- በአዲስ አበባ መብራት ሙሉ ቀን መጥፋት ጀምሯል
በታምሩ ጽጌ
የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ኮርፖሬሽን ባጋጠመው የኃይል እጥረት ምክንያት፣ ትላልቅ ፋብሪካዎች ማታ ማታ መብራት እንዲያጠፉ የሚያስገድድ ደብዳቤ እንደጻፈላቸው ምንጮች ለሪፖርተር ጋዜጣ ገለጹ፡፡ ኮርፖሬሽኑ በበኩሉ ከሲስተም ውጭ ያለ ኃይል እንዳይጠቀሙ ለማድረግ መሆኑን ገልጿል፡፡
ግልገል ጊቤ ሁለት በተመረቀ በ10ኛው ቀን በደረሰበት ተፈጥሮአዊ አደጋ ምክንያት የተፈጠረውን የኃይል እጥረት ለማካካስ፣ በተለያዩ ሰዓታት ልዩነት በተደጋጋሚ መብራት እየጠፋ እንደሚገኝ የገለጹት ምንጮቹ፣ ሙሉ በሙሉ ወደ ፈረቃ ከመገባቱ በፊት ከፍተኛ ኃይል ተጠቃሚ የሆኑ ፋብሪካዎች ማታ ማታ መብራት እንዲያጠፉ ወይም ማምረት እንዲያቆሙ የሚከለክል ደብዳቤ በሚመለከታቸው ሪጅን መሥሪያ ቤቶች በኩል እየተጻፈ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
በምንጮቹ ገለጻ፣ በተለይ በድንጋይ መፍጨት ሥራ ላይ ተሰማርተው የሚገኙትን ከፍተኛም ይሁን መለስተኛ ፋብሪካዎች ለተወሰነ ጊዜ ሥራ ማቆም እንዳለባቸውና በቀጣይ ሁኔታዎች ላይ የሚያወያይ ኮሚቴ መሰየሙን አስታውቀዋል፡፡
በተለይ ግልገል ጊቤ ሁለት አደጋ ከደረሰበት በኋላ የተሰየመው ኮሚቴ፣ በከፍተኛ ሁኔታ እየተንቀሳቀሰ እንደሚገኝ ምንጮቹ ጠቁመው፤ አንዳንድ ፋብሪካዎች ከቀጥታ መስመር ኃይል ያገኙ ወይም የተቀጠለላቸው በመሆኑም "እንዴት እንዲህ ሊሆን ቻለ?" የሚል ጥያቄ በማንሳት፣ ጉዳዩን ለማጣራት በየዲስትሪክት ጽ/ቤቱ እያጣራ እንደሚገኝ ጠቁመዋል፡፡
በ2001 ዓ.ም. በአገሪቱ ደርሶ የነበረው የኃይል እጥረት ተከዜ ሲመረቅ መቃለል መጀመሩንና ግልገል ጊቤ ሁለት ሲመረቅ ደግሞ ሙሉ በሙሉ ተወግዶ እንደነበር የገለጹት ምንጮቹ፤ ተከስቶ የነበረው የኃይል እጥረት ለቀናት ብቻ ጠፍቶ መመለሱ እንዳሳዘናቸው ተናግረዋል፡፡
በቅርቡ ይመረቃል (መጋቢት መጨረሻ ላይ) እየተባለ ያለው ጣና በለስ የኃይል ማመንጫ በተባለው ጊዜ ኃይል ማመንጨት ካልጀመረ፤ ማታ ማታ መብራት እንዲያጠፉ (ሥራ እንዲያቆሙ) ደብዳቤ በተጻፈላቸው ፋብሪካዎች ላይ ብቻ ሳይሆን ሁሉም የኤሌክትሪክ ኃይል በፈረቃ የሚያበራበት ጊዜ ሩቅ እንደማይሆን ምንጮቹ ስጋታቸውን ገልጸዋል፡፡
የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ኮርፖሬሽን የሕዝብ ግንኙነትና ኮሚዩኒኬሽን የሥራ ሒደት ባለቤት አቶ ምስክር ነጋሽን አነጋግረናቸው፤ ግልገል ጊቤ ሁለት የኃይል ማመንጫ ላይ በደረሰው ችግር ምክንያት የተፈጠረውን ክፍተት ለማስተካከል ፋብሪካዎች ከሲስተም ውጭ ያለን ኃይል በመቀነስ እንዲጠቀሙ እየተደረገ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
የተፈጠረውን የኃይል እጥረት ለማገዝ እንዲረዳ በሚል ቆሞ የነበረውን ዲዝል ጀኔሬተር ለማንቀሳቀስ አስፈላጊ ሆኖ መገኘቱን የገለጹት አቶ ምስክር፤ ቢሾፍቱ (ደብረ ዘይት) ላይ ተተክሎ የነበረውንና 30 ሜጋ ዋት ኃይል ማመንጨት የሚችለውን ጀነሬተር እንዲጀምር ለማድረግ ኮርፖሬሽኑ እየተንቀሳቀሰ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
የተፈጠረው የኃይል እጥረት ችግር መፍትሔ እስከሚገኝና ጣና በለስ ተመርቆ ሥራ እስከሚጀምር ድረስ ሌሎች አማራጮችን እየፈለጉ ክፍተቶችን መሙላት አስፈላጊ በመሆኑ፣ በኃይል አቅርቦቱ ዙርያ የሚሠራ ኮሚቴ ተቋቁሞ እየሠራ መሆኑን አቶ ምስክር አረጋግጠዋል፡፡
ኮርፖሬሽኑ መብራት በፈረቃ ሊጀምር ማሰቡንና ለምን? ለነማንና ለስንት ፋብሪካዎች ደብዳቤ እንደተጻፈ ላነሳንላቸው ጥያቄ፤ ሁሉም ነገር ከተጣራና እነማንና ስንት እንደሆኑ መግለጽ በሚያስፈልግበት ጊዜ ብቻ መግለጽ እንደሚችሉ የተናገሩት አቶ ምስክር፤ የተፈጠረው ችግር በተፈጥሮ በመሆኑና ለኢትዮጵያም ሕዝብ ሆነ ለሚዲያ የሚደብቁት ነገር ስለሌለ ማንኛውንም ነገር ግልጽ እንደሚያደርጉ ገልጸዋል፡፡



