በሰብለወንጌል ሀብታሙ
የስምንቱ ፓርቲዎች ውህደት የሆነው የኢትዮጵያ ፌዴራል ዴሞክራቲክ መድረክ ዕጩዎቹን በተናጠል ሳይሆን፣ የፓርቲዎችን እንቅስቃሴ አይቶ ማን በየትኛው አካባቢ ቢሆን ይሻላል የሚለውን በመገምገም ስምንቱንም ፓርቲዎች እንደሚያሰማራ አስታወቀ፡፡
የመድረክ ሊቀመንበር ዶ/ር መራራ ጉዲና እንደገለፁት፣ በአዲስ አበባ እጩዎቹን ማሰማራት የጀመሩ መሆኑንና በቀጣይም በክልሎች እንደዚሁ መመዘኛዎችን ጨምረው እጩዎቻቸውን በተጠናከረ መልኩ ተፎካካሪ እንዲሆኑ እየሠሩ መሆኑን ገልፀዋል፡፡
በተጨማሪም ስምንቱም ፓርቲዎች ይበልጥ ተጠናክረው የሚንቀሳቀሱባቸው ክልሎች እንዳሏቸው ተናግረዋል፡፡ ይህንን ታሳቢ በማድረግ እያንዳንዱ ፓርቲ የሚያቀርበውን የዕጩ ብቃት፣ ተቀባይነቱንና በሚወዳደርበት አካባቢ ያለውን ሥራ ግንዛቤ ውስጥ አስገብቶ እጩዎቹን እንዲያቀርብ ይደረጋል ሲሉ የመድረክ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ገብሩ አስራት ተናግረዋል፡፡
ሦስትና አራት ፓርቲዎች በአንድ አካባቢ ለመወዳደር ሲፈልጉ የትኛው ነው በእዚያ አካባቢ መወዳደር ያለበት የሚለውን የመወሰኑ ጉዳይ ችግር ሊፈጥር ይችላል ያሉት አቶ ገብሩ፣ ይሁን እንጂ የሁሉም ፓርቲዎች ግብ የመድረኩ ዓላማዎች እንዲሳኩ ማድረግ ስለሆነ እንዲህ ዓይነቶቹን ችግሮች እንደሚወጧቸው ተናግረዋል፡፡
አክለውም "በአዲስ አበባም ስምንቱ ፓርቲዎች ያለምንም መደራረብ እጩዎችን በየፓርቲዎች አቅርበን ችግሩን ተወጥተናል" ብለዋል፡፡ ምናልባት በፓርቲዎች በኩል የመደራረብ ችግር ሊፈጠር ይችላል የሚለውን በውይይትና በመደራደር እንደሚፈቱትም ገልፀዋል፡፡
ዶ/ር መራራ በበኩላቸው የፓርቲዎች ዕጩ አቀራረብ ብዛትና ማነስ ችግር እንደማይፈጥር፣ ዋናው ነገር የፓርቲው እንቅስቃሴና የመመረጥ እድል መሆኑን፣ ስምንቱ አባል ድርጅቶች ሲመሰረቱም በተመሳሳይ ጊዜ ባለመሆኑ፣ እድገታቸውም ሆነ እንቅስቃሴያቸው እኩል ላይሆን ይችላል፡፡ 'ነገር ግን በስፋት የሚንቀሳቀሱ ፓርቲዎች አሉ እኛ ይሄን አውቀን ነው የገባነው" ሲሉ ገልፀዋል፡፡



