በአራቱም ግለሰቦች ላይ ቅጣቱን የጣለው የፌዴራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 10ኛ ወንጀል ችሎት ሲሆን፣ የኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ዓቃቤ ሕግ በግለሰቦቹ ላይ መጋቢት 15 ቀን 2002 ዓ.ም. ባቀረበለት የክስ ማመልከቻ መሠረት ነው፡፡
የባለሥልጣኑ ዓቃቤ ሕግ፣ የጉምሩክ ሕግ አዋጅ ቁጥር 622/2001 አንቀጽ 93(1)(መ) ላይ የተመለከተውን ተላልፈዋል ያላቸውን ሦስት በጉምሩክ ዕቃ አስተላላፊነት ሥራ ላይ የተሰማሩ ግለሰቦችና በኤምባሲው ውስጥ በፀሐፊነትና በቪዛ ክፍል ሠራተኛነት ይሠሩ በነበሩ ግለሰብ ላይ ፈጽመዋል ባላቸው የወንጀል ተግባር ላይ የሰውና የሰነድ ምስክርነት አረጋግጦባቸዋል፡፡
ሙሉጌታ ፀጋዬ የተባለው ግለሰብ ብዛቱ 1,300 የሆነና ስድስት ፓኬት የዲፕሎማቲክ ካርጐ ዕቃ ለቱኒዝያ ኤምባሲ የተላከ በማስመሰልና ሐሰተኛ የውክልና ሰነድ በማዘጋጀት ሐምሌ 26 ቀን 2001 ዓ.ም. የጉምሩክ ሥነ ሥርዓት እንዳለቀ አስመስሎ፣ ከአየር መንገድ መጋዘን ወደ ጉምሩክ የፍተሻ ክልል በማዛወር ወደ ውጭ ለመውሰድ በሒደት ላይ እያለ በመታወቁ፣ በማጭበርበር ወንጀል መከሰሱን የዓቃቤ ሕግ የክስ ቻርጅ ያስረዳል፡፡ ኃይሉ ወርቁና ኤልያስ ገረመው የተባሉት ግለሰቦችም፣ የጉምሩክ ሥነ ሥርዓት ያልተፈጸመበት ዕቃ መሆኑን እያወቁ በዝምታ በማለፋቸው በግብረ አበርነት በፈጸሙት የማጭበርበር ወንጀል መከሰሳቸውን ቻርጁ ያብራራል፡፡
የኤምባሲው ፀሐፊና የቪዛ ክፍል ሠራተኛ የነበሩት ሉዊዛ ፍርቤታ የጉምሩክ ሕግን በመተላለፍ የኤምባሲው ሹፌርና ተወካይ የሆኑትን መስፍን ካሳሁን የሚባሉት ግለሰብ፣ በኤምባሲው ተወክለው ከኢትዮጵያ አየር መንገድ ያመጡትን የማስጫኛ ሰነድ ተቀብለው፣ ለሦስተኛ ወገን አሳልፈው በመስጠታቸውና በሦስቱ ተከሳሾች እጅ እንዲገባ በማድረጋቸው በፈጸሙት የማጭበርበር ወንጀል መከሰሳቸውን የዓቃቤ ሕግ ክስ ያስረዳል፡፡
ፍርድ ቤቱ ዓቃቤ ሕግ ያቀረበውን ክስ ከተመለከተ በኋላ፤ ዓቃቤ ሕግ ያቀረበውን የሰነድ ማስረጃና የሰዎች ምስክሮች መመርመሩንና ማድመጡን በውሳኔው ላይ ገልጿል፡፡ ዓቃቤ ሕግ በተከሳሾቹ ላይ እንደ ክሱ በሰውና በሰነድ ማስረጃዎች ድርጊታቸውን ያረጋገጠባቸው በመሆኑ እንዲከላከሉ ውሳኔ ሰጥቷል፡፡ ተከሳሾቹም እያንዳንዳቸው ይከላከሉልናል ያሉዋቸውን የመከላከያ ምስክሮቻቸውን አቅርበው አሰምተዋል፡፡
ፍርድ ቤቱ የሁለቱንም ወገኖች ማስረጃዎች ከሕጉ ጋር በማገናዘብ መርምሮ፣ ዓቃቤ ሕግ በተከሳሾቹ ላይ ያቀረበው ማስረጃና ምስክሮች ተገቢውን የምስክርነት ቃል መስጠታቸውን ሲያረጋግጥ፣ ተከሳሾቹ ያቀረቧቸው የመከላከያ ምስክሮች ከመከላከል ይልቅ የተከሰሱበትን ወንጀል የሚያጠናክር ሆነው በማግኘቱ፣ አራቱም ተከሳሾች ያቀረቡትን የመከላከያ የምስክርነት ቃል አልተቀበለውም፡፡ በዚህም መሠረት አራቱም ተከሳሾች ጥፋተኛ ተብለዋል፡፡
ጥፋተኛ የተባሉት አራቱም ተከሳሾች የቅጣት ማቅለያ ሐሳብ አቅርበው ነበር፡፡ ሦስቱ የጉምሩክ ዕቃ አስተላላፊዎች ላቀረቧቸው የቅጣት ማቅለያ ሐሳቦች ሦስት፣ ሦስት የማቅለያ ሐሳቦች ሲወሰዱላቸው፤ ለፀሐፊና የቪዛ ክፍል ሠራተኛዋም አራት የማቅለያ ሐሳብ ተወስዶላቸዋል፡፡
ፍርድ ቤቱ በመጨረሻ ላይ በሰጠው የቅጣት ውሳኔ፣ የቅጣት ማቅለያውን ከግምት ውስጥ በማስገባት ሦስቱ ጥፋተኞች እያንዳንዳቸው በሦስት ዓመታት ፅኑ እስራትና በ55 ሺሕ ብር፣ የኤምባሲው ፀሐፊና የቪዛ ክፍል ሠራተኛዋ በአንድ ዓመት ከስምንት ወራት ፅኑ እስራትና በ25 ሺሕ ብር እንዲቀጡ ወስኗል፡፡
ፍርድ ቤቱ ሐምሌ 28 ቀን 2003 ዓ.ም. ቅጣት የጣለባቸውን ጥፋተኞች የገቢዎችና ጉምሩክ ሦስት ኃላፊዎች ከፍርድ ቤት ትዕዛዝ ውጭ ምግብና ሕክምና በማይገኝበት ደረቅ ቦታ አስረው በማቆየታቸው፣ እያንዳንዳቸው በሁለት ወራት እስራት እንዲቀጡ ውሳኔ አስተላልፎ እንደነበር መዘገባችን ይታወሳል፡፡
በታምሩ ጽጌ


