(በጋዜጣው ሪፖርተር)
በቅርቡ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የፀጥታው ም/ቤት ማዕቀብ የተጣለባት ኤርትራ በቅርቡ ከኢትዮጵያ ጋር በዛላምባሳ ግንባር ወታደራዊ ግጭት ማድረጓን ብታስታውቅም፣ እስካሁን ከገለልተኛ ምንጮች ግጭቱ ስለመካሄዱ መረጃ አልተገኘም፣ የኢትዮጵያ መንግሥት አንድ ከፍተኛ ባለሥልጣን ተከሰተ የተባለው ግጭት የኤርትራ መንግሥት የ"ፈጠራ ወሬ" ነው ማለታቸው ተዘግቧል፡፡
ባለፈው ዓርብ የኤርትራ መንግሥት ላይ ጦርነት ያወጁ አማፂያን ኤርትራ ውስጥ በሁለት ወታደራዊ ካምፖች ላይ ጥቃት ከፍተው 25 ወታደሮችን ከመግደላቸውም በላይ 38 ወታደሮች ላይ ከባድና ቀላል ጉዳት ማድረሳቸውን መግለፃቸው ይታወሳል፡፡
ይህንን መግለጫ ተከትሎ በነገታው የኤርትራ መንግሥት በዛላምባሳ ግንባር የኢትዮጵያ ወታደሮች የማጥቃት ሙከራ አድርገው አሥር ወታደሮችን መግደሉንና ሁለቱን መማረኩን አስታውቋል፡፡ ይህ የኤርትራ መንግሥት የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ይፋ ያደረገው መግለጫ እስካሁን ማረጋገጫ እንዳልተገኘለት ነው፡፡
ይሁንና ለጉዳዩ በጣም ቅርበት ያላቸው የመንግሥት ባለሥልጣን ለሪፖርተር እንደገለፁት፣ "ይህ ጉዳይ ከኢትዮጵያ ጋር ምንም ዓይነት ግንኙነት የለውም፡፡ በእርግጠኝነት ውጊያ ነበር፣ ነገር ግን ከኢትዮጵያ ጋር ሳይሆን፣ ከቀይ ባሕር የአፋር ነፃ አውጪ ግንባር ከሚባል የኤርትራ መንግሥት ተቃዋሚ ጋር ኤርትራ ውስጥ የተደረገ ነበር፡፡"
እኚሁ ባለሥልጣን እንደሚሉት የኤርትራ መንግሥት በቅርቡ የተጣለበትን ማዕቀብ ተከትሎ ተቃዋሚዎቹ ይህንን አጋጣሚ በመጠቀም ጥቃት መክፈታቸውንና፣ ወደፊትም በተለይ የጦር መሣሪያ ማዕቀቡ እየጠነከረ ሲሄድ፣ የፕሬዚዳንት ኢሳያስ መንግሥትን በኃይል ለማስወገድ ከወዲሁ ይረዳቸው ዘንድ የጀመሩት የዘመቻ አካል ሊሆን ይችላል፡፡
ከዚህ ውጪ በዛላምበሳ አካባቢ በኢትዮጵያና በኤርትራ መካከል ውጊያ ተደርጐ እንደነበር በኤርትራ መንግሥት የሚናፈሰው ወሬ መሠረተ ቢስ ነው ሲሉ እኚሁ ባለሥልጣን አስተባብለዋል፡፡
ምንም እንኳን የኤርትራ መንግሥት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ አሊ አብዱ መንግሥታቸው በኢትዮጵያ ተሞክሮ ስለከሸፈው ጥቃት "ማስረጃ" አለን ከማለት ውጪና በኤርትራ ቴሌቪዥን በትክክል በየትኛው ጦርነት መሞታቸው ያልታወቁ አስከሬኖችን ከማሳየት የዘለለ ነገር ባለማሳየታቸው፣ ግጭቱን አስመልክቶ በገለልተኛ ወገኖችም ሆነ በዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙሃን በተጨባጭ ማቅረብ አልቻሉም፡፡
ኤርትራ ውስጥ በሁለት ወታደራዊ ካምፖች ውስጥ በአማፂያን ስለደረሰው ጥቃት ተጠይቀው በሰጡት መልስ "ይህ የአዲሱ ዓመት ምርጡ ቀልድ ነው፣ ኤርትራ ውስጥ ምንም ተቃዋሚ የለም፡፡ ምናልባትም የተቃዋሚ ኃይሎች ቅዥት ይሆናል፣ ቢሆንም እንዲህ ዓይነት ተቃዋሚ የለንም" ሲሉ አስተባብለዋል፡፡ በኢትዮጵያ በኩል "የፈጠራ ወሬ" ነው ስለተባለውም ሲመልሱ "የተማረኩትን ወታደሮች ማንም ሊያያቸው ይችላል፡፡ የኢትዮጵያ መንግሥት ጦርነትም አልነበረም፣ ምንም አልተፈጠረም ቢል አይደንቀኝም" ሲሉ አክለዋል፡፡
የኤርትራ ፕሬዚዳንት ኢሣይያስ አፈወርቂ ከኤርትራ ቲቪ ጋር በቅርቡ ባደረጉት ቃለምልልስ የአሜሪካው የስለላ ድርጅቶች ከ1990 እስከ 1992 ዓ.ም. ድረስ በኢትዮጵያና በአርትራ መካከል በተካሄደው ደም አፋሳሹ ጦርነት ዋነኞቹ ቆስቋሾች እንደነበሩ ወንጅለዋቸዋል፡፡ በተለይ ሲአይኤ በአፍሪካ ውስጥ ቀውስ ፈጣሪ ነበር፣ የአፍሪካ ሕዝብን እርስ በርሱ ሲያናክስ ነበር በማለት መክሰሳቸው ሲታወስ፣ ለኢትዮ-ኤርትራ ጦርነት አሜሪካን ተጠያቂ ነች ብለዋል፡፡
በቅርቡ በኤርትራ ላይ የተጣለውን ማዕቀብ ተከትሎም ፕሬዚዳንት ኢሣይያስ አሁንም አሜሪካንን ተጠያቂ ሲያደርጉ፣ ለማዕቀቡ መጣል ኢትዮጵያ ምናልባት ሚና ቢኖራትም የማዕቀቡ ባለቤት ናት ወይም የእሷ ሥራ ነው ማለት አይቻልም ብለዋል፡፡



