- የኢትዮጵያ ልዑክም ወደ ሥፍራው ተጉዟል
(በቃለየሱስ በቀለ)
በቤይሩት አደጋ የደረሰበት የኢትዮጵያ አየር መንገድ አውሮፕላን የበረራ የመረጃ ሳጥን (ብላክ ቦክስ) ምርመራ ወደሚካሄድበት ወደ ፈረንሳይ ከትላንት በስቲያ ተልኳል፡፡
የሊባኖስ ብሔራዊ ዜና አገልግሎት እንደዘገበው፣ የአቪየሽን ባለሙያዎች ሰኞ ንጋት ላይ የበረራ መረጃ ሳጥኑን ይዘው በሊባኖሱ ጠቅላይ ሚኒስትር ሰዐድ ሃሪሪ የግል አውሮፕላን ወደ ፈረንሳይ ተንቀሳቅሰዋል፡፡ የሊባኖስ ሲቪል አቪየሽን ዳይሬክተር ጀነራል ሃምዲ ቻወቅ እና የቦይንግ ኩባንያ ተወካይ ሚስተር ዴኒስ ጆንስ በባለሙያዎቹ ቡድን ውስጥ እንደሚገኙ ተዘግቧል፡፡
የሊባኖስ የትራንስፖርት እና ሥራ ሚኒስትር ጋዚ አርዲ የበረራ መረጃ መመዝገቢያ መሳሪያውን በሊባኖስ ባሕር ኃይል ኮማንዶ ኃይሎች አማካይነት እሑድ ጥር 30 ቀን 2002 ዓ.ም. ናሜህ በምትባል ከተማ አቅራቢያ ከቤይሩት በስተደቡብ በሚገኝ የባሕር ዳርቻ እንደተገኘ ገልፀዋል፡፡ በሚ/ር አርዲ ገለፃ፣ መሣሪያው የተገኘው ከባሕር 45 ሜትር ጥልቀት ውስጥ ነው፡፡ የበረራ መረጃ መመዝገቢያ መሳሪያው ከአውሮፕላኑ አካል ስባሪ ጋር እንደተገኘ ሚኒስትሩ ገልፀዋል፡፡
የሥራ ኃላፊዎች በምርመራ ሥራ ላይ መጠመዳቸውን የገለፁት ሚኒስትሩ፣ ለምርመራው ጊዜ የተሰጠ ቀነ ገደብ እንደሌለ ተናግረዋል፡፡
ከኢትዮጵያ አየር መንገድ የሕዝብ ግንኙነት ክፍል ያገኘነው መረጃ እንደሚያመለክተው፣ በኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ባለሥልጣን የአደጋ መከላከልና ምርመራ ማስተባበሪያ ቢሮ ኃላፊ የሚመራ የኢትዮጵያ ልዑካን ቡድን ወደ ፈረንሣይ አብሮ ተጉዟል፡፡
የቢሮ ኃላፊው አቶ ግርማ ገብሬ በሚመሩት ልዑክ ውስጥ፣ የኢትዮጵያ አየር መንገድ የበረራ ኦፕሬሽንና የምህንድስና የሥራ ክፍሎች ሁለት ኃላፊዎች አብረው እንደተጓዙ አየር መንገዱ ገልጿል፡፡
የአውሮፕላኑ የበረራ መረጃ ሳጥን ወደ ፈረንሣይ ስለተላከበት ምክንያት የተሰጠው ምላሽም፣ አደጋው የደረሰው ሊባኖስ ውስጥ በመሆኑ፣ የበረራ መረጃ ሳጥኑ የት መመርመር እንዳለበት በሊባኖስ ባለሥልጣናት በመወሰኑ ነው፡፡
በበረራ መረጃ ሳጥኑ ላይ የሚደረገውን ምርመራ ከኢትዮጵያ የሔደው ልዑክ በቅርበት እየተከታተለው እንደሆነ የሕዝብ ግንኙነት ክፍሉ አስታውቋል፡፡
የበረራ መረጃ መመዝገቢያ መሣሪያ የሚቀመጠው ብዙውን ጊዜ በአውሮፕላን ጭራ አካባቢ ነው፡፡ የሪፖርተር ጋዜጣ ያነጋገራቸው አንድ የአቪየሽን ባለሙያ መሣሪያው አውሮፕላኑ ይበርበት የነበረውን ፍጥነትና አቅጣጫ፣ የበረራ ከፍታና የሞተሮቹን የሥራ እንቅስቃሴ ከአውሮፕላኑ የተለያዩ ክፍሎች ተቀብሎ ቀርፆ እንደሚያስቀምጥ ገልጸዋል፡፡ ባለሙያው እንዳሉት፣ መሣሪያው በአውሮፕላኑ የመጨረሻ ክፍል ወይም ጭራ አካባቢ የሚገጠመው፣ ብዙውን ጊዜ ይኼኛው የአውሮፕላን ክፍል በአደጋ እንደማይጐዳ ወይም ሙሉ በሙሉ ከጥቅም ውጭ እንደማይሆን ከልምድ በመታየቱ ነው፡፡ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ቦይንግ 737-800 አውሮፕላን የመረጃ ሳጥን መገኘት ትልቅ አንድምታ አለው፡፡
በመሣሪያው ላይ በሚካሄደው ምርመራ አውሮፕላኑን ምን እንደገጠመው ለማወቅ እንደሚቻል የጠቆሙት ባለሙያው፣ የምርመራውን ሥራ ለማጠናከር የድምፅ መቅረጫው መገኘት ወሳኝ ቢሆንም፣ በበረራ መረጃ መመዝገቢያው መሣሪያ ላይ በሚደረገው ምርመራ የአደጋውን መንስኤ ማወቅ እንደሚቻልም አክለው ገልፀዋል፡፡
መቅረፀ ድምፁ የሚቀመጠው በአይሮፕላኑ ጭራ አካባቢ ቢሆንም በበረራ ክፍሉ ውስጥ የሚደረጉ ማናቸውንም ዓይነት ንግግሮች (የሬዲዮ መልዕክት ልውውጥን ጨምሮ) ቀርፆ ያስቀምጣል፡፡ ይህ መሣሪያ አብራሪዎቹ የገጠማቸውን ችግር እና ያደረጉትን ጥረት ለመረዳት ወሳኝ እንደሆነ ካነጋገርናቸው ባለሙያ ማብራሪያ ለመረዳት ተችሏል፡፡
ይህ በእንዲህ እንዳለ የአደጋውን መከሰት ተከትሎ የሊባኖስ መንግሥት ተቃውሞ እየተሰነዘረበት ነው፡፡
በአደጋው ሰለባ የሆኑ ኢትዮጵያውያን መንገደኞች ዘመዶች የሆኑ እና በቤይሩት የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን፣ የሊባኖስ መንግሥት አደጋውን በተመለከተ መረጃ አልሰጠንም፣ ሲሉ ከትላንት በስቲያ የተቃውሞ ሰልፍ ማካሄዳቸውን ከቤይሩት የወጡ የዜና ዘገባዎች ጠቁመዋል፡፡ ኢትዮጵያውያኑ ተቃውሟቸውን ያካሄዱት በራፊቅ ሃሪሪ ሆስፒታል ደጃፍ ላይ ሲሆን፣ አራት ሊባኖሳውያን የሟቾች ቤተሰቦችም በተቃውሞ ኢትዮጵያውያኑን ተቀላቅለዋቸዋል፡፡ የሂዝቦላ ፖሊት ቢሮ ኃላፊ ኢብራሂም አሚን አል ሳይድ መንግሥት ስለደረሰው የአውሮፕላን አደጋ ያሰባሰበውን መረጃ ለሕዝቡ ይፋ እንዲያደርግ ያሳሰቡ ሲሆን፣ ይህን በማድረጉም የሊባኖስን ስም ለመጠበቅ እንደሚረዳ ገልጸዋል፡፡



