- ፍራንስ ቴሌኮም ተቀባይነት አግኝቷል
(በአሰግድ ተፈራ)
የኢትዮጵያ ቴሌኮሙኒኬሽን ኮርፖሬሽን ወደ ዘመናዊ ደረጃ ለማሳደግ ማኔጅመንቱን ለውጭ የቴሌኮም ኩባንያዎች ለመስጠት ባወጣው ጨረታ ከቀረቡት ተወዳዳሪዎች መካከል ቴሌኮም ፍራንስ ተቀባይነት ማግኘቱ ታወቀ፡፡
የፈረንሣዩ ኩባንያ የቅርብ ተፎካካሪዎቹን የደቡብ አፍሪካና የህንድ ኩባንያዎችን ማሸነፉ ተጠቁሟል፡፡
ፍራንስ ቴሌኮም ተገምግሞ የተመረጠው ከስድስት ተወዳዳሪ ኩባንያዎች የተሻለ አቅም አለው ተብሎ ነው፡፡ ቴሌ ያወጣው ጨረታ የበርካታ የውጭ ኩባንያዎችን ቀልብ የሳበ ሲሆን፣ በመጨረሻ ግን ሦስቱ ኩባንያዎች ናቸው ከፍተኛ ፉክክር ያደረጉት፡፡ የደቡብ አፍሪካው ኤምቲኤን እና የህንዱ መንግሥታዊ ኩባንያ ባራለት ሳንቻር ኒጋም በመጨረሻ በፍራንስ ቴሌኮም ተሸንፈዋል፡፡
ቴሌ ማኔጅመንቱን ለውጭ ኩባንያ ለመስጠት ባወጣው ጨረታ መሠረት አሸናፊውን ኩባንያ ይፋ ያላደረገው፣ በርካታ ቴክኒካዊ ጉዳዮች በመኖራቸውና ማኔጅመንቱን በውጭ ኩባንያ ለማስያዝ ቢያንስ የሦስት ወር ጊዜ ስለሚያስፈልግ መሆኑን የዜናው ምንጮች ተናግረዋል፡፡
የኮርፖሬሽኑን አቅም ለማሳደግ ማኔጅመንቱን ለውጭ ኩባንያዎች መስጠት አግባብ እንደሆነ የጠቆሙ አንዳንድ ሠራተኞች፣ "ቴሌ ማኔጅመንቱ ለውጭ ኩባንያ ከተሰጠ ሹመትና ኃላፊነት በብቃት ላይ ብቻ ስለሚሆን በኃላፊዎች ምደባ ላይ ክፍተት ይፈጠራል" የሚል ስጋት እንዳላቸው ተናግረዋል፡፡ በሌላ በኩል የውጭ ኩባንያ የሚሠራው ትርፍን ለማሳደግ በመሆኑ አገልግሎቱን የሚያስፋፋው ገበያው ባለበት አካባቢ በመሆኑ፣ ከመንግሥት የልማት ስትራቴጂ ጋር ጐን ለጐን የመሄዱ ጉዳይና የሠራተኛ ማኅበር በተለያዩ ጉዳዮች "የእንደራደር" ጥያቄ ችግር ይፈጥራሉ ከተባሉት ምክንያት መካከል በዋናነት የተቀመጡት ናቸው፡፡
የቴሌ ማኔጅመንትን ለውጭ ኩባንያ ለመስጠት የተወሰደው እርምጃ፣ እንደ አዲስ ክስተት የተቆጠረ ሲሆን፣ ለረጅም ጊዜ ኮርፖሬሽኑ በመንግሥት ቁጥጥር ሥር በመዋሉ ምክንያት ዓለም አቀፍ የገንዘብ ድርጅትን (አይ ኤም ኤፍ) ጨምሮ ከበርካታ የውጭ የልማት ተቋሞች በመንግሥት ላይ ትችት ይቀርብ እንደነበር አይዘነጋም፡፡



