንኛውም ሁኔታዎን ሳየው እንዲያው የደከምዎት ይመስለኛል፡፡ ማን ነው የደከመው? እርስዎ ነዎታ፡፡ ለዚህ ሥርዓት እኮ እኔ አድራጊ ፈጣሪ ነኝ፡፡ ክቡር ሚኒስትር አሁን ግን አድራጊ ፈጣሪ አይደሉም፡፡ እና ምንድነኝ? ተጧሪ!

ክቡር ሚኒስትሩ ከሌላ ሚኒስትር ጋር እያወሩ ነው

ሰውዬ እየተሳደብክ እኮ ነው? ብንከባበር አይሻልም? ስንተዋወቅ አንተናነቅ አሉ፡፡ ምን እያልክ ነው? እርስዎ አሁን እየፈጠሩት ያለው ችግር አዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር እንዳይሠሩ ለማድረግ ነው፡፡ ታዲያ የማን ሥራ ቆሞ የማን ይቀራል? እሱማ የእርስዎ ዋነኛ ሥራ ሌብነት መሆኑ ይታወቃል፡፡ እኔ ብሰርቅ እኮ መልሼ አገሬን ነው የማለማው፡፡ ትንሽ እንኳን አያፍሩም ክቡር ሚኒስትር? አገሬን ማልማት ምን ያሳፍራል? አገር በስርቆት አይለማም፡፡ ለመሆኑ ምን አጠፋህ ነው የምትለኝ? በየካቢኔ ስብሰባው የሚፈጥሩት ችግር ለምን እንደሆነ ተደርሶበታል፡፡ አሁንም እቀጥልበታለሁ፡፡ እኔ ግን ከዚህ አፍራሽ ተግባርዎ እንዲቆጠቡ እመክርዎታለሁ፡፡ እያስፈራራኸኝ መሆኑ ነው? ይህን አፍራሽ ተግባርዎን ከቀጠሉበት እኛም የዘጋነውን እስር ቤት መክፈታችን አይቀርም፡፡ የትኛውን እስር ቤት? ማዕከላዊን!

የክቡር ሚኒስትሩ ሚስት ወዲያው ባላቸው ጋ ደወሉ

ስማ በተከበርኩበት አገር ልዋረድ? ምን ሆንሽ? ከአገር አትወጪም ተባልኩ እኮ? ማን ነው ያለሽ? የቁም እስረኛ ተደርጌያለሁ። ማን ነው ያሰረሽ? አንተ እያለህ እንዴት ይህ ይፈጸምብኛል? ምንድነው የሆንሽው? ከአገር አትወጪም ተባልኩ። ለምንድነው የማትወጪው? ሊስት ውስጥ አለሽ ተብዬ ነዋ። ምን ላድርግልሽ ታዲያ? በአስቸኳይ ከአገር እንድወጣ አስደርገኝ። እሱንማ ማድረግ አልችልም። ለምን ሲባል? መመርያ ከተላለፈ ምንም ማድረግ አልችልም። እና እኔ ከአገር አልውጣ? የአንቺ ከአገር አትውጪ መባል ይገርምሻል እንዴ? ለምን አይገርመኝም? እኔ ከየት እንዳልወጣ እንደተከለከልኩ ታውቂያለሽ? ከየት አትውጣ ተባልክ? ከቢሮ!

ክቡር ሚኒስትሩ ከሌላ ሚኒስትር ጋር እያወሩ ነው

አሉ እንዴ ክቡር ሚኒስትር? የት እንድሄድ ፈለግህ ደግሞ? በዚህኛው ካቢኔ ውስጥ አሉበት አይደል? ይሻራል ብለህ ጠብቀህ ነበር? እንደ እርስዎ ግን ዕድለኛ ሰው ያለ አይመስለኝም፡፡ ምን እያልክ ነው? ክቡር ሚኒስትር የእርስዎ ቅሌት መቼ ተወርቶ ያልቃል? ስድቡ ቢቆይስ? እርስዎ መሠረታዊ ችግር እኮ ነው ያለብዎት፡፡ የምን ችግር ነው? የስርቆት ነዋ፡፡ ምን? የሌብነት ችግር አለብዎት፡፡ ሰውዬ መስመር እያለፍክ እኮ ነው? እንዲያውም ስለመስመር ካወሩማ፣ በከባድ ሁኔታ መስመሩን ያለፉት እርስዎ ነዎት፡፡ የምን መስመር ነው ያለፍኩት? የጠቅላይ ሚኒስትሩን ቀይ መስመር ነዋ፡፡ እ… ይኼን ሁሉ ጥፋት ሠርተው አሁንም በሥልጣን ላይ መሆንዎ ይገርማል፡፡ የሰው መውደድ ይስጥህ ነው የምልህ፡፡ ለማንኛውም ቀይ መስመሩን በቅርቡ እንደሚጥሱት እርግጠኛ ነኝ፡፡ ለምን ቀይ መስመሩን እንደምጥስ ታውቃለህ? ለምንድነው የሚጥሱት? ከለር መለየት አልችልም፡፡ ማለት? ከለር ብላይንድ ነኝ!

ክቡር ሚኒስትሩ አማካሪያቸውን ቢሯቸው ያስጠሩታል

እኛም አሜሪካኖቹ በሶሪያ የሚሠሩትን ግፍ ካላቆሙ ተመሳሳይ ዕርምጃ እንወስዳለን እንበላ፡፡ ምን ዓይነት ዕርምጃ? የአሜሪካ ባለሥልጣናት ወደ ኢትዮጵያ መግባት አይችሉም፡፡ እ… አንድም ዶላር በኢትዮጵያ ባንክ ውስጥ ማስቀመጥ አይችሉም፡፡ እኛ ግን የዶላር እጥረት አለብን እኮ፡፡ አይቻልም አልኩህ አይቻልም፡፡ እሺ ክቡር ሚኒስትር፡፡ ስለዚህ አሁን የነገርኩህን ነገር እንደ አቋም መግለጫ አድርገህ አዘጋጀው፡፡ ክቡር ሚኒስትር ይህ ግን የአቋም መግለጫ መሆን አይችልም፡፡ ታዲያ ምንድነው? የምኞት መግለጫ!

ክቡር ሚኒስትሩ አንድ ባለሀብት ጋ ይደውላሉ

አሁንማ ብዙ ነገር ተቀይሯል፡፡ ምንድነው የተቀየረው? ያው አሁን ጊዜው መቀየሩን ያውቃሉ፡፡ ምን አንተም እንደ ሌሎቹ ዶላር ምናምን ጨመረ ልትለኝ እንዳይሆን? እሱም እንዳለ ሆኖ ሌሎችም ለውጦች አሉ፡፡ መቼም የዋጋ ግሽበቱ እንዳትለኝ? ከእነዚህ በላይ በጣም የተለወጠ ነገር አለ፡፡ ምንድነው የተለወጠው ነገር? ይኸው እናንተ ራሳችሁ ጥልቅ ተሃድሶ ውስጥ አይደላችሁ እንዴ? ሰውዬ ምንም የተለወጠ ነገር የለም፡፡ ክቡር ሚኒስትር ጥልቅ ተሃድሶውስ? እሱ ለሚዲያ ጥቅም ነው፡፡ እኔ ግን ፓርቲያችሁ እያደረገ ባለው እንቅስቃሴ ለውጦች ያሉ እየመሰለኝ ነው፡፡ አትሸወድ ምንም ለውጥ የለም፡፡ እኔ ግን እውነተኛ ተሃድሶ ውስጥ ገብቼ አቁሜያለሁ፡፡ ምንድነው ያቆምከው? እርስዎን መቀለብ!

ክቡር ሚኒስትሩ ማታ ቤት ሲገቡ ልጃቸውን ያስጠሩታል

ክፍል ውስጥ ገብተህ ተምረህ ቢሆንማ፣ እንደዚህ ዓይነት ውጤት ልታመጣ አትችልም? በጣም ከብዶኝ ነው ዳዲ፡፡ ሁለት ከመቶ ታመጣለህ? ፈተናው ለየት ባለ መልኩ ነበር የወጣው፡፡ ለየት ባለ መልኩ ማለት ምንድነው? በፊት ምርጫ ነበር የሚወጣው፡፡ ምርጫ ቢሆንስ? እሱማ ለማጭበርበር ይቀላል፡፡ የአሁኑስ ምንድነው? የአሁኑማ ካልኩሌሽን ነው፡፡ ካልኩሌሽን ቢሆንስ? ትምህርቱ ካልገባህ እንደዚህ ትዋረዳለሃ? አሁን አንተ የእኔ ልጅ ስትባል አታፍርም? ምነው ዳዲ? እኔ ለአንተ ምንድነው ያስተማርኩህ? ምን አስተማርከኝ ዳዲ? መድፈንና መድፈን ብቻ አይደል እንዴ ያስተማርኩህ?

ለክቡር ሚኒስትሩ ዳያስፖራ ወዳጃቸው ይደውልላቸዋል

- ሰሞኑን በጣም ያዝናናኝን ነገር ግን ላጫውትዎት፡፡ - ምንድነው እሱ? - ሰሞኑን በፌስቡካችሁ የለቀቃችሁት ፎቶ ነዋ፡፡ - የምን ፎቶ? - አንቨርሰሪ ስታከብሩ የለቀቃችሁት ፎቶ ነዋ፡፡ - ምን ሆነ ደግሞ? - አለቆቻችሁ ኬክ እየቆረሱ የተነሱትን ነዋ፡፡ - ለምን ዳቦ አልሆነም ነው ጥያቄህ? - እናንተም ውስጥ ኒዮ ሊብራሎች ገብተዋል ማለት ነው? - መቼ ይጠፋሉ ብለህ ነው? - ለማንኛውም ቤቢ ሻወራችሁን እያከበራችሁ ነው የሚመስለው፡፡ - ምንድነው እሱ ደግሞ? - ያው ሴቶች ከመውለዳቸው በፊት ስጦታ የሚሰጥበት ባህል ነው፡፡ - ልጁ ሳይወለድ እንዴት ስጦታ ይሰጣል? - ያው የፈረንጆች ባህል ነው፡፡ - በእኛ ባህል ግን ከተወለደ በኋላ ነው ስጦታ የሚሰጠው፡፡ - እሱንማ አውቃለሁ፡፡ - እኛም ኬክ የቆረስነው ለቤቢ ሻወር አይደለም፡፡ - ታዲያ ለምንድነው? - ለአራስ ጥሪ!

[ክቡር ሚኒስትሩ ከቀድሞ ጓደኛቸው ጋር ተገናኝተው እያወሩ ነው]

ኩባንያዎቹ የሚፈልጉት የተማረ የሰው ኃይል ነው፡፡ ሥራ አጡ ሁላ የተማረ አይደል እንዴ? እ. . . ያውም ዩኒቨርሲቲ ድረስ ያስተማርነው ሥራ አጥ እኮ ነው ያለን፡፡ ክቡር ሚኒስትር ተማረ የሚባለው ወጣት እኮ በጣም ያሳፍራል፡፡ እንዴት? እኔም ዩኒቨርሲቲ ማስተማር ያቆምኩት በዚህ ምክንያት ነው፡፡ የምትለው አልገባኝም? የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ዕውቀታቸው እኮ አሳፋሪ ነው፡፡ ስማ በዓለም አቀፍ ደረጃ ሳይቀር የተመሰገንበትን የትምህርት ስኬት ስታጣጥለው አታፍርም? ክቡር ሚኒስትር በየመንደሩ የተቋቋሙት ዩኒቨርሲቲዎች የሚያወጡት ትውልድ የተማረ የሰው ኃይል ነው ማለት ይከብዳል፡፡ ታዲያ ምን ይባል? የተማረረ የሰው ኃይል!