(በየማነ ናግሽ)
ኢሕአዴግ በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን እንዲተላለፍለት የላከው የምርጫ ቅስቀሳ መልዕክት የኢፌዴሪ ሰንደቅ ዓላማ አዋጅንና የምርጫ ሥነምግባር አዋጅን የሚጥሱ ይዘቶች በማካተቱ "ለማስተናገድ እቸገራለሁ" በማለት አስተካክሎ እንዲመጣ መልሶለታል፡፡
የካቲት 16 ቀን 2002 ዓ.ም. በቁጥር ቴ10/172-1/10 ከኢትዮጵያ ሬዲዮና ቴሌቪዥን ድርጅት (ኢሬቴድ) ለኢሕአዴግ የተላከው ደብዳቤ እንደሚያሳየው፣ ኢሕአዴግ በ16/06/2002 ዓ.ም. በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን እንዲተላለፍለት የላከው የምርጫ ቅስቀሳ መልዕክት፣ በአዋጁ የተከለከለ የቀድሞ ሰንደቅ ዓላማ በመጠቀሙና የምርጫ ሥነ ምግባር ደንብ የሚጥስ ይዘት ያካተተ ሆኖ ተገኝቷል፡፡
የኢሬቴድ፣ "ሰሞኑን አንዳንድ ተቃዋሚዎች የምኒልክ አልጋ ላይ የተኙ ሰዎች ከእኛ ጋር ስላሉ ሥልጣን ይገባናል ሲሉ የሰማነውም " አልጋውን" በሚል በቅስቀሳ መልዕክቱ ላይ የተካተተው አንቀጽ፣ ከፖለቲካ ፓርቲዎች የምርጫ ሥነ ምግባር አዋጅ 662/2002 ዓ.ም. አንቀጽ 11 ቁጥር 3 የሚጥስ ሆኖ ማግኘቱን በደብዳቤው አመላክቷል፡፡
በአራተኛ ጠቅላላ ምርጫ የፖለቲካ ፓርቲዎች የመገናኛ ብዙኃን አጠቃቀም መምሪያ ክፍል 2 ቁጥር "". ማንኛውም ሕግ የሚተላለፍ መሆኑን ለማመን በቂ ምክንያት ካለው መልዕክቱን አላስተላልፍም፤ የማለት መብት አለው" የሚለውን አንቀጽ ተጠቅሞ ይህ ኢሕአዴግ የላከውን የምርጫ ቅስቀሳ መልዕክት ለማስተላለፍ እንደሚቸገር ድርጅቱ ይገልጻል፡፡
ደብዳቤው በኢትዮጵያ ሬዲዮና ቴሌቪዥን ድርጅት የምርጫ ዴስክ ኃላፊ አቶ ተሻለ በቀለ ተፈርሞ ተመላሽ መደረጉን ለማወቅ ተችሏል፡፡



