Saturday, Jul 31st

English Version

ለኢትዮጵያ እግር ኳስ ድክመት የአውሮፓ እግር ኳስ ወይስ ...?

E-mail Print PDF
User Rating: / 4
PoorBest 

(በደረጀ ጠገናው)

የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 10ኛ ሳምንት ጨዋታ ባለፈው ቅዳሜና እሑድ በክልልና በአዲስ አበባ ስታዲየም ተደርጓል፡፡ የቅዱስ ጊዮርጊስንና ኢትዮጵያ ቡናን ጨዋታ ባለፈው እሑድ ያስተናገደው የአዲስ አበባ ስታዲየም ከዓመታት በኋላ ከአቅሙ በላይ ተመልካች ለማስተናገድ የተገደደበት እለት ነበር፡፡

እለቱ ለኢትዮጵያ እግር ኳስ ድክመት እንደምክንያት ሲቀርብ የቆየውንና ከዘጠኝ ዓመታት በፊት ወደ ኢትዮጵያ የገባውን ዲኤስ ቲቪ ጥያቄ ውስጥ የከተተ ነበር፡፡ በርካቶች ለኢትዮጵያ እግር ኳስ ድክመት ዲኤስ ቲቪ ያመጣው የአውሮፓ እግር ኳስ ሳይሆን፣ አቅማችንን ልንጠቀምበት የሚያስችል መሠረታዊ የሜዳ ላይ ሥራ አለመሰራቱ እንደሆነ ሲናገሩ በከፊል ደግሞ ድሕነትን የሚጠቅሱም አሉ፡፡

ከኢትዮጵያ ክለቦች በርካታ ደጋፊ ያላቸው ቅዱስ ጊዮርጊስና ኢትዮጵያ ቡና ቢሆኑም፣ ቡድኖቹ ሜዳ ላይ የሚያሳዩት እንቅስቃሴ ከሌሎቹ የተለየ ባለመሆኑ አዲስ አበባ ስታዲየም ለተመልካች ድርቅ ተጋልጦ ቆይቷል፡፡ ይሁንና ባለፈው እሑድ የሁለቱን ቡድኖች ጨዋታ ለመከታተል በአዲስ አበባ ስታዲየም የታደመው ተመልካች በዚያኑ ቀን በተለይም በምሥራቅና መካከለኛ አፍሪካ በርካታ ደጋፊ እንዳለው የሚነገርለት አርሴናል ጨዋታ እያለው የአዲስ አበባ ስታዲየም ከሚያስተናግደው በላይ ተመልካች ማስተናገዱ ብዙዎችን አነጋግሯል፡፡ ሁለቱ ቡድኖች የከተማው ተቀናቃኝ ስለሆኑ እንጂ ተመልካቹ ለአገሩ እግር ኳስ ተቆርቁሮ አይደለም የሚሉም አልጠፉም፡፡

ለኢትዮጵያ እግር ኳስ ውድቀት እና ተመልካች ከአዲስ አበባ ስታዲየም እየራቀ ለመምጣቱ ዲኤስ ቲቪ እንደምክንያት ሲነሳ መቆየቱን በተለያዩ አጋጣሚዎች ሲነገር እንደነበረ፣ ችግሩ ከስር ጀምሮ መሰራት ያለበት ባለመሰራቱ፣ እግር ኳስ ከአዝናኝነቱ በተጨማሪ የገቢ ምንጭነቱን ባለመረዳት፣ የማርኬቲንግ ሥራ ባለመከናወኑ የተፈጠረ ስለመሆኑ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ዋና አሰልጣኝ አብርሃም ተ/ሃይማኖት ሲናገሩ፣ የስፖርት ጋዜጠኛ ሰይድ ኪያር በበኩሉ ለእግር ኳሱ ውድቀት ዲኤስ ቲቪ ሳይሆን አቅምን ያገናዘበ መሠረታዊ የሜዳ ሥራ ባለመሰራቱና ተመልካች ከስታዲየም ማግኘት ያለበትን ማግኘት ሳይችል መቅረቱ ነው ይላል፡፡

የአውሮፓ እግር ኳስ እድገት ለኢትዮጵያ እግር ኳስ ተወዳጅነት ወይም ውድቀት መንስኤ ሊሆን እንደማይችል የሚናገረው አሰልጣኝ አብርሃም ከእግር ኳስ አስተዳደር ጀምሮ በየደረጃው ያሉት አካላት ተቀናጅቶ ያለመስራት ችግር ዋናው ምክንያት ነው ይላል፡፡

የኢትዮጵያ እግር ኳስ የወደቀው በአውሮፓ እግር ኳስ ተፅእኖ ቢሆን ኖሮ እግር ኳስን የሚወዱ ኢትዮጵያውያን ብቻ ሳይሆኑ ሙዚቃ የሚወዱ ኢትዮጵያውያን በነማይክል ጃክሰንና ጀምስ ብራውን ዘፈኖች የኢትዮጵያን ሙዚቃ በረሱ ነበር ይላሉ፡፡

ወጣቱ ከአገሩ እግር ኳስ ይልቅ ለአውሮፓ እግር ኳስ ትኩረት መስጠቱ ለኢትዮጵያ እግር ኳስ ውድቀት ምክንያት ሊሆን እንደማይችል የሚናገሩት አሰልጣኝ አብርሃም መሠረታዊ ችግሩ ድሕነት እንደሆነ ገልፀው በተጨማሪም የፌዴሬሽን አመራር፣ አሰልጣኝ፣ ተጨዋች፣ ሚዲያው፣ ተመልካችና የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላትን ለውድቀቱ ተጠያቂ ያደርጋሉ፡፡

የዓለም አገራት እግር ኳስን ከመዝናኛነት አልፎ በማርኬቲንግ ሥራ ላይ የተጠመዱበት ወቅት ነው፡፡ በኢትዮጵያ ግን ይህ የለም፡፡ መድን፣ መብራት፣ ባንኮችና ሌሎችም የሐገሪቱ ክለቦች አሳዳሪዎቻቸው እግር ኳሱን ለማሳደግ ከሚል ባሻገር እግር ኳስን እንደ ገቢ ምንጭ እያዩ አለመሆኑን የሚናገሩት አሰልጣኝ አብርሃም የትኛውም በሐገሪቱ የሚገኝ ክለብ የበጀት አጠቃቀም ችግር ስላለበት ውጤቱም አብሮ እየጠፋ መምጣቱን ይናገራሉ፡፡

ክለቦች ከሕዝብ ጋር የሚተሳሰሩበት አሰራር በኢትዮጵያ አለመፈጠሩ፣ በተለይ በሐገሪቱ የሚገኙ የስፖርት ሚዲያዎች ድክመቶችን ብቻ እንጂ አቅጣጫ ጠቋሚ አለመሆናቸው፣ ለእግር ኳስ በዋነኛነት የሚጠቀሱ ችግሮች መሆኑን አሰልጣኙ ተናግረዋል፡፡

"ተመልካቹ ጥሩ ጨዋታ ይፈልጋል፡፡ ያንን ማምጣት የሚችል አሰልጣኝ ደግሞ አልተገኘም" የሚለው ጋዜጠኛ ሰይድ በበኩሉ ችግሩ ስልጠና መሆኑን ይናገራል፡፡

በሐገሪቱ የሚገኙ አሰልጣኞች ተመልካቹ የሚፈልገውን ነገር በአሰልጣኝነት ዘመናቸው ብቻ ሳይሆን በተጨዋች ዘመናቸውም ያውቃሉ፡፡ ያንን ደፍሮ ሜዳ ላይ ያሳየ ግን እስከ ዛሬ አልተገኘም ሲል መከራከሪያ የሚያቀርበው ጋዜጠኛ ሰይድ "የኢትዮጵያ ተመልካች እንደ አውሮፓ ተመልካች አይደለም፡፡ የአውሮፓ ተመልካች ከጥሩ ጨዋታ ይልቅ ውጤት ይፈልጋል፡፡ የኢትዮጵያ ግን ጥሩ ጨዋታ ተመልክቶ ቢሸነፍ አጨብጭቦ የሚወጣ ነው" ይላል፡፡

ብዙዎቹ የሐገሪቱ ክለቦች ከተመሠረቱ ጀምሮ ለዋንጫ ሳይሆን ላለመውረድና ደረጃ ለመመደብ የሚጫወቱ አሉ፡፡ ተመልካችም የላቸውም፡፡ ተመልካችን እንዴት ማሰባሰብ እንደሚችሉ መንገዶችን አያመቻቹም፡፡ በጀት ሲያፀድቁ በእግር ኳሱ መሠረታዊ ግብዓት ላይ ተነጋግሮ መሆን ሲገባው የሐገሪቱን እግር ኳስ ለማሳደግ በሚል ላይ ብቻ ተወስኖ የክለቡ አሳዳሪ ድርጅት በእግር ኳሱ ተጠቃሚ ሊሆን የሚችልበትን አቅጣጫ እንደማያመላክት ጋዜጠኛው ይናገራል፡፡

የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ከተጀመረ ቅዱስ ጊዮርጊስ ስምንት ጊዜ መብራት ሁለት ጊዜና አዋሳ ከነማ አንድ ጊዜ ዋንጫ አግኝተዋል፡፡

በኢንተርናሽናል ደረጃ ግን የሁሉም ውጤት ከመጀመሪያው ዙር እንደማያልፍ የሚናገረው ጋዜጠኛ ሰይድ ለኢትዮጵያ እግር ኳስ ውድቀት ካለፉት 50 ዓመታት ጀምሮ እየተሰጠ ያለው ስልጠና እንደሆነ ያስረዳል፡፡

ብዙዎች የሐገሪቱ እግር ኳስ ችግር የመዋቅርና አቅም እንደሆነ የሚናገሩ ወገኖች ቢኖሩም፣ ጋዜጠኛ ሰይድ በዚህ አይስማማም፡፡ ምክንያቱም የአትሌቲክስና የእግር ኳስ መዋቅር ተመሳሳይ ነው፡፡ ሐገሪቱ በአትሌቲክሱ ውጤታማ ስትሆን በእግር ኳሱ ግን አልሆነችም፡፡ በአትሌቲክሱም ቢሆን ከረጅም ርቀት እስከ ማራቶን ነው፡፡ አጭር ርቀት እና የእግር ኳሱ ተመሳሳይ ነው፡፡ በረጅም ርቀት ውጤት የተገኘበት ምክንያት ኢትዮጵያውያን አትሌቶች በተፈጥሮ ያላቸው ፍጥነትና ጥንካሬ ለአጭር ርቀት የሚሆን አይደለም፡፡ እንደ መፍትሔ እየቀረበ ያለው ፕሮጀክትና ብቁ አሰልጣኝ ሳይኖር በረጅም ርቀት ኢትዮጵያውያን አትሌቶች ውጤታማ ሆነዋል ሲል መከራከሪያውን ያስረዳል፡፡

እግር ኳሱን በሚመለከት ደግሞ ኢትዮጵያውያን ተጨዋቾች ቴክኒክና ኢንዱራስ (ፅናት) ሲኖራቸው አካል ብቃትና ፍጥነት ግን የላቸውም፡፡ ስለዚህ ባለፈው 50 ዓመታት በሌለ ነገር እየተሰራ ውጤት ሊመጣ አልቻለም፡፡ ለምን ተብሎም አማራጭ አልተሞከረም፡፡

ለሐገሪቱ እግር ኳስ ውድቀት አማራጭ ከመጠቀም ይልቅ መዋቅርና የገንዘብ አቅም እንደምክንያት በመቅረብ ላይ ነው የሚለው ጋዜጠኛው በፕሪምየር ሊጉ ክለብ ካላቸው መብራት ኃይል ባለፉት ሁለት ዓመታት በርካታ ፕሮጀክቶችን ቀርፆ ውጤታማ ሥራ ሰርቷል፡፡ መድን ድርጅትን ብንመለከት ለራሱ ቀርቶ ለታላላቅ ዓለም አቀፍ ካምፓኒዎች የመድን ዋስትና መስጠት የሚያስችል ፕሮጀክት ቀርፆ ውጤታማ ሆኗል፡፡ ኢትዮጵያ ባንኮች በመላ ሐገሪቱ ከ100 በላይ ቅርንጫፎችን ከፍቶ ውጤታማ ሆኗል፡፡ ይህን ሁሉ የሚሰራ መዋቅር ባለበት መሥሪያ ቤት ወደ እግር ኳስ ስንመጣ ውጤት የለም፡፡ የመዋቅርና የአቅም ችግር ከሆነ ሌሎቹ ፕሮጀክቶች ውጤት ሊያመጡ እንዴት ቻሉ?

አቶ ይድነቃቸው ተሰማ ለአገራቸው እግር ኳስ ቀርቶ ለአፍሪካ እግር ኳስ የሚሆን ጠንካራ አመራር ነበራቸው፡፡ በእሳቸውም አመራር ቢሆን እንደሚባለው የኢትዮጵያ እግር ኳስ ውጤት እንዳልነበረው የሚናገረው ጋዜጠኛ ሰይድ ውድቀቱ ከዚያን ጊዜ ጀምሮ መሆኑን ይናገራል፡፡

ፕሮጀክትና የአውሮፓ እግር ኳስ እየተባሉ እየቀረበ ያለውን ምክንያት እንደማይቀበል የሚናገረው ጋዜጠኛው ፕሮጀክት ከጣሊያኖች ጀምሮ በሐገሪቱ እንደነበር መረጃዎች አሉ፡፡ ሆኖም ግን ሐገሪቱ በዓለም አቀፍ ደረጃ ውጤት የላትም፡፡

ባለፉት ዓመታት የነበረው ኳስ አሁን እየቀነሰ ነው ስለሚባለው ደግሞ ኢትዮጵያ በመጀመሪያ የአፍሪካ ዋንጫ 4ለ0 መሸነፏ እስከ አሁን ሪከርድ መሆኑ፣ እንደገና በአምስተኛው አፍሪካ ዋንጫ 5ለ1፣ በሰባተኛው የአፍሪካ ዋንጫ 6ለ1 መሸነፏ እስከ ዛሬ ያልተሰበረ ሪከርድ መሆኑን የሚናገረው ጋዜጠኛ ሰይድ ይህ ሁሉ ጠንካራ አመራርና መዋቅር በነበራቸው አቶ ይድነቃቸው ዘመን ነው ይላል፡፡

የኢትዮጵያ እግር ኳስ ችግር የመዋቅር፣ የአመራር፣ የገንዘብና ሌላም እየተባለ የሚነገረውን እንደማይቀበል የሚናገረው ጋዜጠኛው እነ ናይጄሪያና ካሜሩን የመሳሰሉት ፌዴሬሽኖቻቸው በሙስና የተበላሹ ናቸው፡፡ በዚህ የተነሳ ጠንካራ አመራርና መዋቅር የላቸውም፡፡ ብሔራዊ ቡድኖቻቸው ግን ለአፍሪካና ለዓለም ዋንጫ እየበቁ ነው፡፡

እንግሊዝ በዓለም ላይ ምርጥ የሚባል ሊግ፣ ገንዘብና አሰልጣኝ አላት፡፡ ብሔራዊ ቡድኗ በዓለም ዋንጫ ከ1966 ወዲህ ውጤት የለውም፡፡ አገሪቱ በአውሮፓ ዋንጫ ጭራሽ ታሪክ የላትም፡፡ ገንዘብ ያላቸው ሳውዲ አረቢያና የእሲያ አገሮች አሉ፡፡ የእግር ኳሳቸው ደረጃ ግን ያን ያህል አይደለም፡፡ ምክንያቱ የዓለም እግር ኳስ ስልጠና ቅኝት በአውሮፓውያንና በተመሳሳይ ደቡብ አሜሪካውያን አገሮች ሆኖ ጥቂት የአፍሪካና እሲያ አገሮች ውጤታማ እየሆነበት ቢሆንም የሚፈለገውን ያህል እንዳልሆነ ያስረዳል፡፡

ስለዚህ ለኢትዮጵያ እግር ኳስ እንቆረቆራለን ለሚሉ ሁለት አማራጮች እንዳሉ የሚናገረው ጋዜጠኛ ሰይድ ላለፉት 50 ዓመታት ተሰርቶበት ውጤት ባላመጣው ስልጠና መቀጠል አልያም ተፈጥሮን ማዕከል ያደረገ ሳይንሳዊ ስልጠናን እንደ አማራጭ መጠቀም እንደሚገባ ይገልፃል፡፡

በአንድ ወቅት በኢትዮጵያ ቡና ክለብ ኢትዮጵያዊ ስልጠና በሚል በአሰልጣኝ ካሳዬ አራጌ ተጀምሮ እንደነበረና በወቅቱ ሙያተኞች ሐሳቡን ተቀብለው ስህተት ካለውም ስህተቱን በማረም ጠንካራ ጐን ካለውም ያንን መውሰድ ሲገባ እንዳለ ተቀባይነት እንዲያጣ መደረጉ አግባብ እንዳልነበረ የሚናገረው ጋዜጠኛው አሁንም አማራጮችን ማምጣት የሚችል ሙያተኛ እስካልተገኘ ድረስ ላለፉት 50 ዓመታት በተሞከረው ይቀጥል ከተባለ ውድቀቱ እንደሚባባስ ያስረዳል፡፡