Saturday, Jul 31st

English Version

በአንድ ዓመት ጊዜ የኢትዮጵያ ምርት ገበያ የ4.2 ቢሊዮን ብር የቡና ግብይት ማከናወኑ ተገለጸ

E-mail Print PDF
User Rating: / 1
PoorBest 

(በኃያል አለማየሁ)

የኢትዮጵያ የምርት ገበያ የቡናን ግብይት በጀመረበት በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ ከ170 ሺህ ቶን በላይ የሚሆን የ4.2 ቢሊዮን ብር ቡና በተሳካ ሁኔታ ማሻሻጥ መቻሉን የምርት ገበያው ዋና አስተዳዳሪ ዶክተር እሌኒ ዘውዴ ገ/መድህን ለሪፖርተር ገለፁ፡፡

የምርት ገበያው የቡናን ግብይት ከጀመረበት እ.ኤ.አ. ታህሳስ 2008 ዓ.ም. እስከ ታህሳስ 2009 ዓ.ም. ድረስ የተጠቀሰውን የቡና ምርት ያለአንዳች ክፍያ ወይም የንግድ ልውውጥ ግድፈት ማከናወን መቻሉን የገለፁት ዶክተር እሌኒ ይኸው የቡና ምርት ግብይት ውጤታማነት በቡናው መስክና በሌሎች ሸቀጦች ላይ የተሰማሩ ነጋዴዎችን አትኩሮት መሳቡን ጠቁመዋል፡፡

"የቡና ምርት ግብይት በጀመረበት በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ በንግድ ልውውጡ ላይ ግድፈት ሳይፈጠር በተሳካና በተቀላጠፈ ሁኔታ የቡና ግብይቱን ማካሄድ መቻላችን ስኬታማነታችንን ያረጋገጠ ሲሆን የንግዱ ማኅበረሰብ በኢትዮጵያ ምርት ገበያ ላይ ያለውን እምነት እጅግ አሳድጎታል" ያሉት ዶክተር እሌኒ፣ ባለፉት ሣምንታት የምርት ገበያው ለንግዱ ማኅበረሰብ ያቀረበው 150 የአባልነት መቀመጫ (membership seat) ጨረታ እጅግ በላቀ ዋጋ (ከአምስት እስከ ስድሳ እጥፍ ድረስ) መሸጥ መቻሉም የዚሁ አንዱ ገፅታ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

የምርት ገበያው ባለፉት ሣምንታት ለንግድ ማኅበረሰቡ የቀረበው 150 የአባልነት ወንበር ጨረታ ባለፈው ሳምንት ሐሙስ እለት በተከፈተበት ወቅት፣ የአንድ መቀመጫ ዋጋ እስከ 3.3 ሚሊዮን ብር ሊሸጥ መቻሉ የታወቀ ሲሆን በአማካኝ ለአንድ የአባልነት ወንበር የተከፈለው 270 ሺህ ብር መሆኑን ለማወቅ ተችሏል፡፡

የምርት ገበያው ከተጠቀሰው ከጠቅላላው የአባልነት ሽያጭ ከ34 ሚሊዮን ብር በላይ የሚሰበሰብ ሲሆን፣ ሐሙስ እለት የቀረበው የአንድ አባል ወንበር ዋጋ መጠን የምርት ገበያ ባለፈው ዓመት ካስከፈለው 50 ሺህ ብር ጋር ሲነፃፀር ከአራት እስከ ስድሳ እጥፍ ብልጫ እንዳስመዘገበም ለማወቅ ተችሏል፡፡

የምርት ገበያው ባለፈው ዓመት ከንግዱ ማኅበረሰብ አንድ መቶ የሚሆኑ አባሎችን የያዘ ሲሆን በዚያን ወቅት ለአንድ አባልነት መቀመጫ የተከፈለው ክፍያም 50 ሺህ ብር እንደነበር ይታወቃል፡፡

በአሁን ሰዓት ለአገር ውስጥም ሆነ ለውጭ ገበያ የሚውል የቡና ምርት የሚገበየው በምርት ገበያው አማካኝነት ሲሆን፣ የምርት ገበያው ለቡና ግብይት አመቺ የሆኑ ዘመናዊ መሳሪያዎችንና መጋዘኖቹን የሚጠቀም መሆኑን ዶክተር እሌኒ ጠቁመዋል፡፡