Saturday, Jul 31st

English Version

አቶ በረከትና አቶ ልደቱ በአንድ ምርጫ ጣቢያ ይወዳደራሉ

E-mail Print PDF
User Rating: / 2
PoorBest 

"የቡግና ወረዳ ህዝብ ጠርቶኛል"
አቶ ልደቱ አያሌው
(በአሰግድ ተፈራ)

በመጪው ግንቦት ምርጫ አቶ በረከት ስምዖንና አቶ ልደቱ አያሌው በአንድ ምርጫ ጣቢያ እንደሚወዳደሩ ታወቀ፡፡ አቶ ልደቱ "የቡግና ወረዳ ሕዝብ ጠርቶኛል" ሲሉ ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ኢዴፓ) ሊቀመንበር አቶ ልደቱ አያሌው ለሪፖርተር እንደተናገሩት፣ በመጪው ግንቦት ወር በሚካሄደው ምርጫ የተወካዮች ምክር ቤት አባል ለመሆን ከአቶ በረከት ጋር የሚያደርጉት ውድድር በህዝብ ጥያቄ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡

"ኢህአዴግን መምረጥ ሰልችቶናል" በማለት የቡግና ወረዳ ህዝብ እንደጠራቸው የገለፁት አቶ ልደቱ፣ በምርጫው ውጤት አዲሱን የስነምግባር ደንብ በማክበር እሳቸውና አቶ በረከት መልካም አርአያ በመሆን ቅድሚያውን እንደሚወስዱ ተናግረዋል፡፡

በ1997 ዓ.ም. ምርጫ በወረዳ 21 እና 22 የምርጫ ጣቢያ ተወዳድረው የወቅቱን የትምህርት ሚኒስትር ወ/ሮ ገነት ዘውዴን አሸንፈው ፓርላማ የገቡት አቶ ልደቱ፣ መጪውን ምርጫ አዲስ አበባ ላይ መወዳደር ያልፈለጉበትን ምክንያት እንዲያስረዱ ተጠይቀው ". . . አካባቢው የተወለድኩበት በመሆኑ የአካባቢው ተወላጆች ድረስልን የሚል ጥያቄ በማቅረባቸው ነው" ሲሉ መልስ ሰጥተዋል፡፡ አቶ በረከት ላለፉት ሶስት ምርጫዎች የተወዳደሩበትን የምርጫ ጣቢያ ስለመቀየራቸው የተገለፀ ነገር የለም፡፡

አቶ በረከት ለሶስተኛ ጊዜ ለተወካዮች ምክር ቤት በተወዳዳሪነት በቀረቡበት በሰሜን ወሎ ዞን የምትገኘው የቡግና ወረዳ በ1997 ዓ.ም. ምርጫ ወቅት የተፎካከሩዋቸው ተወዳዳሪ ቅንጅትን በመወከል የኢዴፓ አባል የነበሩት አቶ ደስታው ካሴ እንደነበሩ ይታወሳል፡፡ በወቅቱ ምርጫ ውጤት አቶ በረከት መሸነፋቸው ከተገለፀ በኋላ ምርጫው ላይ በቀረበ አቤቱታ ድጋሚ ድምፅ እንዲሰጥ ተደርጎ አቶ በረከት ማሸነፋቸው የሚታወስ ነው፡፡