"ኢትዮጵያ የባሕር በር ቢኖራት የሚጠላ የለም"
አቶ ኃይለ ማርያም ደሳለኝ
የመንግሥት ዋና ተጠሪ ሚኒስትር
(አሰግድ ተፈራ)
የኢትዮጵያ ሕዝቦች ዴሞክራሲያዊ ግንባር (ኢህአዴግ) ወደብን የያዘው አጀንዳ እንደሌለ፣ ይልቁንም የኤርትራን ሉዐላዊ አገርነት የፓርቲው ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ የመንግሥት ዋና ተጠሪ ሚኒስትር አቶ ኃይለ ማርያም ደሳለኝ ለሪፖርተር ጋዜጣ ተናገሩ፡፡
"ኢትዮጵያ የባሕር በር ቢኖራት አንጠላም" ያሉት አቶ ኃይለ ማርያም፣ ተቃዋሚዎች ኢትዮጵያን የባሕር በር ባለቤት እናደርጋታለን በማለት ቅስቀሳ የጀመሩት የሕዝብ ስሜት ለመግዛት እንጂ፣ ኢትዮጵያን በተግባር የወደብ ባለቤት ለማድረግ እንዳልሆነ አመልክተዋል፡፡
ኤርትራ ሉዐላዊ አገር መሆኗን ያወጀችው በሰላምና በድርድር ሳይሆን በጦርነት መሆኑን አቶ ኃይለ ማርያም አስታውሰው፣ የዓለም ኅብረተሰብና አገራት እውቅና ሰጥተው "ሉዐላዊ አገር" ብለው የተቀበሏትን አገር የመድፈር አቋም ኢህአዴግ እንደማያራምድ አስታውቀዋል፡፡
የተቃዋሚ ፓርቲ አባላት ኢትዮጵያን የባሕር በር ባለቤት የሚያደርጓት በምርጫ አሸንፈው መንግሥት ከሆኑ በኋላ መሆኑን የተናገሩት ሚኒስትሩ፣ "ተቃዋሚ ፓርቲዎች ቀድሞውንም መንግሥት የመሆን አቅም የላቸውም፡፡ በምርጫ መቀስቀሻ የተጠቀሙበትን አጀንዳም ተግባራዊ ሊያደርጉ አይችሉም" ብለዋል፡፡
"አሰብና ምጽዋ የኤርትራ ሳይሆኑ የቀይ ባሕር አፋሮች ንብረት ናቸው" በማለት መግለጫ ስለመስጠታቸው የተጠየቁት አቶ ኃይለ ማርያም፣ "አሰብን በተመለከተ የቀድሞ መንግሥታት የፈረሟቸውን ውሎችና የዓለም አቀፍ ሕጎች የአሰብን ጉዳይ አንሥቶ በመከራከር አሸናፊ እንደማያደርጉን በመግለጽ፣ በአሰብ ለመጠቀም ከኤርትራ መንግሥት ጋር ከመስማማት ውጪ ሌላ አማራጭ እንደሌለ ባለሙያዎች ተናግረዋል" በማለት መልሰዋል፡፡
የባሕር በር ያስፈልገናል ወይም አያስፈልገንም ከሚለው ስሜት በመነሣት ኢህአዴግ የሚሠራውም ሆነ የሚፈጽመው አንዳችም ነገር እንደሌለ የተናገሩት አቶ ኃይለ ማርያም፣ "የባሕር በር ቢኖረን የሚጠላ፣ የባሕር በር አሳልፎ የሰጠ አካል ያለ በማስመሰል ተቃዋሚዎች እያደረጉት ያለው ቅስቀሳ መሠረተ ቢስ ነው" ብለዋል፡፡
ኢትዮጵያ የአሰብ ወደብ ባለቤት ናት የሚሉ ወገኖች በጀመሩት መንገድ መቀጠል እንደሚችሉ ይፋ ያደረጉት ሚኒስትሩ፤ ተቃዋሚዎች በዚህ አቋማቸው ያላቸውን መረጃ አሰባስበው ወደ ሕግ ቢያመሩ ኢህአዴግ ድጋፍ ስለመስጠቱ ለተጠየቁት፣ "ኢህአዴግ የሚሰጠው አንዳችም ድጋፍ የለም፡፡ በጉዳዩ ቢያምንበትና በሕግ ማሸነፍ የሚቻልበት አግባብ ቢኖር ራሱ ኢህአዴግ ይሄድበት ነበር" የሚል መልስ ሰጥተዋል፡፡
የሻዕቢያ መንግሥት የኢትዮጵያን ሉዐላዊነት በመድፈር ያካሄደው ወረራ ከተቀለበሰ በኋላ፣ በዓለም አቀፍ ደረጃ ከፍተኛ ባለሙያዎች የተሳተፉበት ክርክር ኢትዮጵያ የአሰብና የምጽዋ ባለቤት መሆን ስለመቻልዋ አንዳቸውም እንዳልጠቆሙ ሚኒስትሩ ገልጸው፣ "ከዓለም አቀፍ ሕጎች አንጻር ሊያዋጣ ይችላል" የሚል አቋም ያላቸው ክፍሎች በያዙት መንገድ ሊቀጥሉ እንደሚችሉ በድጋሚ ተናግረዋል፡፡
"በአንድ ወቅት ጅቡቲም የኢትዮጵያ አካል ነበረች" በማለት የተናገሩት አቶ ኃይለ ማርያም፣ "ጅቡቲ የኢትዮጵያ አካል ነች የሚሉ ወገኖች ቢነሡ መከራከሪያው ውኃ የሚቋጥር ስላልሆነ ለእንዲህ መሰሉ ስሜት የመፍጠር አጀንዳ ላለው ሐሳብ ምላሽ መስጠት አይቻልም" ብለዋል፡፡
በየካቲት 24 ቀን 2002 ዓ.ም የሪፖርተር ጋዜጣ እትም የተለያዩ የተቃዋሚ ፓርቲ አመራሮችና ባለሙያዎችን በመጥቀስ በተዘገበው ዜና ኢትዮጵያ የባሕር በር ባለቤት የሚያደርጓት በርካታ የሕግ ድጋፍ እንዳላት፣ ኤርትራ ነፃ አገር ነኝ ስትል ቀድሞ እውቅና የሰጠው የኢትዮጵያ መንግሥት መሆኑ ታሪካዊ ስህተት ነበረ ማለታቸውን መዘገባችን ይታወሳል፡፡



