Saturday, Jul 31st

English Version

የእንግሊዝ የንግድ ልዑካን አዲስ አበባ ሊመጡ ነው

E-mail Print PDF
User Rating: / 0
PoorBest 

በምዕራፍ ብርሃነ

አርባ የእንግሊዝ ኩባንያዎች የሚወከሉበት አንድ ልዑክ በአዲስ አበባ የአራት ቀናት ጉብኝት ለማድረግ እንደሚመጣ የእንግሊዝ ኤምባሲ አስታወቀ፡፡


ኩባንያዎቹ በባንክ፣ በምርት አቅራቢነት፣ በግብርና፣ በደህንነት ጥበቃ እና በንግድ ዘርፎች ውስጥ የተሰማሩ እንደሆኑ ታውቋል፡፡

በለንደን የአክሲዮን ሽያጭ ገበያ ላይ ከፍተኛ ካፒታል ካላቸው ኩባንያዎች ውስጥ ዲያጂ ኃ.የተ.የግ.ማ፣ ጂ.ፎር.ኤስ ኃላ.የተ.የግ.ማ. እና ስታንዳርድ ቻርተር በጉብኝቱ ውስጥ እንደሚካተቱ ተገልጿል፡፡ በተመሳሳይ ሁኔታም በምሥራቅ አፍሪካ የሚሠሩ በርካታ ኢንቨስተሮችም በጉብኝቱ ተሳታፊ እንደሆኑ ታውቋል፡፡

"ይህ ጉብኝት ከኢትዮጵያ ጋር ባለን ከ170 ዓመታት በላይ ግንኙነት ጊዜ ውስጥ ከፍተኛ የሆነ የእንግሊዝ የኢንቨስትመንት ተልዕኮ ነው፡፡ ተልዕኮው እያደገ የመጣውን የእንግሊዝንና የዓለም አቀፍ ኩባንያዎችን በኢትዮጵያ ውስጥ ኢንቨስት የማድረግ ፍላጐትን ያንፀባርቃል፡፡ እንዲሁም እንግሊዝ ለኢትዮጵያ ኢኮኖሚያዊና ማኅበረሰባዊ እድገት ያላትን ድጋፍ የሚያሳይ ነው" ሲሉ ኖርማን ሊንግ በኢትዮጵያ የእንግሊዝ አምባሳደር በጋዜጣዊ መግለጫው ላይ አስታውቀዋል፡፡ 

አንድ እንግሊዝ ኤምባሲ ባለስልጣን የልዑካኑ ቡድን ከአቶ ታደሰ ኃይሌ የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ፣ ከአቶ አቢ ወልደ መስቀል የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር እና ከሌሎች ከፍተኛ ባለሥልጣናት ጋር ተገናኝተው ውይይት እንደሚያደርጉ ለሪፖርተር ጋዜጣ ገልጸዋል፡፡

የእንግሊዝ ኤምባሲ ለሪፖርተር ጋዜጣ በላከው ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ፣ ኩባንያዎቹ በኢትዮጵያ ውስጥ በኢንቨስትመንት እና ንግድ ዘርፍ ውስጥ መሳተፋቸው የጉብኝቱ አላማ ውጤት እንደሚሆን ታውቋል፡፡ የንግድ ልዑክ በሚያደርገው ጉብኝት እና በሚኖረው ቆይታ በኢትዮጵያ ውስጥ ስላለው የኢንቨስትመንት ሁኔታ ገለጻ እንደሚደረግለት ተገልጿል፡፡ በተጨማሪም ስለ ኢንቨስትመንት እድገትና ከለላን በተመለከተ ኢትዮጵያ ከእንግሊዝ ጋር ኅዳር 10 ቀን 2002 ዓ.ም. ባደረገችው ስምምነት ጭምር ውይይት እንደሚያደርጉ ታውቋል፡፡ ስምምነቱ ኢንቨስትመንቱ ለሁለቱ አገሮች ሕዝቦችና ኩባንያዎች የተመቻቸ ሁኔታ ለመፍጠር የሚያስችል ይዘት ያለው ነው፡፡

የጉብኝቱን ፕሮግራም ያዘጋጁት የእንግሊዝ ኤምባሲ እና የምሥራቅ አፍሪካ ማኅበር ሲሆኑ፣ ማኅበሩ ከአርባ ዓመታት በፊት የተቆረቆረ እና የውጭ አገር ኢንቨስተሮችን ፍላጎት በምሥራቅ አፍሪካ ለሚገኙ አገሮች የማስታወቅ ሥራ የሚሠራ ማኅበር ነው፡፡ የዚህ ማኅበር አባላት ኬንያ፣ ዩጋንዳ፣ ታንዛኒያ፣ ሩዋንዳ፣ ኢትዮጵያ፣ ኤርትራ፣ ሲሺየልስ እና ብሩንዲ ናቸው፡፡